ባጎረሰ የተነከሰ እጅ

ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ ነግሳ በቆየችባቸው ወቅቶች የበርካታ ወደቦች ባለቤት ነበረች፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በዋነኝነት አዶሊስ፤ ምጽዋ፤ አሰብ፤ ዘይላ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ዘይላ ሶማሊያ እንደ ሀገር ከመፈጠሯ በፊት ኢትዮጵያ የምትጠቀምበት የባህር በር የነበረና ከዛግዌ መንግሥት ጀምሮ ኢትዮጵያ በወደቡ ስትጠቀም ኖራለች፡፡

አሰብ፤ ምጽዋ እና አዶሊስ የኢትዮጵያ በብቸኝነት ስትጠቀምባቸው የነበሩና ኤርትራ ስትገነጠል አብረው የሄዱ ናቸው፡፡ በተለይም አሰብ ኢትዮጵያዊ አፋሮችን ጨምሮ ከነወደቡ ኢፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ ተላልፈው የተሰጡ ኢትዮጵያ ሀብቶች ናቸው፡፡ ይህ ኢፍትሃዊ ውሳኔም ባለብዙ ወደቦች ባለቤት የነበረችውን ሀገር ከነጭራሹ ወደብ አልባ አድርጎ አስቀርቷታል፡፡

ይህ ደግሞ ሀገሪቱን ለበርካታ ቀውሶች ዳርጓታል። የመጀመሪያው ኢኮኖሚያዊ ጫና ነው፡፡ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ በመሆኗ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች አጋጥመዋታል፡፡ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት አንድ ወደብ አልባና ወደብ ያለው ሀገር በሁሉም ነገር ተመሳሳይ የሆኑ ሁለት ሀገሮች በኢኮኖሚ ዕድገታቸው ሲነጻጸሩ ወደብ አልባው ሀገር 1በመቶ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ወደ ኋላ ይቀራል፡፡ ይህም ማለት ወደብ ያለው ሀገር ኢኮኖሚውን በእጥፍ ለማሳደግ 24 ዓመታትን ሲፈጋበት ወደብ አልባው ሀገር ኢኮኖሚውን በእጥፍ ለማሳደግ 36 ዓመታት ይፈጅበታል፡፡ በሌላም በኩል ወደብ አልባ መሆን ብቻ የአንድ ሀገር የውጭ ንግድ መጠንን ከ33 በመቶ እስከ 43 በመቶ ሊቀንሰው ይችላል፡፡ በዚህ ችግርም ኢትዮጵያ በመፈተን ላይ ትገኛለች፡፡

በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪም ሆነ የእርሻ ውጤቶች የሚመረቱት ከወደብ በራቀ አካባቢ በአብዛኛው በመሃሉና በምዕራቡ የሀገሪቱ ክፍል ስለሆነ እነዚህን ምርቶች ወደ ወደቡ ለማዝለቅ ብዙ ወጪ ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም ከባድ ዕቃ ለማምረት ለሚፈልግ ኢንቬስተር ወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ምርጫ ልትሆን አትችልም፡፡

በሀገር ደረጃ ከላይ የተገለጸው እንዳለ ሆኖ ወደብ አልባነት ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የቀን ተቀን ኑሮ ጋር ቁርኝት አለው፡፡ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ለተከሰተውና በቀኑ እንደሮኬት ለሚወነጨፈው የኑሮ ውድነት አንዱ ምክንያት የወደብ አለመኖር ነው። በየጊዜው በወደብ ላይ የሚጣለው ታሪፍና ቀረጥ መናር ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውንና የሚወጣውን ሸቀጥ ዋጋ እንዲንር እያደረገው ይገኛል፡፡ በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ በምትጠቀምበት የታጁራ ወደብ ላይ በአንድ ቅጽበት እስከ 25 በመቶ የዋጋ ጭማሪ መደረጉ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚናገሩትም ወደብ የሌላቸው ሀገራት ዓመታዊ ዕድገታቸው በ25 በመቶ የተገታ ከመሆኑም ባሻገር ወደብ አልባ ሀገሮች ወደ ውጭ የሚልኳቸው ምርቶች በአብዛኛው በአንድና ሁለት ምርቶች ላይ ብቻ የተወሰኑ ናቸው፡፡ ስለሆነም ከድህነት የመላቀቅ እድላቸው በጣም የመነመነ ነው። የውጭ ባለሀብትም አይመርጧቸውም፡፡ በወደብ ኪራይ እና በትራንስፖርት ምልልስ ለተጨማሪ ወጪ ስለሚዳረጉም ለሸቀጦች ዋጋ መናርና ለኑሮ ውድነት የተጋለጡ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ የባህር በር አለመኖር ለኢኮኖሚና ለልማት ዋነኛ ዕንቅፋት መሆኑን ሁሉም ምሁራን ይስማሙበታል፡፡ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ከሆነች ጀምሮም በየቀኑ ለወደብ ኪራይ ከ3 ሚሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱም ከ1ነጥብ 6ቢሊዮን ዶላር በላይ ታወጣለች፡፡

ሌላኛው የወደብ አልባነት ጉዳት ደግሞ ከዲፕሎማሲ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ወደብ ያላቸውና የሌላቸው ሀገራት እኩል ተደማጭነት አይኖራቸውም። ኢትዮጵያም ከቀይ ባህር ከተወገደች ጀምሮ በዓለም ላይ ያላት ተሰማኒት እየተቀዛቀዘ እንደመጣና በምትኩ ጅቡቲን የመሳሰሉ ትንንሽ ሀገሮች የበለጠ ተሰሚነትን እያገኙ መጥተዋል፡፡

ሶስተኛው ችግር ደግሞ ወደብ አልባ ሀገራት የሚገጥማቸው የሉዓላዊነት ፈተና ነው፡፡ ወደብ አልባ ሀገራት እራሳቸውን ከጠላት ለመከላከል ይቸገራሉ። የራሳቸውም ሚስጢር አይኖራቸውም፡፡ በየዓመቱ ለወደብ ከምታወጣው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በተጨማሪ ለሀገር ስትራቴጂክ የሆኑ ዕቃዎችን ለማስገባት ስትፈልግ የግድ ወደብ የሚያከራየው ሀገር ማወቅና መፍቀድ አለበት፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ሚስጢር ነው ብላ የምትደብቀው ነገር አይኖራትም ማለት ነው፡፡ እንደ ሀገር የምትይዛቸው ሚስጦሮቿ ሁሉ በወደብ ሰጪው ሀገር ዕውቅና ውስጥ የሚያልፉ ናቸው ብለዋል፡፡

ለምሳሌ አስፈላጊ የጦር መሳሪያዎች ኢትዮጵያ ማስገባት ብትፈልግ በወደቡ ባለቤት ዕውቅና ማግኘት አለበት፡፡ በአጠቃላይ ጉዳቱ ከኢኮኖሚ እስከ ሉዓላዊነት ድረስ ነው ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል።

እንደ ኢትዮጵያ ያለች ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ እና በየጊዜው እየደገ የመጣ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር እነዚህን ሁሉ ችግሮች ተሸክሞ እንደ ሀገር ለመቀጠል ትቸግራለች፡፡ ልቀጥል ብትልም አትችልም፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት ስትጓዝበት በነበረው ሁኔታ በአንድ ወደብ ላይ ብቻ ጥገኛ ሆና መኖር ከማትችልበት ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡ ስለዚህም መፍትሔ መፈለጉ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡

ስለዚህም ኢትዮጵያ ሰላማዊ አማራጮችን በመጠቀም ለሁሉም የቀጠናው ሀገሮች የባህር በር ጥያቄዋን አቅርባለች፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ሀገራት ግን በጎ ምላሽ የሰጠችው ሶማሊ ላንድ ብቻ ነች፡፡ ይህንኑ መነሻ በማድረግም የኢትዮጵያ መንግሥት ከሶማሊ ላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፡፡ ይህንን ሁኔታ ግን የሶማሊ መንግሥት በበጎ መመልከት አልፈለገም፡፡ ወይንም ደግሞ የኢትዮጵያን ችግር ለመረዳት ፍላጎት አጥቷል፡፡

ከላይ እንደተገለጸው ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ከሆነችበት ቅጽበት ጀምሮ ለውስብስብ ችግሮች ተዳርጋለች፡፡ እነዚህ ውስብስብ ችግሮች ከዚህ በላይ ከቆዩ ከሀገሪቱ አልፈው የቀጠናው ችግሮች መሆናቸው አይቀርም፡፡ ስለዚህም ችሩ ተባብሶ ቀጠናውን ከማወኩ በፊት ሀገራቱ የኢትዮጵያን ችግር ተባብረው ሊፈቱላት ይገባ ነበር፡፡ ሆኖም በተለይ በሶማሊያ በኩል ያለው ሁኔታ ጸብ አጫሪነት የሚታይበት ነው፡፡

ሶማሊያ መንግሥት አልባ ሆና ለዘመናት ቆይታለች፡፡ ኢትዮጵያ ባደረገችው ጥረት እኤአ ከ2008 ጀምሮ ሶማሊያ መንግሥት መስርታ አንጻራዊ ሰላም አግኝታ ቆይታለች፡፡ ለሶማሊያ መረጋጋትና የሶማሊያን ሕዝብ ለመታደግ ሲባልም ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን አጥታለች፡፡

በፊት ‘AMISOM’ አሁን ደግሞ ‘ATMIS’ እየተባለ በሚጠራው የአፍረካ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ በኩል ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም ጉልህ አስተዋጽኦ ስታደርግ ቆይታለች፡፡ በዚህ ተልዕኮም አብዛኛውን የሶማሊያ መሬት በመሸፈንና ከጥቃት በመከላከል የሶማሊያ ሕዝብ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፤ የሶማሊያ መንግሥትም ተረጋግቶ መንግሥታዊ ሥራዎችን እንዲያከናውን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደተናገሩት 60 በመቶ የሚሆነውን የሶማሊያ ክፍል የሚጠብቀውና ከአልሻባብ ጥቃት የሚከላከለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነው፡፡

ኢትዮጵያ በሶማሊያ ጠንካራ መንግሥት እንዲፈጠር መስዋዕትነት ስትከፍል ቆይታለች። አልሻባብ የሁለቱም የጋራ ጠላት መሆኑ ደግሞ ሁለቱ ሀገራት በጋራ እንዲቆሙ የሚያስገድድ ነው፡፡

ሆኖም አሁን ያለው የሶማሊያ መንግሥት ይህን ሁሉ የተመለከተ አይመስልም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ወደብና የባህር በር ለኢትዮጵያ ወሳኝ መሆኑንና የጎረቤት ሀገራትም ኢትዮጵያን እንዲተባበሯት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም በግልጽ የተቀበለ ሀገር የለም፡፡

ስለዚህም በአሁኑ ወቅት 120 ሚሊዮን ሕዝብ በ2050 አካባቢ ደግሞ በዕጥፍ የሚያድግ ሕዝብ ተይዞ “ስለቀይ ባህር እና ስለ ወደብ አታንሳ፤ ዝም ብለህ ተቀመጥ” የሚል አፋኝ አመለካከት ሊኖር አይገባም፡፡ የሶማሊያ መንግሥት ኢትዮጵያ ከሶማሊ ላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ሰነድ ማክበር አሊያም ደግሞ የራሷን የባህር በርና የወደብ አማራጮች ማክበር ይገባታል፡፡ ከሁለቱ ውጭ መሆን ግን በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን የሚቀበሉት አይደለም፡፡

ሶማሊያ በሺዎች ኪሎ ሜትር የሚቆጠር የባህር በር አላት፡፡ ግን ይህ ሁሉ ኪሎ ሜትር ለሶማሊያ ወደብ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል አይደለም፡፡ ስለዚህም ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን ከፈለገች ወደብ ከኢትዮጵያ ጋር ማልማት ትችላለች። ወይንም ደግሞ ለም መሬት ወስዳ በምትኩ ወደብ ልታቀርብልን ትችላለች፡፡ ብቻ አማራጩ ብዙ ነው፡፡

ዘይላ ሶማሊያ እንደ ሀገር ከመፈጠሯ በፊት ኢትዮጵያ የምትጠቀምበት የባህር በር ነው፡፡ ከዛግዌ መንግሥት ጀምሮ ኢትዮጵያ በወደቡ ስትጠቀም ኖራለች፡፡ ለኢትዮጵያ ቅርበት አለው፡፡ ከሞቃዲሾ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን የሚርቅ ስለሆነ ሶማሊያ ልትጠቀምበት አትችልም፡፡ ስለዚህም መነጋገር ከተቻለ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን የዘይላን ወደብ ኢትዮጵያ ብትጠቀምበትና ሶማሊያም በምትኩ ጥቅም ብታገኝ ሁለቱም ሀገራት አሸናፊ መሆን ይችላሉ፡፡

ከዚህ በተረፈ ግን የኢትዮጵያን ፍላጎት አፍኖ አሸናፊ መሆን አይቻልም፡፡ ለሶማሊያ ሕዝብ በርካታ ውለታ ለዋለችው ኢትዮጵያ በየስፍራው እየዞሩ ስም ማጥፋትና በኢትዮጵያን ላይ ሀገራት የተሳሳተ አቋም እንዲይዙ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት የኢትዮጵያን ውለታ የዘነጋ ነው፡፡

ባለፉት 15 ዓመታት እንደታየውም የሶማሊያን ሰላምና ጸጥታ የማስከበር አቅም ያለው የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይል ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይል በሶማሊያ ተልኮ ወስዶ ከተሰማራ በኋላ አልሸባብ ክፉኛ ከመዳከሙም በላይ በአዲስ አበባ በተካሄዱ ተደጋጋሚ ውይይቶች ሶማሊያ አዲስ የሆነ መንግሥት እንድትመሰርት አስችሏታል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረሰም የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይል 60 በመቶ የሚሆነውን የሶማሊያን ክፍል ከአልሻባብ ጠብቆ መንግስቷም የተሻለ መረጋጋት እንዲኖረው አስችሎ ቆይቷል፡፡

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2008 የሶማሊያ መንግሥት ሲቋቋም ቀድማ ኤምባሲ የከፈተችና ዕውቅና የሰጠችው ኢትዮጵያ ናች፡፡ በተለያዩ ጊዜያትም በሶማሊያ ሰው ሠራሽና ተፈጥሮ አደጋዎች ሲያጋጥሙ የሶማሊያ ሕዝብን በሯን ከፍታ የምትቀበለው ኢትዮጵያ ብቻ ነች፡፡ ታዲያ ይህንን ሁሉ ውለታ ለምትውለው ኢትዮጵያ የሶማሊያ መንግሥት በተቃራኒው እየሰራ ያለው ኢትዮጵያን የማጠልሸት ዘመቻ እንቆቅልሽ ሆኖ ዘልቋል፡፡

ከምስራቅ አፍሪካ ውጭ ያሉ ሀገራት ግን ይህንን የጥላቻ ግንብ አፍርሰው በጋራ ለመልማት ጥረት ሲያደርጉ እያየን ነው፡፡ ለአብነትም ሞዛምቢክ እና ማላዊን ማየት ይቻላል፡፡

በደቡብ የአፍሪካ ክፍል የምትገኘው ሞዛምቢክ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኘውን የናካላ ወደብ፣ ወደብ አልባ ለሆነችው ጎረቤቷ ማላዊ ለማከራየት መስማማቷ ተገልጿል፡፡ ስምምነቱ ለሞዛምቢክ የወደብ ኪራይ ገቢ የሚያስገኝ ሲሆን ማላዊ ደግሞ አዲስ የእቃ ማጓጓዣ ወደብ እንድታገኝ ያስችላታል ተብሏል፡፡

የናካላ ወደብ በማላዊ፣ ዛምቢያ እና ሞዛምቢክ በጋራ እየተገነባ የሚገኝ የናካላ ልማት ኮሪደር አካል ሲሆን የፕሮጀክቱ ዋና አላማ ወደብ አልባ የሆነችውን ማላዊ ለማገዝ እና የቀጣናውን የልማት ትስስር ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

አሊሴሮ

 አዲስ ዘመን መስከረም 9/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You