ሰላማዊት ውቤ
ከተሜነት፣ ስልጣኔና አራድነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ያህል እርስ በእርስ የተመሳሰሉና የተሳሰሩ ናቸው። ስለነዚህ ጉዳዮች ለመተረክ ከከተሞች ምስረታ መነሳት ግድ ይላል። የተለያዩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በዓለማችን ከተሞች መቆርቆር የጀመሩት የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶችን በአግባቡ በአንድ ቦታ ላይ ማዘጋጀት መጀመሩን ተከትሎ ነው።
ይሄ ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረውና ኔዎሌቲክ ተብሎ የሚጠራው ዘመን የሰው ልጅ ከአደን እና ፍሬ ለቀማ ወደ ግብርና የተሸጋገረበትና ስልጣኔ የታየበት እንደሆነም ይነገራል። እነዚህ ከተሞች ለኑሮ አመቺ በሆኑ ስፍራዎች ላይ ሰፈራ እንዲጀመር ምክንያት ሆነዋል።
በከተሞች ምስረታ ቀዳሚውን ቦታ የሚይዙት የመካከለኛውና ሩቅ ምስራቅ ጥንታዊ አገራት ናቸው። እነዚህ አገራት ሜሶፖታሚያ፣ ኢራን፣ ግብፅ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ግሪክ እንደሆኑም ይጠቀሳል። በነዚህም አገራት የተቀለሱ ከተሞች በዓመዛኙ የፀጥታ ጉዳይ እና ወታደራዊ ስትራተጂን ከግምት ያስገቡ ነበሩ።
የተቆረቆሩትም በከፍታ ስፍራዎች ላይ ነው። በነዚህ ጥንታዊ ሀገራት ውስጥ ከተቆረቆሩት ከተሞች መካከልም ባቢሎን፣ ትሮይ፣ ስፓርታ፣ አቴንስ፣ ኦሎምፒያ፣ ሜምፊስ እና ካርቴጅ የተሰኙ ከተሞች ተጠቃሽ ናቸው። ቆይቶም ይህ የከተሞች መስፋፋት ወደ ሜዲትራኒያን ባህር አዋሳኝ ሀገራት እየሰፋም ሄደ። ሮም፣ ኮሎኝ፣ ቪዬና፣ ቡዳፔስት፣ ለንደን እና ፓሪስ ለተሰኙ ከተሞች ምስረታ በር ከፈተ።
እነዚህ ከተሞች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፉ በመምጣት ከተለያዩ ስፍራዎች የሚመጡ ነዋሪዎች እንደየ ወቅቱ ሁኔታ በተለያዩ ስራዎች ላይ በመሰማራት የገቢ ምንጭ መፈጠር አስችለዋል። ከከተሞች መመስረት ጋር ተያይዞ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተፈጠሩ የከተማ የሥራ መስኮች መካከል ንግድ፣ ዕደ ጥበብ፣ የፀጥታ ጉዳዮች እና የአስተዳደር ሥራዎች ይጠቀሳሉ።
ወደ ኢትዮጵያ የከተሞች አመሰራረት መለስ ስንል ደግሞ በኢትዮጵያ የከተሞች መቆርቆር ከቅድመ አክሱም ጀምሮ ሰፊ ታሪክ ያለው መሆኑን የከተማና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ላቀው አበጀ ነግረውናል። ምሁራን በዘርፉ ያካሄዱትን ሰፊ ጥናት ዋቢ በማድረግ አቶ ላቀው እንዳስረዱት በኢትዮጵያ የከተሞች አመሰራረትና ዕድገት በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላል። ከአገሪቱ የመንግስት ማዕከላትና ይህን ተከትሎ ከተፈጠሩ የከተሞቹ የጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ እና የከተሜነት ሂደት ይነሳል።
የአክሱም ዘመነ መንግሥት ከተሞች፣ የዛጉዌ ዘመነ መንግሥት ከተሞች እና የጎንደር ዘመነ መንግሥት ከተሞች ዕድገት ተብሎም ይከፈላል። በዛጉዌ፣ የሸዋ እና የጎንደር ዘመነ መንግሥታትም እንዲሁ የከተሞች መስፋፋት የነበረው ሚና ቀላል አልነበረም። የሸዋ ስርወ-መንግሥት ቢታይ በወቅቱ በአብዛኛው ነገሥታቱ ተንቀሳቃሽ ነበሩ። ዋና ከተሞቻቸውም ጦራቸው የሚያርፍባቸው ተለዋዋጭ የካምፕ ቦታዎች ናቸው።
በእነዚህ ጊዜያቶችም ቢሆን የከተሞች መፈጠር እና ማደግ ቀጥሎ ደብረ ብርሃን ከተማን ለመመስረት ተችሏል፡፡ ከተማዋ በተመሰረተችበት ወቅቱ በሀገር ውስጥ በተፈጠረ የእርስ በእርስ ሽኩቻ የሸዋው ስርወዎ-መንግሥት በአዳል ስርወ-መንግሥት ክፉኛ ተሸንፎ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የተሰደደበት ነበር። በኋላም በመጠናከር መልሶ ማጥቃት በማድረግ አሸንፏል። ነገር ግን ሠራዊቱ በጣም በመዳከሙ መቀመጫውን ወደ ጎንደር አካባቢ ቀየረ። የጎንደር ዘመነ መንግሥት ሲጀመር እነ ደንቀዝ፣ እንፍራንዝ፣ ጎርጎራ፣ መቅደላ፣ ጎንደር እና ሌሎች ከተሞች ተከትለው ተመሰረቱ፡፡
ይሁንና የከተሞቹን ስፋት፣ የነዋሪ ብዛት፣ የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ እና አጠቃላይ ተጽዕኖ ሲቃኝ ከአክሱም ስርወ-መንግሥት መውደቅ ጀምሮ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ባለው የኢትዮጵያ ታሪክ ቋሚ የሆነ ከተማ አልነበረም።
ለዚህም ለግንኙነት ችግር የሚፈጥር አስቸጋሪ የመልክዐ ምድር አቀማመጥ፣ ንግድን ጨምሮ ከግብርና ውጭ የነበሩ የተለያየ ሥራ መደቦች አለመዳበር በዋነኛ ምክንያትነት ይጠቀሳሉ። በውስጥ የነበሩ የእርስ በእርስ ሽኩቻዎችና የተለያዩ የውጭ ወረራዎች እንዲሁም ሁሉንም የሚያስተባብሩ ቀጣይ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥታት አለመኖር በክፍለ ዘመኑ ቋሚ ከተማ አለመፈጠር ምክንያት ሆነው ይጠቀሳሉ ፡፡
በነዚህ ምክንያቶች የተነሳ በኢትዮጵያ የዘመናዊ ከተሞች ታሪክ የሚጀምረው በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ሲሆን፣ ዘመኑ አፄ ምኒልክ ከአንኮበር ወደ ሊቼ ቀጥሎም አዲስ አበባን ዋና መቀመጫቸው አድርገው ከመቆርቆራቸው ይነሳል። በዚህ ጊዜም በኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩት ትላልቅ የሚባሉ ከተሞች አዲስ አበባ፣ ሐረር እና መቀሌ ብቻ ነበሩ። የነበራቸው የነዋሪ ቁጥርም 10 ሺህ የሚደርስ አልነበረም።
እነዚህ ቀድመው የተቆረቆሩት ከተሞች በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ለሌሎች በርካታ ከተሞች መቆርቆር በር ከፍቷል። 20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ መንፈቅ ላይ በኢትዮጵያ ከመንግሥት መረጋጋት እና መጠናከር፣ የኢትዮ-ጂቡቲ ምድር ባቡር አገልግሎት እና ሌሎች አዳዲስ የትራንስፖርት መንገዶች የተጀመሩበት ጊዜ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ አዲስ አበባን ጨምሮ ሌሎች መንገዶችን ተከትለው የተፈጠሩ አዳዲስ ከተሞች መታየት መጀመራቸውም ይነገራል። አዲስ አበባን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የተፈጠሩ የኢትዮጵያ ከተሞች ከሌሎች የአፍሪካ ከተሞች አመሰራረት የሚለያቸው ቤቶቹ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን የተገነቡ መሆናቸው ነው።
በዘመናዊ አሰራር በተደገፈ የምህድስና ጥበብ የተከናወኑና እየተስፋፉ መምጣታቸውንም ዳይሬክተሩ መረጃዎችን ዋቢ አድርገው አስረድተዋል፡፡
እርሳቸው እንዳሉት፤ በተለይ ከጥቂቶቹ በስተቀር በብዙዎች ትልልቅ ከተማዎች የመጀመሪያዎቹ የምስረታ ዓመታት የከተሞች አካባቢዎች ከወታደራዊ እስትራቴጂ አንፃር እና በአማካኝ የጉዞ ርቀት ላይ የሚገኙ ነበሩ። ለማረፊያነት የሚያገለግሉ በመንገድ ዳር የሚገኙ ቦታዎች በመሆናቸውም ለከተማነት ለመመረጥ በቅተዋል። መኖሪያዎቻቸውም የድንኳን እና የሣር ቤቶች ናቸው። ቀስ በቀስም እነዚህ የድንኳን እና የሣር ቤቶች በድንጋይ በጭቃ እና በእንጨት ቤቶች እየተተኩ ሄደዋል።
የአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥትም በርካታ አዳዲስ ከተሞች ተመስርቷል። በአፄው ዘመን ከተመሰረቱትም አሰበ ተፈሪ (ጭሮ)፣ ወንዶ ገነት፣ ሀዋሳ፣ ዲላ፣ አርባ ምንጭ፣ ነቀምት ወሊሶ (ጊዎን)፣ አምቦ (ሀገረ-ሕይወት)ከተሞች ይጠቀሳሉ። በደርግ ዘመንም እንዲሁ አዳዲስ ከተሞች ተፈጥረዋል።
ጎን ለጎን በርካታ ከተሞችም በህዝብ ቁጥር እና በመሰረተ-ልማት ስራዎች እመርታ ማሳየት ችለዋል። አሁን ባለው የከተሜነት መስፈርት በኢትዮጵያ ከሁለት ሺህ በላይ ከተሞች ይገኛሉ ለመሆኑ ከነዚህ ከተሞች የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከተሜነት፣ ስልጣኔና አራድነትን እንዴት ይረዱታል? የፒያሳን፣ የካዛንቺስና የኮልፌ ነዋሪዎች እንዲህ ብለዋል፡፡
ወጣት ሀምዛ አህመዲን ያገኘነው መሀል ከተማ ፒያሳ ውስጥ ባለው የተዘጋጁ ልብሶች መሸጫ መደብሩ ውስጥ በሥራ ላይ ነው። ተወልዶ ያደገው የአራዶቹ መንደር ፒያሳ ውስጥ ነው። አራድነትን እሱ እንደሚረዳው ብልጥ መሆን ለራስ ማወቅ ነው። ሲያጠናክረው ‹‹በትክክለኛ መንገድ ሄዶ ለራሱ የሚጠቅመውን ነገር ማድረግ›› ይለዋል። ‹‹አራዳ ማለት የሰውን ስብዕና ሳይነካ የራሱንም ባህል ሳያበላሽ የሀገሩንና የራሱን ጥቅም የሚያስጠብቅ ማለት ነው›› ሲልም ያክልበታል።
ሆኖም ‹‹አራዳ ነን›› ብለው ባልተገባ መንገድ የሚሄዱ፣ አራዳ ነን ብለው ገንዘብ የሚያጠፉ፣ መጠጣት፣ ማጨስ፣ አጉል ቦታ መዋል፣ በአንድ አካባቢ ተሰባስቦ አላፊ አግዳሚውን መልከፍ አራድነት የሚመስላቸውን ወጣቶች ማወቁንም አልሸሸገም። ይሄ ለእሱ ሞኝነት እንጂ አራድነት እንዳልሆነም ነግሮናል። በተለይ በፒያሳ አካባቢ አራድነት መገለጫው ብዙ እንደሆነ የሚጠቅሰው ወጣቱ አንዱ የሚጠቀሙት ቃላት መሆኑንም ጠቁሞናል። ለአብነትም ወንዱን አንቺ ብሎ መጥራት መለመዱን ይናገራል። ‹ይሄ በሃይማኖትም ሆነ በየትኛውም መንገድ መሰረት የሌለው አራዳም የማያስብል› ነው ይላል።
ሰዎች ሉዑል ብለው ይጠሯቸዋል፡፡ ሙሉ ስማቸውን ሊነግሩን ግን ፈቃደኛ አልነበሩም። ፒያሳ ቲሩም ጣፋጭ ኬክና ሬስቶራንት በረንዳ ላይ ተቀምጠው ሻይ ቡና ሲሉ ነው ያገኘናቸው። እንደነገሩን ተወልደው ያደጉት ፒያሳ ነው። ስለ ቦታውም ሆነ ስለ ከተሜነት፣ ስልጣኔና አራድነት ብዙ ያውቃሉ።
በሙሉ ጥቁር ሱፍ ልብስ የተዋቡት እኝህ ሰው በአጭር ጊዜ እንዳስተዋልናቸው ሳቂታና ጨዋታ አዋቂ ናቸው። ዕድሜያቸው ጎልማሳነትን ማገባደድ ውስጥ ቢሆንም እንደ ወጣት መቅበጥበጥ ይታይባቸዋል። አልፎ አልፎ ከተቀመጡበት ብድግ እያሉ በረጅሙ በተከፈተው ሙዚቃ ይደንሳሉ። እንደነገሩን ለእሳቸው አራድነት ማለት ይሄው ሁኔታቸው ነው። ደስተኛ መሆናቸው። እራሳቸው ዘና ብለው ሌላውን ዘና ማድረጋቸው። ስልጣኔ እንደ እሳቸው በአለባበስ ይገለፃል። ከተሜነትም ከዚሁ ጋር አብሮ የሚሄድ ነው። ለስልጣኔና ከተሜነት ፒያሳ ትልቅ ምሳሌው ናት።
ኮልፌ ያገኘነው ወጣት ዳዲ ካሳ ‹‹አራዳ ሰውን የሚረዳና የሚረዳ ለሰው ሟች ደግሞም የገባው ማለት ነው›› ይላል። እንደሱ ዕይታ ስልጣኔ ማለትም ይሄው ነው። ፋሽን ልብሶችን መከታተል በተለይ አለባበስ ማወቅ ብልህነት ነው። ብልህ ደግሞ ምንጊዜም ሱልጡን ነው። በቃ ስልጣኔ ማለት ይሄ ነው ለእሱ። ከተሜነትም አራድነትና ስልጣኔ በሌሉበት ሊገነባ የማይችል የሁለቱ አሻራ ነው ባይ ነው።
ከፒያሳ ወጥተን ወደ ካዛንቺስ በዘለቅንበት ወቅት ታክሲ ተራውና መናኸሪያው አካባቢ ሰብሰብ ያሉ ወጣቶችን አግኝተን ነበር። መናኽርያ ያገኘነውና ራሱን ቢል ብሎ ያስተዋወቀን ወጣት አራድነት በተለያየ ቋንቋ መናገርና መግባባት መቻል መሆኑነ ያምናል።
‹‹ቋንቋ ስል ደግሞ የሀገር ውስጥ ወይም ፈረንጅኛ እንዳይመስላችሁ›› ሲል ፈገግ አደረገን። እርስ በእርሱ የሚግባባበት ማለቱ እንደሆነም አስረድቶናል። እነሱ ‹ቺ› እየጨመሩ የሚግባቡበትና የወፍ ቋንቋ የሚሉት እንዳለ ለአብነት አንስቶልናል።
እዚሁ ካዛንቺስ ታክሲ ተራው ጋር ሰብሰብ ብለው ካገኘናቸው ወጣቶች በተራ አስከባሪነት እንደተሰማራ የነገረን ሳሚሼ ሰይፈ መናኽሪያ ላይ ያገኘናቸው ወጣቶች አራድነትን የገለፁበት ቋንቋን እሱም ይስማማበታል።
‹‹ዴች አስር ብር፣ አመድ መቶ ብር ሲሆን ዴንቲ 20 ብር ነው። ሦስት ዴች ሰላሳ ብር፣ ጫቢ ደግሞ ሃምሳ ብር ነው›› ብሎናል አራድነት በዚህ ውስጥ እንደሚገለፅ በማከል።
ደራሲ አሸናፊ መለሰ ከስነ-ጽሑፉ ዓለም ባሻገር በመምህርነትም ሙያ ረጅም ጊዜ ያገለገሉ ናቸው። ከተሜነትን ስልጣኔንና አራድነትን ከስነ ጽሑፉና ከሀገር በቀል ባህላዊ እሴቶች ጋር አስተሳስረው ገልፀውልናል።
እንደ ደራሲው ለእሳቸው የከተማ ስልጣኔ ማለት የአኗኗር ዘይቤን እያቀለሉ መሄድ ማለት ነው። ይሄ ማለት ትላንት በዶማ ይቆፍር የነበረ አርሶ አደር በሬ ጠምዶ ለማረስ የሚበቃበት ማለት ነው።
በሬ ይጠምድ የነበረው ደግሞ በመኪና መሄድ ወደ መቻል የሚደርስበት የሽግግር ስርዓት ይገለፃል። በዚህ መልኩ ድካምን እየቀነሱ ምቾትን እየጨመሩ መሄድ መቻል ነው። እንደ ደራሲው ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ሀገራችን ላይ በተለይም ወጣቶች ላይ እንደሚታየው ስልጣኔ ማለት ምዕራባዊያንን መምሰል ማለት ግን አይደለም። አሁን እኛ ሀገር ያለው ትልቁ ችግር መሰልጠን ማለት ምዕራባዊያኑን መስሎ መገኘት ተደርጎ መወሰድ እንደሆነም ያሰምሩበታል።
እንደሳቸው ይሄ ፍፁም የተሳሳተ አመለካከት ነው። ‹‹ዕውነተኛ ስልጣኔ ማለት ያለውን እያሻሻሉ መሄድ ነው›› ይላሉ። የሌለንን በጎ ነገሮች ከሌሎች ካላቸው ሰዎች እያመጡ ከራስ ባህል ጋር እያመቻቹ መሄድ መቻል ማለት ነው። ስልጣኔ የየዘመኑ አስተሳሰብ ልኬት ነውም ይላሉ።
ደራሲው ይሄን በምሳሌ አስደግፈው ሲያስረዱ በፍቅር እስከ መቃብር ውስጥ ሰብለ ወንጌል አለፈባት የተባለችው 15 ዓመት ሆኗት ነው። ይሄ በዚያ ዘመን የአስተሳሰብ ልክ ነበር። ዛሬ ላይ ሆኖ ሲታይ ግን ስህተት ሆኖ ይገኛል። ይሄን እያሻሻሉ መሄድ ማለት ከትላንትና የተሻለና የራስ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ ይዞ ለመዝለቅ ያለ ተነሳሽነት ማለት ነው።
‹‹ይሄኛውን አስተሳሰብ ይዘን ከሄድን ኢትዮጵያዊ ስልጣኔ መፍጠር እንችላለን›› ያሉን ደራሲው በሀገራችን ወርቅን ማቅለጥ፣ ድንጋይ ማለዘብ፣ ቆዳ መፋቅ የሚችል ሕዝብ መኖሩ ለዚሁ ግብዓት መዋል የሚችል መሆኑንም አጫውተውናል። ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ የሚሸምነውን ከጉድጓድ ውስጥ አውጥቶ ድካሙን የሚቀንስ አውቶማቲክ የሽመና ማሽን መግዛት ሰለጠን ለማለት የሚያስችል መሆኑንም ይናገራሉ። እንደ እሳቸው በአስተሳሰብም፣ በባህልም፣ በአመራር፣ በአኗኗር ዘይቤም ይሰለጠናል። ከተሜነትም ከዚህ ጋር አብሮ የሚኖር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ነው። ከተሜነት ‹‹ሰብሰብ ብሎ ለመኖር የሚደረግ ብስለት ነው›› ይላሉ።
አንድን መሰረተ ልማት በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር መቻል ነው ሲሉም ያክሉበታል። ሰዎች ችምችም ብለው በአንድ አካባቢ ሲገኙ የጋራ መንገድ፣ የጋራ ኤሌትሪክ አቅርቦት፣ የጋራ የቴሌኮም አገልግሎት ይኖራቸዋል። ሰዎች በዚህ መልኩ እያደጉ ሲሄዱ ከተሜነት እየበለፀገ ይመጣል።
‹‹አራድነት እንደኔ ሀሳብ የተሻለውን ይዞ መገኘት ማለት ነው›› ይላሉ። የተሻለውን ይዞ መገኘት ማለት ግን የማግኘት ሂደቱ ባህልን ያለቀቀ፣ ሥነ ምግባርን የተከተለና ነገን ያሰበ፣ ለትውልድም የሚተርፍ መሆን እንዳለበትም ይመክራሉ። በምሳሌ ሲያስረዱም አንድ ግለሰብ ያገኘውን ወንበር ተጠቅሞ ዘርፎ ሀብት ማካበቱ አራድነት እንዳልሆነ ይገልፃሉ።
ምክንያቱም የእሱ ልጆች ነገ ሰርተው ከማግኘት ይልቅ እሱ በሄደበት መንገድ ሄደው ሀብት ማፍራት ይመኛሉ። ይሄደግሞ በአጠቃላይ ማህበረሰቡን የሚያጠፋ ባህል ነው። በመሆኑም አራድነት ከስነ ምግባር፣ ከዕምነት፣ ከራስ ማንነትና ከዕውቀት ጋር አብሮ የሚያድግ እንደሆነ በመግለፅ ያካፈሉንን ያሳርጋሉ።
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 03 /2013