ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ዱሮ በ1950ዎቹ ይዟቸው ከወጣ የዜና ዘገባዎች የተወሰኑትን ይዘን ቀርበናል።ዜናዎቹ በዘገባ አቀራረባቸው እና በይዘታቸው ዘና ያደርጋሉና ለዛሬ ይዘናቸው ቀርበናል።
ጅብ ለምዶ ሳሎን ገባ
ከጅማ ከተማ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሠቃ ተብሎ የሚጠራው ከተማ ነዋሪ የሆኑ 40 ዓመት ያላቸው እመት የሺ ግርማ የተባሉ ሴት አንድ ጅብ ለማዳ በማድረግ የሚመግቡት መሆኑ ታውቋል።
እመት የሺ ግርማ ጅቡን ለማዳ ለማድረግ የቻሉበትን ሁኔታ ሲናገሩ በዚሁ ከተማ ውስጥ አንድ ፎቅ ቤት አሠርቼ ለቤቱ ምረቃ ግብዣ አድርጌ ስለነበረ ፤በግብዣው ዕለት ተጋባዡ ሁሉ ወደ ቤቱ ከሄደ በኋላ አንድ ጅብ ከፎቁ ወደ ምድር የተወረወረውን አጥንት ሲቆረጥም የእጅ ባትሪ አብርቼ አየሁት ።በዚሁ ጊዜ ጅቡ ደንግጦ ለመሸሽ ሲሞክር የሀገሩ ሰዎች በሚጠሩት ስም አባ ገሮ ና ና አይዞህ አትሂድ ብዬ ስጠራው መሸሹን ትቶ ቆሞ ወደኔ ማስተዋሉን ቀጠለ።እኔም የሥጋ ትርፍራፊ ወረወርኩለት ፤ይህንንም የወረወርኩለት የስጋ ትርፍራፊ በልቶ ወደ ጫካው ሄደ።
በማግስቱም ይኸው ጅብ በለመደው ሰዓት መምጣቱን አይቼ ሥጋ ወርውሬለት በልቶ ከሔደ በኋላ በቀጠሉት ቀናቶች በዚያው ሰዓት ሳያቋርጥ ይመጣ ጀመር። እንዲያውም እንደ መጀመሪያው ቀን መበርገጉን ትቶ ወደኔ ቀረብ እያለ የምጥልለትን ሥጋ መብላት ስለጀመረ የምሰጠውን ስጋ ወደ ምድር መወርወሩን ትቼ ወደ ፎቁ ደረጃ ስወረውርለት እደረጃው ላይ እየወጣ መብላቱን ቀጥሎ ከቀን ወደ ቀን የፎቁን ደረጃ በሙሉ አልፎ ወጥቶ የምሰጠውን ሥጋ እየተመገበ ይሄድ ጀመር።
በዚህም ሁኔታ ከስምንት ቀን ባልበለጠ ጊዜ ልምምድ አድርጎ እፎቁ ላይ ባለው አንድ ክፍል ሳሎን ውስጥ ከ25 ሰዎች በላይ ባሉበት እወለሉ ላይ ለመመገብ ችሏል።ይህ ጅብ እስካሁን ድረስ ባለማቋረጥ ይመጣል።እኔም ከቤት እንኳ ሥጋ ባይኖር ለሱው ስል በገንዘቤ ሥጋ እየገዛሁ እመግበዋለሁ።ጅቡ በጣም ከመላዱ የተነሳ የኔንም ድምፅ ለይቶ ስለሚያውቅ አባገሮ ና ና ብዬ ስጠራው ገብቶ ይመገባል።
ሰዎች ግን ቢጠሩት በነሱ ድምፅ አይቀርብም፤ ሥጋም ቢሰጡት አይበላም። እኔ እንኳ ያመጣሁለትን ሥጋ ሌላ ሰው ከእኔ እጅ ተቀብሎ ቢወረውርለት አይበላም። እንደገና ያንን ሌላ ሰው የወረወረለትን ሥጋ ከመሬት አንሥቼ እኔ ስወረውርለት ነው የሚበላው።ወደ ቤት በጠራሁትም ጊዜ ብዙ ሰዎች ቢኖሩም አይፈራም።ሰተት ብሎ በሰው መሐከል ወደ ቤት ውስጥ ይገባል።የሰጠሁትንም ይመገባል ሲሉ ገልጸዋል።
ታኅሳስ 9 ቀን 19 56ዓ.ም የወጣ አዲስ ዘመን
የገሙ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማ አርባ ምንጭ እንዲሆን ተፈቀደ
የገሙ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማ ጨንቻ መሆኑ ቀርቶ አሁን ከአለበት 35 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው አርባ ምንጭ ቀበሌ ልዩ ስሙ ሸቻ በተባለው አስደሳች እና ነፋሻ ስፍራ እንዲዛወር ከግርማዊ ንጉስ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ስለተፈቀደ የጠቅላይ ግዛቱ እንደራሴ ክቡር ፊት አውራሪ አዕምሮ ስላሴ አበበ ከጠቅላይ ግዛቱ ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ጋር ጥቅምት 2 ቀን 1955 ዓመተ ምህረት ወደ ተባለው ቀበሌ ሄደው ለመንግስት መስሪያ ቤቶች ለሆስፒታል እና ለትምህርት ቤት ለቤተ መንግስት እና ለቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ለወህኒ ቤትና ለፖሊስ ትምህርት የሚሆኑትን ልዩ ልዩ ቦታዎች እየተዘዋወሩ በመምረጥ ለየክፍሉ ባለስልጣን ሲያስረክቡ ሰንብተዋል።
አዲስ የታቀደው የከተማ ቦታ ከፍተኛነት 1ሺህ 29 ሲሆን ባቅራቢያው ኩልፍ የተባለ ታላቅ ጅረት ይገኛል።ምዕራቡ በታላቅ ጋራ የተጋረደ ሲሆን የቦታው አቀማመጥ ለሕዝብ መደሰቻ ሆነ ብሎ በሚሊዮን ገንዘብ የተገነባ ፎቅ ይመስላል።በዚህ ቀበሌ ሆኖ ያለመነጽር የፈለጉትን አገር ለማየት ይቻላል።
በስተምስራቅ ታላላቅ መርከብ የሚያንሳፍፉ ሐይቆች ይታዩበታል።ሸቻ በልምላሜ የተከበበ የታሪክ ቅርስ ያለው ቀበሌ እንደመሆኑ መጠን እንደ ጨንቻ ከተማ ብርድ የሚበረታበት አይደለም።
በየአውራጃው የሚገኙት ነጋዴዎች ወደዚሁ ለምለም ቀበሌ እየመጡ የንግድ ሱቆች መስራት ጀምረዋል።ሕዝቡም ሆነ የመንግስት ሰራተኛ በመዘጋጀት ላይ ይገኛል፤የጠቅላይ ግዛቱ እንደራሴ ክቡር ፊት አውራሪ አዕምሮ ስላሴ ከአሁን በፊት ነጭ ባህር፣ቀይ ባህር በተባሉት ሃይቆች መካከል የእግዜር ድልድይ በተባለው ተራራ ሲዳሞንና ገሙ ጎፋን ለማገናኘት ባቀዱት ፕላን መሰረት ጥቅምት 4 ቀን 1955 ዓመተ ምህረት ሲዳሞ ወሰን ሰንጣቃ ድንጋይ እተባለው ድረስ በእግር ጉዞ ሔደው የመንገዱን ቀጥታ ፕላን ሲያወጡ ውለው ከምሽቱ 3 ሰዓት አርባ ምንጭ ተመልሰዋል።
በማግስቱ ጥቅምት 5 ቀን ከጋርዱላ አውራጃ ገዥ ከተከበሩ ደጃዝማች ደስታ በርኼ እና ከፊታውራሪ ክብረት ዘሚካኤል እንዲሁም ከወረዳ እና ከምክትል ወረዳ ገዢዎች ጋር ስለ መንገድ ስራ አጀማመር ጉዳይ የሐሳብ መለዋወጥ ካደረጉ በኋላ ጥቅምት 12 ቀን 1955 ዓመተ ምህረት ስራው እንዲጀመር ተደርጎ በዚሁ ቀን ስራው ተጀምሮ በመስራት ላይ ይገኛል።
የገሙ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት ወኪል
አዲስ ዘመን ጋዜጣ 1955 ዓ.ም
አዲስ ዘመን ታህሳስ 5/2013