ዳግም ከበደ
እውቁ ፈላስፋ ፕሌቶ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ375 አካባቢ ‹‹The Republic›› በሚል ስያሜ በጻፈው መጽሐፍ ላይ ‹‹ሶክራተስ›› የተሰኘ ገፀ ባህሪ ከአቴናዊያን እና ከበርካታ የውጪ ዜጎች ጋር ስለ ፍትህ፣ ትክክለኛ መንግስትና ትክክል ስለሆኑና ስላልሆኑ ሰዎች ማንነት ሲወያይ ይነበባል።
ይህ ታላቅ ሰው የደረሰው መፅሀፍ እስካሁን ከተፃፉ የፍልስፍና እና የፖለቲካ መጽሐፍት ፅንሰ ሀሳቦች ወደር የማይገኝለት በሚል በከፍታ ማማ ላይ የተቀመጠ ነው። ብዙዎችን በእውቀት ማዕበል ያጥለቀለቀ፤ ያወያየ እንዲሁም ደስተኛ በመሆን ምንነት ላይ አበክሮ ትርጉም ለመፈለግ የማሰነ የህይወት መንገድን የሚያሳይ ነው።
የፕሌቶ ‹‹ዘሪፐብሊክ›› መጽሐፍ በጣም በርካታ ገፆች አሉት፤ሰፊ ውይይት ወይም በፈረንጅኛው አፍ ‹‹Socratic dialogue›› የቀረበበት ሲሆን፣ ለዛሬ በቀጣይ ለማወጋው ሀሳብ ጠቃሚ ነው ብዬ ያሰብኩትን አንድ ክፍል ወስጄ ሀሳቤን ለመሰንዘር እሞክራለሁ።
በዚህ እሰጣ እገባ በበዛበት የፍልስፍና እይታ ውስጥ ሀሳብ ሲብላላና በየፈርጁ ሲሰደር እውቀት የሁሉም ችግሮች ቁልፍ መሆኑን እንገነዘባለን። በቀጣዩ ክፍል ይህን የሚያስረዳልን የፕሌቶን ፅንሰ ሀሳብና አሁን ያለንበትን አገራዊ ውጥንቅጥ በጥቂቱ ተመልክቼ የግል አስተውሎት የታከለበት የመፍትሄ ሀሳብ ለመስጠት እሞክራለሁ።
በ‹‹ዘሪፐብሊክ›› ላይ ‹‹The Allegory of the Cave›› ወይም ‹‹plato cave›› በሚል ፅንሰ ሀሳብ ዙሪያ በገፀ ባህሪነት የተሰየሙት ሶክራቲስ እና የፕሌቶ ወንድም ግላውኮን በአንድ ጉዳይ ላይ መወያየት ይዘዋል። በዚህም ፈላስፋ ማለት ለዘመናት ከታሰረበት ዋሻ ውስጥ አምልጦ እንደወጣ እስረኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ይህ ፈላስፋ ቀሪው የሚያየው ሁሉ ከዚህ ቀደም በህሊናው ካስቀመጠው ፍፁም የተለየ እንደሆነ የተረዳ መሆኑን በሚያስቀምጥ ጉዳይ ላይ ይወያያሉ።
ፕሌቶ በ‹‹ዘሪፐብሊክ›› ውስጥ ሶስት ከልጅነታቸው ጀምሮ በጨለማ ዋሻ ውስጥ ፊታቸውን ወደ ግድግዳው አዙረው የታሰሩ ሰዎችን እንድናስብ ይነግረናል። ከጀርባቸው ሁልጊዜም የሚነድ እሳት ያለ ሲሆን፣ በእስረኞቹና በእሳቱ መሀል ደግሞ በዋሻው አካባቢ የሚኖሩ የመንደር ሰዎች ያልፋሉ።
በዚህ አጋጣሚ እሳቱ የሰዎቹን እና የሚተላለፈውን ማንኛውንም ነገር እስረኞቹ ማየት በሚችሉት ግድግዳ ላይ ጥላ በመፍጠር እንዲያዩት ያደርጋል። በዚህ የተነሳም ለዘመናት የሚሰሙት ድምፅና የሚያዩት እውነት ሁሉ ከጥላው የሚወጣ መሆኑን ብቻ ይገነዘባሉ። ሶስቱ የዋሻው እስረኞች ‹‹እውነት›› ማለት እነሱ ከሚያዩትና ከሚንቀሳቀሰው ጥላ ውጪ እንዳልሆነ አምነዋል።
ከዘመናት በኋላ አንዱ እስረኛ ከታሰረበት ያመልጣል። ከዋሻው ውስጥ መውጣትም ይችላል። በዚህ ጊዜ ከእሳቱ በላይ ሌላ ብርሀን የሚሰጥ የተፈጥሮ ብርሀን (ፀሀይ) መኖሩን ይገነዘባል። ከዋሻው ሲወጣ ከተፈጥሮ ብርሃን ጋር ለመላመድ እና በትክክል ለማየት ተቸግሮ ነበር። ቀስ በቀስም ጥላው ብርሃኑ የሚፈጥረው አርቴፊሻል እውነት እንጂ ትክክለኛው ምስል ወይም ቁስ አለመሆኑን ይረዳል። ይህንንም ለማመን ጊዜ ይወስድበታል።
በአጠቃላይ እድሜውን ሙሉ ሲያየው የነበረው እና እምነቱ ያደረገው የዋሻ ህይወት የተዛባ መሆኑን ይገነዘባል። አብሯቸው የታሰሩት ሁለት ሰዎች እርሱ የተረዳውን እውነት መመልከት እንዲችሉ በመጓጓትም ወደ ዋሻው ይመለሳል። የሆነውን ነገር ለሁለቱ የዋሻ እስረኞች ይነግራቸዋል። ያየውን እና የተመለከተውን ከዛም ሲያልፍ ትክክል የሆነውን ነገር ሊያስረዳቸው ይሞክራል።
ሆኖም ሁለቱ እስረኞች ጓደኛቸው አብዷል እስከ ማለት ይደርሳሉ፤የሚለው ሁሉ ትክክል እንዳልሆነ በመግለጽም ሊቀበሉት አልፈለጉም። እውነት እነሱ ከሚያዩት አርቴፊሻል ብርሃን እና ጥላ ውጪ ምንም አይነት ነገር እንደሌለም አስረግጠው ይነግሩታል። ሁኔታውን ሳይቀበሉት ቀርተውም ከአጠገባቸው ዞር እንዲል ጫና ይፈጥሩበታል።
የፕሌቶ ምናብ
የፕሌቶ የምናብ ዋሻ ‹‹allegory›› በርካታ ምሳሌዎችን ‹‹symbolism›› የያዘ ነው። ዋሻው በአርቴፊሻል እውነት ‹‹superficial physical reality›› ሲመስል ከዚህ ባለፈም በ‹‹መሀይምነት›› እና በ‹‹አለማወቅ›› ይወከላል። አለማወቅ ደግሞ በይበልጥ በጭለማው ይወከላል። ምክንያቱ ደግሞ እስረኞቹ ከሚያዩት ጥላ ውጪ እውነተኛ ቁስ ወይም ተንቀሳቃሽ ነገር እንደሌለ እንዲያምኑ በመሆናቸው ነው።
የታሰሩበት ሰንሰለት ደግሞ በአለማወቅ ወጥመድ መጠለፋቸውን እና ቀሪውን ዓለምና እውነት ማየት እንደተሳናቸው የሚያሳይ ነው። ከዋሻው ያመለጠው እስረኛ ደግሞ ከፍ ያለውን እና ትክክለኛውን ‹‹the higher truth of ideas›› እውነት እንዲወክል ሆኖ የተቀረፀ ሲሆን ፣ብርሃኑ ደግሞ ጥበብን ‹‹wisdom›› እንዲወክል ተደርጎ ተቀርጿል።
አርቴፊሻሉን ብርሃን የፈጠረው እሳት እና ከጀርባው እንዲመላለሱ የተደረጉት ሰዎች ደግሞ ስልጣን ላይ ያሉ ፖለቲከኞችን፣ ሚዲያውን እና የማህበረሰቡን አመለካከት በሚፈልጉት መንገድ ጠርዝ የሚያሲዙትን ግለሰቦችን እንዲወክሉ ተደርገው ተቀርፀዋል።
እኛስ?
አሁን ላይ ያጋጠመን እውነት ከላይ ያነሳነው የዋሻው ታሪክ ይመስላል። ሰዎች ትርክት በማዛባት ብዙኃኑን የህሊና እውር ለማድረግና ከራሱም ከወንድሙም ጋር ሲያላትሙት እንመለከታለን። የመገናኛ ብዙኃን ልክ እንደ አርቴፊሻሉ እሳት ለተከታዮቻቸው የሚሰብኩት ፕሮፓጋንዳ ‹‹superficial truth›› ከእውቀት እና ጥበብ ጋርዶታል። ጥላውን አይቶ ከግድግዳው ጋር ይጋጫል። ተፅእኖ የሚፈጥሩ እና የገንዘብ አቅም ያላቸው ግለሰቦች ማህበረሰቡን ወደ ለምለሙ ሜዳ ሳይሆን ጥልቅ ወደ ሆነው ገደል ይመሩታል።
በአውድማ ላይ ፍሬውን ከገለባው ለመለየት መንሽ እንደሚያስፈልገን ሁሉ እውነቱን ‹‹ከተዛባው እውነት›› ለመነጠል ጥበብ ‹‹wisdom›› ሊኖረን ይገባል። ሰንሰለቱ ጠፍሮ እንደያዛቸው የዋሻው እስረኞች ማህበረሰባችንን ጠፍሮ የያዘውን ‹‹አለማወቅ›› በጥሶ ለመውጣት የአንደኛውን እስረኛ ፈለግ መከተል ያስፈልጋል። እውቀትን መከተል እውነትን ማሳደድ ይኖርብናል። ነፃ የሚያወጣውን ጥበብ መሻት ነው።
በፕሮፖጋንዳ እና መርዝ በተለወሰ ቃላት እያረሰረሱን እነርሱ ወደሚፈልጉት አቅጣጫ የሚወስዱንን ጥቂት ሰዎች ሳይሆን ማመን የሚኖርብን መርምሮ የሚያውቀውን መዝኖ የሚረዳውን ህሊናችንን ነው። ለዚህ ደግሞ እውቀትን መከተል ይኖርብናል። ምክንያቱም እውቀት እንጂ ጥቂቶች ነፃ አያወጡንም!!
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 03 /2013