ማህሌት አብዱል
ተወልደው ያደጉት በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ፍኖተ ሰላም ከተማ ነው:: አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በዚያው ከተማ ውስጥ በሚገኘው ዳሞት በተባለ ትምህርት ቤት ውስጥ ሲሆን ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ገብተውም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማቲማቲክስ ትምህርት ማግኘት ችለዋል::
ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሳይኮሎጂ ትምህርት ከዛው ዩኒቨርሲቲ ተቀብለዋል:: ትምህርታቸውን እንደጨረሱ በአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ያገለገሉት እኚሁ ሰው የብአዴን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነውም ሰርተዋል::
በመቀጠልም የአማራ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ በመሆን ለክልላቸው ሁለንተናዊ ልማት የበኩላቸውን ሲወጡ ቆይተዋል:: ለጥቂት ዓመታት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ካገለገሉ በኋላም በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ::
በበሳል ንግግራቸው የሚታወቁት አቶ ብናልፍ አንዷለም የዛሬ የዘመን እንግዳችን ናቸው:: በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ ከእንግዳችን ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ቆይታ::
አዲስ ዘመን፡– ሰሞኑን የብልፅግና ፓርቲ ስብሰባ ማካሄዱ ይታወሳል፤ ፓርቲው በዚህ ስብሰባ የተወያየባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ምን ነበሩ? ምን ዓይነት ውሳኔዎች እንዳስተላለፈም ይጥቀሱልንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ ብናልፍ፡- የፓርቲያችን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰሞኑን መደበኛ ስብሰባውን ሲያካሂድ በዋናነት በሶስት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቷል:: አንደኛው ወቅታዊ የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ የሚመለከት ሲሆን በተለይም ደግሞ በቅርቡ የህወሓት የጥፋት ቡድን በአገሪቱ ሉዓላዊነት ላይ የሰነዘረውን ጥቃት በተመለከተ ሰፋ ያለ ምክክር ነው ያደረግነው::
በተጨማሪም ዝርዝር ግምገማም ተካሂዷል:: ከጥቃቱ በፊትም የነበረው ሴራ እንዲሁም ጥቃቱ ያስከተለው ጉዳት ዓላማው ምን እንደነበር አንስተናል:: ከዚያም በኋላ የተሰሩ ስራዎችንና የአገርን ሉዓላዊነትን የማስቀጠል ሕግ የማስከበር ዘመቻ ውስጥ የተገባበትን ሁኔታና የተገኙ ውጤቶችን በዝርዝር ለማየት ተችሏል:: ከዚህ በመነሳትም ወደፊት መሰራት ያለባቸው ስራዎችና አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል::
ሁለተኛው አጀንዳ የነበረው ደግሞ አለማቀፍና የፖለቲካ ኃይሎች አሰላለፍ ምን እንደሚመስል ያየንበት ነው:: ይሄ እንግዲህ በአገራችን ያለው አስቀድሜ ከገለፅኩት ሁኔታ ጋር የሚተሳሰር ነው:: በአገሪቱ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ አገረ መንግስትና ብሔረ መንግስት ግንባታን ስኬታማ ከማድረግ አኳያ ያሉ ምቹ የፖለቲካ ሁኔታዎችና ተግዳሮት የሆኑ ጉዳዮች ምን እንደሆኑ ዳሰናል::
በዋናነት ደግሞ ፅንፈኛ የሆኑ የፖለቲካ አመለካከቶች ዋልታ ረገጥ የሆኑ የፖለቲካ አመለካከቶች በአገር ግንባታ ላይ የሚያስከትሉትን ጉዳት፤ ይህንን ጉዳት ደግሞ ለመቀነስ ብሎም ለማስቆም ምን አይነት የፖለቲካ ስራዎች መስራት ይኖርብናል? የሚሉ ጉዳዮችን ዝርዝር ባለ ሁኔታ ለማየት ተሞክሯል::
ከዚህ ጋር ተያይዞ አሁናዊ አለምአቀፍ ሁኔታዎች በአገራችን ላይ በአሉታም ሆነ በአዎንታ የሚኖራቸው ተፅእኖዎችን የዳሰስንበት የውይይት መድረክ ነበር ማለት ይቻላል:: ከዚህ አንፃርም መልካም ዕድሎችን እንዴት አድርገን ልንጠቀምባቸው ይገባል? ፈተናዎችን ደግሞ እንዴት ተቋቁመናቸው ማለፍ ይኖርብናል? የሚል ዝርዝር ጉዳዮችን አይተናል::
ሶስተኛውና የመጨረሻው አጀንዳ የነበረው ቀጣዩ አገር አቀፍና የአካባቢ ምርጫ በሚመለከት ነው:: በዚህ ዓመት የሚደረገው የ2013 ዓ.ም አገራዊና ክልላዊ ምርጫ አጠቃላይ አገራዊ ሁኔታ ምን ሊሆን ይችላል? በሚል መነሻ እኛም እንደተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲ ወደ ምርጫ ቅስቀሳ በምንገባበት ጊዜ የምረጡኝ ቅስቀሳው እንዴት መመራት እንዳለበት የሚያብራራ ማኒፌስቶ አዘጋጅተናል::
በዚህ ማኒፌስቶ ላይ ውይይት ማድረግና ማኒፌስቶውን በሥራ አስፈፃሚ ደረጃ ፀድቆ ወደሚቀጥለው ማዕከላዊ ኮሚቴ መድረክ እንዲሄድ፤ ብሎም ታይቶ እንዲፀድቅ የማድረግ ስራ ነው የተሰራው:: በአጠቃላይ በእነዚህ ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የተካሄደ ስብሰባ ነበር ማለት ይቻላል::
አዲስ ዘመን፡– በመድረኩ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ከገመገማቸው ጉዳዮች አንዱ ጁንታው የህወሓት ቡድን ያደርጋቸው የነበሩ ሴራዎች በሚመለከት እንደነበር ጠቅሰውልኛል፤ ለመሆኑ ሴራዎች ምን ምን ነበሩ? በምንስ መልኩ ነበር ይገለፁ የነበሩት?
አቶ ብናልፍ፡- እንግዲህ የህወሓት ፅንፈኛ ቡድን ወደ ለውጥ እንቅስቃሴ ከገባንበት ከ2010 ጀምሮ የተለያዩ ሴራዎችን ሲያደርግ ነበር የቆየው::
በእርግጥ የለውጥ እንቅስቃሴው እንደሚታወቀው ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ነው በጣም ተጋግሎ የቀጠለው:: እናም እስከ 2010 ዓ.ም መጋቢት ወር ድረስ በርካታ መድረኮች ነበሩ፤ ብዙ ግምገማዎች ተካሂደዋል:: አገሪቱ ላይ በጣም አደገኛ የሆነ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር:: በሥርዓቱ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ቅሬታ ሕዝቡ ያቀርብ ስለነበር ከዚህ ተነስተን ለውጥ ካላመጣን በስተቀር አገር የማፍረስ አደጋ ሊያጋጥም ይችላል የሚል በጣም ጠንካራ የሚባሉ ግምገማዎች ተካሂደዋል:: በእነዚህ ግምገማዎች መጠነኛ የሚባሉ መሻሻሎች የመጡ ቢሆንም ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚፈልገው ደረጃ ለውጥ ማምጣት አልተቻለም::
ከዚያ በኋላም የለውጥ እንቅስቃሴው በጣም እየተጋጋለ ሲሄድ በፍጹም በዚህ አይነት ሁኔታ መቀጠል እንደማይቻል አብዛኛው አመራር ተገንዝቦት ነበር:: የሕዝቡ የለውጥ ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ያደገበት፤ ሁለተኛ በራሱ በኢህአዴግ ውስጥም የለውጥ ኃይል በስፋት መንቀሳቀስ የጀመረበት ጊዜ ነበር:: ሕዝቡ ውስጥ እየተቀጣጠለ ያለው ፍላጎት አንድ ምላሽ ካላገኘና ያንን የሚመጥን ለውጥ ካላደረግን አገር እንዳልኩት አደጋ ላይ ይወድቃል፤ በዜጎች ላይ የሚደርስ ጉዳት ይኖራል እምነት በአብዛኛው አመራር ተይዞ ነበር::
በመሆኑም የግድ ስርነቀል የሚባል ለውጥ ያስፈልጋል የሚል ግምገማና ክርክር ሲደረግ ቆየ:: ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ህወሓት ከፍተኛ ተፅእኖ ለመፍጠር ጥረት ያደርግ ነበር:: በተለያዩ መንገዶች ለውጡ በሚፈለገው አቅጣጫ እንዳይሄድ እንቅፋት እየሆነ ያስቸግር ጀመረ::
በዚህም አልተወሰነም፤ የተለያዩ የማደናቀፊያ ጥረቶችን ሲያደርግ ቢቆይም በ2010 ዓ.ም ላይ የአመራር ለውጥ ከተደረገ በኋላ ለውጡ ወደሚፈለገው አቅጣጫ ለመምጣት ቻለ:: የሕዝቡን ጥያቄዎች የሚመልሱ ትልልቅ ውሳኔዎች ተወስነው ለኢትዮጵያ ሕዝብም እፎይታ ማምጣት እንዲሁም ለዓለም ማህበረሰብም አድናቆትን የተቸሩ ለውጦች ተካሄዱ::
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ህወሓት ከፍተኛ የሆነ የለውጥ ማደናቀፍ እንቅስቃሴ ውስጥ ገባ:: በነገራችን ላይ የአመራር ለውጥ ባደረግን ጊዜ ህወሓት አሁንም እሱ የሚፈልጋቸውንና ተላላኪ የሆኑትን ሰዎች ለማስመረጥ ከፍተኛ ግብግብ አድርጓል:: ያም ሆኖ ኢህአዴግ ውስጥ የነበረው የለውጥ ኃይል ደግሞ ከፍተኛ ኃይል በማሰባሰቡና አሸናፊ ሆኖ ሊወጣ የሚያስችልበት ሁኔታ ስለነበር በህወሓት ፍላጎት አልሄደም:: ይልቁኑ ለውጡን በሚፈልጉ ኃይሎች ፍላጎት ነው እየሄደ የቀጠለው::
የለውጥ ኃይሉን ወደፊት ከማምጣቱ ጎን ለጎን በጣም ትልልቅ የሚባሉ አገራዊ ለውጦች ተካሂደዋል:: ከዚያ ጊዜም በኋላ ቢሆን ህወሓት ለውጡን የማደናቀፍ እንቅስቃሴው ቀጠለበት:: ለምሳሌ እንኳ ብጠቅስልሽ ኢህአዴግ አንድ አጀንዳ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ በሚያሳልፍበት ጊዜ የውሳኔዎቹን ሃሳብ በመግለጫ ከወጡ በኋላ ህወሓት ለብቻው ወጥቶ እንደገና ሌላ መግለጫ ያወጣል:: የሚያወጣው መግለጫ ደግሞ ፈጽሞ የኢህአዴግ ውሳኔ የተቃረነ ነበር:: በጋራ መድረክ ተስማምተን ስናበቃ ለብቻው መግለጫ ካወጣባቸው ጉዳዮች መካከል የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ውዝግብ ወደ እልባት እናምጣው የሚለው አጀንዳ ይጠቀሳል::
በነገራችን ላይ ይህ ውሳኔ የተወሰነው ኢህአዴግ ከመፍረሱ በፊት ሲሆን በጋራ ራሳቸው የህወሓት አመራሮች በተገኙበት የተወሰነ ነው:: እንዳውም አብዛኛውን ጊዜ ራሳቸው ነበሩ የጉዳዩ አስረጅ ሆነው ይቀርቡ የነበሩት:: ይሁንና እንደምታስታውሺው ልክ ውሳኔው ተወስኖ ለሕዝቡ ይፋ ከተደረገ በኋላ በሁለተኛው ቀን ወይም በማግስቱ ህወሓት ያንን ውሳኔ የሚቃረን መግለጫ አወጣ::
በተመሳሳይም የፕራይቬታይዜሽን ጉዳይም ሌላው አወዛጋቢ ጉዳይ ነበር:: የልማት ድርጅቶችን ደረጃ በደረጃ አንዳንድ ተቋማት አዋጭነታቸው እየታየ ወደ ግል ሴክተር እንዲዛወሩ የተወሰኑ ውሳኔዎችንም አብሮ ነበር የወሰነው:: ይህንንም በጋራ ከወሰነ በኋላ በሚቀጥለው ቀን በመቃወም እንደገና መግለጫ አውጥቷል:: በነገራችን ላይ አሁን የምነግርሽ ነገሮች በሙሉ ሪከርድ የተደረጉ ናቸው::
በፓርቲው ጽሕፈት ቤት ውስጥ በሰነድ ደረጃ የተቀመጡ ናቸው:: ስለዚህ እንደዚህ አይነት ጫወታ የሚያዋጣ አልነበረም:: እንዲህ አይነቱ የህወሓት ድርጊት ከጅምሩ ለውጡን ለማደናቀፍና የሚታሰቡትን ነገሮች እንዳይቀጥሉ የማድረግ እንቅስቃሴ ነበር ሲያደርጉ የነበሩት::
በዚህ ሁኔታ ከቀጠሉ በኋላ አንዱ የለውጡ አካል አድርገን የወሰድነው የፖለቲካ ሪፎርም ማድረግ አለብን ብለን መስራታችንን ቀጠልን:: ለምሳሌ የኢኮኖሚ፤ የፖለቲካ ሪፎርም ማካሄድ እንዲሁም የፍትህ ስርዓቱን የማሻሻል ስራ ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው::
ሌሎቹን ለጊዜው ልተዋቸውና አንዱና ትልቁ የነበረው የፖለቲካ ሪፎርም ነበር:: ይህንን ሪፎርም በከፍተኛ ደረጃ ለማደናቀፍ ህወሓት ሲሰራ ነበር:: ይህም ኢህአዴግ በተለያዩ ምክንያቶች አሁን ባለው ቁመናውና አሁን ባለው አደረጃጀት አገሪቱን በፍፁም ወደፊት ሊያራምድ በሚችልበት ደረጃ ደርሷል የሚል አቋም አልነበረብንም:: ለምሳሌ ኢህአዴግ የሚመራበት አብዮታዊ ዲሞክራሲ በሚል ፍልስፍና ጠላትና ወዳጅ ብሎ የሚለይ ነው:: ሰዎችን በአመለካከታቸው ብቻ ይሄኛው ጠላቴ ነው፤ ሌላኛው ደግሞ ወዳጄ ብሎ የሚያስቀምጥ መሆኑ በሕዝቦች መካከል የጥላቻ ግድግዳ ፈጥሮ ኖሯል::
የሚገርመው ጠላት ወይም ወዳጅ ከሚለው ውጭ ሌላ ሶስተኛ መንገድ አለ ብሎ አያምንም:: በዚህ ርዕዮተ አለም አንድ ዜጋ ምንም አይነት አስተሳሰብ ይኑረው ገለልተኛ ሆኖ መኖር አይፈቀድለትም:: ይህም አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሕዝብ የፖለቲካ ንቃት፤ የአገሪቱ የአለምአቀፍ ሁኔታ በፍፁም አያስኬድም የሚል አቋም በአብዛኞቹ የለውጡ ኃይሎች ዘንድ ተይዞ ነበር:: ሰዎች የሃሳብ ልዩነት ሊኖራቸው ይችላል፤ በሃሳብ ስለተለያዩ ብቻ «ጠላት» ተብለው መፈረጅ የለባቸውም::
ሁሉም የየራሳቸውን ሃሳብ ሊያራምዱ ይችላሉ፤ ክርክሮች ሊካሄዱ ይችላሉ:: ሕዝቡ የመረጠው ደግሞ በምርጫ ተፈፃሚ እየሆነ ይሄዳል እንጂ ከእኔ የተለየ አስተሳሰብ ይዘሃልና ጠላት ተብሎ የሚፈረጅበት መንገድ በጣም ትክክል አልነበረም:: ስለዚህ አብዮታዊ ዲሞክራሲ በዚህ ምክንያት አያስኬድም የሚል ሃሳብ መንሸራሸር ጀመረ:: በምትኩም ሁሉንም ሃሳቦች በሚዛኑ የሚቀበልና የሚያጣጥም፤ እንዲሁም ልዩነቶች ቢኖሩም እንኳን እየተወያዩ ሰላማዊና የሰለጠነ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ እንዲራመድ ነው በአገሪቱ ማካሄድ የሚያስፈልገው የሚለው ሃሳብ እየበረታ መጣ::
ማንም ምንም ሃሳብ ይኑረው ወደ ጠረጴዛው ይዞ ይምጣ፤ ውይይት ይደረግና በዚያ ላይ ተመስርተን እስከምንግባበት በጋራ እየሰራን በምንለያይባቸው ሁኔታዎች ላይ ወደፊት ሕዝቡ ብይን ይስጥ የሚል አቋምም ተያዘ:: ነገር ግን ህወሓት እንደተለመደው ይህንንም ሃሳብ አልተቀበለውም ነበር:: በመቃብሬ ላይ ካልሆነ በስተቀር የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር በፍፀሙ መነቀል የለበትም ብሎ ይሟገት ገባ:: እንዳውም አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ፈረሰ ማለት የአገሪቱ ህልውና አከተመ እስከማለት ደረሰ::
ሁለተኛው የኢህአዴግ መሰረታዊው ችግር ደግሞ አቃፊ ያለመሆኑ ነበር:: እንደሚታወቀው ኢህአዴግን የመሰረቱት አራት መሰረታዊ ድርጅቶች ናቸው:: የአራት ክልል ብሔራዊ ፓርቲዎች ቢመሰርቱትም ግን ከእሱ ውጭ አምስት የሚሆኑ ሌሎች ክልል የሚመሩ ፓርቲዎች አጋር ተብለው ይጠሩ ነበር::
ይህም ማለት የኢህአዴግ አባል መሆን አይችሉም ተብሎ አስቀድሞም ተወስኖባቸው ነበር ማለት ነው:: አባል መሆን ካልቻሉ ደግሞ መወሰን አይችሉም:: ይህ ፍትሃዊ ባለመሆኑ ለዚህች አገር የሚያስፈልጋት አቃፊ የሆነና ሁሉንም እኩል የሚሳተፍበት እንዲሁም የሚደመጥበትን፤ የሚወስንበትና የሚተገብርበት ስርዓት ነው::ይህ ካልሆነ በስተቀር አሁን ባለው እሳቤ የምንቀጥል ከሆነ ትክክል አይደለም የሚል አቋም ነበረው የለውጥ ኃይሉ:: የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን አግልሎ እነሱን የዳር ተመልካች አድርጎ እኛ የምንላችሁን ብቻ ትፈፅማላችሁ እያሉ መሄድ አይቻልም::
በነገራችን ላይ ይህ ስር የሰደደ አግላይ አስተሳሰብ ሌላም ችግር አለው::እነዚህ ክልሎች የሞግዚት አስተዳደር እየተቀመጠላቸው እንዲመሩ ነበር ይደረግ የነበረው:: ስለዚህ በሪፎርሙ ይህ አስተሳሰብ ከመሰረቱ መቀየር አለበት የሚል አቋም ነበረ::
ህወሓት ይህንንም ሃሳብ አጥብቆ ነው የተቃወመው:: ህወሓቶች እነዚህ ክልሎች ማህበራዊ መሰረታቸው አርብቶአደር በመሆናቸው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መሰረት መሆን አይችሉም የሚል ዋልታ ረገጥ አቋም ነበራቸው:: የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ማህበራዊ መሰረቱ አርሶአደሩ፤ የከተማው ነዋሪና ዝቅተኛው ምሁር ብሎ የሚገልፀው:: ከዚህ ውጭ ያለውን ማህበራዊ መሰረቴ ነው ብሎ አይቀበልም:: ስለዚህ እነዚህ ክልሎች በአብዛኛው የአርብቶአደር ክልሎች ስለሆኑና አርብቶአደር ለአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስፈርት ስለማይሆን እነሱን በኢህአዴግ ውስጥ ማካሄድ አይችልም በሚል ለ28 ዓመታት አግልሏቸው የቆየው::
በነገራችን ላይ በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ራሱ እርስበርሱ የሚጣረስ ነገር አለ:: ለምሳሌ ከተማን ያየን ከሆነ አርብቶአደርም አይደለም አርሶአደርም አይደለም ግን ደግሞ ማህበራዊ መሰረቴ አይደለም የሚባልበት ምክንያት ምንም የለውም::
በሌላ በኩልም ቤኒሻንጉል አርሶአደር ክልል ነው:: በሚሉት እንኳ ፍልስፍና አርሶአደሩ ነው ማህበራዊ መሰረት ነው ካልን ቤኒሻንጉል በምን ምክንያት ኢህአዴግ ውስጥ እንዳይካተት ሊደረግ ይችላል ተብሎ ሲጠየቅ መልስ አልነበራቸውም:: ስለዚህ በምን ምክንያት እነዚህ ክልሎች እንዲገለሉ እንደተደረገ ግልፅ አይደለም::
ይህ አይነቱ አሰራር መቀየር አለበት የሚል የፖለቲካ ሪፎርሙ ላይ ስለነበር ይህንን ፈፅመው ሊቀበሉት አልቻሉም:: በመሆኑም ህወሓቶች በዚህ ምክንያት ማፈንገጥ መጀመሩ:: ለውጥ አይቀሬ መሆኑን ሲረዱም ለውጡን በይፋ መፃረር ቀጠሉ:: እነሱ ቢፃረሩትም ግን ተግባራዊ ተደረገ::
ኢህአዴግን አፍርሰን ህብረብሔራዊ የሆነ፤ ሁሉንም ያቀፈ፤ ሁሉንም የአገሪቱ ሕዝቦች በእኩል የሚያሳትፍ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወደ ውሳኔ የሚያመጣና እኩል የሚሳተፉበትን እድል የሚፈጥር ፓርቲ መመስረት አለብን ብለን ተንቀሳቀስን:: ይህ የብልፅግና ጎዳና እውን እንዳይሆን በጣም ከፍተኛ የሆነ የስም ማጥፋት ዘመቻ ማካሄድ ጀመሩ::
ለአብነት ያህልም ብጠቅስልሽ «የለውጥ ኃይሉ ስልጣኑን ለማራዘም ሲል ነው ብልፅግናን የሚያቋቁመው፤ አሀዳዊ መንግስት ነው፤ የድሮውን ስርዓት ለመመለስ ነው፤ የፌደራል ስርዓቱን ለማፍረስ ነው» የሚሉ የማያቋርጥ ዘመቻ ሲያካሂድ ነው:: ግን አልቻለም:: መጨረሻ ላይ አስቀድሜ እንዳልኩት የፓርቲው ምስረታ እውን ሆነ::
ይሄ ብቻ ግን አይደለም፤ በጣም በሚገርም ሁኔታ ብልፅግና የፌደራል ስርዓቱን የሚያፈርስ ነው በሚል ሰበብ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በገንዘብ በመግዛት ሌሎቹን ደግሞ በተለያየ ማደነጋገሪያ የፌዴራሊስት ኃይሎች የሚል ስብስብ ፈጥሮ በከፍተኛ ደረጃ መቀሌ ላይ ገንዘብ እየከፈለ፤ ፓርቲዎችን እየደለለ መቀሌ እየወሰደ ብልፅግናን ለመቃወም ከፍተኛ ጥረት ያደርግ ነበር:: ይህ ፅንፈኛ ቡድን እንዲህ እያለ ለውጡን እየተቃወመ ቢቀጥልም አልተሳካለትም::
ፓርቲውም እውን ሆነ እንዳውም በሚፈለገው ደረጃ የቀጠለ ሲሄድ አሁንም ሌላ አጀንዳ ይዘው መቅረብ ጀመሩ:: በመካከል ላይ ኮረና ቫይረስ ሲመጣ በ2012ዓ.ም ሊካሄድ የነበረው ምርጫ እንዲራዘም ተደረገ:: በወቅቱ ደግሞ ከፍተኛ ድንጋጤ በዓለም ላይ ተፈጥሮ ነበር፤ ብዙ አገሮችም ምርጫዎችን እያራዘሙ እንደነበር የሚታወስ ነው::
በዚህ ምክንያት ውይይት ተደርጎ በመጨረሻ በወረርሽኙ ምክንያት ምርጫውን ማካሄድ እንደማይቻል አቋም ተወሰደ:: ከዚያ በኋላ የፌደሬሽን ምክር ቤትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት አማራጮችን አጥንተው ለተወሰነ ጊዜ ምርጫው እንዲራዘም ተወሰነ:: ይህንን ውሳኔ ተቃውመው ወዲያውኑ መግለጫ አወጡ:: በየቀኑም በዚሁ መንገድ ለውጡን እየተቃወሙ መግለጫ ማውጣታቸውን ቀጠሉ::
በነገራችን ላይ ምርጫው ሲራዘም ሙሉ ዝግጅት አድርገን ወደማጠናቀቅ ደረጃ የደረስንበት ነበር:: እንደሚታወሰው ኮቪድ እኛ አገር ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተው እኛ ከሞላ ጎደል ዝግጅት ጨርሰን ወደ ምርጫ ቅስቀሳ የምንገባበት ጊዜ ነበር:: ግን እንደማይቻል ሲታወቅ ምርጫው ተራዘመ::
ይህንን የምርጫ መራዘም ምክንያት አድርገውም ሌላ የመቀስቀሻ አጀንዳ አገኙ:: «ስልጣን ለማራዘም ነው» የሚሉ በርካታ የስም ማጥፋት ዘመቻቸውን ማድረጋቸውን ቀጠሉ:: ግን እነሱ ስለተቃወሙት ተግባራዊ ከመሆን አልቀረም:: እናም ይሄን ተከትሎም ይህ ኃይል «በራሴ ክልል ምርጫ አደርጋለሁ» ብሎ ፍፁም ኢ-ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ተነሳ::
በኢትዮጵያ ሕገመንግስት ምርጫ ማካሄድ የሚችለው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው:: ይህንን የምርጫ ቦርድ ሕግ ጥሶ ለማካሄድ ወሰነ:: ሲፈልገው ደግሞ ሕገመንግስት ተጣሰ ብሎ ይከሳል፤ አንዳንዴ ደግሞ ሕገመንግስቱን ራሱ እየጣሰ ይሄዳል:: ለዚህ ደግሞ ማሳያ የሚሆነው ሕገ መንግስቱን በሚጣረስ መንገድ ያካሄደው ምርጫ ሲሆን ይሁንና በፌደሬሽን ምክር ቤት ምርጫቸው ውድቅ ተደረገ::
ይህንኑ ሁሉ ሲያደርጉ ግን መንግስት እነዚህ ሰዎች ምንአልባት ከነገ ዛሬ ከስህተታቸው ይማሩ ይሆናል፤ ወደቀልባቸው ሊመለሱ ይችላል የሚል ተስፋ ነበረው:: ነገር ግን በመጨረሻ ተስፋ ያስቆረጠውና ቀይ መስመሩን ወደ ማለፍ ነው የመጣው::
እነሱ የሚሉት እንደማይሆን ሲረዳ አቋሙን የትግራይ ሪፐብሊክ መመስረት አለበት ወደሚል ወይም ደግሞ “ዲፋክቶ ስቴት” ለመመስረት ዝግጅታቸውን ጀመሩ:: በነገራችን ላይ ምርጫ ያደረጉበት ዋነኛ ምክንያት አንዱ የፌደራሉ መንግስት ያልተመረጠ መንግስት ነው ብለው ለመቀስቀስ ነው::
ያንን ተከትሎ ደግሞ በትግራይ ክልል እኛ የምንፈልገውን እንወስናለን በሚል ሃሳብ በመጠንሰስ ነበር ምርጫውም ያካሄዱት እንጂ ሕገወጥነቱ ለእነሱም ጠፍቷቸው አይደለም:: ከዚያ በኋላ ይህ ሴራቸው በግልጽ እየታወቀ መጣ:: አገር የማፍረስ ሴራ መሆኑ ግልፅ እየሆነ ሲመጣ የወሰዱት አማራጭ በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት የመሰንዘርና እሱን የማፈራረስ ዘመቻ ነው የጀመሩት:: ከዚያ ቀድሞ በጣም ብዙ ዝግጅት ያደርጉ ነበር::
በጣም በርካታ ሚሊሻና ልዩ ኃይል ያሰለጥናሉ፤ በክልል ደረጃ ሊያዙ የማይገባቸው ከባድ መሳሪያዎችን ያስታጥቃሉ፤ የወታደር ትርኢት ያሳያሉ:: በአጠቃላይ ቀን ተቀን የጦርነት ጉሰማ ነበር ሲያሰሙ የነበሩት::
እነዚህ ፅንፈኛ ኃይሎች ሁሌም ትንኮሳ ሲያደርጉ ቢቆዩም የፌደራል መንግስት በትዕግስት ዝም ብሎ ነበር ሲመለከታቸው የቆየው:: እነሱ የሚፈልጉት ግን ትንኮሳውን በመመስረት መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ነው:: እሱንም ደግሞ እንደማይደረግ ሲገባቸው በመጨረሻም ቀዩን መስመር አልፈው መከላከያ ላይ ጥቃት ሰነዘሩ::
ያው ሰሜን እዝ ላይ እጅግ ዘግናኝ የሆነ በኢትዮጵያ ታሪክ ብቻ ሳይሆን በዓለም ታይቶ የማይታወቅ አሳዛኝ ተግባር ፈፀሙ:: በተለይ ደግሞ የትግራይን ሕዝብ ለመጠበቅ ከ20 ዓመታት በላይ ጉድጓድ ውስጥ የኖረ፤ በክፉም ሆነ በደጉ ከትግራይ ህዝብ ጎን ቆሞ የኖረውን ወታደር ከጀርባው መውጋታቸውና ጥቃት መፈፀማቸው የመላውን የአገሪቱን ልብ ሰበረ:: በጣም የታወቁ ጄኔራሎችንና የጦር መኮንኖችን ረሽነዋል፤ አፍነው ወስደዋል፤ በርካታ ጉዳት አድርሰዋል:: ሰሜን እዝ ይዞት የነበረውን በአገሪቱ ከፍተኛ የሚባለው መሳሪያ ለመዝረፍና ለመውሰድም አልመው ሰርተዋል::
በተመሳሳይ አማራ ክልል በተለይ ቀራቀር በሚባል የጠገዴ ዋና ከተማ ላይ ጥቃት ሰንዝረው ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል:: እቅዳቸው የነበረው ጥቃት ሰንዝረው ወደ ወልዲያ መምጣት፤ ከዚያ በኋላም ከተሳካላቸው አራት ኪሎ ገብተው መንግስትን መገልበጥ ነበር::
ይህም ካልተሳካ ደግሞ የትግራይ ሪፐብሊክን መመስረት ነበር:: የሴራቸው ዋና ዓላማ ኢትዮጵያን የማፈራረስና ድሮ የነበረውን የዝርፊያ ፍላጎታቸውን ማስቀጠል ነው:: አገሪቱ ከተበተነች ብቻ እንደሆነ ያውቃሉ ዓላማቸውን ሊያሳኩ የሚችሉት:: ጠንካራ መንግሥት ካለ ግን ዓላማቸው ሊሳካ እንደማይችል ያውቃሉ:: በተቻለ መጠን የተዳከመ ወይም የተበተነ መንግስት እንዲኖር ማድረግና አገሪቱን ወደ እርስበርስ ጦርነት እንድትገባ ማድረግ ነበር መሻታቸው:: ያንን ለማሳካት ነበር ይህንን ጥቃት የፈፀሙት::
ግን ባሰቡት ልክ አልሆነም:: አንደኛ የትግራይም ሕዝብ እነሱ እንደሚያስቡት አይነት ቅዠት የለውም:: እነሱ ለስልጣናቸው ሲሉ ነው ያንን ሁሉ ነገር የሚያደርጉት እንጂ የትግራይ ሕዝብ ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ የተለየ ፍላጎት የለውም:: እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገሪቱ መሰረት የሆነ ሕዝብ ነው:: በተለይም በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ከሌላው ጋር ተመሳሳይ አቋም ነው ያለው:: ስለዚህ ይህ እንደማይሳካ ሲያውቁ አገርና መንግሥትን አፍርሰው የራሳቸውን ዓላማ ለማስፈፀም ነው ወደዚህ አይነት ሕገወጥ ተግባር የገቡት::
አዲስ ዘመን፥– በክልል አመራርነት በቆዩባቸው ዓመታት ቡድኑ በክልሉ ሕዝብ ላይ ሲያሳድር የነበረው ፖለቲካዊ ተፅእኖ ይጥቀሱልን?
አቶ ብናልፍ፡- በአማራም ሆነ በሌሎች ክልሎች ሕዝቦች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና እየፈጠረ፤ ዘረፋ እየፈፀመ የቆየ ቡድን ነው፤ ይሄ ይታወቃል:: ለምሳሌ በቤኒሻንጉል፤ በጋምቤላ፣ በኦሮሚያ፣ በሱማሌ እና በአፋር ያሉ የእርሻ መሬቶችን ሲበዘብዝ ቆይቷል:: በተለያየ መንገድ የእሱ ተላላኪ የሆኑ ሰዎችን በኢንቨስትመንት ስም እያስገባ ከፍተኛ ዘረፋ እያደረገ ቆይቷል:: ይህንን በሚያደርግበት ጊዜ ደግሞ ዜጎችን በጅምላ እየገደለ ነበር ሲፈፅም የነበረው::
ለምሳሌ ሱማሌ ክልል ላይ በርካታ ሰዎችን በአንድ ጊዜ ረሽኖ በአንድ ጉድጓድ እንዲቀበሩ በማድረግ ትልቅ ግፍ ፈጽሟል:: ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በአማራ ክልልና ሕዝብ ላይ እየፈፀመ የቆየው ግፍና በደል ደግሞ ከአስተሳሰቡ ነው የሚጀምረው:: እሳቤው ራሱ ድርጅቱ ትግል እጀምራለሁ ብሎ ሲመሰረት ጀምሮ የሃሳቡ ጥንስስ የጨቋኝና የተጨቋኝ ትርክት ይዞ ነው የተነሳው:: ህወሓት በኢትዮጵያ ውስጥ ጨቋኝና ተጨቋኝ ብሔር አለ በሚል የያዘው ዋልታረገጥ አቋም ሲያራምድ ነው የቆየው::
በዚህ አቋሙ መሰረት ደግሞ ጨቋኝ ብሎ የሚነሳው የአማራ ሕዝብን ሲሆን፤ በትግራይና በሌሎች ሕዝቦች ላይ ጭቆና አድርሷል ብሎ የተሳሰተ ትርክት እንዲስፋፋ አድርጓል:: አማራን እንደጨቋኝ አድርጎ የተነሳ ፓርቲ ስለሆነ በአማራ ላይ ደግሞ የተለየ የሚባል የጠላትነት መንፈስ ይዞ የተነሳ ድርጅት ነው::
ስለዚህ ከዚያ በኋላ በቆየባቸው ዓመታት በሙሉ ይህንን ፅንፍ የረገጠ የጥላቻ አስተሳሰብ እየተገበረ ነው የቀጠለው:: በሕዝቦች መካከል የጠላትነት መንፈስ እንዲያዳብር በጣም ከፍተኛ ስራ ሰርቷል:: ይህንን ያደርግ የነበረበት አንደኛው ምክንያት በስልጣን ላይ ረጅም ጊዜ መቆየት የሚቻለው ሕዝቦችን ከፋፍሎ ሲገዛ እንደሆነ በማሰብ ነው:: የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች በመከፋፈል በጠላትነት እንዲተያይ በማድረግ በጋራ የመሰረቱትን የአንድነት እሴታቸውን እያፈረሰ በልዩነቶቻቸው ላይ እያነጣጠረ በቀየሰው ዘዴ ከፍተኛ የሚባል ጉዳት ማድረስ ችሏል::
የልዩነቶቻቸውአንኳር ጉዳይ አድርጎ የቀጠለው አማራ የሚባል ጨቋኝ ብሔር አለ የሚል ትርክት ላይ ተመስርቶ ነው::
ከዚህ ተነስቶ ወደ ተግባር አፈፃፀሙ ደግሞ ሲመጣ በአማራ ክልል የሚኖሩ፤ እንዲሁም በሌላ ክልል የሚኖሩ አማሮች የተለያየ ታርጋ እየለጠፈ ነበር ጭቆና ሲያደርስባቸው የነበረው::
በተለይ ደግሞ ስርዓቱን ይቃወማሉ ብሎ የሚያስባቸውን ሰዎች «ትምክህተኛ፤ ነፍጠኛ» የሚል ታርጋ ይለጥፋባቸው ነበር:: የኦሮሞ ወጣቶችንም «ጠባብ» እያለ የተለያየ ስያሜ እየሰጠና እያሸማቀቀ ሲሄድ ነው የቆየው:: ይህንን የሚቃወሙ ሰዎችንም በሽብር ተሳትፈዋል ብሎ በእስር ቤት ያጉራቸዋል፤ ይገርፋቸዋል፤ አካላቸውን ያጎላል፤ ያኮላሻል፣ ይገድላል፤ አገር ጥለው እንዲሰደዱ ያደርጋል::
በተለይም በአማራ ህዝብ ላይ እንዲህ አይነት በደል ሲፈፅም ነው የኖረው:: እናም በአማራ ክልል ሕዝብ ላይ ግፍ በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም:: በኋላም ለለውጡ መነሻ ምክንያት የሆነው ይሄ በሕዝቦች ላይ ይፈፅም የነበረው ግፍ ነው:: እናም እኔ የአማራ ክልል አመራር ሆኜ በቆየሁበት ጊዜ በየጊዜው በየግምገማው በተለይ በጋራ በምንገናኝበት በኢህአዴግ መድረክ በጣም ብዙ ስንታገል ነው የኖርነው::
በዚያ ጊዜ ግፍ የሚፈፀምባቸው ዜጎች በተለያየ መድረክ እየወጡ ብሶታቸውን ይናገሩ ነበር:: ለዚህ ግፍ ማስፈፀሚያ ትልቅ መሳሪያ የሆናቸው ደግሞ የደህንነት መዋቅሩ ነው:: የደህንነት መዋቅሩ ጽንፈኛው ቡድን ባስቀመጣቸው ሰዎች የሚመራ ስለነበር ሁሉም ነገር በምስጢር ነው የሚደረገው:: አብዛኛው የፖለቲካ አመራር አያውቀውም ነበር::
ለምሳሌ ድብቅ እስር ቤቶች ቢኖራቸውም ሌላው አመራር ግን አያውቃቸውም ነበር:: እነዚያ ድብቅ እስር ቤቶች ውስጥ የሚፈልጉትን ሰው ይወስዳሉ፤ ለምሳሌ ቶርች ለማድረግ የሚፈልጉትን ሰው ከግንቦት ሰባት ጋር በማያያዝ ሽብር ለመፍጠር ሲንቀሳቀስ ነበር በድብቅ እስር ቤት ውስጥ በማስገባት ከፍተኛ የሆነ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ይፈፅሙባቸው ነበር::
እንደሚታወቀው በአብዛኛው እስር ቤት የአማራና የኦሮሞ ተወላጆች ነበሩ:: የኦሮሞ ተወላጆችንም በተመሳሳይ ከኦነግ ጋር አብረው የሽብር ተግባር ሲፈፅሙ ነው የያዝኳቸው በሚል ከፍተኛ ስቃይ ያደርስባቸው ነበር:: በአማራ ክልል በኩል ያሉትን ደግሞ የግንቦት ሰባት ተላላኪዎች ናቸው እያለ ነበር መከራና ግፍ ሲያደርስባቸው የነበረው::
ከዚህም ባሻገር ብዙ ሲያነታርከንና ሲያወዛግበን የነበረው የማንነትና የራስ አስተዳደር በሚጠይቁ ሕዝቦች ላይ ይፈፅሙት የነበረው በደል ነው:: ለምሳሌ ወልቃይት ጠገዴ፤ ሁመራ፤ ጠለምትና ራያ የመሳሰሉት አካባቢዎች በቃላት ሊገለፅ የማይችል በደል ነበር ሲፈፅምባቸው የነበረው::
በመሰረቱ ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ እጅግ ሕገወጥ በሆነ መንገድ ያለፍላጎታቸው ማንነታቸውን ጨፍልቆ ያኖራቸው ህዝቦች ናቸው:: እነዚህ ሕዝቦች ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ነው መቃወም የጀመሩት:: ያ ሕዝብ የራሱን ማንነት በራሱ እንዳይወስን መደረጉን ፍትህ መነፈጉን በግልፅ ነበር ሲናገር የቆየው:: ይህንን ጥያቄ በሚያነሱበት ጊዜ ሌላ ስም ይሰጣቸው ነበር:: ጥያቄው የትምክህተኞች ጥያቄ ነው፤ ርስት የማስመለስ ጥያቄ ነው እያሉና የተለያየ ስያሜ እየሰጡ ሰዎቹን ሲያስሩ፤ ሲገድሉና ሲያሳድዷቸው ነው የኖሩት::
አስታውሳለሁ አንድ ጊዜ እዛው አማራ ክልል እያለሁ የታዘብኩት አንዱ ጉዳይ የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ የሚባል ነበር:: ያ ኮሚቴ በክልሉ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ ስለማያገኝና እስርና ግድያ ሲያጋጥመው በየጊዜ እየመጡ ለፌደራል ተቋማት አቤቱታ ያቀርባሉ::
ለተለያዩ አካላት «ድምፃችን ይሰማ፤ ፍትህ እናግኝ፤ ማንነታችን በሕገወጥ መንገድ ተገፏል፤ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብታችን እየተረገጠ ነው፤ በሚያሳዝን ሁኔታ ክብራችንን እያዋረደ ነው» የሚሉ ቅሬታዎችን ያቀርቡ ነበር:: በዚህ ምክንያት በጣም በርካታ ዜጎች ግፉን እየፈሩ አገር ጥለው ተሰደዋል:: አንድ ጊዜ ታዲያ በተመሳሳይ እነዚሁ ኮሚቴዎች በአንድ መኪና ሆነው አቤቱታ ለማቅረብ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ላይ ሳሉ ሱሉልታ ላይ በማይታወቅ ኃይል ታፍነው ተወሰዱ:: ማን እንዳሰራቸው ግምገማ ላይ ሁሉ ተነስቶ ማንም ኃላፊነቱን ሊወስድ አልቻለም::
የፌደራል ፖሊስን ስንጠይቅ እኔ አላውቅም ብሎ ምላሽ ሰጠ፤ ብሔራዊ ደህንነትም ሲጠየቅ አላውቅም አለ፤ ግን ያሳፈናቸው ብሔራዊ ደህንነት ሆኖ ነው በመጨረሻ የተገኘው:: እንደሚታወቀው እነጌታቸው አሰፋ የሚመሩት ተቋም የራሱ የተደራጀ ወታደር ነበረው፤ ስለዚህ በዚህ ኃይል አፍነው ወሰዷቸውና የተወሰነ ቀን አቆይተው ብዙ ጩኸት ሲመጣ መጨረሻ ላይ ለቀቋቸው:: በዚህ መልኩ ወደዚህም እንዳይመጡና አቤቱታቸውን እንዳያሰሙ ይከለክሏቸው ነበር::
ሌላ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ጎንደር ላይ ተፈፅሞ የነበረው ድርጊት ነው:: የማንነት ኮሚቴ አባል ከነበሩት አንዱ ኮሎኔል ደመቀን ለመያዝ ጥረት በሚደረግበት ጊዜ የክልሉ መንግስት ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም::
እንደክልል አመራር ምንም አይነት መረጃ አልተሰጠንም ነበር:: እንደዚህ አይነት አሰራር መሆን ያለበትና ሰውየው በሕግ የሚፈለግ ከሆነ በሕግ ይፈለጋል ተብሎ መጥሪያ ይደርሰዋል፤ ወደሚፈለገው ፖሊስ ጣቢያ ወይም ወደሚፈለግበት ሕጋዊ ተቋም ላይ ነው ሪፖርት መደረግ ያለበት:: ይሁንና ግለሰቡን ለመያዝ ይህ አካል በሚንቀሳቀስበት ጊዜ የክልሉ መንግስት በማያውቀው ሁኔታ ሌሊት ላይ ታጣቂዎች ልከው እንዲከበብ አደረጉ::
ከዚያ በኋላ ኮሎኔል ደመቀ ደግሞ ከቤት ውስጥ ሆኖ እጅ ላለመስጠት ባደረገው የተኩስ ልውውጥ ጎንደር ላይ በጣም ከፍተኛ ውጥረት ተከሰተ፤ በአሳፋሪ ሁኔታ ከተማዋን የሚያውክ ተግባር ፈፀሙ:: በዚህ ምክንያት በጣም ብዙ ጉዳት ደረሰ፤ ከፍተኛ የሆነ ብጥብጥና ሁከት ተነሳ፤ ንፁሃን ዜጎች ሞቱ ከፍተኛ የሆነ ትርምስ ተፈጠረ:: ያን ያህል ነበር በክልሉ በማን አለብኝነት ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ሲፈፅሙ የነበሩት::
በነገራችን ላይ ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ወዲያውኑ በጋራ መድረኮቻችን ላይ ገምግመናል፤ ግን እነሱ የፀረ ሽብር ህጉን በመጥቀስ በሽብር የሚፈለጉ ሰዎችን የፌደራል መንግስት በፈለገው ሁኔታና ጊዜ የመያዝ መብት እንዳለው ነው ምላሽ የሰጡት:: እነዚህ ሰዎች ግን እያንዳንዱን የማንነት ጥያቄ የሚያነሳ ሕዝብና የኮሚቴ አባል በሽብር ተሳትፏል እያሉ ነበር ሲያድኑት የነበረው:: እንዳልኩሽ ይህንን ተግባር በሚፈፅሙበት ጊዜ የሚጠቅሱት ህግ አላቸው::
ነገር ግን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ነው የሚፈፅሙት:: እናም እንዲህ አይነት ተቆጥረው የማያልቁ ግፍና በደል ነበር ሲፈፅሙ የቆዩት:: ይህ ሁሉ ሲሆን የሕዝቡ ትግል አልተቋረጠም ነበር፤ ክልሉን በሚመራው አመራር ውስጥም አለ፤ በየመድረኮቹ ላይ ቢነሳም ሁልጊዜም ይክዱና ሕግን ሰበብ እያደረጉ ይሸፋፍኑት ነበር:: አይናቸውን ጨፍነው አናውቅም ብለው ይክዱ ነበር::
በዚያ መንገድ የአማራ ሕዝብ ላይ የፈፀሙት ግፍና በደል በጣም ከባድ ነው:: እኔ በዚያ አጭር ቃለመጠይቅ የሚያልቅ አይመስለኝም:: ወደፊት የነበረው ነገር ሁሉ በጥልቀት ተጠንቶና በመረጃ ዳብሮ የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ የዓለምአቀፉ ማህበረሰብም እንዲያውቃቸው ማድረግ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ:: ይህ ደግሞ ይዞት ከተነሳውና አማራን እንደጠላት ፈርጆ መነሻ የሆነና ፀረ- አማራ የሆነ አቋም የያዘ ድርጅት ነበር ማለት ይቻላል::
አዲስ ዘመን፡– ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአማራ ሕዝብ ላይ ይፈፀሙ የነበሩ የኢኮኖሚ ተፅዕኖችና ሕዝቡ በድህነት እየማቀቀ እንዲኖር ያደርጓቸው የነበሩ ድርጊቶች ምን ምን ነበሩ?
አቶ ብናልፍ፡- በኢኮኖሚ ረገድ በመላ አገሪቱ በሚባል ደረጃ ኢ-ፍትሃዊነት የሆነ አሰራር ነበር ሲከተሉ የነበሩት:: ይሄ ቡድን በአጠቃላይ በሁለት አይነት መንገድ ነበር ይህንን ሕገወጥ ድርጊቱን ሲያስፋፋ የነበረው:: አንደኛው ሕጋዊ በሆነው የመንግስት ተቋማትን በመጠቀም ሲሆን ለምሳሌ የመንገድ ግንባታን ወስደን ብናይ በአማራ ክልል ውስጥ የተሰሩ መንገዶች ከክልሉ ስፋትና ከሕዝቡ ብዛት አኳያ ሲታይ እጅግ በጣም ዝቅተኛ የሚባል የመንገድ ልማት ነበር:: በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ነበር:: ስለዚህ ይህንን የመንገድ ፕሮጀክቶችን የሚመሩት የእነሱ ሰዎች ስለነበሩ እንዲህ አይነት ፕሮጀክቶች በሚያዙበት ጊዜ ኢ- ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ስርጭቱ እንዲቀጥል ያደርጉ ነበር::
እዚህ ላይ በጣም ትልቅ ጩኸት ነበር የነበረው:: በክልሎችም የጋራ ግምገማዎች በሚደረግበት ጊዜ በኢ-ፍትሃዊነቱን አንስተው ይሞግቱ ነበር:: እናም እንደዚህ አይነት የመሰረተ ልማት ስርጭት ላይ አድሏዊነት በነገሰበት መንገድ እንዲቀጥል የሚደረግበት አሰራር ነበር ይታይ የነበረው::
ሁለተኛው ደግሞ በልማት ድርጅቶች አማካኝነት የሚደረግ ዘረፋ ነው ኢ-ፍትሃዊነቱን እያባባሰው የሄደው:: የመንግስት የልማት ድርጅቶች የሚባሉ ለምሳሌ እንደባንክ፥ ቴሌና በመሳሰሉት ተቋማት ላይ በጣም ብዙ ዘረፋዎችና በደሎች ተፈፅመዋል:: ለምሳሌ ሜቴክ የሚባለው ተቋም ሲፈፅም የነበረው ግፍ ይታወቃል:: በእነዚህ ተቋማት አማካኝነት ከፍተኛ ዘረፋ የተፈፀመባቸው ተቋማት አሉ:: ለምሳሌ በኢንቨስትመንት ስም የሚደረገውን ዘረፋ ብናይ ሰፋፊ የእርሻ ቦታ ባላቸው አካባቢዎች ላይ የእነሱ ተላላኪ፥ ዘመድ ወይም ደግሞ የቅርብ አስፈፃሚ የሆኑ ሰዎችን ፍቃድ እንዲያወጡ አድርገው በኢንቨስትመንት ስም እርሻ እንዲወስዱ ያደርጋሉ::
በተለይ በጣም በከፍተኛ ደረጃ ሊጠቀስ የሚችለው ቤኒሻንጉልና ጋምቤላ ክልሎች ላይ የፈፀሙት ምዝበራ ነው:: በእነዚህ ክልሎች በጣም በከፍተኛ ደረጃ ሰፋፊ እርሻዎችን የእነሱ የቅርብ ዘመዶች ወይም ደግሞ የእነሱ ጉዳይ አስፈፃሚ ሰዎች ናቸው እንዲይዙ የተደረገው::
ይህንን እርሻ መውሰዳቸው ብቻ አይደለም ትልቁ ወንጀላቸው:: ከዘረፉ አይቀር መሬቱን ወስደው ቢያለሙት እንኳ አንድ ጥሩ ነገር ነበር:: ምክንያቱም ቢያንስ ለአገር ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ ይኖረው ነበር የሚል እምነት ስላለኝ ነው:: ግን እነሱ ይህንን አይደለም ያደረጉት:: መሬቱን ከወሰዱ በኋላ ከባንክ ጋር ይገናኙና በመሬቶቹ ከፍተኛ የሆነ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ብድር ይወስዳሉ::
ያንን የወሰዱትን ገንዘብ እርሻው ላይ ኢንቨስት አያደርጉትም:: የሚወስዱትን ገንዘብ ወደውጭ ያሸሹታል:: ስለዚህ በዚህ መልክ የአገሪቱን ሃብት እያሟጠጡና ብድር እየወሰዱ ባንኮች በከፍተኛ ኪሰራ ውስጥ እንዲወድቁ አድርገዋል:: የሚገርምሽ ከባንክ ጋር በኔትወርክ የተሳሰሩ ናቸው:: ባንክ ውስጥ የሰገሰጓቸው ሰዎች ስላሉ በእነሱ አማካኝነት ብድር ለእነዚህ ሰዎች በቀጥታ የሚሰጥበትን መንገድ ያመቻቹ ነበር::
አሁን ላይ በየከተሞቹ ባለቤት አልባ የተባሉ ትላልቅ ህንፃዎች በዚህ መልኩ የተሰሩ ናቸው:: ምንም ያልነበረው ሰው በዚህ ሕገወጥ መስመር ይገባና በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ይወስዳል፤ ትላልቅ ህንፃ ገንብቶ ሚሊየነር ይሆናል:: እንደዚህ እያደረጉ ሃብት እየመዘበሩ በጥቂቶች እጅ እንዲገባ እያደረጉ ይሄዱ የነበረው::
ኢ-ፍትሃዊነት እየነገሰ፤ ግለሰቦች በአጭር ጊዜ እየከበሩ፤ ከምንም ተነስተው ባለሃብት እንዲሆኑ የተደረገበት ስርዓት ፈጥረው ነበር:: በመንግስት ከፍተኛ አመራር ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች የሚዘርፉትን ገንዘብ በራሳቸው ስም አያደርጉትም ነበር፤ አብረዋቸው በሚሰሩ ሌሎች ግለሰቦች ስም እያደረጉ ነበር የሚጠቀሙት:: በዚህ ምክንያት ኢ-ፍትሃዊነቱ እየሰፋ የመጣውና የለውጡ ዋነኛ ሰበብ የሆነው አንዱ ይኸው ጉዳይ ነበር::
ይህ ድርጊታቸው እየቆየ ሲሄድ ደግሞ በግላጭ እየወጣ ነው የመጣው::ለምሳሌ በኮንትሮባንድ ንግድ ነጋዴውን ከጨዋታ ውጭ ያደረጉበት ሁኔታ ነበር:: መከላከያ ውስጥ ባሉ በእነሱ ሰዎች አማካኝነት በመከላከያ መኪና ያለፍተሻ የኮንትሮባንድ እቃ እንዲገባ ይደረግ ነበር:: ሌላው ይቅርና በአየር መንገድም በኩል በጉምሩክ ያሉ የእነሱ ሰዎችን በመጠቀም ያለቀረጥ የሚገቡበት ሁኔታ ነበር::
በዚህ መልኩ ሕገወጥ ምርቶችን አገሪቱ ላይ እያፈሰሱ፤ ግብር የሚከፍለው ነጋዴ ደግሞ ከጨዋታ ውጭ እንዲሆን በማድረግ ከንግድ ስርዓቱ ነቅለው አውጥተውታል:: እናም የእነሱ ኔትወርክ ብቻ ገበያውን እየተቆጣጠረ ሕጋዊ ነጋዴውን ከጥቅም ውጭ እያደረገ የሄደበት ሁኔታ ነበር የነበረው::
እናም በእንደዚህ አይነት መንገድ አገሪቱ ትርምስ ውስጥ እንድትገባና ጥቂት ቡድኖች የከበሩባት፤ ከፍተኛ ሃብት የዘረፉበት ሁኔታ እንዲፈጠር ተደርጓል:: እነዚህ ናቸው ለውጡን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀጣጠል ያደረጉትና የኋላ ኋላ ይህ ቡድን በዚህ የለውጥ እንቅስቃሴ ተገፍቶ እንዲወጣ ያደረጉት:: ከሚዘርፍበት ኔትወርክ እንዲነቀል የተደረገው:: በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ እርምጃዎች እየተወሰዱ ሲመጡ የዘረፋ ድርሻቸው እየተመናመነ መጣ::
በኋላም ጠቅልለው ወደ መቀሌ ገቡና ከዚያም ለውጡን በመቃወም ሂደት ላይ ተሰማርተው አገር ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ ቆዩ:: እናም ከኢኮኖሚም አኳያ የነበረው ኢ- ፍትሃዊነት በእነዚህ አሁን በገልፅኳቸው መንገድ ሲሰራ የነበረ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል::
አዲስ ዘመን፡– በወልቃይትና ራያ በመሳሰሉት አካባቢዎች በሕዝቡ ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን በምን አግባብ ነው ለመመለስ የታሰበው?
አቶ ብናልፍ፡– እነዚህ ጥያቄዎች ላይ አንዱ መሰረታዊ መዛባት ያለው ጥያቄው ራሱ ምንድን ነው በሚለው ላይ ነው:: መዛባቱ ለምን እንደመጣ አነሳዋለሁ:: የእነዚህ ሰዎች ጥያቄ የፍትህ ጥያቄ ነው:: በሰውነታቸው የሚጠይቁት የፍትህ ጥያቄ ነው:: ይህም ማለት ለምሳሌ እኔ አማራ ነኝ የምለው በሌላው ሰው ግፊት መሆን አይገባውም:: እኔ ራሴ አማራ ነኝ ብዬ ስለማምንና ስለምቀበል ነው:: ከዚያም ኢትዮጵያዊ ነኝ::
በተመሳሳይ ኢትዮጵያዊ መሆኔን ማንም ሰው አይደለም የሚወስንልኝ:: እያንዳንዱ ሰው ማንነቱን በራሱ ነው እንዲወስን ሊደረግ የሚገባው:: ይህ የግለሰቦች መብት ነው:: እነዚህ ሰዎች ግን ይህንን መብት ነው የተነፈጉት:: የእኔ ማንነት ነው ብለው በራሳቸው ለመወሰን የማይችሉበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው:: ስለዚህ ይሄ ቡድን በአገር ክህደት ወንጀል ውስጥ የገባው ቡድን የእነዚህን ሰዎች መብት አፍኖ ነው የኖረው::
አስቀድሜ እንደገለፅኩት ለጥያቄያቸው የተለያየ ታርጋ በመለጠፍ ፈፅሞ ድምፃቸው እንዳይሰማ በማድረግ መብታቸው ተረግጦ እንዲኖር ነው ያደረገው:: እነዚህ ሰዎች ከመጀመሪያው ጀምሮ የሚያነሱት ጥያቄ ማንነታችን ራሳችን መወሰን አለብን የሚል ነው:: ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻችን በማንም እጅ ሊሆን አይገባም:: ይህ መብት ሰው በመሆናችን ምክንያት የተሰጠን ፀጋ ነው:: እነዚህን ጥያቄዎች ያለማጋነን ላለፉት 30 ዓመታት በተለይም እኔ አማራ ክልል በነበርኩባቸው ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ሲያነሱ ነው የቆዩት:: አሁንም ድረስ ይህ ጥያቄ እየተነሳ ነው::
አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ ይህንን ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች የአማራ የመሬት አስመላሽ የሚል ታርጋ ይሰጧቸዋል:: ጥያቄው የትምክህተኛ ኃይል እንጂ የሕዝብ ጥያቄ አይደለም ብለው ያፍኑታል:: የሚገርመው ለመስማት እንኳ ፍላጎት አልነበራቸውም:: ስልጣን ላይ በቆዩባቸው ዓመታት ሁሉ ሕዝቡ የሚለውን ላለመስማት ጆሮአቸውን ደፍነው የሚፈልጉትን ብቻ ነበር ሲያደርጉ የኖሩት::
የእነዚህን ሰዎች መብት የረገጡበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የሰዎቹን መሬትና ሃብታቸውን ለመውሰድ ስለፈለጉ ነው:: ስለዚህ ይህ ነገር እንዳይጋለጥ፤ እንዳይወጣ፤ ብሎም የኢትዮጵያ ሕዝብም በትክክል እንዳይረዳው፤ ብሎም የአለምአቀፉ ማህበረሰብም የችግሩን መሰረት እንዳያውቀው ሸፋፍነው ነው ያኖሩት:: አሁንም ራሱ በሚገርም ሁኔታ ይህንኑ ሙዚቃ እየሞዘቁ ነው ወደመቃብር እየወረዱ ያሉት:: ዛሬም ድረስ ሚዲያ ላይ እየወጡ የአማራ መሬት ማስመለስ ዘመቻ ነው እያሉ ነው በቅርቡ የተወሰደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ ሲጠቅሱት የነበረው:: ይህንን ሃሰተኛ ትርክት ለአለምአቀፉ ማህበረሰብ ለማስተላለፍ ሲሞክሩ የነበሩት::
በነገራችን ላይ አጀንዳና አቅጣጫ ማሳት ከድሮም ጀምሮ የተካኑበት ባህሪ ነው:: ስለዚህ መሰረታዊ የሆነውን የሰው ልጆች መብት በወልቃይት፤ በጠገዴ፣ በራያና በመሳሰሉት አካባቢዎች ያሉ ሕዝቦች ድምጽ እንዳይሰማ አጀንዳ እያስቀየሩ ነው የኖሩት:: አሁን የተፈጠረው አዲሱ ነገር ጥያቄው ከዚህ በኋላ መታፈን አይችልም:: ይሄ አፋኝ ቡድን ላይመለስ ወደመቃብሩ ወርዷል፤ ስለዚህ የመጨረሻ የሞት ሞት ያደረጉት ትግል ይህንን የሕግ ማስከበርና አገር የማዳን ዘመቻ የመሬት ማስመለስ ዘመቻ ነው በሚል አገናኝተውት ቀላል የማይባል መደነጋገር ፈጥረዋል::
ግን ሃቁና እውነቱ ደግሞ ተደብቆ አይቆይም::የእነዚህ ሰዎች ጥያቄ የመብት ጥያቄ ነው:: መሬት ማንም ሰው ሊያርሰው ይችላል፤ ከትግራይ አካባቢ የመጡ ሰዎች ያርሳሉ፤ ከአማራ ክልልም የመጡም እንዲሁ ያርሳሉ:: ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ የእርሻ መሬት አለ በሚባልበት ቦታ ሁሉ የተለያየ አይነት የህብረተሰብ ክፍሎች እየሄዱ ማረስ የተለመደ ነው:: ይህም ማለት በግለሰብ ደረጃ እንጂ እንደማህበረሰብ የሚፈፀም አይደለም::
ስለዚህ እዛ አካባቢ ያለ የእርሻ መሬትም በተግባር ሄዶ ሲታይ አማራም ሆነ ትግሬ ሄዶ ሊያርስ ይችላል:: ዋናው ነገር እሱ አይደለም፤ ዋናው ነገር የሰው ልጆች ክብር ነው:: የማንነት ጥያቄው ምላሽ ማግኘቱ ነው:: ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል::
ስለዚህ ጽንፈኛው ቡድን የማንነት ጥያቄውን አጀንዳ እያስቀየረ የሕዝቡ መሰረታዊ ጥያቄ ለ30 አመት ተዳፍኖ እንዲኖር አድርጓል:: በዚህ ምክንያት ብዙ ትግል ተደርጓል፤ ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሏል፤ በርካቶች ተሰደዋል፤ አካላቸው ጎሏል፤ ተኮላሽተዋል:: ገና ወደፊትም አፍነው የኖሩት ብዙ ሚስጥር ይወጣል የሚል እምነት ነው ያለኝ:: የህወሓት የግፍ ጫካ ገና ብዙ እየተገላለጠ ይወጣል::
እነዚህ ማንነታቸው እውቅና ያልተሰጣቸው ዜጎች ለ30 ዓመታት ሲበደሉና ሲገፉ ቢኖሩም ጥያቄአቸውን በአመፅ ለመፍታት አንድም ቀን ተንቀሳቅሰው አያውቁም:: ሁሌም ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ነው ሲጠይቁ የኖሩት:: ግን ማንም ጆሮ ሊሰጣቸው አልቻለም:: በምላሹ ግን ግፍና በደል ሲደርስባቸው ነበር::
አሁን ግን ይሄ ሊቀጥል አይችልም:: ከዚህ በኋላ መብት ማፈን፥ መርገጥ ፤ እኔ ብቻ አውቅልሃለሁ ማለት አይፈቀድም:: በተለይም ደግሞ አሁን በጀመርነው ለውጥ እንኳን ሊተገበር ሊታሰብም አይችልም:: ስለሆነም በዚህ የለውጥ እንቅስቃሴ የእነዚህ ሰዎች ጥያቄ እንደሚመለስ ፅኑ እምነት አለን::
እንደበፊቱ አፍኖ መቀጠል አይቻልም:: ስለሆነም ሲጠይቁ የኖሩት በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ነው፤ አሁንም አሰራሩን ተከትሎ ጥያቄያቸው ይመለሳል የሚል አቋም ነው ያለው::
አዲስ ዘመን፡– የትግራይ ክልልን መልሶ የማደራጀት ሥራው አሁን ላይ ምን ያህል ውጤታማ እየሆነ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ብናልፍ፡- መንግስት ሕግን ወደማስከበርና ሃገር ወደማስቀጠል ዘመቻ የገባው አስቀድሜ በገለፅኩት መንገድ በአገር ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ ሴራ በመፈፀሙ ነው:: አገር ለመበተን የተቃጣው ወንጀል ተከትሎ ሳይወድ በግድ መንግሥት ሕግን ወደማስከበር ዘመቻ ውስጥ ገብቷል::
ይሄ ቡድን ደግሞ ላለፉት በርካታ ዓመታት በሚባል ደረጃ ለውጡ ከመምጣቱ በፊት ጀምሮ ብዙ ሴራዎችን ሲሰራ ነው የቆየው:: ከዚያ በኋላ ደግሞ ባለፉት ሶስት ዓመታት ለጦርነት ሲዘጋጅ ነው የቆየው:: በጣም ብዙ ወታደሮች ወይም ልዩ ኃይል የሚባሉ ፖሊሶችን አሰልጥኗል:: በብዙ ሺ የሚቆጠር ሚሊሽያ አሰልጥኗል፤ ጦር መሳሪያ በኮንትሮባንድ መልክ ሲያስገባ ነው የኖረው::
በክልል የፀጥታ ተቋማት መያዝ የሌለባቸው የቡድን መሳሪያዎችን ጭምር እያስታጠቀ ነው የኖረው:: ስለዚህ ይህንን ድርጊት ለመፈፀም የልብ ልብ የሰጠው እንዲህ አይነት ዝግጅት አለኝ በሚል ነው::
በነገራችን ላይ ወደመጨረሻው አካባቢ ሚዲያ ላይ እየወጡ ሲናገሩት የነበረው ነገር በጣም አስገራሚ ነበር:: «ለእኛ ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው» የሚሉ ትዕቢት የተሞላባቸው ንግግሮችን በድፍረት ይናገሩ ነበር:: እውነት ለመናገር እነዚህ ቡድኖች የእብሪታቸው ልክ ወሰን የለውም:: ሁሉም በሚባል ደረጃ ትዕቢትና እብሪት ወጥሮ የያዛቸው ሰዎች ናችው:: «ከእኛ በላይ ለጦርነት የተፈጠረ የለም፤ ከእኛ በላይ ውጊያ ላሳር ነው» የሚሉ እብሪት የተሞሉ ሰዎች ነበሩ:: ግን ይህንን እብሪታቸውን እንዲፈፀም ያደረጉት በሚያሳዝን ሁኔታ በደሃው ልጅ ላይ ነው::
የእነሱ ልጆች በዚህ ጦርነት አይማገዱም:: አይለበለቡም:: እነዚህ አረመኔ ሰዎች እድሜ ልካቸውን ድሃውን የትግራይ ወጣት በጦርነት ውስጥ እየማገዱ የኖሩ ሰዎች ናቸው:: ስለዚህ አሁንም እያደረጉ ያሉት ይህንኑ ነው:: በሕግ ማስከበሩ ዘመቻ የተማረኩት ህፃናት ልጆች ከትምህርት ገበታ ላይ ተነቅለው ተወስደው የተመለመሉ ናቸው:: ልክ እንደሌላው ህዝብ ሁሉ እጅግ በጣም ኢ-ሰብዓዊ በደል ነው በትግራይ ህዝብ ላይ ያደረሱት:: ከጅምሩም ቢሆን ይህ ሕግ ማስከበር ስራ ሲሰራ ተጎጂ የሚሆነው የትግራይ ሕዝብ እንደሆነ በጣም ግልፅ ነው::
አንደኛ ልጆቹን መስዋዕት እያደረገ ነው ያለው:: ሁለተኛ ደግሞ ጦርነት ምንም ቢሆን ውጊያ መስዋዕትነት ያስከፍላል፤ አካባቢ ይረብሻል፤ የሚወድም ሃብት አለ፥ ንፁሃን ይሞታሉ፤ ይፈናቀላሉ:: እንዳውም ይሄ ኦፕሬሽን በጥንቃቄ ባይሰራና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እነኚህን ሰዎች ንፁሃን ዜጎች እንዳይጎዱ የጁንታውን ቡድን ነጥሎ ብቻ ለመውሰድ ጥንቃቄ የተሞላበት ስራ ባይሰራ ኖሮ በጣም ከፍተኛ ቀውስ ያስከትል ነበር::
በሌሎች አገራት ማየት እንችላለን፤ አገር አልባ የሆኑ ሕዝቦች አሉ እንደሶሪያ ያሉ ብዙ አገሮችን መጥቀስ እንችላለን:: የአለም አገራት እንኳ አምባገነን መንግስት እናስወግዳለን ብለው ጣልቃ ገብተው በዜጎች ላይ ያደረሱትን ግፍና በደል እናውቀዋለን:: እኛ ሀገር ትልቅ ስኬት አድርጌ የምወስደው በንፁሃን ዜጎች ላይ የደረሰ ጉዳት የለም::
በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሰራዊት የተሰጠውን ግዳጅ በጥንቃቄና በብቃት በመወጣት ረገድ ንፁሃን እንዳይጎዱ በማድረግ ረገድ ጥፋተኛውን ሃይል ብቻ ነጥሎ በመምታት ሕግን ለማስከበር የወሰደው እርምጃ ትልቅ አድናቆት ሊሰጠው የሚገባ ነው፤ በታሪክ መዝገብም ሊመዘገብ የሚገባ ትልቅ ክስተት ነው:: የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ጥቃት ሲሰነዘርባቸውና ክልሉን ለማፍረስና በተሰነዘረባቸው ጥቃት መልሰው በመቋቋም መልሰው በማጥቃት እንቃስቃሴያቸው ንፁሃን እንዲጠበቁ ያደረጉበት መንገድ ትልቅ ታሪክ ይመስለኛል::
ሌላው ይቅርና በጦርነቱ የተማረኩና እጃቸውን የሰጡ ዜጎችን በአግባቡ ተንከባክበው፤ ቁስላቸውን ጠርገው፤ መጠለያ ውስጥ አስገብተው ሕዝቡ ምግብ እያቀረበ ነው የጠበቃቸው:: ምክንያቱም እነዚህ ልጆች በማያውቁትና ያለምንም አላማ እሳት ውስጥ ስለማገዷቸው ነው እንጂ የእነሱ ፍላጎት አልነበረም:: ስለዚህ ጉዳት እንዳይደርስ የተደረገው ጥንቃቄና የተገኘው ስኬት ወደፊት በታሪክ ሊወሳ የሚገባው ክስተት ነው::
በዚህ ግጭት ወቅት አንዳንድ የተጎዱ መሰረተ ልማቶች አሉ:: ከሃዲው ቡድን ሽንፈቱ አይቀሬ መሆኑን እየተገነዘበ ሲሄድ የያዛቸውንና ምሽግ የሰራባቸውን ቦታዎች እየለቀቀ በሚሄድበት ጊዜ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን እያፈረሰ ሄዷል:: ለምሳሌ መከላከያ ሰራዊት አልፎና ተሻግሮ እንዳይሄድ መንገድ ሲቆርጡና ሲያፈርሱ ነበር:: አየር ማረፊያዎችን ከጥቅም ውጭ አድርገዋል:: ስልክና ኤሌክትሪክ የመሳሰሉትን መሰረተ ልማቶች ቆራርጠዋል::
እነዚህን መሰረተ ልማቶች ተጠግነው ቶሎ አገልግሎት የሚሰጡበትን መንገድ ለመፍጠር እየተሰራ ነው:: ይህ ሲባል ግን አንዳንድ ሰዎች ክልሉ በጠቅላላ እንደወደመ አድርገው የሚጠቅሱ አሉ:: ግን ይህ ስህተት ነው::
አንዳንድ ቦታዎች ላይ የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን በመጠገን መልሶ ወደ አገልግሎት እንዲገቡ የማድረግ ስራ ነው እየተሰራ ያለው:: ለምሳሌ መቀሌን እንዴት መጠበቅ እንደተቻለ ይታወቃል፤ ይሄነው የሚባል ውድመት ሳይደርስበት በጥንቃቄ ኦፕሬሽኑን ለመስራት ነው የተሞከረው::
እንደአጠቃላይ የተፈናቀሉ ስላሉ እነሱን ወደቀያቸው መመለስ ያስፈልጋል:: የተጎዱ ተቋማችን መጠገንና አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ያስፈልጋል:: ለጊዜው ምግብ የሌላቸውን ሰዎች የዕለት ሰብአዊ እርዳታ ያስፈልጋል:: እነዚህ ስራዎች ትልልቅ ናቸው::
በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ደረጃ በተደረገው ውይይት መንግስት የጀመረው ስራ አለ:: ነገር ግን ተጠናክረው የጥፋት ኃይሉን መሪዎች ከገቡበት ጉድጓድ አውጥቶ ወደፍርድ አደባባይ የማቅረቡ ስራ እንዲፋጠን ከማድረጉ ስራ ጎን ለጎን ህብረተሰቡ አገልግሎት የሚያገኝበት ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል::
በነገራችን ላይ ጠቅላላ የገጠሩም ሆነ የከተማውን ሕዝብ ማለት አይደለም እንደዚህ አይነት ውጊያ የነበረባቸውና የመሰረተ ልማት ጉዳት የደረሰባቸው ጥቂት ከተሞች ናቸው:: እነዚህን ወደነበረበት እንቅስቃሴ የመመለስ ስራ መጠናከር አለበት የሚል አቅጣጫ ተቀምጧል:: ለዚህም የተለያዩ ቡድኖች ተልከዋል:: የመብራት፥ የውሃ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ጥገና የሚያከናውኑ ባለሙያዎች ወደአካባቢው እንዲንቀሳቀሱና የመልሶ መገንባት ስራው በፍጥነት እንዲከናወንና አገልግሎቱ እንዲቀጥል እየተደረገ ነው::
ምክንያቱም የትግራይ ሕዝብ ከእነዚህ ጁንታዎች ጋር ፈፅሞ የዓላማም የአስተሳሰብም አንድነት የለውም:: ስለዚህ ይህ ሕዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ ይገባል:: በእነሱ ምክንያት በሕዝቡ ላይ የሚደርስ ጉዳት መኖር የለበትም በሚል እየተሰራ ነው ያለው::
አዲስ ዘመን፡– እስካሁን ባለው ሂደት ከትግራይ ክልል ወደ ውጭ የተሰደዱ ዜጎችን የመመለሱ ሂደት ምን ደርሷል? የስደተኞቹ ቁጥር በውል ይታወቅ ይሆን?
አቶ ብናልፍ፡– ይህ ስራ የተጀመረው በቅርብ ነው:: ምክንያቱም ሕግ የማስከበር ዘመቻውም የተጠናቀቀው በቅርቡ በመሆኑ ነው:: በአሁኑ ወቅት በመከላከያና በጁንታው መካከል የሚደረግ ውጊያ የለም:: ግን ፖሊሶች እነዚህን ወንጀለኞችን በማሰስ ወደ ፍርድ የማቅረብ ስራውን እየሰሩ ነው ያሉት:: ስለዚህ ከዚህ በኋላ ዜጎች ወደቀያቸው እንዲመለሱ የሚያግድ ምክንያት የለም ማለት ነው:: በመሆኑም በቅርቡ እነዚህን የተሰደዱ ዜጎች ወደቀያቸው መመለስ አለብን በሚል ስራ ተጀምሯል:: እስካሁን ወደሱዳን የሄዱትን ዜጎች ቁጥር በተጨባጭ አሁን መናገር አልችልም::
በግምት ግን ከ30 እስከ 40 ሺ ሰዎች ሄደዋል የሚል ግርድፍ መረጃ አለ:: ይህንን ማጥራት ይጠይቃል:: በውጊያው በተለቀቁ ቦታዎች ላይ የፈፀሙት ኢ-ሰብአዊ ድርጊት አለ፤ ለምሳሌ ማይካድራ ላይ የተፈፀመው ጭፍጨፋና በደል ታሪክ ይቅር የማይለው በጣም ትልቅ ወንጀል ነው:: በማንነታቸው ላይ የተመሰረተ ጥቃት ነው የተፈፀመባቸው::
በነገራችን ላይ አማራን ጠላት አድርጎ የሚያይበት አንዱ መገለጫ ማይካድራ ላይ የፈፀመው ማንነት ተኮር ጭፍጨፋ ነው:: ቤኒሻንጉልም ሆነ ኦሮሚያ ክልል የተፈፀመው የዚሁ አካል ነው::
የማይካድራው ጭፍጨፋ ከሌሎቹ የሚለየው ራሳቸው መፈፀማቸው ሲሆን በሌሎች አካባቢዎች ላይ ግን ገንዘብ እየከፈሉ፤ እያደራጁ፤ እያስታጠቁ በሌሎች እኩይ ሰዎች አማካኝነት ነው የፈፀሙት:: ስለዚህ ይህንን ግፍ እየፈፀሙ በሄዱባቸው አካባቢዎች ዜጎች ለጊዜ ነፍሳቸውን ለማዳን ሲሉ ወደተለያዩ አካባቢዎች የተሰደዱ እንደሚኖሩ ምንም ጥርጥር የለውም:: እነሱ እንደሚሉት ጦርነት ጫወታ ወይም ፌዝ አይደለም:: ጦርነት የሰው ህይወትን ነው የሚበላውና የሚያወድመው:: በዚህ ምክንያት የተጎዱና ከአካባቢያቸው የራቁ ሰዎችን የመመለስ ስራ እየተሰራ ነው::
በእርግጠኝነት ደግሞ በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል ይሄ ስራ:: ሰብዓዊ ድጋፉም አሁን ላይ እየቀረበ ነው ያለው:: ምክንያቱም ውጊያው ከቆመ ወደ ቀያቸው የመመለሱ ስራ ቀላል ነው:: የተራዘመ ጦርነት ቢሆን ኖሮ የተፈናቃዩ ቁጥር እየጨረ ነው ሊሄድ የሚችለውና መመለሱም ከባድ የሚሆነው:: የዘመቻ ስራ ነው ወንጀለኛ የመያዝ ስራ ነው በአጭር ጊዜ ተጠናቋል:: እነሱ ለብዙ አመት ተዘጋጅተው የፈፀሙት ቢሆንም ህግ የማስከበር ስራው ግን በአጭር ጊዜ ነው ማከናወን የተቻለው::
አዲስ ዘመን፡– አንዳንድ የውጭ የእርዳታ ድርጅቶች የሰብዓዊ ድጋፍ እናደርጋለን በሚል የጁንታውን ቡድን የመርዳት አዝማሚያ ታይቶባቸዋል የሚሉ አሉ:: ይህ የድጋፍ ስራ ምን ያህል ጥንቃቄ እየተደረገበት ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ብናልፍ፡– እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው፤ ለእነዚህ ሰዎች ከማንም በላይ ግድ የሚለውና ኃላፊነት የሚሰማው የኢትዮጵያ መንግስት ነው:: ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ ድጋፍ እያደረገ ነው:: ነገር ግን አንዳንድ የውጭ ኃይላት በእርዳታ ሰበብ ጁንታውን ለማስመለጥ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይታወቃል:: ወደፊት ተጣርቶ የሚገለፅ ቢሆንም አሁንም ቢሆን በርካታ ጩኸቶች አሉ::
የእኛን መልማት የማይፈልጉ የኢትዮጵያን ሰላም የማይፈልጉ እድገታችን አደጋ መስሎ የሚታያቸው አገራትና መንግስታት እንዳሉ እሙን ነው:: እኛ እድገት የምንፈልገው ራሳችንን ለመጥቀም እንጂ ማንንም ለመጉዳት እንዳልሆነ ይታወቃል:: ግን ደግሞ እኛ እንድናድግ አይፈልጉም:: ለምሳሌ የአባይ ፖለቲካ አለ፤ በዚያ ላይ የህዳሴ ግድቡን ሙሌት እንዳናጠናቅቅና የኃይል ማመንጨት ስራውን እንዳንጀምር ለማድረግ የተለያዩ የቅስቀሳ ስራ አለ::
በዚያ ውስጥ እኛን እንደጠላት የሚቆጥሩ አገራትና ድርጅቶች ስላሉ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው እኛ ወደዚህ ሁኔታ ውስጥ ስንገባ በደስታ ጮቤ ሲረግጡ ነበር::አሁን ደግሞ በአጭር ጊዜ ይህንን ነገር መልክ ስናሲዘውና ሲጠናቀቅ ቁጭት አድሮባቸዋል:: ምክንያቱም እንደዚህ ይሆናል ብለው አልጠበቁም:: ወደ ትርምስና ወደተራዘመ ጦርነት ውስጥ የምንገባ አድርገው ነበር የሚገምቱት::
ግን እነሱ እንደተመኙት አልሆነም:: እነሱ የቆጫቸውና ያበሳጫቸው ነገር ስላለ ያንን ለማድረግ የጁንታውን ቡድን በተለያየ መንገድ ለመርዳት ጥረት ሲያደርጉ ነው የቆዩት:: የኢትዮጵያ መንግስት በጁንታው ላይ ሌላ ፍላጎት ስላለው ሊጎዳቸው አስቦ እንደተነሳ በማስመሰል ይቀሰቅሳሉ:: ለእነሱ ያላቸውን ውግንናም በግልጽ አሳይተዋል::
አሁንም ቢሆን ጁንታውን ለመርዳት በሚዲያም ሆነ በፕሮፖጋንዳም ጭምር ይሰራሉ:: ከቻሉና መግቢያ ቀዳዳ ካገኙ እነዚህ ሰዎች እንዲያመልጡ ይፈልጋሉ:: መሞከራቸው ይቀራልም ብዬ አላስብም ፤ ነገር ግን ሊሳካላቸው አይችልም:: ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ወደፊት መረጃዎች ግልፅ ሲሆን ለሕዝቡ ይፋ ማድረግ ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን፡– ዘንድሮ በሀገሪቱ ምርጫ እንደሚካሄድ ብልፅግና ጨምሮ በርካታ ፓርቲዎች ስምምነት ላይ ደርሰዋል:: ለመሆኑ ከዚህ አንፃር እየተደረገ ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል?
አቶ ብናልፍ፡– የዘንድሮ ምርጫ መካሄድ የነበረበት ባለፈው አመት ነው:: አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ በኮረና ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫው ወደዚህ ዓመት ተሸጋግሯል:: ዘንድሮ ምርጫው ይካሄዳል ተብሎ ምርጫ ቦርድም እየሰራ ነው ያለው:: የጊዜ ሰሌዳም አውጥቶ እሱኑ እየገለፀ ነው ያለው::
በተቋማት አካባቢ ብዙ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው:: ምርጫ ቦርድ የመንግስት የፀጥታ ተቋማት፤ ሕግና ስርዓትን ከማስከበር አኳያ ተልዕኮ ያለባቸው አካላት የራሳቸውን ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን አውቃለሁ:: ከፓርቲዎች አኳያ ተመሳሳይ ዝግጅቶች አሉ:: ለምሳሌ የፓርቲዎች የጋራ የውይይት መድረኮች አሉ፤ በተለያየ ጊዜ በምናካሂዳቸው መድረኮች በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይቶች ይደረጋሉ:: ፓርቲዎች በጋራ ጉዳይ ላይ በጋራ ስብሰባ እናደርጋለን፤ ርዕሶች እንመርጣለን::
የተመረጡትን ርዕሶች እነማን ጥናታዊ ፅሁፎች ይዘው ያቅርቡ፤ እነማን ደግሞ በማወያየት ይሳተፉ ብለን በጋራ እየወሰንን ነው የምናካሂደው:: በዚህ መንገድ የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ነው እየሰራን ያለነው:: በዚሁ መንገድ ወደ ምርጫ ክርክር በምንገባበት ጊዜ ባህሉን እያዳበርን እንሄዳለን የሚል ነው እምነታችን::
ይህም ሲባል ግን ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ አቋም አላቸው ማለት አይደለም:: አንዳንዶቹ «ምርጫ መካሄድ የለበትም» የሚል አቋም አላቸው:: ግን ደግሞ የመንግሥትን ሥልጣን ይፈልጋሉ:: እነዚህ ሃሳቦች እርስበርሳቸው የሚጣረሱ ናቸው:: አብረው አይሄዱም:: ግን ስልጣን የሚፈልጉት በሌላ መንገድ ነው:: የሽግግር መንግስት እናቋቁም፤ የባላደራ መንግስት ይመስረት የሚል ፍላጎት ያላቸው ፓርቲዎች አሉ::
ይህም አስተሰሰብ ግን ሁሉንም ፓርቲዎች አይገልፅም:: ይህ ደግሞ ከኢትዮጵያ ሕገመንግሥት ውጭ ነው፤ ምክንያቱም ስልጣን የሚያዘው በምርጫ ብቻ ብሎ ስለሚደነግግ ማለት ነው:: ከምርጫ ውጭ የሚመጣ ስልጣን ስለሌለ ያንን ታሳቢ አድርጎ ነው እንጂ መሰራት ያለበት በአቋራጭ እንዲህ አይነት መንግስት እናቋቁም የሚለው ነገር አያስኬድም::
እንዳልኩሽ እንዲህ አይነት አመለካከት ያላቸው አሉ:: ግን ገዢው ነገር ምርጫው መደረጉ የማይቀር መሆኑ ነው:: ለዚህም ዝግጅት ማድረግ ነው የሚያስፈልገው ማለት ነው:: በአጠቃላይ ከአብዛኛው ፓርቲዎች ጋር አስቀድሜ ባልኩት መንገድ እየቀጠልን ነው ወደ ክርክሩም ስንገባ በዚያ መልኩ እንቀጥላለን::
ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ከብልፅግና አኳያ ግባችን ሁለት ነው:: የመጀመሪያው የዘንድሮውን ምርጫ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ማድረግ ነው:: በተጨማሪም በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድም ሆነ በአለምአቀፉ ህብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ምርጫ ማካሄድ ዋነኛውና የመጀመሪያው ግባችን ነው:: ይህንን የምንለውም ለመናገር ያህል አይደለም:: ባለፉት አምስት ምርጫዎች የኢትዮጵያ ህዝብ ስምምነት የለውም:: ቅቡልነታቸው በጣም ዝቅተኛ ነው::
ድምፃችንን የሰጠነው መንግስት መርቶናል የሚል ስምምነት አልነበራቸውም:: ብልፅግና ይህ አይነቱ አሰራር ከዚህ በኋላ መቆም አለበት የሚል አቋም አለው:: ለዚህ ደግሞ የዘንድሮውን ምርጫ ሰላማዊና ነፃ የማድረግ ብሎም በዚህ ሂደት ውስጥ ከምርጫ ምዝገባና እስከምርጫው ውጤት ድረስ ሕዝቡ የሚያምነው የሚቀበለው ማድረግ ነው የሚገባው የሚል አቋም ነው የተያዘው::
በነገራችን ላይ ምርጫው ነፃ ሰላማዊና ቅቡልነት የማድረጉ ስራ ቢሳካልን ብቻ ቀላል ነገር አይደለም ብለን ነው የወሰድነው:: በኢትዮጵያ ታሪክ በዲሞክራሲ ውስጥ ትልቅ መሸጋገሪያ ምዕራፍ ተደርጎ የሚወሰድ ነው:: በእርግጥ ምርጫ ብቻውን በአንድ አገር ውስጥ ዲሞክራሲን ለማረጋገጥ ብቸኛው አማራጭ አይደለም::
ግን ደግሞ የዲሞክራሲ ግንባታ አንድ አካል ነው:: ዜጎች መብታቸውን የሚለማመዱበት የሚተገብሩበት በፈለጋቸው ሰዎች የሚተዳደሩበት እድል የሚያገኙበት የምርጫ ስርዓት ነው:: ስለዚህ ይህ የምርጫ ስርዓት አንድ ቁልፍ ነገር ነው:: በዚህ ምርጫ ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሂደቱም ሆነ በውጤቱ በሙሉ ግልፅነት የሚሳተፍበትና በመጨረሻም አምኖ የሚቀበለው አይነት ምርጫ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል:: የአለምአቀፉ ማህበረሰብም ምርጫውን የመታዘብ እድል ስላለው በታዘበው ትዝብት መሰረት የሚመሰክርበት አይነት መሆን እንፈልጋለን:: ይሄ የመጀመሪያው ግባችን ነው::
ለብልፅግና ይህንን ማሳካት የለውጡ አንድ መገለጫ ተደርጎ የሚወሰድ ነው:: እውነትም በአገሪቱ የጀመርነው ለውጥ እውነተኛ ለውጥ ነው የሚለውን ነገር ማሳያ ነው:: ይሄ ግብ ተሳክቶ ግን ደግሞ አብላጫ ድምፅ አግኝተን ባናሸንፍም እንደሽንፈት የምንቆጥረው አይደለም::
ይልቁንም ትልቅ ድል ነው:: ይህንን ደግሞ ከልባችን ነው የምናምነው፤ ለንግግር ብለን የምናደርገው አይደለም:: እዚህ ላይ ግን ሌሎች ፓርቲዎችን ተመሳሳይ አቋም ሊኖራቸው ይገባል ብለን ነው የምናምነው:: የተሸነፈ ሽንፈቱን በፀጋ ተቀብሎ ለቀጣይ ምርጫ ራሱን የሚያዘጋጅበት፤ ያሸነፈውም አሸንፌያለሁ ብሎ ቃል የገባውን የሚፈፅምበት ምህዳር መፍጠር ያስፈልጋል:: ቅድም እንዳልኩት ግን መሰረቱ ሕዝቡ ነው:: ሕዝቡ አምኖ እስከተቀበለ ድረስ አንቀበልም ቢባልም እንኳ ምንም ማድረግ አይቻልም::
በሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ መግባባት ሊኖር የሚገባው አገር ስትኖር ነው ሁሉም ነገር ሊኖር የሚቻለው የሚለው ነው:: ስለዚህ ከምንም በላይ አገር እንዳትበተን ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ መስራት ነው የሚገባን:: በፈረሰች አገር ውስጥ ምርጫም ሆነ ፖለቲካ የሚታሰብ አይደለም:: ስለዚህ አገር እንድትቀጥል ምርጫው በተረጋጋ ሁኔታ መካሄድ አለበት:: ህዝቡ የመረጠውና የሚቀበለው መንግስታዊ ስርዓት መመስረት አለበት:: ይህንን ለማድረግ የመጀመሪያ ግብ አድርገን መስራት አለብን የሚል ነው እንደግብ ያስቀመጥነው::
ሁለተኛው ግብ በምርጫው አብላጫ ድምፅ አግኝቶ ማሸነፍ ነው:: ይህም ሁሉም ፓርቲዎች ለውድድር ሲቀርቡ ሲፎካከሩ እናሸንፋለን ብለው ነው የሚነሱት:: በእኛ አገር የመንግስት ሥልጣን ሕዝብ ማገልገያ ሳይሆን መዝረፊያ ሆኖ ስላገለገለ እንጂ የምናሸንፈውም ሆነ ስልጣን የምንይዘው ሕዝብን በቀናነት ለማገልገል አገር ለማሳደግ ነው:: ምርጫ አገርን ወደፊት ለማስቀጠል መሳሪያ በእጅ ማስገባት ማለት ነው::
ዲሞክራሲ በዚህ አገር በሰለጠነ መንገድ እንዲገነባ በተለይ ባለዘርፈ ብዙ የዴሞክራሲ ስርዓት/Multi Democracy System/ ተግባራዊ ማድረግ ነው የብልፅግና ዋነኛ አላማ:: ስለሆነም ለዚህ አላማ ሁሉም ፓርቲዎች አብላጫ ድምፅ አግኝተው መንግስት ለመሆን ይሰራሉ፤ ብልፅግናም በተመሳሳይ አብላጫ ድምፅ አግኝቶ ኢትዮጵያ ወደብልፅግና የምትራመድበትን መሰረት ለመጣል እመረጣለሁ የሚል እምነት ይዞ ነው እየሰራ ያለው::
ያንን ስትራቴጂና እቅድ ይዞ ነው ለመስራት ያቀደው:: ግን ይሄ የምርጫው ውጤት ነው የሚወስነው:: ዝግጅታችንን ጀምረናል፤ ግን የዘንድሮውን ስራ የሚያቃልልን አምና ብዙውን ዝግጅት ማጠናቀቅ በመቻላችን ነው:: አሁን የቀረን አምና የሰራናቸውን ስራዎች ከዘንድሮ ሁኔታ ጋር ማጣጣም ነው:: በመሆኑም ምርጫ ቦርድ በሚያመጣው የጊዜ ሰሌዳ አማካኝነት የሕዝብን ይሁንታ ለማግኘት ዝግጅቶችን እያደረግን ነው ያለነው::
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ ጊዜዎትን ሰውተው ከእኛ ጋር ቃለምልልስ በማድረግዎ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ
አቶ ብናልፍ፡- እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ::
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 03 /2013