ዳንኤል ዘነበ
በዓለም ላይ መጥፎ የሚባል ሰላም፣ ጥሩ የሚባል ጦርነት እስካሁን አልታየም። ጦርነት የሃገርን ሃብትና ንብረት ያወድማል፤ ዜጎችን ለህልፈትና ስደት ይዳርጋል። የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በኖቤል ሽልማት ወቅት አድርገው የነበሩትን ንግግር እዚህ ላይ ማስታወስ ተገቢ ነው። «…ጦርነትን አውቀዋለሁ።
ጦርነት ላይ ለተሳተፉ ሁሉ የሲኦል ዋና ምልክት ነው። ምክንያቱም እዚያ ቆይቼ ስለተመለስኩ። በጦር ሜዳ ወንድም ወንድሙን ሲያርድ ወይም ሲገድል አይቻለሁ። አዛውንት ወንዶች፣ ሴቶች እና ልጆች ሞት በሚፈነጥቀው በጥይት እና በተኩስ ፍንዳታ ሲሸማቀቁ አይቻለሁ። እኔ በጦርነት ውስጥ ተዋጊ ሰው ብቻ አይደለሁም።
በጦርነት ያለውን የጭካኔ ተግባር እና በሰዎች ላይ ምን ሊደረግ እንደሚችል ምስክር ነበርኩ» የሚል ነበር። «መሪ ሕዝብን ይመስላል» እንደሚባለው የዶክተር ዓብይ ጦርነት ጠልነት ሰላም ናፋቂነት የኢትዮጵያን ሕዝብ ስሜት የያዘ ይመስላል። እንዳለመታደል ሆኖ የኢትዮጵያ ታሪክ ‹‹በውጭ ሰርሳሪዎች እና በውስጥ መሰሪዎች›› ምክንያት በጦርነት የታጀበ በመሆኑ፤ የጦርነትን አስከፊ ገጽታን በተለየ መልኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቀዋል።
በጦርነት የከበረ ሃገር እና የሰለጠነ ህዝብ አለመኖሩን፤ ጦርነት የስልጣኔ ልጓም፣ የድህነት ድልድይ እንደሆነ በሚገባ ይረዳል። በተለይ የእውቀት ማዕድ የሆኑ ትምህርት ቤቶችን በማውደም፤ ሀገርን የመሃይማን መፈንጫ የሚያደርግ መሆኑን ሕዝቡ በተግባር ኖሮበት ጉዳቱን አይቶታል።
የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ጦርነትን በተመለከተ አቋማቸው መሳለመሳ ቢሆንም፤ የህወሓት ጁንታ ቡድን በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የማይፈልገው ጦርነት ለመጀመሩ ምክንያት ሆኗል። በዓለም ላይ ጥሩ የሚባል ጦርነት እንዳለመኖሩ በህውሓት ጁንታ ቡድን ቆስቋሽነት ተጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ኩራት የሆነው መከላከያ በአጭር ጊዜ ድልን በተቀዳጀበት ጦርነት፤ የእውቀት ማዕድ በሆኑ ትምህርት ቤቶች ላይ ተመሳሳይ ታሪክ ተፈፅሟል።
በትግራይ ክልል የሚገኙ ቁጥራቸው ያልተገለፀ ትምህርት ቤቶች ወድመዋል። የትምህርት ተቋማትን ሳይቀር የጦር ካምፕ ያደረገው የህውሓት ጁንታ ቡድን ለትምህርት ተቋማቱ ውድመት በቀጥታ ተጠያቂ ያደርገዋል። በጦርነቱ ወጣቶችን ከትምህርት ገበታቸው እየነጠለ ወደ እሳት ከመማገድ እስከ ህፃናትን ለስደት በመዳረግ የትምህርት ተቋማቱን ተማሪ አልባ እንዲሆኑ ምክንያት ከመሆኑ ባሻገር፤ በትምህርት ዘርፍ ላይ የጦርነቱ የተፅእኖን ደረጃ እንደ ማሳያ ማቅረብ ይቻላል።
የህውሓት ጁንታው የከፈተው ጦርነት በትምህርት ተቋማት ላይ የደረሰው ውድመት በትምህርት የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር የሚደረግን ጥረት የሚገዳደር ይሆናል። መንግስት ሀገር አፍራሹን በመደምሰስ ቀጣዩን ትኩረቱን ሀገር ገንቢ የትምህርት ተቋማትን ወደ መገንባት የሚሸጋገር መሆኑን ተገልጿል፤ ለችግሩ አጽንኦት የሰጠው መሆኑን አመላካች ይሆናል።
የትግራይ ብሔራዊ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ፤ «..ትግራይን መልሶ የመገንባቱ ሥራ የድኅረ ዘመቻ ዋናው ተግባራችን ነው። አንድ ሆነን የተቋረጠውን እናስቀጥላለን፣ የፈረሰውን እንገነባለን፣ የነገውንም እናለማለን» ሲሉ መናገራቸው፤ በወንጀለኛው ቡድን የፈረሱና አገልግሎት ያቋረጡ
የትራንስፖርትና መገናኛ መሰረተ ልማቶችን መልሶ መገንባት እየተከናወኑ ከሚገኙ ተግባራት መካከል ዋነኛው እንደሆነ ዶክተር ሙሉ መናገራቸው፤ በጦርነቱ ውድመት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶችን መልሶ በመገንባትና በመጠገን በክልሉ የመማር ማስተማር ሂደቱ በቅርቡ እንደሚጀመር የተጣለውን ተስፋ የሚያጠናክር ይሆናል።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስትር በሰላም ማስከበር ወቅት የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን በመጠገን የመማር ማስተማሩ ስራ በሁሉም ቦታ ለማስጀመር የሚያስችል ስራዎች እየተሰራ መሆኑን ነው ያስታወቀው። ሚኒስቴር ዴታው አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ እንዳብራሩት፤ በጽንፈኛው የህወሓት ቡድን በክልሉ ጉዳት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማት ለማሟላት ለጊዜው 50 ሚሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን፤ የማሟያ ድጋፉ እንደ ሁኔታው ሊጨምር ይችላል። ሚኒስቴሩ በክልሉ ከተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር ጋር የሚነሱትን የአቅርቦት ችግሮች ለመፍታት ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ነበር ያስታወቁት።
መንግስት ሀገር አፍራሹን በፍጥነት እንደደመሰሰው ሁሉ ሀገር ገንቢ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ያለውን የቁርጠኝነት ጥግ ከአቶ ሚሊዮን ንግግር መረዳት ይቻላል። በሌላ ወገን ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ተገዶ በገባበት በዚህ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶችን በአጭር ጊዜ ተጠግነው አገልግሎት እንዲሰጡ ከማድረጉ ጎን ለጎን በክልሉ የገጽ ለገጽ ትምህርት ለማስጀመር ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ይታመናል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ላለፉት አስር ወራት በኮሮና ወረርሽኝ ተቋርጦ የነበረው የገጽ ለገጽ ትምህርት ከትግራይ ክልል ውጪ ሙሉ ለሙሉ እንደመጀመሩ፤በጦርነቱ ምክንያት በክልሉ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስጀመር ሳይቻል ቀርቷል። በዚህ ረገድ ሚኒስቴሩ እያደረገ የሚገኘውን እንቅስቃሴ በተመለከተ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ “በክልሉ ትምህርት ለማስጀመር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርና የፀጥታ አካላት ጋር በቅርበት እየተሰራ ይገኛል።
ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት የተመቻቸ ሁኔታና አስተማማኝ ሰላም ሲፈጠር የመማር ማስተማር ሂደት የሚጀመር ይሆናል። ለትግራይ ክልል ከ700 ሺህ በላይ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ተዘጋጅቷል። የተመደበው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ወይም ማስክ ትምህርት ቤቶች ከመከፈታቸው አስቀድሞ የሚሰራጭ ይሆናል» ብለዋል።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት በትግራይ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ተንጠልጥሎ ሀገርን ለማፍረስ ረጅም እቅድ የነበረው የህውሓት ጁንታ ቡድን ከነቅዠቱ በመደምሰስ ወደ ጉድጓድ ማስገባቱ ይታወቃል። በመሆኑም የመንግስት ቀጣዩ ምዕራፍ ሀገር አፍራሹን ከመደምሰስ፤ ሀገር ገንቢ የሆነውን የትምህርት ተቋማትን ዳግም ወደ መገንባቱ ተሸጋግሯል። በዚህ ረገድ የታየውን ቁርጠኝነት በጦርነቱ ምክንያት በክልሉ የሚገኙ የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎች አለመፈተናቸውን ከግንዛቤ በማስገባት፤ የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናን በቅርብ ጊዜያት ለመስጠት የሚያስችል ስራ በተለየ ሁኔታ ማከናወን እንደሚገባ ሁኔታዎች ያመላክታሉ።
ስለዚህ በትግራይ ክልል በሁሉም አካባቢዎች በፍጥነት የገጽ ለገጽ ትምህርቱን ለማስጀመር በሚደረገው የመልሶ መገንባት ጥረት ውስጥ ሕዝቡን በሚያሳትፍ መልኩ መደረጉ የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርግ መገንዘብ ይቻላል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 5/2013