አብርሃም ተወልደ
ከ1966 አብዮቱ በፊት ዙፋኑን ክፉኛ ያናጋ ተቃውሞ ቢኖር የ1953ቱ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ነው።ሙከራው ባይሳካም ከፍ ብለን እንደጠቀስነው በፖለቲካ ተቃውሞ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ የሆነ ምዕረፍ መክፈቻ ነበር።ሙከራውን ያቀነባበሩት ሁለቱ ወንድማማቾች መንግስቱ እና ግርማሜ ንዋይ ከ1953 በፊትም ሆነ በኋላ የታየውን የተቃውሞ ሁለት ገጽታዎች ማለትም ወታደራዊ እና ሲቪላዊ የሚያንጸባርቁ ናቸው።
ብርጋዲዬር ጄኔራል መንግስቱ ንዋይ ከ1928 በፊት በካዴትነት ይሰለጥኑ ከነበሩትና ከጦርነቱ በኋላ የጥቁር አንበሳ ድርጅትን አቋቁመው ጠላትን የተፋለሙት የወጣት አርበኞች ትውልድ አባል ናቸው። ገርማሜ ንዋይ የአገር ቤት ትምህርታቸውን በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ኮተቤ) ካጠናቀቁ በኋላ ወደ አሜሪካ ተጉዘው ከዊስኮንሲን ዩኒቨርሲቲ በቢኤ ዲግሪ ተመርቀዋል። ቀጥሎ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ተከታትለው በኤም ኤ ተመርቀዋል።
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ታሪክ” በተሰኘ መጽሐፋቸው የመፈንቅለ መንግስቱ ጠንሳሽ ገርማሜ ለመሆኑ ብዙ ጠቋሚ ማስረጃዎች አሉ ላሉ። ትምህርቱን ጨርሶ በመንግስት ስራ ከተሰማሩ ጊዜ አንስቶ አይነተኛ ባህሪያቸው ከፍተኛ የኃላፊነት ስሜትና መቆርቆር ነበር። መንግስት ይህን አዝማሚያቸውን አልወደደላቸውም። ስለዚህ በተከታታይ በስውር ግዞት የሩቅ ግዛቶች አስተዳዳሪ ተደርገው ተሾመው መጀመሪያ ወላይታ ቀጥሎ ጅግጅጋ ተልከዋል።
እርሳቸው ግን የተመደቡባቸውን አካባቢዎች የፍትሐዊ አስተዳደር መሞከሪያ ጣቢያዎች አደረጓቸው። የወላይታ ገዥ በነበሩበት ጊዜ የሰፈራ ፕሮግራምን ጀመሩ።በጅግጅጋም የሱማሌዎችን ህይወት ለማሻሻል በወሰዷቸው እርምጃዎች ከፍተኛ ተወዳጅነትን አገኙ። ነገር ግን መንግስት ጠረፍ አገር መላኩ ሳይበቃ በስራቸው
ጣልቃ እየገባ ማደናቀፍን ተያያዘ። በዚህ ጊዜ ነው ገርማሜ ማዕከላዊውን መንግስት መቀየር አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑን ተረድተው ወንድማቸውን ማነሳሳት የጀመሩት።
ገርማሜ ንዋይ እና የክቡር ዘበኛው አዛዥ ጄኔራል መንግስቱ ንዋይ የመፈንቅለ መንግስቱ ጠንሳሽ ሆኑ። ሁለቱ ወንድማማች ሌሎች ተባባሪዎችን ከጐናቸው አሠለፉ። ዋና ተባባሪያቸው የደህንነት ሹሙ ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁና የፖሊስ ኮሚሽነሩ ጄኔራል ፅጌ ዲቡ ናቸው። ንጉሡ ለጉብኝት ወደ ብራዚል ማምራታቸውን እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ታህሳስ 3 ቀን 1953 አብዛኛውን የአዲስ አበባ አካባቢና እንደ የገንዘብ ሚኒስቴር ፣ብሔራዊ ባንክና ሬዲዮ ጣቢያ ያሉ ዋና ዋና የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ተቆጣጠሩ።
ታህሳስ 4 እና 5 ቀን 1953 ዓ.ም ለመፈንቅለ መንግስቱ እንቅፋት ይሆናሉ ተብለው የታሰቡትን ባለስልጣናት በገነተ ልዑል ቤተ መንግስት (በአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በዋና ግቢ ) አሰሩ። የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ መንግስት መውረዱን በልጃቸው አልጋ ወራሽ አስፋው ወሰን ድምፅ በብሔራዊ ሬዲዮ ጣቢያ በተሰራጨ መግለጫ ታውጆ አዲሱ መንግስት በአልጋ ወራሹ እንደሚመራ ተገለጸ።
በብርጋዲየር ጄኔራል መንግስቱና በወንድማቸው ገርማሜ ንዋይ የተረቀቀው ባለ 16 ነጥብ ማሳሰቢያም ተነበበ።የማሳሰቢያው አብይ መልዕክት ኢትዮጵያ በቅርብ ነጻ ከወጡት የአፍሪካ አገራት ጋር እንኳን ስትነጻጸር ምን ያህል ወደ ኋላ እንደቀረችና መፈንቅለ መንግስቱም ያስፈለገው የአገሪቱን የቀደመ ዝናና ክብር ለመመለስ መሆኑን ነበር። ሊወሰዱ ስለታሰቡ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችም ተተረኩ።
ንጉሠ ነገሥቱ ዜናውን በመስማታቸው በደቡብ አሜሪካ የሚያደርጉትን ጉብኝት አቋርጠው አደጋ ላይ የወደቀውን ዙፋናቸውን ለማዳን መገስገስ ጀመሩ። የንጉሱ ታማኞችም መፈንቅለ መንግስቱን ለማክሸፍ ተዘጋጁ።የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ሜጄር ጄኔራልመርዕድ መንገሻ የሚመሩት የምድር ጦር ኃይል የክብር ዘበኞችን እንቅስቃሴ ለማኮላሸት ተንቀሳቀሰ።አየር ኃይሉን ከጐናቸው አሰልፈው የፓትርያርኩ የአቡነ ባስልዮስ የውግዘት ቃልን ጨምሮ መፈንቅለ መንግስቱን የሚያወግዙ በራሪ ወረቀቶች እንዲበተኑ አደረጉ። ከመፈንቅለ መንግስቱ በተጻራሪ የቆሙ ወታደሮች ከዳር አገር ወደ አዲስ አበባ ተሰበሰቡ። ይህን የተባባረ ኃይል ለመቋቋም የክብር ዘበኛና በብርጋዴል ጄኔራል ጽጌዲቡ የሚመራው የፖሊስ ሰራዊት በቂ አልነበረም።
ይህ የኃይል አሰላለፍ አስፈርቷቸው ይመስላል መፈንቅለ መንግስት አድራጊዎቹ ወታደሮች የተኩስ ልውውጥ እንደ ተጀመረ ብዙም ሳይቆይ ተኩስ ለማቆም መስማማታቸውን ገለጹ። የንጉሡ ታማኞች ግን ድልእንደሚያደርጉ ስለተረዱ ሳይስማሙ ቀርተው ከሁለት ቀን ጦርነት በኋላ ተሳካላቸው።
እነጄኔራል መንግስቱ ንዋይ ሙከራቸው እየከሸፈ መሆኑን ተረዱ። በዚህ ጊዜ በገነተ ልዑል ቤተ መንግስት ከአገቷቸው ሹማምንት መካከል ታህሳስ 6 ቀን 15 ባለሥልጣኖችን ረሸኑ።መንግስቱ እና ገርማሜም ከአዲስ አበባ በመውጣት ሽሽት ጀመሩ። ወንድማማቾቹ ከተማውን ለቀው ሲወጡ ንጉሡ በድል ወደ ከተማዋ ገቡ። የደህንነት ክፍሉ የበላይ ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ ራሳቸውን አጠፉ።ገርማሜ ዝቋላ አካባቢ ከሚያድኑት ፖሊሶች እና ወዶ ዘማቾች ጋር ተታኩሰው ሞቱ። መንግስቱ ንዋይ ክፉኛ ቆስለው ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ለፍርድ ቀርበው በስቅላት ተቀጡ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 4/2013