ከፊደል ቆጠራ በዘለለ፣ በአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ለውጥ እና ዕድገት ውስጥ ዜጎችን ከፍ ያለ ድርሻ እንዲኖራቸው የሚያስችላቸውን የእውቀት፣ የክህሎት፣ የሥነምግባርና የአመለካከት ከፍታን የሚያጎናጽፍ መሳሪያ ነው፡፡ ኢትዮጵያም እንደ ሀገር በዚሁ አውድ ውስጥ ለመራመድ የሚያስችሏት ዜጎች ባለቤት ለመሆን ባላት መሻት ምክንያት፤ ዘመናዊ ትምህርትን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች ለአንድ ምዕተ ዓመት የተጠጋ ታሪክ አላት፡፡
ይሄ ሂደት ደግሞ በብዙ ስኬቶችም፣ በብዙ ፈተናዎችም የታጀበ ነበር፡፡ በተለይም አንዴ በትምህርት ተደራሽነት፣ ሌላ ጊዜ በትምህርት ጥራት ችግር ምክንያት በሚፈለገው ልክ ተተግብሮ፤ የሚፈለገውን ያህል ሀገርን በሁሉም መስክ የሚያራምድ ትውልድን በሙላት መፍጠር አስችሏል ብሎ አፍ ሞልቶ የሚያናግር አይደለም፡፡
ለምሳሌ፣ በንጉሳውያኑ ዘመን በነበረው አካሄድ፣ የትምህርት ጥራት አለው ሊባል ቢችልም፤ ከትምህርት ተደራሽነት አኳያ ግን በእጅጉ ውስንነት ያለው ስለነበር፤ ዜጎች ውስጥ ያለውን አቅም በትምህርት አዳብሮ የሚፈለገውን ከፍታ ማምጣት አስችሏል ለማለት አያስችልም፡፡ ምክንያቱም፣ ለትምህርት ቅርብ የነበሩት ያሳዩትን አቅም፤ በብዙ እጥፍ ትምህርት ያልደረሳቸው ዜጎች መግለጥ የሚችሉበት ሰፊ እድል ይኖር ነበርና፡፡
በደርግ ዘመን የነበረው አካሄድም በአንድ በኩል የትምህርት ጥራትን፤ በሌላ በኩል ተደራሽነትን ለማስፈን የተሞከረበት ነበር፡፡ ሆኖም በሁለቱም በኩል ያለው ጉዞ በሚፈለገው ልክ ያልደረሰ፤ በብዙ ፈተናዎች መካከል እንዲራመድ የተገደደ ስለነበር፤ የታሰበውን ያህል ውጤት አምጥቷል ለማለት አያስደፍርም፡፡
ይሁን እንጂ በእነዚህ ሁለት ሥርዓቶች የነበረው ውስንነት እንዳለ ሆኖ፤ በትምህርት አውድ ውስጥ ያለፉ ዜጎች ከትምህርት ማግኘት የሚገባቸውን ነገር በልኩ ተገንዝቦ ወደተግባር በመለወጥ ረገድ እምብዛም እንከን ነበረባቸው የሚያስብሉ አይደሉም፡፡
ከዚህ መንገድ በተቃራኒው ግን በዘመነ ኢህአዴግ የነበረው የትምህርት ጉዞ፤ ከትምህርት ጥራት ይልቅ ለትምህርት ተደራሽነት ትኩረት በመስጠቱ፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶችንና በርካታ ዩኒቨርሲቲዎችን መገንባት ቢቻልም፤ በዚህ ልክ የሚገለጽ የበቃ የሰው ኃይል ከማፍራት አኳያ የበዛ ችግር ያለበት ሆነ፡፡ ይልቁንም ትምህርት ፊደል መቁጠሪያ (እሱም ያልተሳካለት)፣ ተማረ የመባያ የምስክር ወረቀት መቀበያ ሆኖ ተከሰተ፡፡
ይሄ ሲሆን ደግሞ ተማረ የተባለው ኃይል የሚፈለገውን እውቀት ሳይጨብጥ በኩረጃ ላይ ተመስርቶ ከፍተኛ ትምህርት የሚደርስበት፤ ከከፍተኛ ትምህርትም ቢሆን የሚፈለገውን ክህሎት ሳይጨብጥ ተመርቆ በሥራ መስክ ላይ በመሠማራት ውጤታማ ተግባርን መከወን የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሶም ታየ፡፡ ይሄ ደግሞ እንደ ሀገርም፣ እንደ ማኅበረሰብም ከፍ ያለ ውድቀትን የጋበዘ ሆነ፡፡
ይሄን ችግር በመገንዘብም ከ2010 ሀገራዊ ለውጥ ማግስት የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ ጭምር የትምህርት ተደራሽነትን ከጥራት ጋር ለማስተሳሰር የሚያስችል አሠራር ተዘረጋ፡፡ ትውልዱ በእውቀትም፣ በክህሎትም፣ በአመለካከትና ሥነምግባርም ብቁ ሆኖ እንዲወጣ የሚያስችል የትምህርት ፍኖተ ካርታም ተግባራዊ ተደረገ፡፡ የፈተና ሥርዓቱ ላይ ያለውን ክፍተት ከመድፈን አኳያም በተለይ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሰጥ ተደረገ፡፡ ይሄ መደረጉ ደግሞ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ያለውን ከፍ ያለ ስብራት አግጥጦ እንዲወጣ አደረገው፡፡
በዚህ መልኩ ከሦስት ዓመታት በላይ የተጓዘው የትምህርት ዘርፉን ስብራት ለይቶ የማከም ጉዞ ግን፤ ዛሬም ላይ ይሄ ነው የሚባል ለውጥ ሳይታይበት በየዓመቱ ፈተና ያላለፉ ተማሪዎች ቁጥር በመቶኛ እያሰሉ በማቅረብ የታጀበ አካሄድ ላይ ተቸክሎ ቆሟል፡፡ ምክንያቱም ዛሬም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተፈታኝ ተማሪዎች 97 በመቶዎቹ አላለፉም ከሚለው የመጀመሪያ መግለጫው፤ ዘንድሮ ከተፈታኝ ተማሪዎች 94 ነጥብ ስድስት በመቶዎቹ አላለፉም የሚል መጠነኛ የቁጥር ማሻሻያ ላይ ደርሶ ከመገለጥ የዘለለ የሚጨበጥ ርምጃ አልታየበትም፡፡
ይሄ ደግሞ ፖሊሲ ለውጦና አዲስ የትምህርት ፍኖተ ካርታም ቀርጾ ላለፉት ሦስትና አራት ዓመታት እየተገበረ እንዳለም ሆነ፤ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን አጣምሮ በዘርፉ ውጤት ማሳየት ሥራው እንደሆነ አንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ቆም ብሎ ራሱን እንዲፈትሽ፤ እየተመዘገበ ባለው ውጤትም ተማሪዎችን ተጠያቂ ሊያደርግ ሳይሆን የራሱን የሥራ ውጤት ሊገመገምበት የሚገባው ነው፡፡
ምክንያቱም፣ የትምህርት ውድቀትም ሆነ ውጤት የመጀመሪያው ጉዳይም፣ ሥራም የትምህርት ሚኒስቴር ነውና፡፡ ሆኖም ዛሬ ላይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በትምህርቱ ዘርፍ የተፈጠረው ስብራት የሚያስደነግጠው ሳይሆን፤ በስብራቱ ምክንያት በተፈጠረ ችግር በየዓመቱ ከተፈታኝ ተማሪዎች መካከል ከ94 በመቶ የሚልቁት ፈተና ማለፍ አለመቻላቸውን፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪዎች አለማሳለፋቸውን፤ እና መሰል ጉድለቶችን ከመናገር በላይ የማስተካከሉ ኃላፊነት በትምህርት ሚኒስቴር ጫንቃ ላይ የወደቀ ኃላፊነት ነው፡፡
በመሆኑም፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ ከእስከዛሬው ጉዞው ትምህርት ወስዶ፤ በቀጣይ መሰል ሪፖርት ሕዝብ ፊት ይዞ ላለመቅረብ የሚያስችለውን የቤት ሥራ ከወዲሁ ወስዶ መሥራት ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ተማሪዎችን ማሳለፍ ያቃታቸው ሺህዎቹ ትምህርት ቤቶችን ችግር ቀርቦ መረዳትና መፍታት፤ ከመምህራን፣ ከተማሪዎች፣ ከወላጆችና ሌሎችም ለውጤቱ መነሳትም ሆነ መውደቅ ድርሻ ካላቸው አካላት ጋር ተቀራርቦ መሥራት ይኖርበታል፡፡ ጥቂትም ቢሆኑ የተጀማመሩ መልካም ሥራዎችን ማስፋትና አጠናክሮ ማስቀጠልም ይጠበቅበታል፡፡
ምክንያቱም፣ የበርካታ ተማሪዎች መውደቅ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ጨምሮ የዘርፉ ተዋንያን ውድቀት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ይሄ ደግሞ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተማሪዎችን በፈተና የመውደቅ ዜና ከመግለጽ የተሻገረ ከፍ ያለ የቤት ሥራ እንዳለበት የሚያመላክት ነው!
አዲስ ዘመን መስከረም 9/2017 ዓ.ም