መንግሥት ከብዙ ትዕግስትና ሆደ ሰፊነት በኋላ ሕግ የማስከበሩን ሥራ በፍጥነትና በማያዳግም ሁኔታ በስኬት አጠናቋል። ዘመቻው መንግሥት በአስገዳጅ ሁኔታ የገባበት፤ ችግሩም የሀገር ሉአላዊነትን አደጋ ውስጥ የሚከት መሆኑ፣ መላው ሕዝብ ከመንግሥት ጎን ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ በመቆም በርግጥም ኢትዮጵያውያን በሀገር ጉዳይ እንደማይደራደሩ በተጨባጭ ያሳየ ክስተት ነው።
የህወሓት ጁንታው ከእኔና ከእኔ ውጭ ስለ ትግራይ ህዝብ ሊያስብ የሚችል ሌላ አካል በምድር የለም፤ አለሁም ቢል ከእኔ እውቅና ውጭ ሕልውና ሊኖረው አይችልም። ሊኖር ከቻለም ሊኖር የሚችለው በመቃብሬ ላይ ነው በሚል ጊዜ ባለፈበት የሻገተ አስተሳሰብ ላለፉት 50 ዓመታት የትግራይን ህዝብ ያለ አማራጭ በአስገዳጅ ምርጫ ውስጥ እንዲኖር አድርጓል።
የትግራይ ህዝብ ስለ ነፃነት፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ትግል ከጀመረበት 1967 ዓ.ም ጀምሮ ይህ ጁንታ የትግራይን ህዝብ ጨምሮ ለመላው የሀገሪቱ ህዝቦች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ልዕልና ለመታገል ወደ ክልሉ የገቡ የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖችን በሴራ በማጥፋት ራሱን ለትግራይ ህዝብ አልፋና ኦሜጋ አድርጎ ሲቆጥር ቆይቷል።
ጁንታው ስለ ነፃነት፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ብዙ ባዜመባቸው ባለፉት 27 ዓመታት ጭምር የትግራይ ህዝብ አማራጭ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን እንዳያገኝ በማድረግ በከበደ ጭቆና እና አፈና ውስጥ እንዲኖር አድርጎታል። የትግራይ ህዝብ ከፍ ያለ ዋጋ ስለከፈለበት ነፃነት ፣ ፍትህ እና ዴሞክራሲ መናገርና ማሰብ እንዳይችልም አድርጎት ቆይቷል።
የጁንታው አባላት በትግራይ ህዝብ ስም እየማሉና እየተገዘቱ በተደራጀ መልኩ የህዝብና የመንግሥት ሀብት ዘረፋው በሀብት ማማ ላይ በተቀመጡበት፤ የሚይዙትና የሚጨብጡት ጠፍቷቸው ከፍ ባለ መፋነን ውስጥ በገቡባቸው ዓመታቶች ሳይቀር የትግራይ ህዝብ በነፃነትና በዴሞክራሲ ስም በለኮሱት ጦርነት ካስከፈሉት የከፋ ዋጋ ሳያገግም ዓመታትን በቁዘማ እንዲያሳልፍ ሆኗል።
የትግራይ ህዝብ በአንድ በኩል ልጆቹን ከገበረበት የትጥቅ ትግል ቢያንስ ልጆቹ የሞቱለትን የዴሞክራሲና የነፃነት ሕይወት መኖር ሳይችል በነፃነትና በዴሞክራሲ ስም የከፋ የነፃነት እጦት፤ የከፋ አፈናና የመብት ጥሰት ውስጥ ለመኖር የተገደደ ህዝብ ነው። በሌላ በኩል እነዚህ ጥቂት ጁንታዎች ህዝቡ እንደ ህዝብ የተጠቀመ እስኪመስል ድረስ በመላው ህዝብ ውስጥ የተሳሳተ ምስል እንዲሳል በማድረግ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነውበት ቆይተዋል።
ይህ ህዝብ ባለፉት 27 ዓመታት በስሙ እየተገጠመና እየተዜመ ጭፈራውና ዳንኪራው ከልክ በላይ በሆነበት ወቅት፣ በአብዛኛው ሕይወቱ በድጎማና በዕርዳታ ላይ የተመሰረተ እንደነበር የአደባባይ ሚስጥር ነው። የክልሉ ህዝብ የሴፍቲኔት ስንዴ እየተሰፈረለት አንገቱን ደፍቶ የሚታደገው እየጠበቀ የኖረ ነው።
ይህ ሁሉ ግፍ ሳያንሰው የወደደውን ማሰብና ያሰበውን መኖር እንዳይችል ከላይ እስከታች በተዋቀረው የደህንነት መዋቅር ፋታ በሌለው ግምገማና ግራ መጋባት በልጆቹ የመስዋዕትነት ደም ተስፋ ያደረገውን ዘመን ለማሳለፍ የተገደደ፤ በክልሉ በሚገኙ በግልጽ በሚታወቁና በማይታወቁ እስር ቤቶች ልጆቹ ብዙ መከራና ስቃይ እንዲያዩ የተደረገ ህዝብ ነው።
በትጥቅ ትግሉ ወቅትም ሆነ በጁንታው የከፋ አገዛዝ ሰፊ ቁጥር ያለው የትግራይ ህዝብ ለአካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ተዳርጓል፤ በዚህም ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቦቻቸውም ሸክም ለመሆን የተገደዱ ቁጥራቸው በቀላሉ የሚገመቱ አይደሉም። ከዚህ የሚከፋው ደግሞ ይህ ህዝብ ከሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች ጋር በፍቅርና በወንድማማችነት እንዳይኖር በጁንታው የተሠራው ነው።
በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር፣ በቀደሙት ዘመናት ከሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች ጋር በፍቅርና በወንድማማችነት ለረጀም ዘመን አብሮ የተጓዘ፤ በክፉም በደግም ከሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች ጋር ዕጣ ፈንታው ተለይቶ የማያውቀውን የትግራይ ህዝብ ለመነጠል፤ በጥርጣሬ እንዲታይና እንዲገለል ለማድረግ ጁንታው የሄደበት ርቀት አጭር አይደለም።
መንግሥት ተገዶም ቢሆን የገባበት የሕግ ማስከበር ዘመቻ በመሰረታዊነት ሕግን የማስከበር ተልዕኮ ቢኖረውም ስኬቱ ግን እነዚህን ሁሉ በትግራይ ህዝብ ላይ የተጫኑ ጭነቶችን የማራገፍና የትግራይ ህዝብ ልጆቹን እና የልጅ ልጆቹን ህይወት በመስዋዕትነት የከፈለበትን የነፃነት፣ የፍትህና የዴሞክራሲ ሥርዓት ትሩፋት የሚያቋድሰው እንደሚሆን ይታመናል።
አሁን ላይ በክልሉ እየተካሄደ ያለው መልሶ ግንባታ ስናስብም ይህንን ሙሉ እውነታ ታሳቢ ማድረግ ካልቻልን፤ ብዙ መስዕዋትነት የጠየቀውን ሕግ የማስከበር ዘመቻ ትርጉሙ ጎደሎ ያደርገዋል። ጉድለቱ ደግሞ የትግራይ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የነገ ተስፋ ላይ የሚኖረው አዎንታዊ ተጽዕኖ ቀላል ሊሆን አይችልም።
ጁንታው በትግራይ ህዝብ ላይ ያደረሰው በደልና ግፍ በሉዓላዊነታችን ላይ የተካሄደ የከፋ ጥቃት እንደሆነ ከማንም የሚሰወር አይደለም። ይህንን ህዝብ ከዓመታት ከተጫነበት አስከፊ ቀንበር ተላቆ ቀና ብሎ በኢትዮጵያዊ ማንነቱ እንዲሄድ ማስቻል የሁሉም ሀገር ወዳድ ኃላፊነት ነው።
የሕግ ማስከበሩ ዘመቻ በአጭር ጊዜ በስኬት እንዲጠናቀቅ መላው ህዝብ ያሳየውን አጋርነት ለትግራይ ህዝብ ድጋፍም በመድገም ባለፉት 50 ዓመታት በህዝቡ ላይ የደረሰው በደልና እንግልት፤ ግፍና ስቃይ እስከወዲያኛው እንዲያበቃ በማድረግ ሊሆን ይገባል። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት በቂና ከበቂም በላይ ነው።አዲስ ዘመን ህዳር 30/2013
አዲስ ዘመን ህዳር 30/2013