አብርሃም ተወልደ
በህይወታችን ብዙ ነገሮችን አይተናል፤ ሰምተንማል፡፡ በአንዳንዶቹ ስናዝን በሌሎቹ ስንደሰት ስንቱን አልፈናል:: አንዳንዱን ስንረሳ አንዳንዱን ደግሞ ተሸክመን ኖረናል፤ ለዘመናት ከኅሊና የማይጠፉ ሁሌም የሚጎረብጡ ንግግሮች አሉ፡፡
በበጎ በኩል ደግሞ በህይወታችን ያሳለፍናቸው መልካም ውሳኔዎች ሁሌም ይታወሳሉ፤ በህይወታችን የተጎናጸፍናቸው ለውጦች አይረሴ ናቸው፤ መልካም ሰዎች ወደ ልቡናችን ጣል ያደረጉት በጎ ሀሳብ እንደዚያው፡፡
ጆሮ በመስማቱ ብዛት አይሞላም፤ አይንም በማየቱ ብዛት አይጠግብም አይደል የሚባለው፡፡ በሁለቱም የስሜት ህዋሶቻችን ያገኘናቸው መረጃዎች እንደ ክብደታቸው እና ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው ከእኛ ጋር ይቆያሉ አሊያም ይረሳሉ፡፡ ህሊና ግን አጥርታ ታያለች፡፡ በምላሳችን የረጨናቸው ክፉም ሆነ በጎ ሃሰቦች ወደ አንድ ግለሰብ ልብ ከገቡ አይወጡም፡፡
ምላስ እንደተጠቀምንበት ሁኔታ አልሚም አጥፊም ሆኖ ሊገኝ ይችላል፡፡ በቀና ከተጠቀምክበት ያለማል፤ የትውልድን የሩጫ ፍጥነት እንዲጨምር ያደርጋል፤ በክፉ ከተጠቀምንበት ትውልድን ተብትቦ በማሰር መድረስ ከሚገባው ቦታ እንዳይደስ ያደርጋል፤ ያሰነካክላል፡፡
ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ይባል የለ፤ እውነት እኮ ነው! ባሻዬ አየህ ምላስ የጦር መሳሪያም ጭምር ነው፤ በሃሰትም ይሁን የእውነት ፕሮፖጋዳዎች ብዙዎችን ትጥቅ ታስፈታለህ፤ በጦር ሳትገጥም ታሸንፋለህ፤ እረ ስንቱ …ብቻ ምላስ እንደተጠቀምክበት ሁኔታ ውጤቱ ይመዘናል፡፡
አንዳንድ ደግሞ ምላስ አለ፡፡ እሳት ያዘለ፣ የሚያቃጥል፣ የሚለበልብ አይደለም መስራት ማሰብ እንዳትችል የሚያደርግ፡፡ አንድ ምሳሌ ልጠቅስ ነው፤ በአንድ በህይወት በሌለ መጽሔት ላይ ያየሁት ጽሁፍ ትዝ ያለኝ፤ ጽሁፉ “አጥንት የሌለው፤ ነገር ግን አጥንት የሚሰብር›› ይልና ከታች እንደ መልስ ‹‹ምላስ›› ተብሎ ተጽፏል፤ አየህ ምላስ ምን ያህል አቅም እንዳላት፤ እንዴት አንድ ሰውን ማነሳሳት ወደ ላቀ ተግባር ማሻገር የምትችል እንደሆነች በቀና ካልተጠቀምናት ደግሞ እንዴት አጥንት ሰባሪ እንደሆነች፡፡
አቅም ገዳይ እንደሆነች ለመግለጽ ይመስለኛል ይህ አባባል የመጣው ደግሞም እውነት ነው፤አንዳንድ ምላስ ደግሞ አለ እየተሸነፈ እንድትበረታ ድካምህን ሽንፈትህን ለሌላ ድል መነሻ አድርገኸው እንድትጠቀምበት የሚያደርግህ፤ አንድ የማውቃት ጨዋታ ትዝ አለችኝ፤ አንድ አትሌት ከወሎ ለመላው ኢትዮጵያ ጨዋታ ተወክሎ አዲስ አበባ ይመጣል አሉ፤ ድሮም ወሎዎች ፍቅር ማበረታታት እና ድጋፍ እንጂ ለሰው እንቅፋት መሆንን የማይወድ የመቻቻል እንዲሁም የመቻል ምሳሌዎች ናቸው፤ ታዲያ ከዚህ አካባቢ የፈለቀው አደም የተባለው ሯጭ ውድድር ለመጀመር ከሚያሟሙቅበት አንስተው እስከ ወድድሩ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የተሰጠው ድጋፍ ከአሸናፊዎች እኩል እንዲሰማው የሚያደርግ ነበር፡፡
አደም በውድድሩ መሐል እየመራ ባለበት ደጋፊዎቹ “አደም መራቸው ….!”እያሉ ሲጨፍሩ ቆዩ፤ ከጥቂት ቆይታም በኋላ አደም በሯጮች መሃል ገባ፤ እነዚሁ ደጋፊዎች አሁንም ከአደም ጋር ናቸው፤ “አደም ታጀበ…!” በማለት ድጋፋቸውን ቀጠሉ፡፡ ወድድሩም ቀጠለ … አደም ትንሽ ደከም አለው፤ ከኋላ ቀረ፤ ደጋፊዎቹ “አደም ታጀበ…!”ብለው ደገፉ፤ መመራቱን ሳይቀር ማበረታቻ አደረጉት፤ በዚህ ብቻ አለበቁም አደም ውድድሩን የመጨረሻ ሆኖ ሲያጠናቀቅም ደጋፊዎቹ አደምን ማለታቸውን አላቆሙም፤ “አደም ናቃቸው…” በማለት ደጋፋቸው እስከ መጨረሻ በመስጠት አበረታቱት ይባላል፡፡
አየህ ባሻዬ! ነገሩ ቀልድ አዘል ፈገግታን የሚያጭር ቢሆንም ፣ የአደም ደጋፊዎች ልብ እና አይን ግን መልካሙን ብቻ የሚያይ ስለነበር ነው፤ በሁሉ ሁኔታዎች ውስጥ በጎ የሚታያቸው ናቸው፡፡
ዋናው ጉዳይ በበጎ ሃሳብ እና ንግግር አቅም ለሌለው አቅም መስጠት፤ ለደከመው የመበርታት ምክንያት መሆን፤ እንዲሁም ለወደቀው የመነሻ ድጋፍ ለመሆን መጣር ነው፤ ይህ ቀላሉ መርህ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ድርጊት ነው፡፡
በታሪኩ ላይ የተገለጸው “አደም” ያገኘው ድጋፍ በቀጣይ በሚያደርገው ውድድር የተሻለ ነገር ለማሳየት የሚያስችል ይሆናል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ ቢያንስ ለእነዚህ በጎ ደጋፊዎቹ ሲል በርትቶ ይሰራ ይሆናል፡፡ ስለሆነም እክል ከመሆን አቅም መሆን አስፈላጊም ወሳኝም ነው፡፡
አለ ደግሞ ሞክረህ አይደለም ሰርተህ ከአመጣኸው ነገር መልካም ማየት የሚሳነው፤ የሚባላ ምላስ፤ ገዳይ የሆነም አለ፡፡
ከታላቁ መጽሐፍ ላይ አንድ ታሪክ ላንሳ፤ ዳዊት እና ጎልያድ የተባሉ በተለያየ ጎራ የተሰለፉ ናቸው፤ አንደኛው ጦረኛ የጦር ጥቅም ያሟላ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ብርቱ እና ብልህ ነው፣ ብልሁ በቁመትም በጦር ትጥቅም ከተጋጣሚው ጋር ሊተያይ አይደለም ለማሰብ የሚከብድ አቋም ላይ ያለ ነው፡፡ ታዲያ ዳዊት ጎሊያድን እገጥመዋለሁ ሲል ትችት ተሰነዘረበት፤ ትችቱም ከየትም ከሩቅ የመጣ አልነበረም፤ ከገዛ ወንድሞቹ የመጣ ነበር፡፡ ድሮም አንተ እኮ…! የሚል ሰባሪ ምላስ የገጠመው፡፡
ዳዊት ግን አሸነፈ፤ አየህ ባሻዬ! ዳዊት አደናቃፊ ምላስ አይቶ ቢቀር ኖሮ የትም አይደርስም ነበር፡፡ አገር ያስጨነቀውን ጣለ፤ ሰላምም አመጣ፡፡ እንዲህ ያሉ አደናቃፊ ምላሶችን በመተው ወደ ፊት …አዎ ወደ ፊት ብቻ፡፡ ምክርን ስንሰጥም ሆነ ስንቀበል ከመልካሙ ብንጀምር ለምንመክረውም ሆነ ለሚመክረን ምቹ አየር ለመፍጠር ይረዳናል፤ ስለሆነም ሁሌም ከበጎ ጎን መጀመር መልካም ተግባቦትን ይፈጥራል፡፡
እኛ አኮ ባሻዬ! የደረጀ ባህላዊ እውቀት ያለን ለሁሉ በሁሉ ምሉዕ የሆንን ህዝቦች ነን፤ አበው ሲናገሩ እህልን አላምጦ ነገርን አዳምጦ ይላሉ፤ ባፍ ይጠፉ በለፈለፉ፣ የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ፣ ወዘተ ማለታቸውም ምላሳችን ቀናቀናው ላይ እንዲያተኩር የሚያስገነዝብ ነው፡፡
አየህ! ይህ ቱባ እውቀት በስርዓት በመርህ እንድናወራ ይረዳናል፡፡ ከማን ጋር እንዴት እንደምናወረ የሚገራም ነው፤ በዚህ መርህ ውስጥ ስትሆን ከችግር ይልቅ መልካምነት ከድካም ይልቅ የነገ ብርታት ይታይሃል፤ አንድን ግለሰብ ወደ ፈለግነው አቅጣጫ መውሰድ እንድንችል ይረዳናል፤ አለውሉ ከመተቸት እንዲሁም ከመሳደብ ይልቅ በጎውን ነግረን ወደ መልካም ለመምራት ያግዘናል፡፡
በአገሪቱ ባህላዊ እወቀት ውስጥ የደረጀ ድንቅ የመቻቻል የሰላም እና የፍቅር እሴቶች አሉ፤ እኛም ከእነዚህ ውስጥ መልካም መልካሙን በመውሰድ ለብርታት መጠቀም ይገባናል፡፡ ከአገር አልፎ ለዓለም ምሳሌ ሊሆን የሚችለውን ድንቅ ባህላዊ ዕውቀት በማበልጸግ ለግልና ለአገራዊ መግባባት መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን ኢትዮጵያ የፍቅርና የመቻቻል አገርነቷ ይቀጥላል፡፡ አንደበታችን ሆይ! መልካም መልካሙን አርግ !!
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 3/2013