አብርሃም ተወልደ
የጥቁር እንቁ፣ የጀግንነት መስፈሪያ፣ የስልጣኔ በር ከፋች… አጼ ምኒልክ ያረፉት በወርሃ ታህሳስ 3 ቀን 1906 ዓ.ም ነው:: የንጉሱ አሟሟት ዛሬም ድረስ አወዛጋቢነት ያልተለየው ሆኖ ቀጥሏል:: ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ስለ አፄ ምኒልክ አሟሟት ሲጽፉ፣ “ንጉሱ የሞቱት መድኃኒት ተደርጐባቸው ነው” የሚል ወሬ እንደነበር አስፍረዋል:: ይህ ወሬም በወቅቱ ከፍተኛ ውይይትና ክርክር አስነስቶ እንደነበር ጽፈዋል::
ዳግማዊ አጼ ሚኒልክ ወደ አስራ ዘጠነኛው ምዕተ አመት ቢሻገሩም ከሙሉ ጤንነት ጋር ነበር ለማለት አይቻልም፤ ዕድሜያቸው ወደ ሰባ እየተጠጋ ነበር።በዚያን ዘመን በአፍሪካ አንድ ሰው ለመኖር የሚችለው በማዕከላዊ ግምት ሃምሳ ዓመት ሲሆን፣ ከነበረበት ጭንቀትና ኃላፊነት አንጻር ይህን ያህል ዕድሜ ማግኘቱ ተመስገን እንደሚያሰኝ ደግሞ ያስነበበው የኢትዮጵያ ታሪክ ከሚኒሊክ እስከ አሁን የሚለው የደራሲ ተክለፃዲቅ መኩሪያ መጽሐፍ ነው።
ከዓድዋ ዘመቻ በኋላ የሩሲያ ሐኪሞች ኢትዮጵያ ስለደረሱ ንጉሱ እነርሱ ዘንድ አልፎ አልፎ ምርመራ አካሂደዋል።አጼ ምኒልክ የኩላሊት ህመም እንዳለባቸው ቢታወቅም፣ ይህ በሽታ አስገድዶ አልጋ ላይ እንዳልጣላቸው ይነገራል፤የልብ ህመም እንደነበረባቸውና ለመታመማቸውና ለመድከማቸው ዋናው ምክንያት እሱ መሆኑንም ቪታሊን የተባለው ሐኪም በ1900 ባደረገው ምርመራ አረጋግጦ እንደነበርም ተፅፏል::
ጸጥታ እንዳይደፈርስ እየተባለ የነገስታት ህመም በይፋ አይነገርም፤በዘመን ታሪክም እንዲህ ዓይነቱ ዜና አይነገርም፤ሕዝቡ የሚሰጋው ሰውና እንጨት ተሰባሪ ስለሆነ ከምኒልክ ሞት በኋላ ላለው ዘመን እንጂ በቅርቡ ምኒልክ ይታመማል የሚል በሚል አልነበረም።
ገናናው ንጉሰ ነገስት በ1990 ዓመተ ምህረት የጀመራቸው በሽታ እየጸናባቸው ሄዶ በመጨረሻ ሰውነታቸው ዝሎ አንደበታቸው ተዘግቶ ቆይቶ ታህሳሰስ በደግነት እየመለሱ ጥፋቱን ሁሉ በትዕግስት እያሸነፉ አገር የሚሰፋበትን ልማት የሚዳብርበትን ሕዝብ ዕረፍትና ሰላም የሚያገኝበትን ከማሰብና ከማስፈጸም አልተቆጠቡም፤የአውሮፓውያን ኃያል መንግስት በጦር ሜዳ በማሸነፍ ኢትዮጵያውያን በዓለም እንድትደነቅ አድርገዋል።
ስለዚህ ስርዓተ ቀብራቸው በታላቅ ስነ በዓል መሳፍንትና መኳንንት የውጭ መላክተኞች በተሰበሰቡበት በወግ በማዕረግ ሊፈጸም በተገባ ነበር።ዳሩ ግን ባልሰለጠኑና በሕግ መንግስት መተዳደርን ባልለመዱ አገሮች ማለትም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች በወግ በማዕረግ የሚቀበር ንጉሱ በዙፋን በሰላም የሚተካ አልጋ ወራሽ ማግኘት ብርቅ ነው።
በዚህ ምክንያት የሞተን ንጉስ ግርግር እንዳይነሳ አቻኩሎ በድብቅ መቅበር የተለመደ ነበር።ይህንንም በኩር ጋዜጣ ታህሳስ 8 ቀን 2011 ዓ.ም ሰኞ የምትታተም ጋዜጣ የንጉሱን ህልፈት ባስነበበት አምድ እንዲህ ብሎ ነበር ፤ ታላቁ ንጉስ ከዚህ ሁሉ ህመምና ውጣ ውረድ በኋላ ታህሳስ ሦስት ቀን 1906 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ:: በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ የተመለከቱት በርትሊ እንዳሰፈሩት በመጨረሻው ሰዓት ንጉሱ በጠና ታመው ሐኪማቸው ህክምና ሲጀምሩ ባጠገባቸው የነበሩ ታላላቅ ሰዎችና የሐይማኖት አባቶች በመከልከላቸው አረፉ::
የንጉሱን መሞት የሰሙት የግቢው የሥራ ቤቶች የለቅሶ ድምፅ ቢያሰሙም፣ የልጅ እያሱ ባለሟሎች አገር እንዳይሸበር በመስጋት ዝም አሰኝተዋቸዋል:: አቤቶ እያሱ በዕለቱ ያደሩት ፍልውሀ በሚባለው የመታጠቢያ ቤታቸው እንደነበረም ተገልጿል:: ማለዳ የንጉሱን ሞት ሲሰሙ ግን መደናገጣቸውንና ቤታቸው ትንሽ ከተቀመጡ በኋላ አገር እንዳይሸበር በማለት ሐዘናቸውን በይፋ አለማሳየታቸውን ታሪክ መዝግቧል::
እንዲያውም በማግስቱ ቅዳሜ ወደ ጃንሜዳ በመውጣት ከአሽከሮቻቸው ጋር ፈረስ ጉግስ ሲጫወቱ ዋሉ::የንጉሱ አስክሬን አምሮ በተሰራ ብረት ሳጥን ተደርጐ በቤተመንግስቱ ውስጥ ባሉት የስዕል ቤት ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን በክብር ተቀመጠ:: ከዚህ በኋላ ዓፄ ምኒልክ በህይወት እንዳሉ እየተነገረ እስከ ሰገሌ ዘመቻ ድረስ ለሁለት ዓመት ከአስር ወራት ተደብቆ ቆየ::
አዲስ ዘመን ታህሳስ 4/2013