አዲስ አበባ:– የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራው ብዙም ዘግይቶ የሕዝብን አመኔታ እንዳያጣ በጣም ፈጥኖ ተገቢ ውይይት ሳይደረግበት ወደ ትግበራ እንዲገባ አይደረግም ሲል ፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ።
የፍትሕ ሚኒስቴር እና የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች ቡድን በትግበራው ዙሪያ ከጋዜጠኞች ጋር ውይይት አካሂደዋል።
በፍትሕ ሚኒስቴር የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሀ ግብር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አወል ሱልጣን፤ ትግበራው ብዙም ዘግይቶ የሕዝብን አመኔታ እንዳያጣ፤ በጣም ፈጥኖ ተገቢ ውይይት ሳይደረግም ወደ ትግበራ እንዲገባ አይደረግም ብለዋል።
ትግበራው ሕዝባዊ ገጽታ እንዲላበስ፣ ገለልተኛ፣ ግልጽ፣ አሳታፊ እና አካታች እንዲሆን ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባ ገልጸው፤ ሀገርን የማዳን፣ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ችግርና ጨለማ ማሸጋገሪያ ድልድይ እንደመሆኑ ሀገር ወዳድ ሁሉ ለትግበራው ትኩረት ሊሰጥ መተባበር እንደሚገባም አቶ አወል አሳስበዋል።
ኅብረተሰቡ በባለቤትነት ሊሳተፍ፣ መገናኛ ብዙኃንም አሳማኝ እና ተጨባጭ መረጃ በማቅረብ ለትግበራው ስኬታማነት ትብብር ሊያደርጉ እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።
በቀጣይ 25 የሚደርሱ ሀገር አቀፍ ውይይቶች እንደሚካሄዱ እና እስከ አምስት ወራት ድረስ ለትግበራው አስፈላጊ ሕጎች ለምክር ቤቱ እንደሚቀርቡም ነው የገለጹት።
በቀጣይ አራት የፍትሕ ተቋማት እንደሚቋቋሙ፣ ምርመራና ክሱ በአዲስ ተቋም እንዲመራ በመወሰኑ ልዩ የዐቃቤ ሕግ ተቋም እንደሚቋቋም፣ ክሱ በልዩ ችሎት እንዲታይ እንደሚደረግም ተጠቁሟል።
አምስት የሚሆኑ አዳዲስ ሕጎች ይወጣሉ። የሕጎቹን መጽደቅ ተከትሎም አስፈላጊ ተቋማቱ እንዲቋቋሙ ይደረጋል ብለዋል። የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች ቡድን አባል አቶ ሲሳይ አስፋው በበኩላቸው፤ ትግበራው ያለጣልቃ ገብነት እየተካሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የሽግግር ፍትሕ ተግባራዊ ለማድረግ አምስት ዋና ዋና ምክንያቶች መኖራቸውንና ሀገራዊ አውድ በተለይም ባለመረጋጋት ውስጥ፣ በእርስ በእርስ ግጭቶች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አሉ። ለእነዚህ ዜጎች ማካካሻ በመስጠት መፍትሄ ማበጀት ስለሚያስፈልግ ነው ብለዋል።
የቀጠሉ የትጥቅ ትግሎችን መፍትሄ ለመስጠት ስለሚያስችል ተግባራዊ ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑ እንደታመነበትም ጠቁመዋል። በሂደቱ ተጠያቂነትን ለማስፈን ከመደበኛ ከፍትሕ ሥርዓቱ ይልቅ በሽግግር ፍትሕ መፍትሄ በመስጠት ወደፊት ለመሻገር ያስችላል። ለፖሊሲ ቀረጻው 80 የሚደርሱ የምክክር መድረኮች መካሄዳቸውንም ተናግረዋል።
ሀገራዊ ግንባታን ለማረጋገጥ፣ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የሚረዳ መሆኑን በመታመኑ መሆኑን ጠቁመው፤ ትግበራው ለሰብአዊ መብቶች መከበር እና ለሕግ የበላይነት መከበር ወሳኝ መሆኑ እንደታመነበትም ነው የተናገሩት።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች፣ ሰዎችን ማፈናቀል፣ አስገድዶ መድፈር፣ በሰው መብት ላይ የሚፈጸሙና ጉልህ የሆኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ ሁሉን አካታች የሕግ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ያቀረቡትን መሠረት ማድረጉን ተናግረዋል።
የፕሪቶሪያው ስምምነትም የሽግግር ፍትሕ ተግባራዊ በማድረግ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ማመልከቱንም ጠቁመዋል።
በርካታ ሀገራት ሂደቱን በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ እንዲተገበር ወስነው ተግባራዊ ማድረጋቸውን በመጠቆምም፤ ኢትዮጵያም ተመሳሳይ በሆነ መልኩ በፖሊሲ እንዲተገበር ወስና እንቅስቃሴ መጀመሯን ተናግረዋል።
ጉልህ በሆኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ ያተኩራል ያሉት አቶ ሲሳይ፤ የወንጀል ተጠያቂነት እንዲሰፍን ይደረጋል። ለሁሉም ጥሰትና ግጭት ምክንያት የነበሩ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የመብት ጥሰቶችን ሽፋን እንዲያገኙ በማድረግ እውነት የማፈላለግ ተግባራዊ እንደሚሆንም ነው ያነሱት።
በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የወንጀል ተሳትፏቸው ጉልህ ያልሆኑ ሰዎች በተጠና መልኩ፣ በሕግ በተቀመጠ አሰራር የምህረት ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሰራር የሚዘረጋ መሆኑንም ነው የገለጹት።
ለተጎጂዎች ማካካሻ እንደሁኔታው ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሥርዓት ፖሊሲው ማመልከቱንና ሕገ መንግሥቱ ከጸደቀበት ከ1987 ዓ.ም አንስቶ የተፈጸሙትን እንዲያካትት ውሳኔ ላይ መደረሱንም ነው የገለጹት።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን መስከረም 9 ቀን 2017 ዓ.ም