ራስወርቅ ሙሉጌታ
ለአዲስ አበቤ ነዋሪ አውራ ጎዳና ዳርቻና በየመናፈሻው ተኝተው የሚውሉ ሕፃናት ልጆችን ማየት አዲስ አይደለም። እነዚሁ ልጆች ረፈድ ፈድ ሲል ደግሞ በየገንዳው ምግባቸውን ከውሻ እየተናጠቁ ሲበሉ ማየትም የየዕለት ትእይንት ነው፤ ከስድስት ሰዓት በኋላ ደግሞ ግማሾቹ የራሳቸውን ሱስ ለመሸፈን ቀሪዎቹ ደግሞ በሌሊት ከሚደርስባቸው የተለያዩ በደሎች ራሳቸውን ለመታደግ በጎረምሶች ታዘው በየመኪናው ስር እየተሯሯጡና በየአስፋለቱ ዳርቻ እየቆሙ ይለምናሉ።
ከነዚህ ሕፃናት ልጆች መካከል ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል በጎዳና ተወልደው የሚያድጉ ሳይሆኑ በተለያየ ምክንያት በተለይም በቤተሰብ መፍረስ በየቀኑ የጎዳና ሕይወትን የሚቀላቀሉ ናቸው። እንደ መንግሥት፤ እንደ ግብረሰናይ ድርጅትም ሆነ እንደ ግለሰብ አንድን ልጅ ከጎዳና ሕይወት ከማላቀቅ ይልቅ ጎዳናን እንዳይቀላቀል ማድረግ አዋጭም ተመራጭም ቢሆንም በዚህ ረገድ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ግን ብዙ ጊዜ ውጤታማ ሲሆኑ አይታይም።
ሌላው ቀርቶ የመንግሥትን ለመንግሥት የግብረ ሰናይ ድርጅቶችንም ሥራ ለራሳቸው ትተን እንደ አንድ ግለሰብ፤ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በአቅራቢያችን ላሉ እጃችንን ብንዘረጋ እንደ ሀገር ለውጥ ልናመጣ መቻላችንን እንኳ ስንቶቻችን ግንዛቤ እንዳለን አይታወቅም። ይህም ሆኖ «ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም» እንዲሉ አንዳንዶች ምንም ምክንያት ምንም መነሻ ሳይፈልጉ የማይደፈረውን ደፍረው ባለቻቸው አቅም ሰዎችን ከመከራና ከእንግልት ሲታደጉ ይታያሉ።
ወይዘሮ መቅደስ አበጀሁ ትባላለች የተወለደችው አዲስ አበባ ቢሆንም አራት ዓመት እስኪሆናት የኖረችው አፋር ክልል ነው። አራት ዓመት ሲሞላት በእናትና አባቷ መለያየት ምክንያት ወደ አዲስ አበባ በማቅናት ኑሮዋን የእናቷ ወንድም ጋር ታደርጋለች። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የልጅነት ዘመኗ በፈተና የተሞላ እንደነበር ትናገራለች። የአባት ያህል የምትወዳቸው አጎቷ በጣም ጥሩ ሰው ቢሆኑም በሥራ ምክንያት ይኖሩ የነበረው ከአዲስ አበባ ውጪ በመሆኑ ሕይወት ለመቅደስ አስቸጋሪ ይሆንባትና በርካታ መከራዎችን ለማሳለፍ ትገደዳለች።
ከጊዜ በኋላም ወደ እናቷ ጋር በመመለስ ጨርቆስ አካባቢ መኖር ትጀምራለች እዚያም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በፈለገ ዮርዳኖስና ወንድማማች እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃ በሽመልስ ሀብቴ ተምራለች። ያሰበችውን ያህል ባይሳካላትም የአስራ ስድስት ዓመት ልጅ እያለች ጀምሮ ሕይወትን ለማሸነፍ አራት ጊዜ ያህል በተለያዩ አረብ ሀገራት በመሄድ ስትሰራ ቆይታለች።
እነዚህ የሕይወት ተሞክሮዎች መቅደስን በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር በእናት ጉያ በአባት እቅፍ ማደግ እንዳለባቸው እንድታምን አድርገዋታል። እናም በሕይወት አጋጣሚ አጠገቧ እናትና አባታቸውን ያጡ የቲም ልጆች ሲገጥሟት እናትም አባትም ሆና ለማሳደግ እጇን ዘርግታ ለመቀበል ትበቃለች።
ከሦስት ዓመት በፊት ነበር ቡልጋርያ ከሚባለው አካባቢ በልማት ከተነሱት መካከል አንድ ቤተሰብ እነሱ ይኖሩበት የነበረው የቀበሌ ቤቶች ያሉበት ግቢ ውስጥ መጥተው መኖር የጀመሩት። መቅደስና እናቷም ከአዲሶቹ ቤተሰቦች ጋር ቀን ቀንን እየወለደ ሲመጣ ጉርብትናቸውም መግባባታቸውም እየተጠናከረ ይመጣና እንደ ቤተሰብ መተያየት ይጀምራሉ።
በተለይም መቅደስ የቅዱስ ገብርኤልን ወርሃዊ በዓል ታዘክር ስለነበር በየወሩ እየመጣች ሥራ ከምትረዳት ጎረቤቷ ጋር ያላት ቁርኝት ከጉርብትና ባለፈ መረዳዳትንም መደጋገፍንም ያካተተ ነበር። መቅደስ በራሷ ግምገማ ጎረቤቷ በተወሰነ ደረጃ ኑሮዋ ችግር የጎበኘው እንደሆነ ብትረዳም ጣልቃ ለመግባት ግን አልደፈረችም ነበር።
መቅደስ በኋላ እንዳረጋገጠችው የልጆቹ አባት ጎበዝ ታታሪ ሠራተኛ ጥሩ ሞያ የነበረውና በስሩም ሰዎችን ቀጥሮ ያሰራ የነበረ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ የገጠመው የእእምሮ መታወክ ግን ሥራ ከማስፈታት አልፎ ለበርካታ ችግሮች ዳርጎት ነበር። አንዳንድ ቀን መንገድ ላይ ታሞ ይወድቃል እቤት አምጥተውት ቆይቶ ካገገመ በኋላ ደግሞ ተመልሶ ይወጣና በተመሳሳይ ችግር ይመለሳል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እቤትም ሲሆን አውቆም ባይሆን ቤተሰቡን የሚረብሹ ነገሮችን ይፈጽም ነበር።
ትንሽ ቀለል ሲለው ደግሞ እንደሱ ቤተሰቡን የሚንከባከብ አልነበረም ሌላው ቀርቶ ለአራስ ባለቤቱ ከገንፎ ጀምሮ ምግብ ያዘጋጅ ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ ነበር ሦስተኛው ልጅ ገና የስድስት ወር ሕፃን እያለ ነበር አባታቸው እንደ ቀልድ ከቤት ወጥቶ የውሃ ሽታ ሆኖ የቀረው።
ከጊዜ በኋላ ደግሞ ጻድቃኔ ማርያም አካባቢ ታይቷል የሚል ዜና ለእናትየው ይደርሳታል። መስከረም ሲጠባ ልጆቹም ትምህርት ሲጀምሩ ክረምቱም ሲወጣ ወደዚያው በማቅናት ባሏን ለማየት ዝግጅቷን አጠናቃ ለጎረቤትም ልጆቿን እንዲጠብቁላት ቃል አስገብታ እያለ ነበር ያልታሰበው ዱብ ዕዳ የደረሰው። በዕለቱ የተፈጠረውን ነገር መቅደስ እንዲህ ታስታውሰዋለች።
ነሐሴ አስራ ስድስት ቀን ረፋድ ላይ ረቡዕ ዕለት የነአብርሃም እናት ኪዳነ ምህረት ንግስ አንግሳ ወደ ቤቷ ስትመለስ ከቀኑ አምስት ሰዓት አካባቢ እበር ላይ ከመቅደስ ጋር ተገናኝተው ሰላምታ ተሰጣጥተው ማታ እንደሚገናኙ ተነጋግረው ይለያያሉ። መቅደስ አገር ሰላም ብላ ቆይታ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ተኩል ላይ ወደ ቤቷ ስትመለስ እመቤት ወድቃለች ይሏታል። ነገሩ ቀላል የመሰላት መቅደስ ጸበል ምናምን አደረጋችሁላት እያለች ወድልጆቹ እናት ስትጠጋ እመቤት ዓይኗን ጨፍና ተኝታለች።
መቅደስ ጠጋ ብላ ካየቻት በኋላ አልነቃ ስትላት መኪና አስጠርታ በቅርብ ወዳለ ጤና ጣቢያ ትወስዳታለች። እዚያ ስትደርስ ግን «ሴትየዋ ሕይወቷ አልፏል ይዘሻት የመጣሽው ከሞተች በኋላ ነው» ሲሉ ፈጽሞ ያላሰበችውን አስደንጋጭ ነገር ይነግሯታል። መቅደስ ከዚህ በፊት የሞተ ሰው አይታ ስለማታውቅና እመቤትም ሰውነቷ ይዝለፈለፍ ስለነበርና ሙቀት ስለነበራት ማመን ትቸገራለች። ቤቱ የጣውላ ቤት ነው ሴራሚክ ቢሆን ነፍስ ለማጥፋት ይበቃል በዚያ ላይ ከአንድ አሮጌ የሽቦ አልጋ በቀር ብዙ ዕቃ እንኳን የለም።
አንዴት ይሄ ሊሆን ይችላል የሚል ሀሳብ ስለመጣባት ምን አልባት የተመረዘ ነገር በልታ ከሆነ በሚል አስክሬኑ እንዲመረመር ጥያቄ ታቀርባለች። ትንሽ ከተከራከሯት በኋላ የአስክሬን ምርመራ ተደርጎ ምንም ፍንጭ ሳይገኝ ይቀራል። እናም እመቤትን የሚያውቋት ጓደኞቿና ዘመዶች ደብረ ብርሃን አካባቢ ሀገሯ ወስደን እንቀብራታለን ይላሉ። መቅደስ ይህንን ውሳኔያቸውን ብትቀበልም ለቀብር ግን ከእነሱ ጋር ለመሄድ ፈቃደኛ አልነበረችም ምክንያቷ ደግሞ እነዛ አለሁ ባይ ጠያቂ የሌላቸውን ልጆች ለማን ትቼ የሚል ነበር። ሄደው ገጠር እንዳያስቀሯቸው የሚል ስጋትም ስለነበራት ልጆቹንም እንዳይሄዱ ታደርጋለች።
እመቤት አፍሪካ ህብረት ውስጥ የቀን እስራ በመስራት ነበር ሦስት ልጆቿን ብቻዋን የምታሳድገው። በግቢው አምስት አባወራ ያለ ቢሆንም ጥሩ ቀረቤታ የነበራትና ችግሯንም ታዋያቸው የነበረው ለመቅደስ እናት ብቻ ነበር። የመጨረሻውን ልጇን እንኳን የወለደችው ካለ አዋላጅ ብቻዋን እቤት ውስጥ ነበር። ከወለደች በኋላ ነበር የመቅደስ እናት ሰምተው ወደ ጤና ጣቢያ የወሰዷት። በዚያ ላይ ከሰው ጋር እንኳን ከተነጋገረች ለሰው መልስ አትሰጥም ይልቁንም ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ ነበር ጊዜዋን የምታሳልፈው።
እናም ይህንን ሁሉ ችግሯን ትረዳት የነበረችው መቅደስ በዚያ በጭንቅ ሰዓት ካለ ማንም ጠያቂ ልጆቹን በኃላፊነት ለመያዝ ለራሷ ቃል ትገባለች። እናም ዛሬ የብዙዎች መፈክር እንደሆነው ሳይሆን መቅደስ ከተረፋት ላይ ሳይሆን ካላት ላይ በመስጠት እነዚህን የቲም ልጆች ለመታደግ ትወስንና ካላት ገንዘብ፣ ካላት ጊዜ፣ ካላት ፍቅር ጭምር ሰውታ ድርብ ቤተሰብ ይዛ መኖር ትጀምራለች። ልጆቹም በብቸኝነት ተውጠው በእናታቸው ሞት ኀዘን በተያዙበት ወቅት ካጠገባቸው ያልተለየቻቸው በመሆኗ መቅደስን የሚያዩዋት ልክ እንደ እናታቸው ሲሆን ትንሹ ልጅ ቅዱስ ግን ዛሬም ድረስ ሙሉ ለሙሉ እናቱ እሷ መሆኗን አምኖ ተቀብሏል።
ከቀብር መልስ ልጆቹን በተመለከተ የተለያዩ ሀሳቦች መቅረብ ይጀምራሉ የመጀመሪያው ለድርጅት ይሰጡ የሚል ነበር ሴቷን ልጅ ብቻ ነጥሎ ለመውሰድም ጥያቄ ያቀረቡ ነበሩ። መቅደስ ግን ሁሉንም ሳትቀበል ትቀራለች፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ልጆቹ ተነጣጥለው ፍቅር አጥተው ማደግ የለባቸውም፤ ሁለተኛም ልጆቹ ለድርጅትም ተሰጡ ለግለሰብ ቤታቸውን መልቀቃቸው አይቀርም።
የትም ቢሄዱ አስራ ስምንት ዓመት ከሞላቸው በኋላ ለብቻቸው እንዲኖሩ ይገደዳሉ፤ የቀበሌ ቤት ደግሞ አንዴ ከለቀቁት በኋላ ሊያገኙት አይችሉም፤ በዚህ ዘመን ደግሞ ያለቤት መኖር ለማንም ይከብዳል። ስለዚህ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም አልፌ ብሆን ልጆቹን ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሄዋን ማድረስ አለብኝ። ከምንም በላይ ደግሞ የእናትና አባታቸው ቅርስ የሆነውን ዞሮ መግቢያ ቤታቸውን ሊያጡ ስለማይገባ የተቻለኝን አደርጋለሁ ብላ ትወስናለች።
ይህን ሀሳቧን ይዛ ወደ እናቷ ታመራለች ወትሮም ሆዳቸው ሲባባ የነበረው እናትም ያለማንገራገር ሃሳቧን ይቀበሏታል። ለባሏም ይሄንኑ ሀሳቧን ታጋራዋለች፤ ለደግ ሥራ ከጎንሽ ካልቆምኩ ለመቼ ልሆን ነው ብሎ እሱም በሙሉ ልብ ይቀበላታል፤ ለምትሰራውም ሥራ ድጋፉም እንደማይለያት ቃል ይገባላታል። ይህም ሆኖ ከአካባቢው ሰውና ከሌሎች ሰዎች ግን ብዙ ተቃውሞዎች ነበሩባት ግማሹ ለራሷ ምን አላትና ነው ሦስት ልጅ የምታሳድገው መለመኛ ለማድረግ ካልሆነ ሲል፤ ቀሪው ደግሞ ያቺኑ የቀበሌ ቤት ልትበላ ፈልጋ ነው ይላታል።
መቅደስ ግን ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም እንዲሉ ለሁሉም ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ጉዞዋን ትቀጥላለች። መጀመሪያ ያደረገችው የእናታቸውን የእህት ልጅ ከደብረ ብርሃን በማምጣት ልጆቹ አስራ ስምንት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ቤቱን በሞግዚትነት እንድትቀበል ማድረግ ነበር።
ለሦስቱም በኦሮሚያ ባንክ ዝግ አካውንት የከፈተችላቸው ሲሆን ትንሽ ትንሽ ቁጠባም እየተቀመጠላቸው ይገኛል። በዚህ ጊዜ ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ ወረዳ ይሰሩ የነበሩ ሰዎች ትብብር አልተለያትም ነበር በተለይ አንድ ነጋሽ የሚባል የወረዳው ሠራተኛ በፍርድ ቤት ስም ከማዛወር ጀምሮ በርካታ ድጋፎችን ሲያደርግላት ቆይቷል። ይህም ሆኖ ዛሬም ድረስ የሚቃወሟት ዛሬም የሚጠረጥሯት አሉ።
የለቅሶ ወቅት ካለፈ በኋላ ግን ነገሮች እየተወሳሰቡ መምጣት ጀመሩ፤ የሦስት ልጆች ቀለብ በየቀኑ የሚጠብቀው መቅደስን ነው፤ ትንሹ ልጅ ደግሞ አራስ እንደ መሆኑ ከዳይፐር ጀምሮ በርካታ ነገሮች ያስፈልጉታል። በወቅቱ ወደ ሚድያ ለመውጣት ብትሞክርም ነገሮች ቀላል አልሆን ይላሉ ጆሮ የሚሰጣትም ታጣለች። ነገር ግን በፊት የምትሰራበት ድርጅት አሰሪዎችና አብራቸው ማህበር የምትጠጣ ጓደኞቿ እንዲሁም የቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ግን ሊተዋት አልፈለጉም፤ ከሀሳብ እስከ ቁሳቁስ የቻሉትን ሲያደርጉላት ቆይተዋል።
በዚህ ሁሉ ጉዞ ግን ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ አልነበሩም ብዙ ውጣ ውረዶች ነበሩ ከሁሉም በላይ ግን በአንድ አጋጣሚ ትንሹ ልጅ ላይ ደርሶ የነበረው ነገር ክፉኛ አስደንግጧት ነበር። አንድ ቀን ሴቷ ልጅ ቡና ለማፍላት እሳት አያይዛ ስትጠብቅ ሕፃኑ እሳቱን ይነካውና ጣቱን ያቃጥለዋል። በወቅቱ ወደ ጤና ጣቢያ ይዛው ሄዳ ህክምና ያገኘ ቢሆንም ትንሽ ቆይቶ ግን ጣቱ ተጣብቆ ይቀራል እናም ወደ የካቲት ሆስፒታል በመሄድ ቀዶ ጥገና ተደርጎለት ለመዳን ይበቃል።
በወቅቱ ግን መቅደስ እሱ ላይ የደረሰው ችግር ከሚያሳስባት ባልተናነሰ ከአንዳንድ ሰው ልጇ ስላልሆነ ስላልጠበቀችው ነው በሚል ይወራ የነበረው ሀሜት ይረብሻት እንደነበር ታስታውሳለች። መቅደስ ከአዲሱ ቤተሰቧ ጋር ሁለት ቤት እየመራች ያለፈውን ሦስት ዓመት በዚህ ሁኔታ አሳልፋለች። እናት አባታቸውን ያጡትም ልጆች ከመበታተን ድነው ዛሬ አብርሃም አስራ ስድስት ዓመቱ ሲሆን የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነው፤ አርሴማ አስራ ሁለት ዓመት ሆኗት ስድስተኛ ክፍል ቅዱስ ደግሞ አራት ዓመት ሞልቶት ለቅድመ መደበኛ ትምህርት እየተዘጋጀ ይገኛል።
መቅደስም ከጥቂት ዓመታት በኋላ ቢያንስ ሁለቱ ራሳቸውን እንደሚችሉ ተስፋ ሰንቃ ተቀምጣለች። መቅደስ የአብራኳ ክፋይ የሆነች የአምስት ዓመት ልጅ ያለቻት ሲሆን እሷም ራሷን እንደ አራት ልጅ እናት ታያለች እነሱም እርስ በእርሳቸው እንደ አራት እህትና ወንድማማቾች ይተያያሉ።
ብዙ ነገር ላይሟላላቸው ይችላል ግን ያለንን ተካፍለን እንበላለን ከምንም በላይ ሦስቱም በአንድ ላይ መኖራቸው ግን ለእኔ ትልቅ ድል ነው የምትለው መቅደስ እኔ ብቻዬን በመሆኔ ብዙ መከራ አሳልፌያለሁ የማዋየው ሰው እንኳን በወቅቱ ሁሌም አጠገቤ ወንድም ወይንም እህት በኖረኝ እል ነበር። ዛሬ በአቅሜ እኔ ያሳለፍኩት ችግር በእነዚህ ልጆች ላይ እንዳይደገም ለማድረግ በመቻሌ ትልቅ እፎይታ ይሰማኛል ትላለች።
በቅርቡ ታሪካቸው ኢትዮ ኢንፎ በተባለ አንድ የዩቲብ ቻናል ለሕዝብ ከቀረበ በኋላ ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገላቸው በመሆኑ በርካታ ነገሮች እየቀለሉላት እንደመጡ የምትናገረው መቅደስ፤ ሰውን ለመርዳት ትርፍ ብር አልያም ትርፍ ጊዜ ሳይሆን ቀናነት ብቻውን በቂ እንደሆነ የራሷን ተሞክሮ በማንሳት ትናገራለች።
አዲስ ዘመን ህዳር 30/2013