በብዙ መድረኮች ላይ እና በመገናኛ ብዙኃን ውይይቶች እንደምንሰማው አካል ጉዳተኞችን እና መገናኛ ብዙኃንን በተመለከተ በተደጋጋሚ የሚሰማው ቅሬታ በቂ ሽፋን አላገኙም የሚል ነው፡፡ ቁጥሩን በመናገርም ይህን ያህል አካል ጉዳተኛ ባለባት ሀገር የመገናኛ ብዙኃን አካል ጉዳተኛን በተመለከተ ያላቸው ፕሮግራም ግን ይህን ያህል ብቻ ነው የሚል ነው፡፡ ይህ ራሱ የተሳሳተ ነው፡፡
ለአካል ጉዳተኞች ሽፋን መስጠት ማለት ‹‹የአካል ጉዳተኞች›› የሚል ስያሜ ያለው ራሱን የቻለ (እነርሱን ብቻ የተመለከተ ማለት ነው) ፕሮግራም ማዘጋጀት ማለት መሆን የለበትም፡፡ ከዚህ ይልቅ መሆን ያለበት እና መበረታታት ያለበት በየትኛውም ፕሮግራም ላይ እነርሱን አካታች የሆነ ይዘት ማካተት ነው፡፡ ፕሮግራሙ የመዝናኛ ወይም የኢኮኖሚ ወይም የፖለቲካ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲህ አይነት ፕሮግራም ላይ አካል ጉዳተኞችን ማሳተፍ ወይም እነርሱን የተመለከተ ነገር ማቅረብ ማለት ሽፋን መስጠት ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ፦ የኢኮኖሚ ጉዳይ የሚተነተንበት ፕሮግራም ላይ ከአካል ጉዳተኞችም አንፃር መተንተን ማለት ነው፡፡
አለበለዚያ ግን በሳምንት ወይም በአሥራ አምስት ቀን አንድ ጊዜ በሚካሄድ አካል ጉዳተኞችን የተመለከተ ፕሮግራም ብቻ በማዘጋጀት ሽፋን ሰጠን ማለት አይቻልም፡፡ በየትኛውም ነገር ላይ ከማንኛውም ኅብረተሰብ ጋር እኩል ማድረግ የሚቻለው በእንዲህ አይነት አሰራር እንጂ እነርሱን ብቻ የሚመለከት ፕሮግራም በማዘጋጀት አይመስለኝም፡፡
አካል ጉዳተኝነት በሆነ ዓውድ የሚታይ አንድ የኅብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ለምሳሌ፦ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ መምህራን፣ መሐንዲሶች፣ ጋዜጠኞች…
የሚባሉ ምድቦች አሉ፡፡ ወይም የሰሜን ኢትዮጵያ፣ የደቡብ፣ የምሥራቅ…. እየተባለ የባህል እና የአየር ንብረት ልዩነት እንደሚነገረው ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ፤ በፕሮግራሞች ውስጥ ‹‹በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል፣ በጎንደር አካባቢ፣ በሐመር ባህል….›› እየተባለ ይወራል፡፡ ልክ እንደዚህ ሁሉ የሆነ ነገር ስናብራራ ወይም ስንተነትን ‹‹ለምሳሌ ዓይነ ሥውራን፣ ለምሳሌ ድምጽ መስማት ለማይችሉ፣ ለምሳሌ የእግር ጉዳተኛ የሆኑ….›› እያልን ነገርየውን ከእነርሱ አንጻር መቃኘት ማለት ነው፡፡ እንዴት ለእነርሱ ምቹ ይሁን? እያልን መጠቆም ማለት ነው፡፡
አካል ጉዳተኝነትን ከልክ በላይ ማክበድ እና መፍራት ለአካል ጉዳተኞችም ምቾት የሚሰጥ አይሆንም፡፡ ለምሳሌ፦ የቴሌቭዥን የካሜራ ባለሙያዎች የመብራት ምጥጥን የሚያመቻቹት በሰውየው የቆዳ ቀለም ልክ ነው፡፡ ለጥቁር ሰው፣ ለቀይ ሰው… እየተባለ እንደ ሰውየው ሁኔታ ይደረጋል፡፡ አካል ጉዳተኝነትንም ልክ እንደዚህ ማየት ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ፦ እግሩ ላይ ጉዳት ያለበት ሰው ደረጃ መውጣት አይችልም፤ ስለዚህ ከንፈር ከመምጠጥ ይልቅ ወይም ከልክ በላይ አዝኖ ‹‹አይዞህ!›› ከማለት ይልቅ፤ ቀለል አድርጎ ለእርሱ የሚመች ነገር ማድረግ ማለት ነው፡፡ ታዲያ ቀለል አድርጎ ሲባል ነገሩን ማቅለል ማለት አይደለም፤ እሱማ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ነው፤ ቀለል ማድረግ ማለት ለሰውየው የምናሳየውን ድርጊት ነው፡፡ ከልክ ያለፈ ከንፈር መጠጣ ልክ ያልሆነ ስሜት ይፈጥራል፡፡
ወደ መገናኛ ብዙኃን ሽፋን ስንመለስ፤ ሌላው በተደጋጋሚ አከራካሪ የሆነው እና አሁን ድረስ የጠራ መልክ ያልያዘው የቃላት አጠቃቀም ነገር ነው፡፡
በነገራችን ላይ እዚህ ላይ አንድ ልብ መባል ያለበት ነገር እነዚህ አወዛጋቢ የቃላት አጠቃቀሞች የመጡት ከክፋት አይደለም፡፡ ምናልባት አካል ጉዳተኞች ሆን ተብሎ ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ግን ነገረየው የመጣው ከልክ ያለፈ ጥንቃቄና ጭንቀት ከማብዛት ነው፡፡ ለምሳሌ፦ ‹‹ዓይነ ሥውር›› የሚለው ቃል ለረጅም ዘመን አገለገለ፤ እናም ሰዎች ያለዘብን መስሏቸው፣ በተሻለ አገላለጽ የገለጽን መስሏቸው ‹‹ማየት የተሳነው›› ማለት ተጀመረ፡፡ ይህ የቃል አጠቃቀም እየቆየ ሲሄድ ነገሩን በጥልቀት ማሰብ ተጀመረ፡፡ እናም ‹‹ማየት የተሳነው›› መባል የለበትም ተባለ፡፡ ምክንያቱም ዓይነ ሥውር ማለት አካላዊ ዓይናቸው አያይም እንጂ ልበ ብርሃን ናቸው፡፡ በሥውር ያያሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹ዓይነ ሥውር›› የሚለው አገላለጽ ነው መሆን ያለበት ተብሏል፡፡
አሁንም ግን አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን ላይ ‹‹ማየት የተሳናቸው›› ሲባል እንሰማለን፡፡ ይህን የቃል አጠቃቀም የሰማ አንድ ሰው ሊናደድ ይችላል፤ የሚያናድደው ግን ‹‹ዓይነ ሥውር›› የሚለው ነው መሆን ያለበት የሚለውን አለመስማታቸው እንጂ ከክፋት አይደለም፤ በእነርሱ ቤት አለዝበው መጠቀማቸው ነው፡፡
‹‹መስማት የተሳናቸው›› የሚለው ግን አሁንም በአገልግሎት ላይ ያለ ይመስለኛል፡፡ ምናልባት ‹‹ድምጽ መስማት የተሳናቸው›› ቢባል ይሻል ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ቀጥታ ድምጽ አይሰሙም እንጂ ውስጠ ብርሃን ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ ገጠሩ ማህበረሰብ ለዚህ ድርጊት አንድ አጠቃቀም አላቸው፡፡ ‹‹ጆሮው ትንሽ ያዳምጣል›› ይላሉ፡፡ ‹‹ያዳምጣል›› የሚለው ቃል በጣም ገላጭ ይመስለኛል፡፡ እንደ ብዙዎቻችን የሚጮኸውን ነገር ሁሉ አይሰማም፣ በትኩረት ለእርሱ የሚሆነውን ነገር ለይቶ ነው የሚሰማ የሚል ይዘት ይኖረዋል፡፡ ጆሮው ያዳምጣል የሚሉት በከፊል የሚሰማውን ሰው ብቻ አይደለም፤ ሙሉ በሙሉ በምልክት ቋንቋ የሚግባባውንም ጭምር ነው፡፡ ‹‹ጆሮው አይሰማም›› ከማለት ይልቅ ‹‹ያዳምጣል›› በሚለው ይግባባሉ ማለት ነው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን አንድ ለስድብነት የሚያገለግል ቃል ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ይህን ቃል ሲጠቀሙ ድምጽ መስማት የማይችሉ ሰዎችን የሚያስቀይም ይመስላቸዋል፡፡ ምናልባትም የሚቀየሙም ሊኖሩ ይችላሉ፤ ዳሩ ግን በፍጹም አይገኝም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ያንን ቃል የሚጠቀሙት የአንድን ሰው አላዋቂነት፣ መሃይምነት፣ የነገሩንን ነገር የማይሰማ መሆኑን ለመግለጽ እንጂ ድምጽ ከመስማት አለመስማት ጋር አይገናኝም፡፡ እየሰማ የማይሰማ ለማለት ነው፡፡ በምንም ነገር ቢነግሩት የማይረዳ ለማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን የትኛውም ስድብ ነውር ቢሆንም ይህኛውን ግን ድምጽ ከማይሰሙ ሰዎች ጋር ማገናኘት ልክ አይደለም፡፡ ዋናው ይዘት ያለው ከቃሉ ሳይሆን ከተነገረበት ዓውድ ነው፡፡ ግልጽ ለማድረግ ሌላ ምሳሌ እንጠቀም፡፡
ለምሳሌ አንድ ሰው ‹‹አህያ!›› አለኝ እንበል፡፡ አህያ ታታሪ ሰራተኛ ናት፣ አህያ ብርቱ እና ጠንካራ ናት፡፡ ይህን እውነታ ይዤ ‹‹አህያ! ስላልከኝ አመሰግናለሁ!›› ብዬ ብናገር ራሴን ማሞኜት ነው፡፡ ነገሮችን በበጎ ማየቱ ጥሩ ሆኖ ሳለ፤ ‹‹አህያ!›› ብሎ የሰደበኝ ሰውዬ ግን ጥንካሬዬን እና ታታሪ ሰራተኛ መሆኔን ለመግለጽ ሳይሆን አላዋቂ ወይም መሃይም ወይም በነውር ቃል ‹‹ደደብ›› ለማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዋናው ነገር ተሳዳቢው አካል ቃሉን የተጠቀመበት ዓውድ እንጂ ቃሉ ብቻውን አይደለም፡፡ ጆሮው ድምጽ መስማት የማይችል ሰው ምንም የሚሰደብበት ምክንያት የለም!
የመገናኛ ብዙኃን እና የአካል ጉዳተኝነትን ነገር ስናጠቃልል፤ የቃል አጠቃቀምን በተመለከተ ከአካል ጉዳተኞች ጋር መመካከርና ማህበራትን ማማከር ያስፈልጋል፡፡ አጠቃላይ ሽፋንን በተመለከተ ግን ለአካል ጉዳተኞች ሽፋን መስጠት ማለት በሳምንት አንድ ቀን የአየር ሰዓት መስጠት ሳይሆን በአጠቃላይ ይዘቶች ውስጥ ጉዳዩን አካታች ማድረግ መሆን አለበት!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መስከረም 9/2017 ዓ.ም