ሙሉቀን ታደገ
ከአጼዎቹ ዘመን ማክተም ጋር ተያይዞ ፍትህ ለኢትዮጵያውያን ይገባቸዋል የሚሉ ኃይላት ቁጥራቸው ቀላል አልነበረም። የወታደራዊ የደርግ መንግሥትም የአጼ ኃይለሥላሴን ፈላጭ ቆራጭነትን በመቃወም መሬት ለአራሹ፣ ኢትዮጵያ ትቅደም ያለምንም ደም ወዘተ ሲል ለሰማ ከአሁን በኋላ ለኢትዮጵያውያን በሁሉም ረገድ ተስፋ የሚደረግበት አስተዳደር ሊመሰረት ነው የሚል አመለካከት የብዙ ኢትዮጵያውያን ግምት ነበር።
ነገር ግን ሁሉም ነገር በጅምር ቆመና እንኳንስ በኢትዮጵያ የተስፋ ብርሃን ወጋገን ሊታይ ይቅር እና ደመና የበዛበት የሐምሌ ሌሊት ዓይነት ድቅድቅ ጨለማ ኢትዮጵያን ወረሳት። በዚህም ድቅድቅ ጨለማ ፍትህን ፍለጋ የሚጋልቡ ወጣቶች በጨለማው ውስጥ ባሉ ነፍጥ ባነገቡ አውሬዎች ተበሉ።
ይህን ድቅድቅ ጨለማ አጥፍቼ ፍትሀዊነትን አመጣለሁ ያለው ህወሓት መራሹ ግንባር ኢህአዴግም በህልም እንጂ በእውን ልናየው የማንችለው ቅዠት የሚመስል ከደርግ መንግሥት በባሰ ፍትህን በድቅድቅ የዋሻ ጨለማ ውስጥ ጨመራት። በዚህም የፍትህን የስሟን ትርጓሜ እንኳን እስኪጠፋን ድረስ ፍትህ ተደፍጥጣ ተቀበረች። በመሆኑም ፍትህ ፈላጊዎች ፍትህን ሲፈልጉ ቀን ቀንን ሲወልድ ፍትህን ሳያገኙ ፍትህን እንደተራቧት እስከወዲያኛው ላይመለሱ የአለፉ ኢትዮጵያውያን እልፍ ናቸው።
ፍትህን ፈልገው ፍትህን እንደተጠሙ መፍትሔ ፍለጋ ላይ ታች ብለው የደከማቸው ዜጎች በርካታ ሲሆኑ፤ በዚህ ጽሑፍ የእነዚህን ዜጎች ውጣውረድ በተመለከተ ለማሳያ የሚሆኑ የአንድ ግለሰብ ታሪክ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
አቶ ዲሮ ዲርባ ይባላሉ። በአሁኑ ሰዓት በኦሮሚያ ክልል በአምቦ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ፤ በቀድሞው የከፋ ክፍለ ሀገር ጅማ አውራጃ የትምህርት ቤቶች ጽሕፈት ቤት የንብረት እና የዕቃ ግዢ ኃላፊ ነበሩ። አቶ ዲሮ ዲርባ በቀድሞው የከፋ ክፍለ ሀገር በጅማ አውራጃ የትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት የንብረት እና የዕቃ ግዢ ኃላፊ በነበሩበት ወቅት በ1977 ዓ.ም በተቀነባበረ እና በተደራጀ ሐሰተኛ ክስ ለተለያዩ ከአእምሮ በላይ ለሆኑ የከፉ ችግሮች ተጋልጫለሁ በማለት ቅሬታቸውን አቅርበዋል። ቅሬታ አቅራቢውም ከ1977 ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም እስከመጣው ለውጥ ድረስ ለ192 ጊዜ ለተለያዩ መንግሥት አካላት አቤት ቢሉም አጥጋቢ መልስ ባለማግኘታቸው ሕዝብ ይፍረደኝ ሲሉ አቤት ብለዋል።
ከዚህ በፊት ቅሬታ አቅራቢው ለተለያዩ የህትመት እና የኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ብዙኃን ቅሬታቸውን ቢያቀርቡም መፍትሔ ባለማግኘታቸው ወደ ዝግጅት ክፍላችን ቀርበው ደርሶብኛል የሚሉትን የፍትህ መጓደል አስረድተውናል።
እኛም ለውድ አንባቢያን አቶ ዲሮ ያቀረቡትን አቤቱታ ግራ ቀኙን ተመልክታችሁ የእራሳችሁን ፍርድ (ብይን) ትሰጡ ዘንድ በማሰብ የቅሬታ አቅራቢውን እሮሮ እንደሚከተለው በወፍ በረር ቃኝተነዋል።
የቅሬታው መነሻ
«ከልጅነቴ ጀምሮ ከምመኛቸው ምኞቶቼ መካከል በምሰራበት በማንኛውም የሥራ መስክ ሁሉ ባለኝ ችሎታ በትጋት እና በታማኝነት እየሰራሁ ለራሴም ሆነ ለምሰራበት ድርጅት አጥጋቢ ውጤት በማስመዝገብ ለሀገሬ እድገት እና ብልፅግና የበኩሌን በማበርከት ልጆችን ወልጄ፤ ለልጆቼ ጥሩ አባት መሆን እፈልግ ነበር» በማለት የሚናገሩት ባለታሪኩ ፤
ነገር ግን «ያልታደለ ከንፈር ሳይሳም ያረጃል» እንዲሉ ከልጅነቴ ጀምሮ እመኛቸው የነበሩት ምኞቶቼ የመንግሥትን ገንዘብ እንደፈለጉ ሲመዘብሩ በኖሩ የበላይ አለቆቼ ተንኮላሸ። ነገሩ እንዲህ ነው ፤ አቶ ዲሮ በቀድሞው የከፋ ክፍለ ሀገር በጅማ አውራጃ የትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት የንብረት እና የዕቃ ግዢ ኃላፊ ነበሩ። በዚህ በተሰጠ ኃላፊነታቸው መሠረት ጅማ አውራጃ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማሩ ሂደት የተቃና ይሆን ዘንድ የተለያዩ ቁሳቁሶችን የሚገዙት ሕጉን ተከትለው በጨረታ ከመንግሥት ዕቃ አቅራቢ ድርጅቶች ነበር።
ይሁን እና እኔ ወደዚህ መስሪያ ቤት ከመምጣቴ በፊት የነበሩ የሥራ ባልደረባዎቼ እንደፈለጉ ዕቃዎችን በመግዛት እና በማጭበር የመንግሥትን ሀብት ሲዘርፉ ስለነበሩ እና እኔ በዚህ ቦታ ከመጣሁ ጊዜ ጀምሮ ይህን ስርቆታቸውን ማስቀጠል ባለመቻለቸው ጥርሳቸውን ሲነክሱብኝ ኖረው አንድ ቀን አንድ ሰነድ ከእኔ በመስረቅ እና በማጭበርበር የ2ሺ 7መቶ ብር ከ63ሳንቲም የኦዲት ጉድለት አለብህ በማለት ያለ ምግባሬ ስም ሰጥተው በሥራዬ ላይ እንቅፋት ሆኑብኝ። በዚህም በ28/1 /1977 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ከሥራ ገበታዬ መታገዴ ተገለጸልኝ ሲሉ ያስረዳሉ።
በዚህም እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሬ በ1977 ዓ.ም አገራችን በከፍተኛ ረሃብ በተጠቃችበት ዘመን ያለ አግባብ ከደመወዝ እና ከሥራ ታግጄ በአሰቃቂ የረሃብ አደጋ ላይ ወደኩ። ከደመወዜ እና ከሥራዬ የታገድኩት በተሰጠኝ ኃላፊነት እና እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የመንግሥትን እና የሕዝብን ገንዘብ ከምዝበራ ለመታደግ ዘብ በመቆሜ ነበር። መንግሥት የጣለብኝን ኃላፊነት እንዳላጓደልኩ እና ሥራዬ የሚጠይቀውን ትክክለኛውን መስመር ተከትዬ እየሰራሁ መሆኑን የሚገልጽ አሳማኝ የሆነ ማስረጃ ማቅረብ እችላለሁ።
የተመሰረተብኝም ክስ ሐሰት መሆኑን በማስረጃ እንዳሳይ ይፈቀድልኝ። ደመወዜም በወቅቱ ተለቆልኝ እኔ እና ቤተሰቦቼን የነፍስ አድን ሥራ ይሰራልኝ ብዬ ለተለያዩ በላይ ሹሞች ቅሬታዬን አቀረብኩ። በተለያዩ የበላይ ሹሞችም የነፍስ አድን ጥሬዬን ተከትለው ወደ ሥራዬ እንድመለስ የተለያዩ ውሳኔዎችን ቢያስተላልፉም ከታች ያሉ ሹሞች ከላይ የሚተላለፈውን ውሳኔ የቋጥኝ ድንጋይ እየጫኑበት ስለሚጨፈልቁት የሚከተሉት አሰቃቂ ችግሮች እና በደሎች እንደደረሱባቸው ይናገራሉ።
አንደኛ፡- በወቅቱ በሀገራችን በድርቅ ሳቢያ ረሃብ የተከሰተበት ዓመት በመሆኑ ምግብን ጨምሮ የመሠረታዊ ፍላጎቶች ዋጋቸው የማይቀመስ ነበር። በዚህም ከመሞት ለመትረፍ ቤታችን ውስጥ ያለንን ዕቃ በመሸጥ ረሃባችንን ማስታገስ ሞከርን። ነገር ግን የሚሸጥ ቤት ዕቃ ሲጠፋ ቤተሰቤ ለረሃብ ተጋለጠ። በወቅቱ ባለቤቴ የ3 ወር አራስ ነበረች። የሚላስ የሚቀመስ በቤታችን በመጥፋቱ ባለቤቴ ወደ ገጠር ዘመዶቻችን እንድትሄድ አደረኩ። ይሁን እንጂ ይህን የረሃብ አለንጋ መቋቋም ያልቻለው አራስ ልጄ በረሃብ ምክንያት በአንድ ዓመቱ ሞተብኝ ። በረሃብ ልጄ ሲሞት ሳይ አምርሬ አለቀስኩ። ቅስሜም ክፉኛ ተሰበረ።
ሁለተኛ፡- ከቤተሰቦቼ ያመጣኋት እህቴ የዓመቱን ፈተና ለማጠናቀቅ ሁለት ወር ሲቀራት ረሀቡን መቋቋም ስላቃታት የምትወደውን ትምህርት ለማቋረጥ ተገደደች። «የወደቀ እንጨት ምሳር ይበዛበታል» እንዲሉ በዚህ አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ በፖሊስ ተይዤ ቀጠሮ እየተጠየቀብኝ ቀለብ በማይሰጥበት የፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ለ30 ቀናት ታሰርኩ። በእስር እንዳለሁ ስንቅ የሚያቀርብልኝ ወገን በማጣቴ ስንቅ ያላቸውን እስረኞችን እግር እና ካልሲ እያጠብኩ ከእነሱ በማገኛት ፍርፋሪ እና ከውስጡ ተበልቶ የተጣለን የሙዝ ልጣጭ በመብላት ለጊዜው ሕይወቴ ቢተርፍም ከዘለቄታው የሥነልቦና እና አካላዊ ጉዳት እንዲሁም ከአሳፋሪ ውርደት ግን ባለመዳኔ የሚሰማኝ ህመም ዛሬም ውስጤን ክፉኛ እንዳቆሰለው ነው።
ሦስተኛ፡- ለስምንት ተከታታይ ዓመታት የአገልግሎት እርከን በተዛባ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ አልፎኛል።
አራተኛ፡- በማንኛውም የደረጃ እድገት እንዳልሳተፍ ተደርጓል።
አምስተኛ፡- እንደ ሥራ ባልደረቦቼ በማህበር ተደራጅቼ ቤት እንዳልሰራ ተከልክያለሁ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለሚመለከታቸው አካላት አቤት በማለቴ ከ 11 ወር በኋላ ወደ ሥራ ገበታዬ እንድመለስ ከበላይ አካላት የሥልጣን እርከኑን፣ ሕግን እና መመሪያን ተመርኩዞ ለበታች ባለሥልጣናት ትዕዛዝ ተላለፈ። ነገር ግን የተላለፈውን ውሳኔ ለማጓተት በዝርፊያ የተማሩት የሥራ ባልደረቦቼ የሐሰት ክስ በመክሰስ በፍርድ ቤት ለ8 ዓመታት ከተከራከርኩ በኋላ የሰራሁት ምንም ዓይነት ጥፋት ባለመኖሩ የካቲት 11 / 1984 በዋለው ችሎት በፍርድ ቤት ውሳኔ ነፃ ተባልኩ ይላሉ አቶ ዲሮ።
ፍርድ ቤቱ በወሰነው ውሳኔ መሠረትም ያለአግባብ ላወጣሁት የጠበቃ ወጪም ጭምር እንዲከፈለኝ ተወሰነልኝ የሚሉት አቶ ዲሮ፤ ለ8 ዓመታት በሐሰት መንገላታቴ እና ልጄን በረሃብ በማጣቴ ይቅርታ ተጠይቄ ለተጎዳሁት ጉዳት ካሳ መከፈል ሲገባኝ ከፍርድ በኋላም ወደ መደበኛ ሥራዬ በመመለስ በመደቡ የሚገባኝን ደመወዝ መክፈል ሲገባቸው ከነበረኝ የሥራ መደብ አውርደው ጊዜያዊ ሥራ ሰጥተው አስቀመጡኝ።
በዚህም ለጊዜው ከሞት ጥላ ስር አንድ እርምጃ ብርቅም በተገቢው ሥራዬ ባለመመደቤ ማግኘት የነበረብኝን ደመወዝ ማግኘት አልቻልኩም። በበደል ላይ በደልም ተፈጸመብኝ። ይህን የበደል በደል አቤቱታ ለማመልከት የማውቀውን ሁሉ ቢሮ እረግጫለሁ ሲሉ አቶ ዲሮ በኀዘን ስሜት ውስጥ ሆነው ያስረዳሉ።
በመጨረሻም የተፈጸመብኝን በደል አቤት ለማለት ወደ አዲስ አበባ መጥቼ በ1984 ዓ.ም የሽግግር መንግሥቱ ምክትል የትምህርት ሚኒስትር ለሆኑት ዶክተር በየነ ጴጥሮስ 1 መቶ 31ኛ የሆነውን አቤቱታዬን አቀረብኩ የሚሉት አቶ ዲሮ፤ ዶክተር በየነ ጴጥሮስም የተፈፀመብኝን ግፍ በመረዳት እና የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በማጤን ለኢሉባቡር አስተዳደር አካባቢ ጽሕፈት ቤት እና ለኢሉባቡር አስተዳደር አካባቢ የፋይናንስ መምሪያ የሚከተለውን ውሳኔ አስተላለፉ ሲሉ ያስረዳሉ።
አንደኛ፡- በፍርድ ቤት የተወሰነላቸውን ለጠበቃ
ያወጡትን ወጪ በሙሉ እንዲከፈለኝ።
ሁለተኛ፡- በዚሁ ክስ ምክንያት የተዘለለውን የአገልግሎት እርከን ጭማሪ ቢኖር ተጣርቶ ሲረጋገጥ ሊስተካከልልኝ እንደሚገባ እና በዚሁ ክስ ምክንያት ከደንብ እና መመሪያ ውጪ ከሥራ በመታገዴ ተመላሽ የተደረገብኝን ደመወዝ ተጣርቶ እንዲከፈለኝ ተወስኗል። ይህም ከ1985 ዓ.ም ከበጀት ውስጥ ውጪ ሆኖ ሊከፈለኝ እንደሚገባና ለወደ ፊቱም ከደንብ እና መመሪያ ውጪ በቂነቱ ባልተረጋገጠ መረጃ ሠራተኞችን ከሥራ የማገዱ ሁኔታ ላይ ብርቱ ጥንቃቄ እንዲደረግ በ3/13/1884 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ ውሳኔ ተላልፎላቸው እንደነበር ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ ይህን ግልፅ እና ፍትሃዊ ትዕዛዝ በፍርድ ቤት ነፃ ከወጣሁ በኋላ የተላለፈልኝ ወሳኝ የበላይ አካል ትዕዛዝ ቢሆንም የበታች ሹማምንቶች በእኔ ላይ በነበራቸው ጥላቻ የተላለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ ሊደረጉት አልቻሉም። እዚህ ላይ አቶ ዲሮ የሚሉት ነገር ምንድን ነው፤ እኔ ፍትህ ተጓደለብኝ ብዬ አቤት ባልኩ ጊዜ ለ8 ዓመታት አንድም ቀን ግድ ያልሰጠው እና ጆሮውን ክፍት አድርጎ በደሌን ለመስማት ፈቃደኛ ያልነበረው የከፋ አስተዳደር ከትምህርት ሚኒስትሩ ውሳኔ መልዕክት ይዤ በሄድኩ ሰዓት ግን የሚኒስትሩን ውሳኔ በመቃወም የኔን ጥቅም ለማሳጣት ሲሆን፤ በስድስት ቀን ውስጥ የሚኒስትሩን ትዕዛዝ የሚያጥፍ ውሳኔ ደረሰኝ። በዚህም ክፉኛ አዘንኩ፤ ፈጣሪዬን አማረርኩ። ነገር ግን ፍትህን ሳላገኝ ተስፋ መቁረጥ የሚታሰብ አይደለም የሚሉት አቶ ዲሮ፤ ለ132ኛ ጊዜ ለጅማ ዞን አስተዳዳሪ ለነበሩት አቶ ሙክታር እንድሪስ የፍትህ ተጓደለብኝ አቤቱታቸውን አቤት አሉ።
‹‹ለግፍ እና ለበደል ብቻ የተፈጠርኩ በመሆኔ በ1997 ዓ.ም በጂማ ቴ/ሙ/ት/ሥ/ኮሌጅ የመዋቅር ለውጥ እና ድልድል ሲመጣ መስፈርቱን የሚያሟሉ ተወዳድረው ማለፍ ይችላሉ የሚል መመሪያ ስለወጣ እና እኔም መመሪያውን ስለማሟላ ለወጣው ሥራ ተወዳደርኩ:: ነገር ግን በተለያዩ ተጽዕኖዎች ምክንያት አድሎ ስለተፈጸመብኝ ለመዋቅር ድልድሉ እንዳልወዳደር ተከለከልኩ›› ይላሉ። ‹‹በዚህም የሚገባኝን እድገት በመነጠቄ ለጅማ ዞን አስተዳደር ለነበሩት ለአቶ ሙክታር እንድሪስ ለ132ኛ ጊዜ አቤቱታን አቀረብኩ። በዚህም ሁለት የጅማ ዞን መዋቅር እና ድልድል ኃላፊዎች አቶ ሙክታር ቢሮ ድረስ በማቅረብ የተሰራው ድልድል እኔን የሚመለከት እና በስህተት ድልድሉ ውስጥ ያልተካተትኩት እንደሆነ ለአቶ ሙክታር አስረድተው በድልድሉ እና በመዋቅር ሥራው የእኔን በማካተት እንደሚስተካከል ቃል ገቡ። ይህን ተከትሎ የዞኑ አስተዳዳሪ ወደ ቦታዬ እንድመለስ ለዞኑ የትምህርት ጽሕፈት ቤት ትዕዛዝ ቢያስተላልፉም ቅሉ ትዕዛዙን ለመቀበል ግን የዞን የትምህርት ጽሕፈት ቤት ፈቃደኛ አልሆነም›› ሲሉ የደረሰባቸውን በደል አስረድተዋል።
በመሆኑም እንደዚህ ዓይነቱን የፍትህ መጓደል ለመቅረፍ የኢፌዴሪ የሕዝብ የእንባ ጠባቂ ተቋም በአዋጅ ቁጥር 211/92 በተሰጠው ሥልጣን እና ተግባር መሠረት ዜጎች ተፈፀመብን የሚሉትን አስተዳደራዊ በደሎችን ተቀብሎ በመመርመር ተገቢውን መፍትሄ ሐሳብ ይሰጣል የሚለውን ያዩት አቶ ዲሮ፤ በዚህ ተቋም መመስረት ደስ ተሰኝተው የደረሰባቸውን በደል አቤት ለማለት በ22/02/06 ዓ.ም ወደ ተቋሙ በማምራት ከ1977 ዓ.ም ጀምሮ የተፈፀሙባቸውን በደሎች ለተቋሙ አቤት አሉ። ይሁን እንጂ ከልፋት በስተቀር ለሌላ አልተፈጠርኩም የሚሉት አቶ ዲሮ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ የእንባ ጠባቂ ተቋም ያቀረበኩትን አቤቱታ ደረጃውን ጠብቆ ለኮሚሽኑ ከተጻፈ በኋላ በዚሁ ትዕዛዝ መሠረት ተገቢውን ውሳኔ ማግኘት ሲገባው አንድ የበታች የሕዝብ የእንባ ጠባቂ የመስሪያ ቤት ኃላፊ በደል ካደረሱብኝ የጅማ ቴ/ሙ/ት/ሥ/ኮሌጅ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የጥቅም ኔትወርክ በመፍጠር የፌዴራሉ የሕዝብ የእንባ ጠባቂ ተቋም በሰጠው አቅጣጫ ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ጉዳዩ የሥልጣን ዕዝ ሰንሰለቱን አልጠበቀም በማለት አቤቱታዬን እንዲሁ ተድበስብሶ እንዲቀር በማድረግ ተገቢ ያልሆነ የውሳኔ ሳይሰጡበት ቀረ። በመሆኑም የዕዝ ሰንሰለቱን ጠብቆ ይሂድ በተባለው መሠረት በኦሮ/ቅ/ጽ ቤት በኩል በአዋጁ መሠረት ይግባኝ ብጠይቅም አሁንም ምንም ዓይነት የፍትህን ሽታ እንዳላገኙ ይናገራሉ።
አሁን ላይ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ አገራችን በጉልበት የምትመራበት ጊዜ አብቅቷል። የግለሰቦች ብሎም የቡድኖች በደል ለማዳመጥ የሚያስችል መንግሥት አሠራር ለመዘርጋት ጅምሮች እንዳለ አምናለሁ። ስለሆነም በተደጋጋሚ የጠየኩት አቤቱታዬ ምን አልባት ፍትህ ያገኛል የሚል ተስፋ አለኝ ሲሉ አቶ ዲሮ ጠቁመዋል። ከ35 ዓመታት በላይ የቆየውን በደሌን ክብደት እና እውነተኛነት አይተው ከተረዱልኝ፤ በዚህ ምድር ላይ እንደ እኔ ተበድለው ፍርድ አጥተው ለተጨነቁ ሰዎች የሀገር መሪዎች ሁሉ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እግዚአብሔር ራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ 31÷8-9 ላይ ያስቀመጠውን ቃል (ትዕዛዝ) እና በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም አንቀፅ፡ 37 ላይ የተቀመጠውን የሕገ መንግሥታዊ ሕግ ተግባራዊ እንደሚያደርጉልኝ በማመን እና ሁሌም በንግግራቸው መጨረሻ ላይ የፈጣሪን ስም ሳይጠሩ ንግግራቸውን እንደሚያጠናቅቁ በተደጋገሚ ስላየሁ፤ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረብዎት እና ፈጣሪ ለፈጠራቸው ሰዎች አላግባብ በደል ሲፈጸምባቸው ዝም ብለው አያዩም ብዬ ስለማስብ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በ30/12/2013 ዓ.ም ለ1 መቶ 92 ኛ እና ለመጨረሻ ጊዜ የአቤቱታ ደብዳቤ አስገባሁ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም የተፈፀመብኝን በደል ተረድተው ችግሬን ይቀርፉልኛል የሚል ተስፋ አለኝ።
ለአቤቱታ ተስፋ ያለመቁረጣቸው ምስጢር
አቶ ዲሮ እንደሚሉት የተፈጸመባቸውን በደሎች አቤት ለማለት እና የደረሱባቸው ሰቆቃዎች ለሕዝብ ለማሳወቅ ያልሄዱበት የለም ቢባል ይቀላል። ከመንግሥት ባለሥልጣናት እስከ ሚዲያዎች ተንከራተዋል። አቶ ዲሮ ለአቤቱታ የደረሱባቸውን የመገናኛ ብዙኃንን ለአብነት ብንመለከት ለቪኦኤ የአማርኛ ክፍል፣ ዶቼ ቬሌ፣ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣ ለኢትዮጵያ ሬዲዮ ድርጅት፣ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድርጅት፣ ለሬዲዮ ፋና ፣ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጅማ ቅርንጫፍ፣ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጅማ ቅ/መ/ቤት፣ ለሪፖርተር ጋዜጣ እና ሌሎች።
በእርግጥ ተፈጥሮ በምታስከትላቸው እና በተለያዩ ምክንያቶች በድህነት ተቀፍድደው በየደግሱ ቤት የድግስ ዕቃ በማመላለስ ረሃባቸውን ለማስታገስ እንደሚቀላውጡት እና አንዳንድ ጊዜም በየድግስ ቤቱ የቱንም ያህል ሥራ ቢሰሩም በድግስ ቤቱ ክብር አጥተው ሊጥ እንደ ደፋች ውሻ በፍልጥ ባልቀጠቀጥም እና በየድግሱ ቤት እንኳን የመቀላወጥ አቅም አጥተው በየመንገድ ዳሩ ወድቀው በተስፋ መቁረጥ መሞታቸውን ብቻ የሚጠባበቁ እና ከሞቱ በኋላ እሬሳቸው በከተማው ማዘጋጃ ቤት ተለቅመው በአንድ ጉድጓድ ውስጥ ከአንድ በላይ ሆነው የሚቀበሩ በርካታ ችግርተኞችን እያየሁ እኔ እፅናና ይሆናል ሲሉ ይናገራሉ።
ነገር ግን የኔ ችግር ተፈጥሮ ያስከተለችብኝ ወይም ባልታወቀ ምክንያት የመጣብኝ ችግር ሳይሆን ለእኔም ሆነ ለመስሪያ ቤቱ ይጠቅማል በሚል እና የመንግሥትን እና የሕዝብን ንብረት ከዝርፊያ በተከላከልኩ የመንግሥት እና የሕዝብን ሀብት የሚዘርፉ እና የሕዝብን እና ሀገራቸውን አደራ ፈፅመው በረሱ፤ ለዘረፋ በተደራጁ ቢሮክራቶች እና ሕገ ወጦች በደረሰብኝ በደል ለበላይ መስሪያ ቤቶች ያቀርብኩት አቤቱታ ተግባራዊ ምላሽ በማጣቱ ከዛሬ ነገ፤ ከዘንድሮው የመጪው ዓመት ለበደሌ ምላሽ የሚሆን አጥጋቢ እና ቁርጥ ያለ ውሳኔ አገኛለሁ እያልኩ ያለ የሌለ ጥረቴን ሁሉ ለአቤቱታ ጨርሼ አንዳችም ውሳኔ ሳላገኝ ሞራሌ እንደወደቀ ለጡረታ መድረሴ እንደ እግር እሳት ስላንገበገበኝ እና እንዴት ይህን ያህል ፍትህን ፍለጋ ኳትኜ ፤ ከላይ ከታች ወጥቼ እና ወርጄ ፤ ስንት እና ስንት ከአእምሮ በላይ ለሆኑ ችግሮች ተጋልጬ አንድ ውሳኔ ሳላገኝ ፍትህን በጨለማ ዋሻ ውስጥ እንዳለች አበባ ለማግኘት እንደሚያንጋጥጥ ሰው ፍትህ ከእኔ እርቃኝ በደሌን ተሸክሜ ለምን ወደ መቃብር እወርዳለሁ የሚል እልህ ውስጥ ገብቼ እንደ እብድ ውሻ ወዲያ እና ወዲህ ለአቤቱታ መንከራተቱ ስላደኸየኝ እንጂ ተፈጥሮ በሚያስከትለው በሀገር የመጣ ችግር በተፈጠረ የመጣብኝ ድህነት ቢሆን ኖሮ ችግሩን ከመቋቋም በስተቀር እንዲህ የሚያስጨንቀኝ ጉዳይ አይሆንም ነበር።
በግፍ ከደረሰብኝ ሰው ሰራሽ ችግር በመላቀቅ ቤተሰቦቼን በሥርዓት ለማስተዳደር እና በጥቅሉ ከሕግ ውጪ የተገፈፍኩትን መብቴን ለማስከበር ያልፈነቀልኩት ድንጋይ እና ያላደረኩት ጥረት የለም። ይሁን እንጂ ተበዳይ መብቱን ማስከበር የሚችለው በደሉን በየደረጃው በሚያቀርባቸው አቤቱታዎች መሠረት ከላይ ወደታች የሚተላለፉ መመሪያዎችን እና ሕግን መሠረት ያደረጉ የበላይ ትዕዛዞች ከታች ባሉ የመንግሥትን መዋቅር እንደ ምስጥ እየቦረቦሩ የመንግሥትን መመሪያ እና ፖሊሲዎች በአግባቡ እንዳይተገበሩ ሲታትሩ ይታያሉ። እኔ ላይ የደረሰው በደል ይላሉ አቶ ዲሮ፤ የበላይ አካላትን ትዕዛዝ ለመፈጸም ፍላጎት ባነሳቸው ከሕግ የበላይነት ይልቅ የእራሳቸውን ጥቅም ባስቀደሙ የበታች አመራሮች በመሆኑ ነገሩ ፍትህን በተስፋ ለሚናፍቁ ዜጎች ተስፋ የሚያስቆርጥ እና ጨርቅ አስጥሎ የሚያሳብድ ተግባር ነው በእኔ የደረሰው።
አንዳንዴ ለእግዚአብሔር፣ በሌላ ጊዜ ለሀገሪቱ እርሰ ብሔር እና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ወዘተ የሚጻፈው አቤቱታ ምን ያህል ከባድ ሆኖ ነው? ወይስ ሥራ ፈት ሰው ነው ዘወትር እያሾፈ የሚያስቸግረን እስቲ እንየው ሌላ ተልዕኮ ይኖረው ይሆን? በሚል ስሜት እንኳን ተገፋፍተው ችግሬን ለማወቅ ያህል አንድ ጥያቄ የሚሰነዝር ሰው ወይም ተቋም ከተገኘ በዚያው ሰበብ እግረ መንገዳቸውን በዚህ አቤቱታ የተነሳ ስለ ደረሰብኝ አስከፊ ችግር እና ዛሬም ልጆቼን ለማስተማር አይደለም የዕለት ጉርስ ለማጉረስ አቅቶኝ ያለሁበትን ሁኔታ እና ስላሳለፍኳቸው የስቃይ ኑሮ ጊዜያት ይረዱልኝ ይሆናል በሚል ነው። የበላይ ባለሥልጣኖች ወይም ጋዜጠኞች ችግሬን ከተረዱኝ እና አቤቱታዬ እውነትን የተከተለ እና በቀላሉ ለመረዳት የሚቻል በመሆኑ ለአቤቱታዬ ሁነኛ እና ጥብቅ ማንም የበታች ሹም እንደፈለገ የማይሽረው ከሆነ ልጆቼ ቢያነስ እንኳን በረሀብ አለንጋ ከመገረፍ ወጥተው አንድ የተሻለ ነገር ይኖራቸዋል በሚል ተስፋ ነው።
በአጠቃላይ ተስፋ ሳልቆርጥ ለዓመታት አቤቱታዬን ለተለያዩ አካላት ያቀረብኩበት ዋነው ምስጢር
አንደኛ፡- መብታቸውን ትክክል ባልሆነ መንገድ የተነጠቁ ሰዎች መብታቸውን ለማስጠበቅ የትኛውንም ዓይነት ዋጋ መክፈል እንዳለባቸው ለማሳየት ነው።
ሁለተኛ፡- መንግሥት የእኔን ጥያቄ በአግባቡ የሚመልስ ከሆነ በአሁኑ ሰዓት ለሚገኙ ወጣቶች እና ሕፃናት ሕዝብ የሰጣቸውን ኃላፊነት በትክክል በመመሪያው እና በሕጉ ሲፈፅሙ የትኛውንም ዓይነት በደል ቢደርስባቸውም ለሚፈጸምባቸው ማንናቸውም ዓይነት የፍትህ መጓደል መንግሥት አፋጣኝ እና ሚዛናዊ ውሳኔ መስጠት የሚችል ከሆነ ወጣቶቹ በመንግሥታቸው መተማመን እንዲጎለብቱ ለማድረግ ነው።
ለመንግሥት እንዲፈፅምልኝ የምጠይቀው ነገር
አንደኛ፡- ያለፉት የመንግሥት የበላይ ባለሥልጣናት እና በፍርድ ቤት ተወስኖልኝ ነገር ግን በበታች ሹሞች እስከ ልጅ ማጣት ያሳደረብኝን በደል በመገንዘብ መንግሥት ካሳ እንዲከፍለኝ።
ሁለተኛ፡- የበላይ አካላት እና ፍርድ ቤት የተላለፉትን ውሳኔዎች ነገር ግን በበታች የመንግሥት ሹሞች ትዕዛዝን ባለመቀበላቸው የደረጃ እድገቶች እኔን በማለፋቸው አሁን ጡረታ በወጣሁበት ሰዓት ለጡረታ ክፍያ ማነስ በዋናነት የሚጠቀስ ምክንያት ነው። በዚህም የምትሰጠኝ የጡረታ ገንዘብ ማነስ ጋር በተፈጠረ ችግር አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ ቤተሰቦቼ ለችግር በመዳረጋችን እና ለረሀብ በመጋለጣታችን ሕይወትን ለማስቀጠል ተስኖናል።
የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ምላሽ
የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ቶላ በሪሶ እንደሚሉት፤ ለውጡ ከመጣበት ጊዜ አንስቶ ለኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ የቀረበ ምንም ዓይነት አቤቱታ የለም። ነገር ግን ለውጡ ይዟቸው ከመጡት አንዱ የዜጎችን አቤቱታ ከስር መሰረቱ በማዳመጥ አፋጣኝ እና ሁነኛ መፍትሄ መስጠት ነው። ስለሆነም አቤቱታ ያቀረቡት ሰው ለሚዲያ ከመሄዳቸው በፊት ወደ ኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ቢመጡ በተሻለ ደረጃ ፍትህ እንደሚያገኙ አምናለሁ ብለዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 30/2013