ግርማ መንግሥቴ
በአንድ ወቅት ስለ “ኦግዚሞሮን” ምንነትና ፋይዳ አስነብበን ነበር። “ትሁት ነፍሰ ገዳይ”ም የዚሁ አካል ነው። ማለትም “ትሁት ነፍሰ ገዳይ” የሚለው አገላለፅ በቋንቋ ቴክኒካዊ አጠቃቀም ምድቡና አፃፃፍ ብልሀትነቱ ከ”ኦግዚሞሮን” ነው።
ይህንን ሥነጽሑፋዊ ቃል (“አሀዝ” ወይም “term” ይሉታል እጓለ ዮሀንስ) እዚህ ስንጠቀም ያለ ምክንያት ሳይሆን በምክንያት ነው። ለዛውም ከበቂ በላይ ምክንያት።
አንዳንዴ ነገሮች ያለ ቦታቸው ሲውሉ፤ አለዚያም በተቃራኒው ሲያገለግሉ ይታያሉ። በዚህም ብዙዎቻችን ግራ ስንጋባ፣ አሊያም ለስላቅ መስሎን እኛም ልንሳለቅ እንችላለን። ግን አይደለም፤ ኦግዚሞሮን (Oxymoron) ስልጡን ሰው ካገኘ፤ በሙያ ስራ ላይ ከዋለ ሥነጽሑፋዊ ፋይዳው ከፍ ያለና ሲበዛም አመራማሪ ነው። “ትሁት ነፍሰ ገዳይ”ም የዚሁ ፍንካች ነውና እንቀጥል።
ሞት የነበረ፣ ያለና የሚኖር ነው። ምንም እንኳን ተገቢ ባይሆንም ገዳይ ነበር፣ አለ፣ ይኖራልም። ስለዚህ ሟችና ገዳይ የማይነጣጠሉ ናቸው ማለት ነው። ይህ ሲባል ግን የግድ እያልን አይደለምና የገዳይ አስፈሊጊነትን እየሰበክን አይደለም። “ገዳይ እወዳለሁ” ያለችውም ንግስትም አውዱ ከጀግንነት ጋር እንጂ ከገዳይና ተገዳይ ጋር በተያያዘ ባለመሆኑ ልትጠየቅ አይገባትም።
መቸም የዚህ ጽሑፍ አንባቢያን፣ በተለይም ከ”ትሁት ነፍሰ ገዳይ” ጋር ትውውቅ የሌለው የመጀመሪያው ጥያቄ “ደሞ ከመቼ ወዲህ ነው ገዳይ ትሁት ለሚለው አቅመ ተመስጋኝነት የደረሰው?” የሚል ስለመሆኑ አይጠረጠርም። እውነት ነው። እንዲህ የሚባል ማእረግ ቢኖር ኖሮ በፈፀመው አሰቃቂ ግድያ (ከ1992 እስከ 1999 በተካሄደ የፍርድ ሂደት) 1ሺህ 853 አመታትን የእስር ቅጣትን የተከናነበው ሉዊስ ጋራቪቶ (Luis Garavito) ነበር የመጀመሪያው የማእረጉ ተቋዳሽ። በዲሞክራሲ ስም፣ በልማት ስም፣ ከባህልና ቋንቋ ጀርባ በመመሸግ ሲምልና ሲገዘት፤ በብሄርም ይሁን ሌላ እኩልነት ስም እየተገዘተ ወዘተ ሰው አልገደለምና ማእረጉን ሊያገኘው አልቻለም።
በሕግ የሚፈፀመውን ባላውቅም፣ በየትኛውም መስፈርት መግደል ትክክል ሆኖ አያውቅም። በየትኛውም አገርም ሆነ ፕላኔት ሀጢያት እንጂ ለፅድቅ ሲያበቃ አልተሰማም። እኛም የአለም አካል ነንና ያው ነው።
ሌላውና ከሰው ወደ አገራት ስንመጣ የምናገኘው የግድያ አይነት ፖለቲካዊው ነው። ከ2000 እስከ 2017 ባሉት አመታት ውስጥ በትንሹ 80 ፖለቲካዊ ግድያዎችን በማስተናገድ የምትታወቀው በኖቬምበር 1956 የተመሰረተችው ኬራላ ግዛት (Kerala) በ2015 ከአለም በፖለቲካ ምክንያት ፖለቲካዊ ግድያን በመፈፀም፤ እንደ National Crime Records Bureau (NCRB) መረጃ፣ በከፍተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ሰው መግደል፣ በምንም ይሁን በምንም ምክንያት፣ አሁን ብቻ አይደለም ችግሩ፤ ችግሩ ወደ ፊት “Ethnographic and Archaeological Evidence on Violent Deaths”ን የመሳሰሉ ጥናቶች ሲመጡ ነው ጣጣውና የታሪክ አተላነቱ አብሮ ከተፍ የሚለው። እነዚህ ጥናቶች ወደ ፊት አስከሬኖችን ከከርሰ ምድር እያወጡ ይህ የሞተው በእከሌ ነው፤ ይህ የሞተው በእንደዚህ ነው ሁኔታ ነው፤ ይህ ደግሞ የተገደለው በእንደዚህ አይነት መሳሪያና ሁኔታ ነው ወዘተ በማለት ሲያጠኑ ነው ጉዳዩ ይበልጥ ገዳይና የገዳይን ወገን አንገት የሚያስደፋው፤ ያሳዝናል።
እንደ ማክስ ሮዘር (2013) ጥናት በቅድመ ታሪክ ዘመን Crow Creek, 1325 CE (South Dakota) ከ60 በመቶ በላይ ድርሻን በመያዝ የአለምን ሪኮርድ የያዘች ሲሆን፤ በመንግስት አልባ አገራት (በአመት በመቶ ሺህ Violent deaths per 100.000 people per year) Kato (Cahto), 1840s (California) 1ሺህ 450 ሞት በማስመዝገብ በግፍ አገዳደል አንደኛነቷን ይዛለች።
በዘመናዊውና በመንግስት በሚመሩ አገራት ከአጠቃላይ ህዝብ ስሌት (ከአንድ ማህበረሰብ ውስጥ በ100,000) ሜክሲኮ (Mexican mestizo village; 1961 – 1965 CE) 251.2 የግፍ አገዳደልን በማስመዝገብ እየመራች ትገኛለች። የእስከ ዛሬዋ ንፅህት ኢትዮጵያ ወደ ፊት የሚጠብቃት በዚህ መልክ መጠናትና የደረጃ ሰንጠተረዥ ላይ መቀመጥ ነውና ያሳዝናል። ይበልጥ የሚያሳዝነው ደግሞ ሁሉም ነገር በእኛው እኛው ላይ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ጥቂት ግለሰቦች አገርና ህዝብን የሚያክል ነገር ለግል ጥቅም ሲባል ወደ ጦርነት መውሰዳቸውና ይህ ሁሉ ጉድ አገርና ህዝብ ላይ መውረዱ ነው።
በአለማችን እጅግ አስከፊና በማንኛውም ዘርፍ ከፍተኛ ውድመት፣ ድቀትና ውድቀት የታየበት ጦርነት ሁለተኛው የአለም ጦርነት (1939 እስከ 1945) ሲሆን 75 ሚሊዮን (26.6 ሚሊዮን ሶቪየት ህብረት፣ 7.8 ሚሊዮን ቻይና) ሰዎችን ሲሆን፤ ይህም በወቅቱ ከነበረው የህዝብ ቁጥር አኳያ 3 በመቶውን ይወክላል። በተለይ ጦርነቱን ከሁሉም የከፋ ያደረገው ሁሉም አይነት ኢሰብአዊ ተግባራት መፈፀማቸው ሲሆን እነሱም ከዘር ማጥፋት ጀምሮ ሁሉም አይነት ኢሰብአዊ ተግባራት የተፈፀሙ መሆናቸው በታሪክ መመዝገቡ ነው፤ ምን ያደርጋል የተማረባቸው ሳይሆን የቆረበባቸው መብዛቱ ከፋ እንጂ።
ከበጀት አንፃር ብዙ የተጠና ነገር ባይኖርም በአደጉት አገራት ግን ጉዳየ ትኩረት ከሚሰጣቸው መካከል አንዱ በመሆኑ ያለ ማሰለስ ይጠናል። እነዚሁ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ የአንድን አገር ኢኮኖሚ ቅርጥፍ አድርጎ ከመብላት አኳያ ጦርነትን የሚያክል ተግባር እስካሁን አልተገኘም። የአሜሪካንን የእስከ ዛሬ ጦርነቶች እንኳን ብንወስድ አገሪቱን ከ$3.2 እስከ $4 ትሪሊዮን ዋጋ አስከፍሏት እናገኛለን፤ በኢራንና አፍጋኒስታን ባካሄደችው ጦርነት ብቻ $2.4 ትሪሊዮን አፍስሳለች።
የ”Costs of War” project እንደሚያረጋግጠው በተለይ እኛን እንደገጠሙን የሰሞኑ አይነት ጦርነቶች በሰብአዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ቀውስን ከማስከተል አኳያ የሚያስከፍሉት ዋጋ ከሌሎቹ ጋር ሲወዳደር ከፍታው ከጣራ በላይ ሆኖ ነው የሚታየው። በመሆኑም ወደ እንደዚህ አይነት ጦርነት ውስጥ የሚገቡ፤ ወይም ሌላውንም እንዲገባ የሚያደርጉ አካላት ጤንነታቸው አጠራጣሪ ብቻ ሳይሆን አላማቸው እራሱ አላማ የለሽ ስለ መሆኑ መከራከር አይቻልም።
አሜሪካ በአሸባሪዎች ምክንያት በደረሰው አደጋ (9/11)ም (በ80 አገራት በወሰደችው መልሶ ማጥቃት ርምጃን ጨምሮ) $6.4 ትሪሊዮን እንዳጣች በጥናቶች የተደረሰበት ሲሆን፤ ብዙ ጊዜ ያልተጠበቁና ድንገቴ አደጋዎች፣ ግጭቶች፣ ጦርነቶች ወዘተ ከፈተኛ ዋጋን እንደሚያስከፍሉ ጥሩ ማሳያ ነው።
ከሰብአዊ ቀውስ አኳያም ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ሲሆን፤ የ2016 ጥናት እንደሚለው ከሆነ ባለፉት 15 አመታት ብቻ አሜሪካ 600ሺህ ዜጎቿን በጦርነት አጥታለች።
“The Battle of Stalingrad” በመባል የሚታወቀው ጦርነትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ2 ሚሊዮን በላይ ህይወትን በመቅጠፉ በአለም ላይ እጅግ አስከፊ ጦርነትና የሰው ልጅ ሁለተኛ ሊደግመው የማይገባ ተብሎ ለመመዝገብ በቅቷል። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ ተምሯል ወይ፤ ተምሮስ ከእንደዚህ አይነት ድርጊት ተቆጥቧል ወይ? የሚል ጥያቄ ከተነሳ ምላሹ በፍፁም ከሚለው የሚያልፍ አይደለም።
ይህ ደግሞ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በእኛ በምስኪኖቹ ላይ ተከስቶ እንዴት እንደሚያሳፍርና እንደ ሚያሳዝን ለመናገር ነብይ መሆን አያስፈልግምና ዋጋ መክፈላችን ብቻ በራሱ ማስረጃ ነው።
አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ህዝብን ቅርጥፍ ያደረገው “የሞስኮ ጦርነት” (“Operation Typhoon” በሚልም ይታወቃል)፤ በጃንዋሪ 1942 ብቻ ከጀርመን በኩል 174,000 እስከ 400,000፤ ከሩሲያ (ቀዩ ሰራዊት) በኩል ደግሞ 650,000 እስከ 1.2 ሚሊዮን ፍጡራንን እንክት አድርጓል። እንክት ያድርግ እንጂ የሰው ልጅ አሁንም በጦርነት ቆርቧልና ከዚህ ሁሉ ሊማር አልቻለም፤ ወይም ሊማር አይፈልግም።
ለውጥ አለ፣ ተምሯል ከተባለም ከለየለት ገዳይነት ወደ ትሁት (በዲሞክራሲ ስም . . . ለሰው ልጆች መብት ቆሜያለሁ፣ ለእኩልነት እሰዋለሁ፣ ለህገ መንግስት እገዛለሁ ወዘተ እያሉ በመማል) ገዳይነት መሸጋገሩ ብቻ ነው።
እነዚህን ከላይ የጠቃቀስናቸውን እንደ መነሻና መንደርደሪያነት ስንጠቀም ጉዟችን ወደ እኛው ወደ ሰሞንኛው ከራሞታችን ለመምጣት በማሰብ ሲሆን፤ በተለይ ጥቅምት 30 2013 በማይካድራ የተፈፀመውን፤ ብዙዎችን በቃላት ለመግለፅ ያቃተ ግድያ ድርጊቱን በቀጥታ በተመለከቱት አይኖች ሲገለፅ ምን እንደሚመስል ለማሳየትና የሰው ልጅ ካለፈው ስህተቱ ለመማር ገና ዝግጁ እንዳልሆነ ለማሳየት በማሰብ ነው።
ማን ይናገር የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረየማይካድራውን እልቂትና ያስከተለውን ሁለንተናዊ አካባቢያዊ ቀውስ በአይናቸው ብረት ከተመለከቱት አንዱ ክፍል የጋዜጠኞች ቡድን ሲሆን፤ ከግንባር መልስም በተካሄደ የእውቅና ፕሮግራም ላይ (ካፒታል ሆቴል) ሁሉም በየግምንባሩ የገጠማቸውን፣ ያዩትን የተናገሩ ሲሆን በተለይ ልብ ይሰብር የነበረው የማይካድራው ነበርና ጋዜጠኛ ወንድአጥር መኮንን ከሰጠው የአይን ምስክርነት ጥቂቱን እንመልከተው።
በማይካድራ ላይ የሞተው በዋናነት አማራ ይሁን እንጂ ኦሮሞም ሞቷል፤ ወላይታም ሞቷል፤ ሶማሌም ሞቷል፤ ትህነግ ለማንኛውም ነገር እንደማይመለስ የስለት ጫፍ ድረስ ከመዝለቅ ወደኋላ እንደማይል ያሳየበት ቦታ ማይካድራ ነው። የትህነግ የማይካድራ ጭካኔና ጭፍጨፋ በፊት ከመጋረጃ ጀርባ እንደሚፈጸም በሀሜት ደረጃ ይሰማ የነበረው አሁን መጋረጃው የተገለጠበት ሰይጣንም ያፈረበት ስራው ነው።
የትህነግ ሀይል ገኖ ነበር የመጣው፤ በተለይ እኔ በነበርኩበት አብድራፊ በኩል አብድራፊን ተቆጣጥሮ ወደ ጎንደር፤ ሶሮቃን በዳንሻ በኩል ተቆጣጥሮ ወደ ጎንደር፤ በራያ በኩል ወደ ወልዲያ የመሄድ እቅድ ነበረው፤ 23ኛው ክፍለ ጦር ተበትኖ ስለነበረ ምንም አያስቀረውም ነበር።
ነገር ግን የአማራ ክልል ልዩ ሃይል ዝግጁ ስለነበረና የኮንትሮባንድ ስራን ሲቆጣጠሩ በነበሩ ከተፈጸመባቸው ጥቃት ያመለጡ የፌዴራል ፖሊስ አባላትም ባደረጉት ተጋድሎና ጀግንነት ትህነግ ሊቆም ችሏል። ከፊት ለፊት በመሳሪያ ከጎናቸው በጓደኞቻቸው አስከሬን ሽታ ተፈትነው ድል ነስተዋል፤ ይሄንን ድል ያደረጉት በኢትዮጵያ ፍቅር ነው፤ በኢትዮጵጽያዊነት ነው።
ሁለተኛው አማራ ልዩ ኃይል ሌላኛው ጫፍ እነማይካድራን ማስለቀቅ፣ የሉግዲ መሿለኪያን ማስለቀቅ ወደ ሱዳን የሚሄደውን የትህነግ ኃይል የሚሾልከበትን በር መዝጋትና የሁመራን ቦታ መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን የተከበቡ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ከጓደኞቻቸው የአስክሬን ሽታ፣ ከተከበቡበትም ሕይወታቸውን ማትረፍ ግዴታው ነበረ፤ ሀላዊና በረከት ላይም ይህንን አደረገ።
እዛ ቦታ ላይ ደም ፈሷል፤ የራሳችንን ወገን ደም ረግጠናል፤ እዛ ቦታ ላይ በወደቀ የአስክሬን ብዛት መካከል መቆም ምናልባትም ትንፋሽን መቁጠር እስከሚያክል ድረስ የምንተነፍሰው አየር ያስጨንቀን ነበር።
እንደዚህ አይነት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ትንፋሽ ቅንጦት ነው፣ የልብ ምት ቅንጦት፤ ሁሉም ጭንቅላታቸው ተከፍቷል፤ ሁሉም ሆዳቸው ተከፍቷል፤ ሁሉም ደምተዋል፤ ሁሉም ወድቀዋል፤ አልጋ ያገኙት በጣም ጥቂት ናቸው።
በእነዚህ መሃል መቆም በጣም ከባድ ነበር። (ድርጊቱን ለማጣራት ወደ አካባቢው ተጉዞ የነበረው አጣሪ ቡድን በሪፖርቱ እንደገለፀው በቦታው በንፁሀን ዜጎች ላይ ከዚህ በላይ ግፍና የጭካኔ ግድያ፤ በሲኖትራክ መከኪና በሰው ላይ እስከ መሄድ ድረስ ተፈፅሟል።)
በጋራ ሆነን ይህንን ነገር ለዓለም ማሳወቅ ነበረብን፤ ይህንን ዘግተነው ካለፍን አደገኛ ነበረ፤ መበርታት ነበረብን፣ ደም ረግጠን ነው የቆምነው፤ ሁላችንም ደም ረግጠናል። ይህንን ለቅሶ እዛ አላለቀስኩትም፣ ሰላም ስለሆነ ነው፤ ማልቀስም ሰላም በሆነበት ቦታ ነው የሚቻለው።
ህዝብን አነጋገርን፤ ወስደው እንደ ቀበሯቸው ነገሩን። ነገር ግን የተገደሉት እነዚህ ብቻ አይደሉም አሉን። ከቢሮ ‘መቀሌ ትገባላችሁ የሚል’ ትዕዛዝ ተሰጥቶናል፤ መቀሌ መግባት ለእኛ መዝናናት ነበር፤ ስለሆነም በየቦታው የተደፉ ሰዎችን ማሳየት ነበረብን፤ አሞራና ዝንብ እየተከተለን በየቦታው የወደቁ አስከሬኖችን አሳየን፤ ዓለም የትህነግን መጥፎነት ያየው ያን ቀን ነበር። ምክንያቱም በፕሮፓጋንዳ ተሸፍኖ ነበረ፤ እኛ ገለጥነው። ከአከባቢው ሰው ጋር ተባብረን በመጀመሪያው ቀን የ74 ሰዎችን አስከሬ አገኘን፤ 74ቱም ስዎች በጋራ ነው የተቀበሩት። የህጻናት ጫማ ነበረ፤ የሴቶች ነጠላ ነበረ።
አቡነ አረጋዊ በሚባለው ቦታ ላይ የተቀበሩት ሰዎች ቁጥራቸው አይታወቅም፤ በጣም የሚገርመው አስክሬኖቹን መቅበር የማይቻልበት ጊዜ ነው የተደረሰው፤ የአካባቢው ሰው የአስከሬኑን ሽታ ለመቋቋም ሲል ሽቶ ተጠቅመዋል። (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም ይህንን አረጋግጧል።)
ከሁለት ቀናት በኋላ ተመሳሳይ ጥቆማ ደረሰን፤ አሞራ አከባቢውን ይዞራል፤ ዝንቦች ወረውታል፤ 18 የደረቀ አስክሬን አንድ ላይ ሳይቀበሩ አገኘን፤ እንዲሁ ነው የተደፉት፤ እስከ መቼ ነው በዚህ ሁኔታ የምንቀጥለው? አሁን ያለን አማራጭ ኢትዮጵያ የሁላችንም ድምቀት መሆን አለባት፤ የሁላችንም ጌጥ ነው መሆን ያለባት። (ይህም በሰመኮ ተረጋግጧል።)
ኢትዮጵያን ተጭኖ የተለያዩ ብሔሮችን ዘር እየለየ የሚያጭድ የተንኮል ገበሬ ካለና እሱ ካልፀዳ ኢትዮጵያዊነት ኢትዮጵያ መሆን አይችልም። እያንዳንዱ ወታደር የተዋጋው በሸተተ ጓደኛው አስክሬ ጎን ሆኖ ነው፤ እዚህ ቦታ ላይ መቆም አስክሬን ማየት በጣም ቀላል ሊሆን ይችላል፤ እኔም አይቻለሁ፤ ከዚህ በፊት ልጄን ቀብሬያለው፤ አልከበደኝም፤ ማይካድራ ላይ ግን መቆም አይቻልም፤ ይህንን መመስከር አይቻልም። ሰው ካልሆንን ኢትዮጵያዊ መሆን አይቻልም፤ እነዛ ሰዎች ሰውነታቸው ስለካዳቸው ነው ኢትዮጵያዊ መሆን ያልቻሉት።
በእለቱ በቦታው ተገኝተን ያነጋገርነው ሌላው ከግንባር ተመላሽ ጋዜጠኛ የዋልታው ሚሊዮን ለማ ሲሆን እሱም እንደነገረን ከሆነ ከወንዳጥር የተለየ አይደለም። ሁሉም ነገር ዘግናኝና ለወሬ እማይመች፣ ሰው መሆንን ሁሉ የሚያስጠላ ነገር ነው የተፈፀመው።
ጋዜጠኛ ወንድአጥር በመልእክቱ መጨረሻ ያለው ነገር ያለ ሲሆን እሱም “ከዚህ በኋላ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የመጨረሻውን የተንኮል ስለት የያዘው አካል በመከላከያ ሰራዊት፣ በልዩ ኃይል አባላት፣ በአፋር ልዩ ኃይል አባላት፣ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ደጀንነት ተሰናብቷል።”
ይህ ከሆነ የሚቀረው ነባሩን ኢትዮጵያዊነት፣ ነባሩን የአብሮነትና መተሳሰብ፣ መከባበርና አንተ ትብስ አንቺ ትብሽነት ወደ ቀድሞ ማንነትና ስፍራው ማምጣት ወዘተ ነው። ለዚህ ደግሞ የሁሉም (ለሁሉም ሲባል) ያልተገደበና ያልተቆጠበ ትብብር ያስፈልጋልና ለዚህ አሁኑኑ ወስኖ መነሳት ያስፈልጋል፤ የግድም ይላል። ከእስከ ዛሬዎቹ ባለመማራችን ተጎድተናልና ሌላው ሁሉ ቢቀር ከዚህ ልንማር ይገባል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2013