ወርቅነሽ ደምሰው
ለሰው ልጁ መሠረታዊ ከሆኑ ሦስት ነገሮች መካከል አንዱ መጠለያ ነው። የሰው ልጅ በሚኖርበት ምድር የዕለት ጎርሱን ለማግኘት ተሯርጦ ሠርቶ፤ ጥሮና ግሮ ሲኖር በድካም የዛለ አካሉን ሊያሳርፍበት የሚችል መኖሪያ ቤት ያስፈልጋዋል። አሁን አሁን የመኖሪያ ቤት እጥረት ከመኖሩ አኳያ እንኳን ጎን የሚያሳርፈበት አንገት ማስገቢያ የሆነች ጎጆ ለመቀለስም ሆነ ለማግኘት እጅግ አዳጋች እየሆነ ይገኛል።
በተለይ በከተሞች አካባቢ ቤት የማግኘት እድሉ እጅግ የጠበበ ነው። መዲናችን አዲስ አበባ የቤት እጥረት በስፋት ከሚታይባቸው ቦታዎች በዋናነት የምትጠቀስ ናት። ቤት የመስራት ቀርቶ ቤት ተከራይቶ ለመኖር ያለው አበሳ የደረሰበት ብቻ ነው የሚያውቀው። አብዛኞቹ የከተማ ነዋሪዎችም ያለቻቸውን ጥቂት ጥሪት ለቤት ኪራይ በማዋል የማይለወጥ ህይወት ለመግፋት ተገደዋል። አብዛኞቹ የቤት ተከራዮች በጣም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሲሆኑ ዛሬ ላይ እየተስተዋለ ካለው የኑሮ ንረትና ተደራራቢ ችግሮች ጋር ተያይዞ ለመኖር አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ኑሮን ይገፋሉ።
የቤት ኪራይ ከግለሰቦች በመከራየት ህይወታቸውን እየገፉ ከሚገኙት የህብረተሰብ ክፍሎች ባሻገር ሌላው የከተማዋ መገለጫ የሆኑት የቀበሌ ቤት ተከራይተው የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው። እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ከግለሰብ ተከራዮች ሻል ያለ እና የተረጋጋ ህይወት ቢኖራቸውም ማህበራዊ ህይወታቸውን የሚፈትኑና ለኑሮ ብዙም የማይመቹ ተግዳሮቶችን መቋቋም ይጠበቅባቸዋል።
የቀበሌ ቤቶቹ ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ ከመሆናቸው በላይ በጣም ያረጁና የከተማውን ውበት የጠበቁ ካለመሆናቸው ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች ቢኖሩም ነዋሪዎቹ አቅማቸው በፈቀደ መጠን በማደስና በመጠጋገን ኑሮን በመግፋት ላይ ይገኛሉ።
የቀበሌ ቤቶች ከቦታ ጥበት በላይ እጅግ የተጠጋጉና የተቀራረቡ ከመሆናቸውም ባሻገር ነዋሪዎቹን በጋራ የሚያስተሳሰራቸው በርካታ ጉዳዮች አሏቸው። ለአብነት መጸዳጃ ቤት፤ የልብስ ማስጫ ገመዶች፤ የጋራ ማብሰያ እና የመሳሰሉት በጋራ ከሚጠቀሟቸው ነገሮች ውስጥ መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ጉዳዮች የቀበሌ ቤት ነዋሪዎችን እርስ በእርስ በማስተሳሰር፤ በመግባባትና በመተሳሰብ እንዲኖሩ የግድ ከሚሏቸው ነገሮች መካከል ናቸው።
የቀበሌ ቤት ነዋሪዎች አካባቢያቸው በጋራ የማፀዳት፤ በጋራ የሚጠቀሙበትን መጸዳጃ ቤት የማፅዳት እና ሲሞላም የማስመጠጥ ተግባራትን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል። ነዋሪዎች የግድ መስማማት የሚጠበቅባቸው በተለይ የጋራ መጠቀሚያቸው ለሆኑ ነገሮች ነው። ይሁን እንጂ በቀበሌ ቤት አማካይነት በጋራ በሚኖሩ ነዋሪዎች በአብዛኛው ቦታ ንጽህና ለኑሮ ምቹ የሆነ አካባቢ ከመፍጠር አኳይ የፉክክር ቤት ሳይዘጋ አደረ የሚለውን ቢሂል ሲያስታወሱን ይስተዋላል። ይህ የምንአገባኝ ስሜት ቀጥሎ ጤናን ሊጎዳ የሚችል ሁኔታ ላይ የሚደርሰበት ፈሳሾች የሚለቀቁበት አጋጣሚዎችን ይፈጥራል።
የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት የአካባቢ ደህንነት መብት አስመልክቶ በወጣ አዋጅ አንቀጽ 44 ላይ ሁሉም ሰዎች ጤናማና ንጽህ አካባቢ የመኖር መብት አላቸው ብሎ ደንግጓል። ይሁን እንጂ አንዳንዱ ነዋሪዎች ይህንን ህገ መንግሥት ላይ የተቀመጠ አዋጅ በማወቅም ሆነ በቸልተኝነት እየጣሱ አካባቢያቸው የሚኖሩ ነዋሪዎች ላይ ችግር ሲያደርሱ ይስተዋላል። ይህ ችግር በነዋሪው ህብረተሰብ ላይ ከሚያደርሰው የተለያዩ የጤና ጉዳቶች በተጨማሪ ሰርቶ የመለወጥ ብሎ የመኖር ህልውናን ቀስ በቀስ አደጋ ላይ በመጣል አምራች የሆኑ ዜጎችን ኃይል በመቀነስ የሰው ሸክምና የመንግሥት ተረጂ የሚያደርጉበት አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው።
በተለይ እንደ መዲናችን አዲስ አበባ ባሉ በርካታ የህዝብ ብዛት የሚኖርባቸውና የመኖሪያ ቤት ጥበት ያለባቸው ቦታዎች በመጸዳጃ ቤት ፈሳሽ ጋር ተያይዞ አስከፊ የጤና እክል የገጠማቸው የሚኖሩ ነዋሪዎች የሚገኙበት መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።
በዛሬው የፍረዱኝ አምዳችንም በዚሁ በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ርግብ ሆቴል አካባቢ ከሚገኝ አንድ መንደር በቀበሌ ቤት የሚኖሩ ነዋሪዎችን ዘንድ ይወስደናል። የእነዚህ ነዋሪዎች ቅሬታ መንታ ገጽታ ያለው ሲሆን፤ መነሻው መግቢያ በር አካባቢ ያለ ዛፍ መንገድ በመዝጋት የመጸዳጃ ቤት ፈሳሽ አገልግሎት የሚሰጥ መኪና ወደ ውስጥ እንዳይገባ መከልከሉ ነው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ነዋሪዎች ለከፋ የጤና ችግር የተዳረጉበት፤ የእሳት አደጋ ቢከሰት የእሳት አደጋ መኪና መግባት የማይችልበት፤ ድንገት ሰው ቢታመምና ለነፍሰ ጡር እናቶች አምቡላንስ መግባት የማይችልበት፤ ሰው ቢሞት አስከሬን የሚወስድ መኪና ለማስገባት እጅግ አዳጋች መሆኑን ለተደራራቢ ችግሮች መጋለጣቸውን ይናገራሉ።
ይህንን የነዋሪዎቹ ቅሬታ ለአንባቢያን ስናቀርብ የአብዛኛው ቀበሌ ቤቶች ነዋሪዎች ጓዳ ጎድጓዳ የሚያሳይ በመሆኑ ችግሮች ተባብሶ ሥር ሳይሰድ በእንጭጩ ለመቅረፍ ይረዳ ዘንድ በማሰብ ነው። የዝግጅት ክፍላችንም የነዋሪዎቹን ጥቆማ ተከትሎ የነዋሪዎችን ቅሬታ ለመመርመር ቦታ ድረስ በመገኘት የተመለከተውንና ከነዋሪዎች ያዳመጠውን ቅሬታ ይዞ የቀረበ ሲሆን፤ ፍርዱን ለእናንተው በመተው፤ የቅሬታ አቅራቢዎቹን እሮሮና ምሬት በማዳመጥ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት አስተያየትና ምላሹን ጨምረን እንደሚከተለው ልናስቃኛችሁ ወደድን።
ጉዞ ወደ ቅሬታ አቅራቢዎች ሰፈር
የዝግጅት ክፍላችንም የነዋሪዎቹን ጥቆማ ከሰማ በኋላ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ዕለቱ አርብ ታህሳሳ 2 ቀን 2013 ዓ.ም አራት ኪሎ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ድርጅቱ ህንጻ ከጠዋቱ 3፡30 ላይ ተነስተን ጥቆማው ወደ ደረስን አዲሱ ገበያ አካባቢ ወደሚገኘው ሳሪም ሆቴል ተገኝተናል። ጥቆሞውን ያደረሱን ነዋሪ የእኛ መድረስ በመጠባበቅ ላይ ናቸውና ወደ ሰፈሩ የሚያስገባው አስፓልት መንገድ በመኪናችን ከተጓዝን በኋላ መኪናችን አንድ ጥግ ላይ አቁመን በጠቋሚያችን መሪነት ከአስፓልት ገባ ብሎ ወደ ሚገኘው ቀጠና አራት ርግብ ሆቴል አካባቢ ወደሚገኘው ሰፈር ገባን።
ሰፈሩ ከአስፓልት ብዙ የማይርቅ በመሆኑ ወደ ውስጥ የሚያስገባው ኮብልስቶን መንገድ በቀኝና በግራ ከሚገኙት መግቢያ መንገዶች ጎንና ጎን ላይ የተተከሉ አትክልቶችና ዛፎች መኖራቸውን አስተውለናል።
እነዚህ አትክልቶችና ዛፎች ያሉበት ቦታ ንጹህና ጥሩ መዓዛ ያለው ሽታ ተቀብሎን ወደ ውስጥ መራን። ከኋላችን ያለውን ጥሩ መዓዛ እያሰብን እግር ወደፊት ነውና የሚጓዘው በጠቋሚያችን አማካይነት ወደ ውስጥ ዘለቅን ብዙም ሳንርቅ ከፊት ለፊታችን መውረጃ ላይ የሚገኝ ፈሳሽ ተመለከትን። ታዲያ የሚገርመው ክረምቱ ወጥቶ እንኳን ቦዩ ባዶውን አይደለም፤ ይልቁን ጥቁር መልክ ያለው አፍንጫን የሚሰነፍጥ ሽታ አካባቢውን አጥለቅልቆታል።
ከዚሁ ፈሳሽ መውረጃ ቦይ ትንሽ ከፍ ብሎ አጠገብ የተቀመጡ በርካታ የግቢው ነዋሪዎች ይታያሉ። ከእነዚህ ውስጥ አዛውንቶች፣ ህጻናት፣ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች በተለያየ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች ይታያሉ። ነዋሪዎቹ በእለት ተእለት ተግባራቸው ተጠምደዋል። ገሚሱ በርበሬ ያሰጣል፤ ገሚሱ ቅመማ ቅመም ይለቅማል፤ ገሚሱ እቃ የሚያጥብ ሲሆን፤ እንዲሁም አዛውንቱ ቁጭ ብለው ያወጋሉ። ህጻናቱ በራሳቸው እየተጫወቱ ይታይሉ። ይህ ሁሉ የሚሆነው በዚያች ጠባብ ግቢ ውስጥ ነው። ቤቶቹ ጎን ለጎን ያሉ ከመሆናቸው የተነሳ አንድ ቤት እንጂ በርካታ ቤቶች መሆናቸውን የሚታወቀው በራቸው ሲታይ ብቻ ነው።
የግቢው ነዋሪዎች እየከወኑ ካሉት የእለት ተግባራቸው እኛን ሲያዩ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት በደስታ ተቀበሉን። ወደ እነሱ ለመሻገር ቦዩን መሻገር የግድ ይላል። ቦዩ በቤቶቹ መሀል አቋርጦ የሚሄድ ሲሆን በፈሳሽ መውረጃው የሚፈሰው አፍንጫ የሚሰነፍጠው ፈሳሽ መነሻው የት እንደሆነ ለማወቅ አይቻልም። ይሄ የቦይ ፈሳሽ ውሃ አንደኛው የነዋሪዎቹ ቅሬታ አካል ነው። በፈሳሽ መውረጃ ቦይ የሚመጣው ፈሳሽ ከጎረቤት የሚፈስ የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽ ነው። በአንደኛው ነዋሪ ቤት በእቃ ቤት በኩል አልፎ የሚፈሰው ፈሳሽ በአብዛኛው ነዋሪ በር ላይ የሚያልፍ ነው፤ የሽታው ነገር አይወራም።
ልክ ይህንን የመጸዳጃ ቤት ፈሳሽ መውረጃ ቦይ እንዳለፍን በስተቀኝ በኩል አራት በር ያለው አንድ መጸዳጃ ቤት ገንፍሎ እየፈሰሰ ይታያል። ይህ ደግሞ ከባዱና ሁለተኛው የነዋሪዋቹ የቅሬታ ምንጭ ነው። እዚህ አካባቢ እንኳን ለመኖር ቀርቶ ለአፍታም ቢሆን ለመቅረብ እጅግ ከባድ ነው። ሽታው ግቢ ውስጥ የማያስቆይ ቢሆንም የዕለት ዕለት ኑሮአቸውን እዚያ የሆነ ከህጻናት እስከ አዛውንት ያሉት ነዋሪዎች እያየሁ መቆየት ግድ ሆኖብናል። ይልቁንም የቅሬታውን ምንነትና መንስኤ እውነተኛ ምንጮች ከሆኑ ከነዋሪዎች አንደበት ለመስማትና ለማጣራት ይረዳ ዘንድ አስተያየታቸውን እንደሚከተለው አቅርበናል።
ከቅሬታ አቅራቢዎች አንደበት
የዚሁ ሰፈር ነዋሪ ከሆኑት መካከል አቶ ያደቴ ሁሬሳ ከ30 ዓመት በላይ በግቢ ውስጥ መኖራቸውን ይናገራሉ። ቅሬታ አቅራቢ ትልቁ ችግራቸው የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም ምክንያቱ መኪና የሚገባበት መንገድ መታጣቱ መሆኑን ይናገራሉ። ከውሃና ፍሳሽ የመጸዳጃ የፈሳሽ አገልግሎት የሚሰጠው ትልቁ መኪና በመምጣት ፈሳሹን ለመምጠጥ ሞክሮ ነበር፤ ነገር ግን ይህ ዛፍ ካልተቆረጠ መስታወት ይመታብኛል ብሎ በመናገር ወደ መጣበት የተመለሰ ሲሆን፤ ‹‹ ዛፉን ከተቆረጠ በኋላ ጥሩኝ ›› ብሎ እንደሄደ ይናገራሉ። በድጋሚም ለውሃና ፍሳሽ ካመለከትን በኋላም መኪና ተመልሶ በድጋሚ ቢመጣ ለመግባት ስላልቻለ መመለሱን ይናገራሉ።
በመጨረሻም በሦስተኛው ጊዜ የመጣችው ትንሿ መኪና ገብታ በስንት መከራ ፈሳሹን ከመጠጠች በኋላ በግድ የወጣች ሲሆን፤ ሹፌሩ ይህ ዛፍ ካልተነሳ ሁለተኛ እንዳትጠሩኝ ዳግም አልመጣም ብሎ መሄዱን ጠቁመው፤ በዚህ ሁኔታ እንደምታዩት መኪና መግባት አይችልም ብሎ ማስታወሻ ጽሁፍ እንደሰጣቸው ተናግረዋል።
አቶ ያደቴ እንደሚሉት፤ የግቢው ነዋሪዎች ከ12 በላይ አባወራዎች ከነቤተሰቦቻቸው በአጠቃላይ ከ60 ሰዎች በላይ የሚኖሩበት ሲሆን፤ መጸዳጃ ቤቱ በርካታ ተጠቃሚዎች ስላለው ወር ሳይሞላ ወዲያውኑ እንደሚሞላ ይገልጻሉ። በዚህ የተነሳ መጸዳጃ ቤቱ ሞልቶ የሚፈሰው ፍሳሽ ከእኛ በታችኛው በኩል ከሚኖሩ ነዋሪዎች ጋ በቀጥታ ስለሚሄድ ሁልጊዜ እንደሚከሷቸው ተናግረዋል። ‹‹እኛም ይህ መጥፎ ሽታ የኛን ጤና የሚያውከው አንሶ የሌላውን ነዋሪ ህይወት ለአደጋ እንዲያጋልጥ አንፈልግም።›› ሲሉ ችግሩ ለብዙዎች መትረፉን ያስረዳሉ።
አክለውም የዚህ ግቢ አብዛኛው ነዋሪ አቅመ ደካም ነው። ‹‹ እኔን እንደምታየኝ አንድ እግሬን ያመኛል፤ በክራንች ነው የምሄደው። ተንፏቅቄም ቢሆን ወረዳ መሄድ አያቅተኝም ነበር። ወክለን የላክናቸው ሰዎች ሆነ በየጊዜው እየመጡ የሚመለከቱት የወረዳው ሰዎች መፍትሔ ከማበጀት ይልቅ ነጋ ጠባ መመላለስ ስራቸው ሆኗል›› በማለት በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 4 አስተዳደር ችግራቸውን እንዳልፈታላቸው ይናገራሉ። የውሃና ፍሳሽ ሠራተኞች እንዳሉት፤ ‹‹ይሄ ዛፍ ካልተነሰ አልገባም ብራችሁ በከንቱ አታወጡ፤ ዝም ብላችሁ አትድከሙ ብለውናል። የግድ መኪና ገብቶ ፍሳሹን እንዲያስወግድ ከተፈለገ ዛፉ እንዲቆረጥ እና መንገዱ ክፍት እንዲሆን የሚያስፈልግ መሆኑ ጠቁመው፤ ዛፉን የተከለውን ሰው እንዲቆርጥ ቢጠይቁትም ቆርጫለሁ ብሎ ቅጠሉን ነካ ነካ አድርጎ ትቷል ብለዋል።
እንደ አቶ ያደቴ ገለጻ፤ ከዚህ ሌላም ትልቅና ዋና አሳሳቢ ስጋት እንዳለባቸው ይናገራሉ። የሰው ልጅ በህይወት እንዳለ በተለያዩ አጋጣሚዎች ውስጥ ማለፉ የግድ ነው። ለምሳሌ ድንገት የእሳት አደጋ ቢከሰት የእሳት አደጋ መኪና እንዲገባ፤ በድንገት የታመመ ሰው ኖሮ አምቡላንስ ቢያስፈልግ፤ እንዲሁም ሰው ቢሞት አስከሬን እንኳን ለማውጣት መኪና የማይገባበት በመሆኑ ከችግርም በላይ የሆነ ችግር ነው የገጠመን ይላሉ።
ከሁለት ወር በፊት ለመጨረሻ ጊዜ የመጣችውን ትንሿ መኪና እንኳን መግባት ያልቻለችውን እንዴት ትልቅ፣ መኪና መግባት ይችላል ብለው ይጠይቃሉ። ስለዚህ መፍትሔ ከጤናና ከማህበራዊ ህይወታችን የሚበልጥ ነገር የለምና ቢታሰብበት ጥሩ ነው። የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል።
ሌላኛዋ ከ50 ዓመታት በላይ በዚህ አካባቢ እንደኖሩ የሚናገሩት ወ/ሮ አየለች አበበ በበኩላቸው፤ እነዚህ ቤቶች የቀበሌ ቤት በመሆናቸው መፀዳጃ ቤት የጋራ ስለሆነ በተደጋጋሚ እንደዚያ አይነት ችግር ይገጥመናል። ይሁን እንጂ በየጊዜው መጸዳጃ ቤቱ ሲሞላ ለማስመጠጥ ችግር አልነበረብንም።
የአሁን ችግሩ ባስ እንዲል ያደረገው ግን፤ የሁለቱ መጸዳጃ ቤት ፍሳሽ በአንድ ላይ መምጣቱና ለማስመጠጥ ያልቻሉበት ሁኔታ በማጋጠሙ እንደሆነ ይናገራሉ። መኪናው በበር ላይ የተተከለ አበባና ዛፍ ምክንያት አድርጎ አለመግባቱና ከአንዴም ሁለትና ሦስት ጊዜ አትክልትና ዛፉ በማደጉ ምክንያት ብንለምናቸውም ዛፉ ካልተቆረጠ አልገባም ብሎ መሄዱን ችግሩን እንዳባባሰውና ዞሮ ዞሮ ችግሩ አለመቀረፉን ተናግረዋል።
አክለውም፤ የዛፉ ባለቤቶችም የዚሁ የመጸዳጃ ቤቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፤ የእነሱ ቤት መግቢያ በር ላይ ከዳር በኩል ላይ በመሆኑም ሽታው ስለማይደርስባቸው እኔን ካልነካኝ በሚል ስሜት ለመቁረጥ ውዝግብ መፍጠራቸውን ይናገራሉ። ‹‹ እኛ የመጸዳጃ ቤቱን ፈሳሽ ለማስመጠጥ ገንዘብ አሰባስበን ስንሄድ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ተቀጥተናል። የተቀጣንበትም ምክንያት ዛፉን ሳታስቆርጡ ለምን ውሃና ፍሳሽ መኪናን ትጠራላችሁ በሚል ነው። ስለዚህ በአንዲት ዛፍ ምክንያት ህይወታችን እየታመሰ ነው›› ሲሉ ምሬት የተቀላቀለበት ሀሳብ ሰንዝረዋል።
በተመሳሳይ ደግሞ የኛ የመጸዳጃ ቤት ፈሳሽ ደግሞ ወደ ሌላ ግቢ እየፈሰሰ ይገኛል የሚሉት ወ/ሮ አየለች፤ ፈሳሹ የሚፈስባቸው ሰዎች እኛን እየከሰሱን እያስቀጡን ነው። ‹‹ለምን አላስመጠጣችሁም፤ ማስመጠጥ አለባችሁ ተብለን ተከሰናል።›› በሌላ በኩል ከሌላ ቦታ ግቢው የሚፈሰው የመጸዳጃ ቤት ፈሳሽ ያለ ሲሆን፤ እኛን የተጠላለፈ ችግር ውስጥ እንደሆንን ሊታወቅ ይገባል።
እና መፍትሔ የሚሰጠን አካል አጥተናልና የመፍትሔ ያለህ እንላለን። እስካሁን የደረሰብን ችግር እጅግ በርካታ ነው በቃ ልንባል ይገባል›› በማለት በምሬት ይናገራሉ። መጸዳጃ ቤቱ በሁለት በኩል ሞልቶ በሰው ላይ እየፈሰሰ በመሆኑ የሚመለከተው አካል መፍትሔ ይሰጠን ዘንድ እንጠይቃለን ሲሉ ተናግረዋል።
ሌለኛዋ ለ10 ዓመታት ያህል በግቢው ነዋሪና የወረዳው የቀጠናው ኮሚቴ አባል የሆኑት ወ/ሮ ምንትዋብ ታምሩ በበኩላቸው፤ ይህንን ያጋጠማቸውን ችግር በተደጋጋሚ ማመልከታቸውን ይናገራሉ። አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት አካባቢ የሚመለከታት ጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኛ መጥታ በማየት ችግሩን መፍታት ስላልቻለች ከአቅሜ በላይ ነው ብላ ለወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ማስተላለፏን ትጠቁማለች። ሌሎችም የወረዳ አመራሮችን ጨምሮ ቦታው ድረስ በተደጋጋሚ በመምጣት ቢያዩም፤ መፍትሔ የሰጣቸው አካል እንደሌለ ምንትዋብ ትናገራለች።
በዚህም ምክንያት ህጻናት ልጆች መታመማቸውንና እሱንም ሄደው ለወረዳው ማስታወቋን ትናገራለች። ህጻናቱ በየቀኑ በጉንፋን የሚታመሙ በመሆኑ ወደ ሀኪም ቤት ማመላለስ የተሰላቹበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁማ፤ ወደ ህክምና ተቋም በሚወሰዱበት ጊዜ ይድናል እንደገና ተመልሶ ይነሳል። በመሆኑም ሀኪሞቹም ችግራቸው አላርጂክ መሆኑን ተረድተው ሽታ ካለበት ቦታ ቦታ አርቋቸው የሚል ምክር ይሰጡናል፤ እኛ ግን ልጆቻችንን የት እናድርሳቸው ስትል የችግሩን አሳሳቢነት ታስረዳለች።
አክላም በግቢው የሚኖሩት ነዋሪዎች ደካሞች አቅም የሌላቸው አዛውንቶችና ህጻናት የሚበዙበት ግቢና መኖሪያ አካባቢ በመሆኑ ዋናው ችግራቸው መፀዳጃ ቤት ሞልቶ የመፍሰሱ ጉዳይ ቢሆንም፤ ፍሳሽ በበራቸው ላይ በቤት ውስጥ የሚያልፍበት ሁኔታ መኖሩን ታስረዳለች።
መጸዳጃ ቤት የጋራ በመሆኑ በርካታ ሰዎች የሚጠቀሙበት ሲሆን፤ ቶሎ ቶሎ የሚሞላበት ሁኔታ መኖሩን የምትገልጸው ምንትዋብ፤ ከላይ በኩል መጸዳጃ ቤት ፈንድቶ በቱቦ በኩል ወደ ግቢ እየፈሰሰ ያለ ፈሳሽ መኖሩን አመላክታለች። ይሁን እንጂ በየቀኑ የደንብ ጽህፈት ቤት ሠራተኞች በመምጣት የሚያዩት ቢሆንም፤ ምንም አይነት መፍትሔ ሊሰጡና አጥጋቢ የሚሆን መልስ ሊሰጣቸው እንዳልቻሉ ትናገራለች።
በግቢው የሚገኙ በርካታ ልጆች በአላርጂክ እየቆሰሉ የጤና እክል እየገጠማቸው ቢሆንም፤ የተወሰኑ ተወካዮች ና ሁለት እርጉዝ እናቶች ወደ ወረዳ ሄደው ችግራቸውን ቢናገሩም መፍትሄ አላገኙም። በዚህ ምክንያት ልጇ አላርጂክ እየታመመ የተቸገረች እናት ቤቷን ለቃ ተከራይታ እየኖረች መሆኗን ገልጻ፤ ልጆቹ በተደጋጋሚ ሳል ስለሚይዛቸው በየጊዜው ወደ ህክምና በማመላለስ ለተጨማሪ ወጭ መዳረጋቸውን ትጠቁማለች።
‹‹እኔ የቀጠና ኮሚቴ እንደመሆኔ ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ለወረዳው በየስብሰባ በመናገር፤ የማሳወቅና መጥተው እንዲያዩ ማድረግ ስራ ሰርቼ ነበር መፍትሔ ይዞ ባይመጣም የምትለው ምንትዋብ፤ በተለይ ኮቪድ ወረርሽኝ ሀገራችን ከገባ በኋላም እንኳን በጣም እየፈሰሰ ስለነበር በጣም ስጋት ውስጥ እንደነበሩም ታስረዳለች። በቅርብ እንኳን‹‹ መፍትሄ መስጠት የማትችሉ ከሆነ የምናመለክትበት መንገድ አሳዩን ብለን ሄደን ነበር ›› ብላ የምትናገረው ወ/ሮ ምንትዋብ እስካሁን ግን አንዳች መፍትሄ እንዳላገኙ ታስረዳለች።
የደንብ ጽህፈት ቤት ሠራተኞች መጥተው በሚያዩበት ጊዜ ፈሳሽ የሚመጣበት ቦታ ባለቤት የሆኑት ሴት የኔ አይደለም በቱቦ ከሌላ ቦታ የመጣ ነው በማለት የሚከራከሩ ሲሆን፤ ይህንን ከየት እንደሚፈስ የሚመረምር ባለሙያ እንልክላችኋለን ብለው ከሄዱ በኋላ በዚያው የውሃ ሽታ ሆነው እንደሚቀሩ ነው የምትናገረው።
መጸዳጃ ቤት ፈሳሽ ችግር ከወረዳ አቅም በላይ ሆኖ አይደለም የምትለው ወ/ሮ ምንትዋብ፤ ይህ የሚያሳየው የመልካም አስተዳዳር ችግር ከወረዳ ጀምሮ መኖሩን ነው። ወረዳው ይህንን መፍታት የሚችል ወረዳ ከመሆኑም በላይ በጣም ቀላልና እጁ ላይ ያለው ነገር ነው። ደንቦች በተደጋጋሚ መጥተው ያዩታል ተነጋግረው ከመፍታት ይልቅ ችግሩን ችግራቸው ባለማድረጋቸው ህብረተሰቡ በስቃይ ለመኖር ተገዷል።
የችግሩ ተጠቂ ከሆኑት ነዋሪዎች መካከል
በዚህ ፈሳሽ ምክንያት ጉዳት ከደረሰባቸው ወላጆች መካከል ወ/ሮ ሽሙ መንግሥቱ አንዱ ናት። ህጻን ልጅ ይዛለች። ‹‹ልጄ ከተወለደ ከስድስት ወር በኋላ ነው የጤና እክል የገጠመው አሁን የአንድ ዓመት ከስድስት ወር ልጅ ሲሆን፤ በተደጋጋሚ በመታመሙ ምክንያት ወደ ህክምና ተቋም ስወስደው አላርጂክ ነው ይሉኛል ››ትላለች። ‹‹አካባቢያችሁ ላይ ሽታ ያለው ነገር አለ ወይ ›› ብለው ሀኪሞች እንደሚጠይቋት ጠቅሳ፤ የመፀዳጃ ቤቱ ፈሳሽ በፈጠረው ችግር ምክንያት ልጁ እግር ላይ የወጣ ቁስል አላርጂክ እጅግ የከፋና ሁልጊዜ የሚያሳክከው መሆኑን ትገልጻለች።
በዚህም ምክንያት በርካታ የህክምና ተቋማት ይዛ ብትሄድ ለልጇ ስቃይ መፍትሔ አለማግኘቷን ጠቁማ፤ በዚህም የተነሳ የልጇ ስቃይ የዘወትር ስቃይ በመሆኑ እረፍት እንደነሳት ትናገራለች።
ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት
ነዋሪዎቹ የፈሳሽ አገልግሎት ለሚሰጠው የተመደበው መኪና የመጸዳጃ ቤቱን ፍሳሽ ለመምጠጥ በተደጋጋሚ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ተመላልሶ ዛፉ አያስገባኝም ብሎ መመለሱን ይገልጻሉ። በቀጣይ ጊዜ በትንሿ መኪና ተገብቶ ፈሳሹን ማንሳት ብትችልም መኪናዋ የምትይዘው መጠን ትንሽ በመሆኑ መጸዳጃ ቤቱ ተመልሶ ወዲያውኑ መሙላቱን ይናገራሉ። በመጨረሻ ከሁለት ወር በፊት ፈሳሹን ለመምጠጥ የመጣችሁ ትንሿ መኪና በትግል መግባቷን ገልጸው፤ ‹‹ በር ላይ ያለው መግቢያ ቅጠሉ (አትክልቱ) ወጣ ያለ ስለሆነ፤ ከዚህ በፊት መጥተን ተመልሠናል ተቀጥተናል አሁንም በመከራ ነው የገባነው መብራት እስፖኪዮውን ሰብሮብናል። ለሚቀጥለው ይህ ካልተነሳ የማንሠራ መሆኑን ይወቁልን ሲሉ›› በቀን 25/01/2013 ዓ.ም የተጻፈ ማስታወሻ እንደሰጧቸው ይናገራሉ።
መንገድ የዘጋው ዛፍ ባለቤት ምላሽ
ወ/ሮ ታደለች በረዳ ትባላለች። መንገድ የዘጋው ዛፍ ባለቤት ናት። ይህ ዛፍ ከተተከለ ከ5 ዓመት በላይ ሆኖታል፤ በጋ ላይ ቅርንጫፉ በስፋት በአደገበት ጊዜ እንኳን መኪና ገብቶ ፈሳሹን መምጠጥ ችሎ እንደነበር ትናገራለች። አሁን ላይ ደግሞ ተከርክሟል። ፍሳሹ ለማንሳት የመጣው መኪና በዚህ ዛፍ ምክንያት ሳይሆን የተመለሰው ሹፌሩ የራሱ ችግር ስላለበት ነው ትላለች።
ይሁን እንጂ ዛፉ ችግር ከሆነ ከላዩ ቅርንጫፉን አስቆርጠነዋል ይህም ሆኖ ሁሉም ካልተነሳ መኪናው መግባት ካልቻለ አሁን ሁሉንም ለማንሳት እኔም ባለቤቴም ፈቃደኛ ነን ትላለች። ነዋሪዎቹ በበኩላቸው፤ መኪናው ዛፉ ሙሉ ለሙሉ ካልተነሳ አልገባም ስላለ የሚነሳ ከሆነ ብቻ ነው ብራችንን ከፍለን መኪናው የምናስመጣው ካልሆነ ግን፤ ብራችንን ከፍለን ለቅጣት አንዳረግም፤ ደግሞስ እንዴት መኪና ቆሞ ዛፍ ይቆረጣል ሲሉ ይጠይቃሉ።
የወረዳ 4 አስተዳደር ምላሽ
በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 4 ምክትል ሥራ አስፈጻሚና የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ኃላፊ አቶ አብዱልጀሊል መዲ ናቸው። የቀጠና አራት የነዋሪዎቹን መንገድ መዘጋት ምክንያት ባጋጠማቸው በፈሳሽ ዙሪያ እያቀረቡ ያለውን ቅሬታ ሰምተዋል ወይ ስንል ጠየቀናቸው ። ‹‹ ኧረ በፍጽም አሁን ገና መስማቴ ነው።
እኔ እዚህ ወረዳ ከመጣሁ አንድ ወር ሆኖኛል፤ ነገር ግን ይህንን ችግር ያደረሰኝም አካል ሆነ የደረሰኝ ማመልከቻ የለም፤ የቀረበም ቅሬታ የለም›› ይላሉ። ‹‹ሆኖም ግን ከእናንተ እንደሰማሁት የነዋሪዎች ችግር ከባድ በመሆኑ ችግሩ ውሎ ማደር የለበትም፤ አሳሳቢ የጤና ጉዳይ የሚያስከትል በመሆኑ ስለዚህ አሁኑኑ እናንተ እያላችሁ ኮሚቴ በማዋቀር ጉዳዩን ለመፍታት እንሰራለን ››ብለዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ እስከ ቀጠና ኮሚቴ ድረስ በመውረድ የሚመለከተው አመራር ጭምር የጽህፈት ቤቱ ባለሙያዎችና የጉዳዩ ባለቤት ከሆኑ ነዋሪዎች ጋር በመሆን በአስቸኳይ መፍትሔ መሰጠት አለበት። የነዋሪዎቹ ችግር አሳሳቢ በመሆኑ የእሳቸው አዲስ መሆን ከግምት ውስጥ መግባት እንደሌለበት ጠቁመው፤ እስካሁን ለምን አልተፈታም ሳይሆን ዛሬ ህዝቡን የሚያሰቃይ የጤና ችግር እስከሆነ ድረስ ውሎ ማደር እንደሌለበት ይናገራሉ። እናም በእርግጠኝነት ችግሩን በግል ብቻ ሳይሆን በጽህፈት ቤት ደረጃ መፍታት የሚችሉ መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም የመጸዳጃ ቤቱን ፍሳሽ ለማስመጠጥ እንደችግር የሚነሳውን የመንገድ ላይ ዛፎችን በተመለከተ ዛፉ ባለቤት ህጋዊ ካርታ ያለው ከሆነ በመስማማት እንዲግባቡ የሚደረግበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው፤ አይ አሻፈረኝ የሚል አካል ካለ ግን መንገድ የመሠረተ ልማት ስለሆነ ለሰፊ ህዝብ ጥቅም ሲባል የግል መብት ሊነካ የሚችል መሆኑን አመልክተዋል። ሌላው ደግሞ ቦታው የቀበሌ ከሆነ ወዲያውኑ ከሚመለከተው ጽህፈት ቤት አካላት ጋር በመሆን መፍትሔ የሚሰጥበት ሁኔታ መኖሩን አመልክተዋል።
‹‹መንገድ የዘጋውን ዛፍ በመቁረጥ መንገድ ማስከፈት የጽህፈት ቤቱ ኃላፊነት ነው›› ያሉት ኃላፊው፤ እዚያ ያለው አመራር ይህንን የማይሰራ ከሆነ ወንበር ይዞ መቀመጡ ብቻ ዋጋ የለውም። ስልጣን መገልገያ ሳይሆን ማገልገያ ነው መሆን ያለበት፤ ማገልገያ ሲባል ደግሞ ጥበብ በተሞላበት መልኩ ማህበረሰቡን ችግር ውስጥ በማያስገባ ለሁሉም ወገኖች በማመጣጠን ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ያስፈልጋል የሚል እምነት እንዳላቸው አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል።
በመጨረሻም የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ፤ ለሚመለከታቸው ሠራተኞች ሁሉ ስልክ ደውለው እንዲመጡ ካዘዙ በኋላ ባለሙያዎች ወዲያውኑ ለመመልከት ችለናል። አቶ አብዱልጀሊል ለባለሙያዎች ወዲያወኑ ቦታ ድረስ በመሄድ በቪዲዮና በፎቶ የታገዘ መረጃ ይዘው እንዲመጡ ነዋሪዎቹን ለቅዳሜ 3፡00 ጠዋት ለመነጋገር ቀጠሮ እንዲያዝላቸው ማድረጋቸውን ተመልክተናል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 7/2013