አስናቀፀጋዬ
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ እየተገነቡ ካሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ የአካባቢውን ማህበረሰብ የአስፓልት መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆን ከማስቻል በዘለለ የእህልና የቡና ምርቶች ወደ ገበያ እንዲወጡ በማስቻል ረገድ ቁልፍ ሚና እንዳለውም ታምኖበታል፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የደንጎሮ-ኪንጊ-መቀቢላ መንገድ ስራ ፕሮጀክት ቆሟል::
የደንጎሮ-ኪንጊ-መቀቢላ መንገድ ፕሮጀክት ተጠሪ መሃንዲስ ኢንጂነር አለማየሁ ጌታቸው እንደሚገልጹት በምእራብ ወለጋ አካባቢ የሚገኘው የደንጎሮ-ኪንጊ-መቀቢላ መንገድ ስራ ፕሮጀክት በታህሳስ ወር 2018 ኮንትራቱ ተፈርሞ ሰኔ ላይ ግንባታው በይፋ ተጀምሯል::
የመንገድ ግንባታውንም ሀገር በቀሉ ሳምሶን ቸርነት ጄኔራል ኮንትራክተር በስራ ተቋራጭነት እንዲሁም የማማከር ስራውን በለስ ኮንሰልቲንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህር እያከናወኑት ይገኛሉ፡፡ ለመንገድ ግባታውም በኢትያጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከ416 ሚሊዮን ብር በላይ በጅት በጅቶለታል፡፡
መንገዱ በአስፓልት ኮንክሪት /double surface treatment/ ደረጃ ግንባታው የሚከናወን ሲሆን ስራውን ሰርቶ ለማጠናቀቅ የሶስት ዓመታት ቀጠሮ ተቆርጦለታል፡፡ የመንገዱ ርዝመትም 30 ኪሎሜትር የሚረዝምና ከደንጎሮ ተነስቶ መቀቢላ ድረስ ይዘልቃል:: መንገዱ በገጠር አካባቢ 7 ሜትር ወደጎን ሲሰፋ በደንጎሮ ከተማ 10 ሜትር የጎን ስፋት አለው፡፡
እንደ ተጠሪ መሀንዲሱ ገለፃ የመንገዱ አጠቃላይ ፊዚካል አፈፃፀም 38 ከመቶ የደረሰ ሲሆን ስራውን ለማከናወን ከተያዘው የ43 ከመቶ አቅድ አንፃር አፈፃፀሙ በ5 ነጥብ 8 ከመቶ ያንሳል፡፡ ይህም አፈፃፀሙ ከእቅድ በታች መሆኑን ያሳያል፡፡
መንገዱ የሚገነባበት አካባቢ ዝናባማ መሆንና በአካባቢው ያለው የፀጥታ ችግር ደግሞ ለአፈፃፀሙ ዝቅተኛ መሆን እንደዋና ምክንያት ይጠቀሳል፡፡ በተለይ በአካባቢው ላይ በሚታየው ተደጋጋሚ የፀጥታ ችግር ምክንያት የመንገድ ስራው ከቆመ አንድ ወር ሞልቶታል::
ከዚህ በተጨማሪም በአካባቢው ህብረተሰብ ጥያቄ መሰረት ቀደም ሲል የነበረው የመንገዱ ዲዛይን ተቀይሮ የመንገዱ አቅጣጫ እንዲቀየር ተደርጓል:: በዚህም መሰረት 13 ኪሎ ሜትር ያህል የሚሆነው የመንገዱ ክፍል አቅጣጫውን ከሚሽን ካምፕ ወደ ቢላ ቀይሯል፡፡ ይህም ተጨማሪ ስራ በመሆኑና ለመንገዱ አፈፃፀም ዝቅተኛ መሆን ያራሱን አስተዋፅኦ ማበርከቱ ተነግሯል፡፡
እስካሁን ባለው የመንገድ ፕሮጀክቱ ሂደት 32 ከመቶ የምንጣሮ ስራ፣ 71 ከመቶ የአፈር ቆረጣና 28 ከመቶ የአፈር ሙሌት ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ ስድስት የማይነር ድሪኔጅ ስትራክቸር ስራዎችም ተሰርተዋል፡፡የወሰን ማስከበር ስራዎችም በአብዛኛው ተጠናቀዋል:: በመንገድ ፕሮጀክቱ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት በተለይ ኮንትራክተሩ ካለው የስራ ጫና አኳያ የስራ ፕሮግራሙን እንዲከልስና ተጨማሪ ማሽኖችን እንዲያንቀሳቅስ በማድረግ በተሰጠው ጊዜ ግንባታውን እንዲያጠናቅቅ ጥረት እየተደረገም ይገኛል፡፡
ተጠሪ መሀንዲሱ እንደሚሉት በቀጣይ ወደ 13 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ባለው የመንገዱ ክፍል ላይ 2 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የአፈር ቆረጣ ስራ ይከናወናል:: የሰብ ቤዝ፣ ቤዝ ኮርስ፣ የሰርፌስ ትሪትመንትና የአስፓልት ስራዎችም ደረጃ በደረጃ ይከናወናሉ፡፡ ወደ 44 የሚጠጉ የማይነር ድሪኔጅ ስትራከቸር ስራዎችም ይሰራሉ፡፡ 16 ሜትር ስፋት ያለው የአንድ ድልድይ ስራም የፕሮጀክቱ አካል ነው፡፡
ከፀጥታና ከዝናብ ጋር የተያያዙ ችግሮች ከማጋጠማቸው ውጪ የመንገዱ አፈፃፀሙ በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህ ችግሮች ባያጋጥሙ ኖሮ የፕሮጀክቱ አፈፃፀም ከዚህም በላይ መሄድ ይችል እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም በኮንትራት ስምምነቱ መሰርት የመንገድ ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ በ2022 መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ወቅት ፕሮጀክቱን የገጠሙት ችግሮች በቶሎ የሚቀረፉ ከሆነም በተያዘለት የጊዜ ገደብ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ስራ ተቋራጩ የስራ ፕሮግራሙን እንዲከልስ ተደርጎ በተያዘው የጊዜ ገደብ ውስጥ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ እየሰራም ይገኛል፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቱ ከመቆሙ ጋር በተያያዘና ቀደም ሲል የተጠቀሱት ችግሮች በቶሎ የማይፈቱ ከሆነ ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁ አይቀርም፤ ራሱ ስራ ተቋራጩም የማራዘሚያ ጊዜ መጠየቁ አይቀርም፡፡
ተቆጣጣሪ መሀንዲሱ እንደሚገልፁት በጥቅሉ ካለው ሁኔታ አኳያ መንገዱ ያለበት ደረጃ የከፋ የሚባል አይደለም፡፡ በዋናነት የአካባቢው የፀጥታ ችግር የሚስተካከል ከሆነና ስራ ተቋራጩ ተጨማሪ ማሽኖችን ማግኘት የሚችል ከሆነ በተያዘው የጊዜ ገደብ መሰረት ፕሮጀክቱን ማጠናቀቅ እንደሚቻል ይታመናል፡፡
የደንጎሮ-ኪንጊ-መቀቢላ መንገድ ስራ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሲሆን ብዛት ያለው የአካባቢው ማህበረሰብ የመንገድ መሰረተ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችለዋል፡፡ አካባቢው እህልና ቡና አብቃይ ከመሆኑ አኳያም እነዚህን ምርቶች ወደ ገበያ እንዲወጡ በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚናም ይጫወታል፡፡
መንገዱ በኪንጊ በኩል ወደ አማራ ክልል እንዲሁም በነቀምት በኩል ወደ አዲስ አበባ ለመንቀሳቀስ ከማስቻሉም በላይ አካባቢው ከፍተኛ የቡና ምርት ያለበት ከመሆኑ አኳያ ነዋሪው ምርቱን እንደልብ ወደ ገበያ ለማውጣትም ያስችለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 3/2013