ራስወርቅ ሙሉጌታ
ወይዘሮ እማዋይሽ ታረቀ ትባላላች ትውልዷ ጎንደር ክፍለ ሀገር ጋይንት የሚባል አካባቢ ነው። እማዋይሽ ስድስት ወንድሞች ያሏት ሲሆን ለቤተሰቧ ብቸኛ ሴት ልጅም ናት። እናቷ ገና በልጅነቷ ነፍስ ሳታውቅ በሞት ስለተለየቻት እምብዛም አታስታውሳትም ስለ አቧቷም የምታውቀው ጅማ የሚባል ሀገር እንደሚኖሩ ብቻ በወሬ ነው በዚህ ምክንያት የልጅነት ግዜዋን ያሳለፈችው ከወንድሟ ቤተሰቦች ጋር ነበር።
የህይወት መስመሯ አይታወቅምና ገና የአስር አመት ልጅ እያለች ነበር አንዲት አዲስ አበባ የምትኖር የአገሯ ሰው ከተማ ወስጄ ላሳድጋት ትምህርቷንም እዛው ትማራለች ብላ ወደ አዲስ አበባ ያመጣቻት። አዲስ አበባ ደርሳ ትንሽ ግዜ ከቆየች በኋላ ግን ከዘመዷ ጋር መስማማት ስላልቻለች በሷው ግፊት ሰው ቤት ተቀጥራ መስራት ትጀምራለች።
በሰራተኝነት መስራት የጀመረችበት ቤት ግን ለእማዋይሽ ያላሰበችውን አስቸጋሪ የህይወት መስመር ገና በልጅነቷ እንድትቀላቀል ይዳርጋታል። አንድ ቀን ትሰራባቸው የነበሩ ሰዎች ባለቤት ልጅ ሳታስበው በጉልበት አስገድዶ ይደፍራታል በወቅቱ በአካሏ ላይ የደረሰውን ጉዳት ከማስታመም የዘለለ ባትረዳውም ትንሽ ቆይታ ግን ማርገዟን ታውቃለች።
ነገሩን በቅድሚያ ለልጁ ያሳወቀችው ቢሆንም የልጁ ምላሽ ክህደት ሲሆንባት ደግሞ ለአሰሪዎቿ ለቤተሰቦቹ ስትነግር ልጃችን እንዲህ አያደርግም ሁለተኛ እንዲህ እያልሽ የልጃችንን ስም እንዳታጠፊ ብለው ከቤት ያባርሯታል። በወቅቱ ምን ማድረግ እንዳለባት ግራ ገብቷት ስለነበር የተወሰነ ግዜ ለማግኘት በሚል ስራ መፈለግ ትጀምራለች፤ ነገር ግን እርግዝናዋ እየገፋ በመምጣቱ የሚቀጥራት ታጣለች።
ቀን ቀንን እየወለደ ሲመጣም እንኳን እሷ ደላሎቹም ተስፋ እየቆረጡ ለእሷ ስራ ማፈላለጉን ችላ ይሉታል። በዚህ ላይ ማደሪያውም መዋያውም የሚበላውም እየጠፋ ይመጣል። በእዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች ነበር አንዲት ደላላ ቤት የምታውቃት ልጅ ከዚህ በኋላ እድልሽ ሊሆን የሚችለው ማዘር ትሬዛ የምትባል ችግረኛ የምትረዳ ስላለች ወደ እሷ ብትሄጂ ትልና ትመክራታለች። በተነገራት መሰረት የማዘር ትሬዛ ማእከል ወደሚገኝበት ስድስት ኪሎ አካባቢ የተሰጣትን ተስፋ ሰንቃ ከልጅቱ ጋር በመሆን ታቀናለች።
እዛም ስትደርስ ተቋሙ በሚተዳደርበት ደንብ መሰረት እርጉዝ ሴት ማስገባት እንደማይችል ይነግራትና ነገር ግን ያለችበት ሁኔታ አስቸጋሪ በመሆኑ ውጪ ሆና ቀን ቀን ምግብ እየመጣች እንድትበላ ለማደሪያዋ ደግሞ በየቀኑ ሁለት ሁለት ብር እንደሚሰጣት ቃል ይገባላታል። ምንም አማራጭ ያልነበራት እማዋይሽ ቀን ቀን ማዘር ትሬዛ ጋር ምግቧን እየበላች ማታ ማታ ማዳበሪያ ተነጥፎላቸው በህብረት የሚታደርበት ቤት በቀን ሁለት ብር እየከፈለች መኖር ትቀጥላለች።
የማይቀረው ቀን ይደርስና ምጥ ሲይዛት በሰው ድጋፍ ሄዳ የካቲት አስራ ሁለት ሆስፒታል የመጀመሪያ ልጇን ለመገላገል ትበቃለች። ከተገላገለች በኋላ እሷም ሆነች ልጇ ሙሉ ጤነኛ ስለነበሩና በሆስፒታሉ የሚያስቆያቸው ጉዳይ ስለሌለ ወዲያው መውጣት እንዳለባት ይነግሯታል።
አማራጭ ያልነበራት እማዋይሽ በነጋታው አራስ ልጇን እንደያዘች ማዘር ትሬዛ በር ላይ ሄዳ ትቀመጣለች እነሱም አራስ መሆኗንና ያለችበትን ሁኔታ በመረዳት ወደ ማእከሉ እንድትገባ ያደርጓታል። ለሶስት ወራት ያህል እዛው እንክብካቤ እየተደረገላት ከቆየች በኋላ ሌላ አማራጭ እንድትፈልግ ነግረው እንድትወጣ ያደርጓታል።
አሁንም ሰው በሰው መረጃ ይሰጣትና ጨርቆስ አካባቢ ጋና ሜዳ የሚባል ቦታ ሙላት የተሰኘ ድርጅት የጎዳና ተዳዳሪዎችን የሚረዳ እንዳለ ይነገራትና ወደዛው ታመራለች። እዛም ደርሳ ተደፍራ የወለደች መሆኗን እስካሁንም በበጎ አድራጊ ድጋፍ እንደቆየችና ከዚህም በኋላ የኔ የምትለው ሰው እንደሌላት በመንገር ድርጅቱ ካልተቀበላት የሶሰት ወር እድሜ ያላትን ህጻን ይዛ ጎዳና ለመቀላቀል እንደምትገደድ ስትነግራቸው ከነልጇ ፈቅደውላት ማእከሉን እንድትቀላቀል ያደርጓታል።
በማእከሉ በአንድ ክፍል ውስጥ በርካታ ሆነው በተደራራቢ አልጋ ላይ የሚኖሩ ቢሆንም ቤቱ ብዙ ነገሮች የተሟሉለት ነበር። ጽዳታቸውን እንዲጠብቁ በቂ ምግብ እንዲያገኙ የሚደረግ ሲሆን አንዳንድ ግዜም ይጠቅማቸዋል ያሉትን ስልጠናም ይሰጧቸው ነበር።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች ነበር ሳሙኤል ከሚባል አንድ ወጣት ጋር ለመተዋወቅ የበቃችው። ወጣቱ ጨርቆስ አካባቢ ማርገጃ ሰፈር ተወልዶ ያደገ ሲሆን በአንድ እንጨት ቤት ውስጥ በረዳትነት የሚሰራ ነበር። እነ እማዋይሽ በሙላት ድርጅቱ ውስጥ እያሉ ቅዳሜና እሁድ ስራ በመፈለግ ልብስ ማጠብና የመሳሰሉትን ይሰሩ ነበር፤ እናም አንዳንድ ቀን ልብስ ለማጠብ ስትሄድ ሳሚ በእረፍት ሰአቱ ልጇን እዛው እንጨት ቤት ውስጥ እየያዘ ያጫውትላት ነበር። አንዳንድ የሚያውቋት የአካባቢው ነዋሪዎች እንዴት አንቺ ተደፍሬ ወለድኩ እያልሽ ይቺን ህጻን ልጅ እዛ ታውያለሽ እያሉ ይመክሯትም ነበር። በወቅቱ ግን ስራውንም መስራት ራሷንም መቻል ስለነበረባት ያላት አማራጭ ልጇን ሳሚ ለሚባለው የዛሬ ባለቤቷ ጋር ማዋል ብቻ ነበር።
በልግስና የተጀመረው የሳሙኤልና የእማዋይሽ ግንኙነት ቀን ቀንን እየወለደ ሲመጣ ወደ ፍቅር መቀየር ይጀምራል። በዚሁ ወቅት ትኖርበት የነበረው ድርጅት ውስጥ የነበሩ አስራ ስምንት ልጆች መነሻው ባልታወቀ ምክንያት በአንድ ግዜ ህይወታቸውን ስላጡ ደርጅቱ እንዲዘጋ በመደረጉ እማዋይሽና ሳሚ አንድ ላይ በመሆን አዲስ ህይወት ለመመስረት ይበቃሉ። ሳሚ እንጨት ቤት በረዳትነት ሰርቶ ከሚያገኛት ላይ አራት መቶ ብር የቤት ኪራይ እየከፈሉ ቡልጋሪያ የሚባል አካባቢ መኖር ይጀምራሉ። እዛም እያሉ ሁለት ልጆችን ካፈሩ በኋላ አካባቢው ለልማት ሲነሳ ሌላ የቤት ችግር ይጋረጥባቸዋል።
በዚህ ወቅትም ደግሞ እማዋይሽ ሶስተኛ ልጇን ከወለደች ገና ሰባተኛ ቀኗ በመሆኑ አራስነቷን አልጨረሰችም ነበር። በሰፈሩ የቤት ኪራይ ዋጋ በአንድ ግዜ ስለናረ በሳሚ ደመወዝ ብቻ ቤት ኪራይ ከፍሎ ቀለብ ሰፍሮ መኖር አዳጋች እየሆነ ይመጣል። በዚህ ወቅት እማዋይሽ ከነበረችበት ትንሽ ከፍ ብሎ ተዘግቶ የተቀመጠ መጠለያ መኖሩን ስትሰማ በሩን ሰብራ ትገባና እቃዋን አምጥታ መኖር ትጀምራለች። ይህንንም አድርጋ አንድ ቀን ተጠያቂ እንድምትሆን በመረዳት በወረዳውና በክፍለ ከተማው በመሄድ የሰራችውን፣ ያለችበትን ሁኔታ ትገልጽ ነበር።
እማዋይሽ አንድ ቀን መንግስት ፈቅዶልኝ ሶስት ልጆቼን ይዤ በዚሁ መጠለያ እከርማለሁ እያለች ስታስብ በሌላ እድለ ቢስ ቀን መነሻው ያልታወቀ እሳት ተከስቶ መጠለያውንና ከአጠገቡ የነበረን ዜሮ ዘጠኝ የሚባለውን ጤና ጣቢያ ሙሉ ለሙሉ ያወድመዋል።
በወቅቱ ቀይ መስቀል የአፋጣኝ ግዜ ድጋፍ በማለት ለእሷ አምስት ቤተሰብ ስለነበራት አስራ ሁለት ሺ ብር ይሰጣታል። ያቺን ብር ይዛ መጀመሪያ ጎዳና ላለመውደቅ ቤት ተከራይታ ከተቀመጠች በኋላ ማረፊያዋን ለማግኘት ተመልሳ ወደ ቀበሌ ብታቀናም ሳይቀናት ይቀራል። ምክንያቱ ደግሞ በቃጠሎ የወደመው ቦታ ላይ ከነበሩት ሰዎች ከሰላሳ በላይ ለሚሆኑት ብቻ ህጋዊ የነበሩ በመሆናቸው ጣፎ አካባቢ ቤት እንዲሰጣቸው ይደረግና ቀሪዎቹ አስራ ሁለቱ ህገወጥ በመሆናቸው ቀበሌው ምንም ሊያደርግላቸው እንደማይችል ይነገራቸዋል።
ከቀይ መስቀል ባገኘችው ድጋፍና በሳሚምም ስራ እሷም እየተሯሯጠች ሁለት አመት ያክል ከቆየች በኋላ ግን ባለችበት ሁኔታ መቀጠል የማትችልበት ሁኔታ ይፈጠራል። በአንድ ወገን የቤት ኪራይ መጨመር በሌላ በኩል ሶስት ልጆች ስላላት የሚያከራያት ታጣለች። የአካባቢው ነዋሪም በአቅሙ ገንዘብ አሰባስቦ ሊደግፋት ቢሞክርም ነገሮች ሊሳኩ አልቻሉም።
ከአካባቢው እርቃ ከከተማ ዳርቻ በተለይ በእሷ እቅድ ሀና ማርያም አካባቢ ለመኖር ብታስብም ሳሚ የእንጨት ስራውን ትቶ በዲሽ ገጠማ ላይ ስለተሰማራ የማያውቁት ሰፈር ሄዶ ስራ ማግኘቱ የማይታሰብ ይሆንባቸዋል። እሷም መነሻውን እንዴት እንደሆነ ባታውቅም በደረሰባት የዲስክ መንሸራተት ምክንያት እንደድሮ ተሯሩጣ የጉልበት ስራ መስራት የማትችልበት ደረጃ ላይ ትደርሳለች።
በዚህ ያልተቋጨ ሁኔታ ውስጥ እያለች ወሯ ስለደረሰ የነበረችበትን ቤት መልቀቅ ስለነበረባት ትወጣና ጎዳና ዳር እቃዋን ይዛ ላስቲክ ለብሳ ከቤተሰቧ ጋር ማደር ትጀምራለች። በዚህ ሁኔታ አንድ ሜትር ከፍታ ባላትና ከሶስት ካሬ በማትበልጠው አስር ሜትር በማትሞላው የድንጋይ ንጣፍ ኮብልስቶን መንገድ ላይ በተተከለች የላስቲክ ጎጆ መኖር ከጀመረች አሁን አራተኛ አመቷን ይዛለች።
ባለፉት አራት አመታት አምስቱ የቤተሰብ አባላት መንገድ ዘግታ በተቀየሰችው ትንሿ ጎጆ ውስጥ በርካታ የህይወት ውጣ ውረዶችን አሳልፈውባታል። ከእነዚህ መካካል እማዋይሽ የማይረሱ አጋጣሚዎቿን እንዲህ ታስታውሳለች። በአንድ ወቅት አንድ መኪና በአስጊ ሁኔታ ተጠግቷቸው ድንጋይ ከልክሎት ይቆማል፤ እነሱ ከላይ እኛ ደግሞ ያለነው ከታች ነበር። ከዛ ግዜ ጀምሮ ቀንም ሆነ ሌሊት የመኪና ድምጽ በሰማሁ ቁጥር ልጆቼን የማደርስበት አጣለሁ።
ሌላ ግዜ ደግሞ ሰፈር ውስጥ ልጆች እርስ በርስ ተጣልተው በር ላይ ጸብ ይገጥማሉ፣ በቡድን ይጣሉ ስለነበር ድንጋይ ውርወራው እየበዛ ሲመጣ ልጆቼን ይዤ ላስቲኳ ውስጥ ገባሁ። ጸቡ ከበረደ በኋላ ውጪ ስወጣ የጣድኩትን ድስት ማንደጃውን ሳይቀር ተወራውረውበት እቃዎቹ ፍርስርስ ብለው አገኘኋቸው።
እንዲህ አይነት ነገር ሲፈጠር ባላድናቸወም ልጆቼን አቅፌ ፍራሽ ውስጥ እደበቃለሁ። በክረምት ዝናብ በጣለ ቁጥር የማይርስ የቤቱ እቃ የለም እናወጣና አስጥተን እንውላለን ታዲያ ደመና ሆኖ ቀኑ ከዋለ አዳር በዝናብ በራሰው ፍራሽና ብርድ ልብስ ላይ ይሆናል ማለት ነው። ይሄ ሁሌም የተለመደ ነው።
መቼም የማይረሳኝ መጥፎ ትዝታ ግን በአንድ ወቅት ከአካባቢው ነዋሪዎች አንዱ ሌሊት ሌባ ቤቱ ውስጥ ይገባበትና ሳይዘው ያመልጠዋል። እናም ሌባ ሊደፍረን የቻለው እናንተ እዚህ ስላላችሁ ነው ብሎ ሌሊት መጥቶ ይረብሸናል፤ ቀን ደግሞ ለቀበሌ ሄዶ በመናገሩ ደንብ አስከባሪዎች ትንሿን የላስቲክ ጎጆ ሙሉ ለሙሉ አፍርሰው ከነእቃዬ በሁለት መኪና ጭነው ወሰዱብኝ። የአካባቢው ነዋሪ ግን በፍጥነት በማሰባሰብ የተቻላቸውን አድርገው በድጋሚ ማደሪያ ቀየሱልኝ። ደንቦቹ ግን አሁንም ሲያልፉ እናነሳችኋለን እያሉ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ይሰጡኛል።
በእርግጥ እነሱም ስራቸው ነው፣ አልቀየምም፤ ህግ የማስከበር ሃላፊነትም አለባቸው። ነገር ግን እኔስ ሶስት ልጆች ይዤ የት ልሄድ አችላለሁ። በዚህ ወቅት ከዚህ ቦታ ማረፊያዬን ሳላዘጋጅ ከተነሳሁ ልጆቼንም የማበላው አጣለሁ ትምህርታቸውም ይቋረጥብኛል ትላለች።
መጠለያ እንዲሰጠኝ የሚመለከተውን አካል ስጠይቅ ባለቤትሽ ስራ ስለሚሰራ እናንተ ቅድሚያ ሊሰጣችሁ አይችልም ይሉኛል። ክፍለ ከተማ ስሄድ ቀጠና ለይቶ ይላክልን ይሉኛል፤ ቀጠናው ደግሞ የባሰ አለበት አሁን ላንቺ ቅድሚያ ልንሰጥ አንችልም ይለኛል። በአካባቢው ብዙ ችግር ያለበት እንዳለ አውቃለሁ። ነገር ግን አንደኛ አካባቢው ባለቤቴ ተወልዶ ያደገበት ነው እዚ ካላገኘን እኛ የትም ሄደን ልንጠይቅ አንችልም። ተከራዮች ሆነው በዝቅተኛ ህይወት የሚኖሩ በሚል ቤት የተሰጣቸው አሉ። የቤተሰብ ጥገኛ በሚል እዛው ተወልደው ያደጉ የወሰዱም አሉ።
አሰራሩ እንዴት እንደሆነ ባላውቅም እስካሁን ለእኔ ግን የተደረገልኝ ነገር የለም። በኮሮና ዘመን እንኳን ሶስት ልጆችን ይዤ እርዳታ የተደረገልኝ አንድ ግዜ ብቻ አስር ኪሎ ፉርኖ ዱቄት ነው። ምክንያቱ ግን ምን እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም። በሌላ ግዜ ደግሞ የውጪ ዜጎች መጥተው አይተውኝ የነበረ ቢሆንም ወይ ትልቋን ልጅ ስጪን አልያም አንቺ ሀይማኖት ቀይሪ ብለው በአስተርጓሚ በኩል ጠይቀውኝ ሁለቱንም ስላልተቀበልኩ ትተውኝ ሄዱ።
በሌላ በኩል እሱ ተሯሩጦ በሚሰራው ለእለት ጉርስ እንኳን የሚበቃ ገንዘብ ማግኘት አይችልም። እኔ ጤነኛ በነበርኩበት ግዜ ከቀን ስራ ጀምሮ ያገኘሁትን እየሰራሁ እደግፈው ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን የሆድ እጢ የዲስክ መንሸራተትና የልብ ህመም ስላለብኝ ልጆቼን አብስሎ ከማብላት ውጪ ምንም መስራት አልችልም። ሌላው ቀርቶ ህክምናዩን እንኳን በተገቢው መንገድ እየተከታተልኩ አይደለም።
በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም ከአንድም ሁለት ሶስት ግዜ ልጆቼን አሞብኝ ጤና ጣቢያ ብሄድም የተወሰነ መድሀኒት ከውጪ ይገዛ ብለውኝ ስለነበር የልጆቼንም ህክምና ላቋርጥ ተገድጂያለሁ። ይህን ሁላ እያስረዳሁ ትንሽ መጠለያ ለማግኘት የሚመለከታቸውን አካላት ብለምንም እንነጋገራለን እያሉ እስካሁን ምንም መፍትሄ ማግኘት ሳንችል ቆይተናል። የባለቤቴ እናትም በአካባቢው ያሉ ቢሆንም የኑሮ ደረጃቸው ዝቅተኛ በመሆኑ እንኳን እኛን ሊደግፉ ለራሳቸውም ደጋፊ የሚያስፈልጋቸው ናቸው።
በአንድ ወቅት የአካባቢው ነዋሪም በተለይ ልጆቹን በመመልከት አንድ መፍትሄ እንዲሰጥ በሚል የሚመለከታቸው አካላት ድረስ ሄደው ጠይቀውልኝ የነበረ ቢሆንም የተገኘ ለውጥ ግን አልነበረም። የአካባቢው ነዋሪ ግን ሁሌም ከአጠገቤ ነው ወጣቶችም እናቶችም ይደግፉኛል ሌላው ቀርቶ በበአል ሁሉንም ነገር ያደርጉልናል። አሁን እንኳን በዚህ ሁኔታ ሆኜ በወር አንድ መቶ ብር እየከፈልኩ መጸዳጃ ቤት እንድጠቀም፣ ባገኘሁ ግዜም ለአንድ ግዜ ሀያ አምስት ብር እየከፈልኩ እንጀራ እንድጋግር ፈቅደውልኛል።
ትልቋ ልጄ መአዛ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን መሀከለኛዋ ቃልኪዳን አንደኛ ክፍል ናት። የሶስት አመቱ የአብ ስራ ግን ገና ትምህርቱን አልጀመረም። እማዋይሽ ዛሬም እነዚህን ልጆች ይዛ መጨረሻውን ሳታውቀው መሀል መንገድ ላይ በወጠረቻት የላስቲክ ጎጆ እየኖረች ትገኛለች።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 7/2013