ሰላማዊት ውቤ
በመካከለኛ ኢንዱስትሪው መስክ የተሰማሩ ወጣቶች የገበያ ችግር እንዳለባቸው ይነገራል። እንደ ሀዋሳው ከተማ ነዋሪ ወጣት ያሬድ እስጢፋኖስ የተለያዩ ማሽነሪዎችን የሚያመርቱ ደግሞ ገበያ የማግኘት ዕድላቸው እጅግ የጠበበ ነው። ‹ያሬድ እስጢፋኖስ ማሽነሪ አምራች ድርጅት› የዛሬ አምስት ዓመት ከአራት ጓደኞቹ ጋር ወደማሽን ማምረት ሥራ ሲገባም የገበያ ሁኔታ ፈተና ሆኖበት ነበር።
ከሦስት ዓመት በፊት በዚሁ የገበያ እጦት ለኪሳራ የተዳረገበትና ተስፋ የቆረጠበት ሁኔታ ገጥሞታል። አብረውት ይሰሩ የነበሩት አራት ጓደኞቹ የያዙትን ይዘው ተለይተውታል፤ ሆኖም መስራችና ባለቤቱ ያሬድ ተስፋ ሳይቆርጥ እስካሁን ዘልቋል ።
የገበያ እጦት ሰቅዞ ቢይዘውም ጥንድ ሀሳቦችን በልቦናው ይዞ ሥራውን አጠናከረ። አንዱ ሀሳብ ኤሌክትሪክ ቆጣቢ የዳቦ መጋገሪያ፣ ኤሌክትሪክ ቆጣቢ የቤት ውስጥ ፉርኖ ዱቄት ወፍጮ፣ ኤሌክትሪክ ቆጣቢ ማቡኪያ፣ ኤሌትሪክ ቆጣቢ የሊጥ ማቡኪያ ማሽኖችን እና የመሳሰሉ ማሽኖችን ማምረት መቀጠል ነው።
ሁለተኛው ሀሳቡ ደግሞ ምርቶቹን በማስተዋወቅ ማሽኖቹን የሚሸጥበት ገበያ ማፈላለግ ነበር። በእርግጥ በዚህ ምርቶቹን በማስተዋወቅና ገበያ በማፈላለግ ሂደት የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን ክንድ ሆኖታል።
በሸማቹ ሕብረተሰብ በተለይ በዳቦ ማምረት ሥራ በተሰማሩ ነጋዴዎች ዘንድ የተዋጣለት ዳቦ ለመጋገር የሚያስችሉና ድካምን የሚቀነሱ ማሽኖችን ገዝቶ መጠቀም እምብዛም ነው። ምክንያቱም እነዚህ ማሽኖች በተሟላ መልኩ በሀገር ውስጥ ተመርተው ለገበያ ሲቀርቡ አይታይምና ነው።
ከውጪ ለሀገር ውስጥ የሚቀርቡት ማሽኖችም የኤሌክትሪክ ፍጆታቸው ከባድ ነው። የያሬድ ማሽነሪ ምርት ደግሞ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄ ይዞ ነው ብቅ ያለው። አንደኛው የኤሌክትሪክ ፍጆታቸው በእጅጉ ዝቅተኛ የሆኑ ማሽኖች ሲሆኑ ከሀገር ውጪ ከሚገቡት
ምርቶች ሲነፃፀሩም በሀገር ውስጥ የሚመረቱት ማሽነሪዎች የዋጋ ቅናሽ አላቸው። በመሆኑም ሀዋሳ ከተማን ጨምሮ በአዲስ አበባ፣ በአዳማ ፣ በቢሾፍቱና በተለያዩ ቦታዎች በመውሰድ በኤግዚቢሽን መልክ ማሽኖችን ሲያስተዋውቅ በሸማቹ ዘንድ ከፍተኛ ተፈላጊነት ማግኘቱን ይናገራል። ምርቱን ማስተዋወቁ በቋሚነት የሚቀጥል መሆኑን የሚጠቅሰው ያሬድ በዚህም ሰፊ ገበያ እንደተፈጠረለትና ከገባበት የኪሳራ አረንቋ ለመውጣት እንደቻለ ነግሮናል። አሁን ላይ በርካታ በማህበርና በግል በዳቦ ማምረት ሥራ የተሰማሩ ደንበኞች ማፍራት ችሏል።
በፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን በተመቻቸለት ዕድል ‹‹የካፒታል ዕቃ ሊዝ ፋይናንስ ተቋም ማሽኑን ከእኔ ገዝቶ በብድር መልክ ለኢንዱስትሪዎች እንዲሸጥላቸው አድርጎልኛል›› ሲልም ስላገኘው የገበያ ዕድል ይናገራል።
አሁን ላይ ወጣቱ ለ30 ወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን ስምንት ሚሊዮን ብር ካፒታልም አፍርቷል። በተጨማሪም የተለያዩ ለዳቦና ለሌሎች ምርቶች መዋል የሚችሉ ማሽኖችን ማምረት የሚያስችል አቅም ገንብቷል። የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ከፍቶ ሠራተኞቹንና ሌሎች ወጣቶችን በዲግሪ ደረጃ በማሰልጠን የሙያ ሽግግር እያደረገ ይገኛል።
‹‹ሰፊ ገበያ መፈጠሩ ሠራተኛው ደስተኛ ሆኖ ሥራውን እንዲሰራ ያስችላል›› ያለንና በኢንዱስትሪው በዳቦ ማሽን ሥራ ላይ ያገኘነው ወጣት ዘሪሁን ተረፈ ነው። አሁን ገበያ በመኖሩ ምክንያት ከድርጅታቸው ጉርሻ (ቦነስ)የሚያገኙበት አጋጣሚም ተፈጥሮላቸዋል። አቶ አውቶ ደሳለኝን ከኢንዱስትሪው በግል ያዘዙትን ማሽን ሲወስዱ ያገኘናቸው ደንበኛ ናቸው።
እርሳቸው እንደሚሉት ማሽኑን በተሟላ ሁኔታ አግኝተው በቤታቸው ውስጥ የመጠቀም የቆየ ፍላጎት ነበራቸው። ነገር ግን ከውጪ የሚገቡት ተመሳሳይ ማሽኖች የኃይል ፍጆታቸው ከፍተኛ ስለሆነና ማሽኖቹ የተሟሉ ስላይደሉ እንዲሁም ያዘዙት ማሽን ሲንግል ፌዝ በመሆኑና የኃይል ፍጆታውም አነስተኛ ስለሆነ ማሽኑን ለመግዛት ወስነዋል።
በተመሳሳይ ወይዘሮ ኢዶት አብርሃ ምንም እዚሁ ኢንዱስትሪ ውስጥ ነው ያገኘናቸው። እንደነገሩን የመጡት ከደብረዘይት ሲሆን ማሽኑን በቅርቡ ባለቤቱ ሲተዋወቅ በማየታቸውና ጥቅሙን በመረዳታቸው ነው ማሽኑን የሚገዙት። የሚተዳደሩት ዳቦ ጋግረው በመሸጥ ነው። ኩፍ ማለቱና መብሰሉን የሚያውቁት በግምት እንደነበር ይናገራሉ። የሚያቦኩትም በእጅ ነው። ይህ ማሽን ኩፍ የሚልበትን፣ ዳቦ የሚበስልበትን ሰዓት ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ችግራቸውን ያቃልለዋል። ዋጋውም ቢሆን ከ150 እስከ 200ሺህ ብር በመሆኑ ተመጣጣኝ ነው።
በፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ መለሰ እንደሚሉት ወጣቱ የኢኮኖሚ አቅሙን መገንባት የቻለው በተፈጠረለት የገበያ ትስስር ሂደት ነው። በባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ከሚሰጡ ድጋፎች ውስጥ አንዱ የገበያ ትስስር መፍጠር እንደመሆኑ የካፒታል ዕቃ ሊዝ ፋይናንስ ተቋም ማሽኑን ገዝቶ በብድር ለኢንዱስትሪዎች እንዲሸጥላቸው የሚያደርግ የገበያ ትስስር ፈጥሮለታል።
ወጣት ያሬድን ጨምሮ በመስኩ ለተሰማሩ ወጣቶች ከሀገር ውጪ ባሉ የገበያ አማራጮች ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ የሚያስችል ሥልጠናዎች ከመስጠታቸውም ባሻገር የተለያዩ የገበያ ዕድሎችም ይመቻችላቸዋል። ወደውጭ ሀገራት እየተጓዙ ተሞክሮ እንዲቀስሙ ያደርጋል።
ሀገር ውስጥም በባዛር በማሳተፍ ከሸማቾች ጋር እንዲገናኙ ይደረጋል። ምርታቸውን ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ በቀላሉ ማስተዋወቅ የሚችሉበት ሥልጠናም ይሰጣቸዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ለወጣቱ ገበያ በመፍጠር የኢኮኖሚ አቅሙን የገነቡለት እነዚህ ብቻ ሳይሆን ማሽኖቹ የግል ፈጠራ ብቃት ላይ የተመሰረቱና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘቡ መሆናቸው ነው። ማሽኖቹ የኃይል ፍጆታቸው አነስተኛ መሆኑ፤ ምርቶቹ የሀገር ውስጥ መሆናቸውና ቢበላሹ እንኳን የመለዋወጫ እጥረት የማያጋጥም መሆኑ ለገበያ ትሥሥሩ ተጨማሪ መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 5/2013