መላኩ ኤሮሴ
የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው በወቅቱ የግብዓቶች አቅርቦትን የማረጋገጥ ሥራ ነው። በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚካሄዱ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች 60 በመቶ የግብዓት አቅርቦት የማረጋገጥ ሥራ መሆኑን በዘርፉ የተሰሩ ጥናቶች ያመለክታሉ። የግብዓት አቅርቦትን በበቂ ሁኔታ ማረጋገጥ መቻል የአንድን የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት አብዛኛውን ሥራ እንደመሥራት ይቆጠራል።
ሆኖም በኢትዮጵያ ውስጥ ዘርፉን ጠፍንገው ከያዙት ችግሮች ውስጥ የግብዓቶች እጥረት በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ነው። የሀገር ውስጥ የግንባታ ግብዓት አቅርቦት የፍላጎቱን ያህል ባለመሆኑ ከውጭ አገር ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ግብዓቶች መጠን ከፍተኛ ነው።
የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ፍላጎት ዕድገት ምክንያት ከሆኑት መካከል ዋና ዋናዎቹ የኢንቨስትመንት መስፋፋት፣ የአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት እና የነፍስ ወከፍ ገቢ መጨመር፣ የከተሞች መስፋፋት፣ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ዕድገት እና የመንግሥት የመሰረተ ልማት ግንባታ ከዋና ዋናዎቹ መካከል መሆናቸውን የከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚንስቴር የተሰራ ጥናት ያመላክታል።
የተቀናጀ የቤቶች ልማት ፕሮግራም፣ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ፣ ስኳር ልማት ቤቶች ግንባታ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ ቤቶች ግንባታ፣ የኢንዱስትሪ ዞን እና ለፌደራል መንግሥት ቢሮዎች ግንባታ፣ የኮብል ስቶን ንጣፍ ሥራ፣ የትራንስፖርት ችግርን ለመፍታት እየተሰሩ ያሉ የመንገድ ግንባታዎች፣ የግድቦች ግንባታና የውሃ አቅርቦትን ለማሻሻል የተፈፀሙት ተግባራት የግብዓት አቅርቦት እጥረት እንዲከሰቱ ካደረጉት መካከል ሳይጠቀሱ የማይታለፉ ናቸው።
የኮንስትራክሽን ግብዓቶች በሀገር ውስጥ ምርት አቅርቦቱን አስተማማኝ ለማድረግ በተለይም ሲሚንቶ እና የኮንስትራክሽን ብረታ ብረት ምርቶችን በሀገር ውስጥ አቅርቦት ለመሸፈን እና ለማጠናቀቂያ የሚያስፈልጉ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ግብ ተጥሎ ሲሰራ የነበረ ቢሆንም ችግሩ ዛሬም አልተፈታም። የኮንስትራክሽን ግብዓቶች በብዛት ከውጭ አገር እየገቡ ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ። ይህም ከፍተኛ ወጪ እያስወጣ እና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ እያሳጣት ይገኛል።
ለኮንስትራክሽን ሥራ የሚውሉ ግብዓቶች እጥረት ችግሮችን ለመቅረፍ ባለፉት ዓመታት የተደረጉ ውስን ጥረቶች ቢኖሩም ዛሬም የዘርፉ ተግዳሮት ሆኖ ቀጥሏል። በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኮንስትራክሽን ዘርፍ እየተነቃቃ መምጣቱን ተከትሎ የግብዓቶች እጥረት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ይህም ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቁ፤ በማድረግ ፕሮጀክቶች ከታቀደላቸው በጀት በላይ እንዲያስቀምጡ ብሎም ግንባታው በጊዜው ቢጠናቀቅ ባለቤቱ ሊያገኝ የሚችለውን ጥቅም እንዲያጣ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ከሚገኙ ምክንያቶች አንዱ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
በኢትዮጵያ ውስጥ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች እጥረት የዘርፉ ተግዳሮት ሆኖ እንዲቀጥሉ ያደረጉ የተለያዩ መንስኤዎች መኖራቸውን ኮንትራክተሮችና አማካሪዎች ያስረዳሉ። ለዚህ ችግር ተጠቃሽ ከሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮች ውስጥ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ግብዓቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ አለማዋል እና ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪውን ግብዓቶች በሀገር ውስጥ የመተካት ሥራ በተገቢው ሁኔታ አለመሰራት ችግሩ ተባብሶ እንዲቀጥል ሆኗል።
የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንት ኢንጂነር አመሃ ስሜ እንደሚሉት፤ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች በሁለት መንገዶች ይገኛል። አንድም በሀገር ውስጥ ከሚገኝ ተፈጥሮ ሀብት ሲሆን፤ ሁለተኛው ከፋብሪካ የሚገኙ ውጤቶች ናቸው። ከፋብሪካ የሚገኙ ግብዓቶችም እንዲሁ በሁለት መንገድ ይገኛል። አንደኛው በሀገር ውስጥ በሚገኙ ፋብሪካዎች ተመርተው የሚቀርቡ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከውጭ ሀገር የሚመጡ የፋብሪካ ውጤቶች ናቸው።
በሀገር ውስጥ የሚገኘው የተፈጥሮ ሀብትም ሆነ ከሀገር ውስጥና ከውጭ አገራት ፋብሪካዎች የሚገኙ ምርቶች ውስን እና አላቂ ናቸው የሚሉት ኢንጂነር አመሃ፤ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ለዘርፉ የሚውሉ ምን ምን ግብዓቶች እንደሚገኙ ተገቢው ጥናት ተካሂዶ ዘርፉ በሚፈልገው ልክ ሥራ ላይ እየዋለ አይደለም ይላሉ። አንዳንድ በሀገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ ግብዓቶች ከውጭ ይገባሉ። ይህም እጥረቱ እንዲከሰት ምክንያት ከሆኑት መካከል ተጠቃሽ ነው።
በተደጋጋሚ ጊዜ ችግሩን ለመቅረፍ ዕቅድ ተይዞ ቢሰራም ዕቅዱን ለሚያስፈፅሙ አካላት ተገቢው ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ አለመቻሉ ችግሩ ዛሬም ችግር ሆኖ እንዲቀጥል አንዱ መንስኤ መሆኑን ያስረዳሉ።
በዚህም ምክንያት የፋብሪካ ምርት ሆነው ከውጭ የሚቀርቡ ግብዓቶች በሚፈለጉበት ወቅት ተወዳዳሪነትን ባረጋገጠ ዋጋ፤ እንዲሁም የጥራት ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ለማግኘት ፈተና እንደሚሆን የሚያብራሩት ኢንጂነር አመሃ፤ በዚህ ምክንያት በግንባታው ዘርፍ የግብዓት አቅርቦት የጥራት መጓደል እና የዋጋ ንረት እየተስተዋለ ነው ይላሉ።
የኮንስትራክሽን አማካሪ እና መምህር ዶክተር ኢንጂነር ውብሸት ዠቅያለ በበኩላቸው፤ የኮንትራክሽን ግብዓቶች እጥረት ለግንባታ ፕሮጀክቶች መጓተት አንዱ ምክንያት መሆኑን በማንሳት፤ አብዛኞቹ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች በገቢ ምርቶችና በውጭ ምንዛሪ ላይ ጥገኛ መሆኑ የችግሩ አንዱ መንስኤ ነው ይላሉ።
ለዘርፉ የሚያገለግሉ ግብዓቶች ከውጭ የሚመጡ በመሆናቸው ከውጭ ንግድና ከምንዛሪ አቅርቦት ጋር ተያይዞ አንድ እክል በአገር አሊያም በዓለም ደረጃ ሲያጋጥም በሀገር ውስጥ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እጥረት እንደሚያጋጥም ያብራራሉ። ይህ የግብዓቶች አቅርቦት ችግር እንዲከሰት አንዱ መንስኤ መሆኑን ያነሳሉ።
እንደ ዶክተር ኢንጂነር ውብሸት ማብራሪያ፤ የብር የምንዛሪ መጠን ከዶላር አንፃር በየጊዜው እየጨመረ ነው። ይህም ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶች ዋጋ በየጊዜው እንዲንር ብሎም እጥረት እንዲከሰት እያደረገው ይገኛል።
የኮንስትራክሽን ግብዓቶች በአብዛኛው ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቁ መሆናቸውን ያብራሩት ዶክተር ኢንጂነር ውብሸት፤ በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ፋብሪካዎች በሀገር ውስጥ በከፊል ሲሚንቶ እና ቆርቆሮ እያመረቱ ሲሆን ሌሎቹ ግን ሙሉ በሙሉ ከውጭ የሚመጡ ናቸው። ይህ በመሆኑ የኮንስትራክሽን ወጪ እንዲንር ግንባታዎች እንዲጓተት እያደረገው ነው ብለዋል። ይህም የኮንስትራክሽኑ ዘርፍ በልማቱ ላይ ሊጫወት የሚገባ ሚናውን እንዳይጫወት አድርጓል ይላሉ።
ኢንጂነር አመሃ እና ዶክተር ኢንጂነር ውብሸት የግብዓት አቅርቦት ችግርን መቅረፍ ለኮንስትራክሽን ዘርፍ ዕድገት ብሎም ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚኖረው ፋይዳ የላቀ መሆኑን ይስማማሉ። በመሆኑም የግብዓቶችን ችግር የመቅረፍ ሥራ ልዩ ትኩረት የሚሻ ነው።
እንደ ኢንጂነር አመሃ ማብራሪያ፤ በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የግብዓት ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ሥራዎች መሰራት አለበት። በተለይም በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ጥሬ ሀብት አሟጦ መጠቀም ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው። ለዚህም በጥናትና ምርምር ላይ በመመርኮዝ ለችግሩ በጥናት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ መስጠት ተገቢ ነው።
ለኮንስትራክሽን ዘርፍ ግብዓትነት ሊውሉ የሚችሉ ነገር ግን እስካሁን ድረስ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ሀብቶች ዙሪያ ጥናት ማካሄድ፣ መለየትና ጥቅም ላይ እንዲውል ማዘጋጀት የዘርፉ ተዋናዮች በጋራ ሊሰሩ ይገባል ያሉት ኢንጂነር በተለይም በሀገሪቱ ውስጥ እንደ አሸዋ ያሉ ጥሬ ዕቃዎች በበቂ ሁኔታ እያለ የግብዓት እጥረት እንዴት ሊከሰት እንደቻለ ጥናቶችን በማካሄድ የሚመለከታቸው አካላት ችግሩን ለመቅረፍ መሥራት አለባቸው ይላሉ።
ዶክተር ኢንጂነር ውብሸትም የኢንጂነር አመሃን ሀሳብ ያጠናክራሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋለው የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ችግር ለመቅረፍ ሁለት መሰረታዊ መርሆዎች ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ። በመጀመሪያ ደረጃ በአሁኑ ወቅት ከውጭ አገራት እየገባ ያለውንና በሀገር ውስጥ በቀላሉ ሊገኙ በሚችሉ ግብዓቶችን በተመሳሳይ ግብዓቶቹን በመተካት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ።
ለምሳሌ ከውጭ የሚመጣው ለቤት ክዳን የሚያገለግል ቆርቆሮ በከተሞች ውበት ላይ ከሚያስከትለው መዘዝ በተጨማሪ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ስለሚያስወጣ የኮንስትራክሽኑ ኢንዱስትሪ ዕድገት ለሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ዕድገት ሊያበረክት የሚችለውን አስተዋጽኦ የሚገድብ ሆኖ ይገኛል። ይህንኑ አጥንቶ ለቤት ክዳን የሚውል ቆርቆሮ በሸክላ የመተካት ሥራ ቢሠራ የግብዓት እጥረት ችግርን ከመቅረፍ ባሻገር ከተማን ለማስዋብ እና የውጭ ምንዛሬን ለማዳን ይረዳል ይላሉ።
እንደ ኢንጂነር ውብሸት ማብራሪያ፤ ሌላኛው ደግሞ ሊተኮርበት የሚገባው ጉዳይ የገበያውን ሁኔታ እየተከታታሉ ከውጭ የሚገቡትን እና ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቁትን ምርቶች በአገር ውስጥ በተወዳዳሪ ጥራት እና ዋጋ መሥራት የሚቻልበትን ሁኔታ ሊፈጥሩ የሚችሉበትን ጥናት በማድረግ እነዚህን ምርቶች የሚተኩ ፋብሪካዎች በአገር ውስጥ እንዲቋቋሙ መንግሥት በትኩረት መንቀሳቀስ ይኖርታል።
ከዚህ በመነሳት መንግሥት መረጃውን በዘርፉ ሊሰማሩ ለሚችሉ የአገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች በማቅረብ ፋብሪካዎችን እንዲያቋቁሙ ማበረታታት አለበት ያሉት ዶክተር ኢንጂነር ውብሸት፤ በዚህም ዘርፍ ሊሰማሩ ለሚችሉ ግለሰቦች የባንክ ብድር እና አበረታች ሌሎች ሁኔታዎች ማመቻቸት አስፈላጊ መሆኑን ያብራራሉ።
እንደ ዶክተር ኢንጂነር ውብሸት ማብራሪያ፤ ከውጭ እየገቡ ያሉ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የነባር ፋብሪካዎችን የማምረት አቅም አሟጦ መጠቀም፣ ፋብሪካዎች የተለያዩ ችግሮች ያለባቸው በመሆናቸው በተገቢው አግባብ እየደገፉ መሄድ፣ በአገሪቱ ያሉ ፋብሪካዎች አሁንም ከውጭ የሚገባውን በመሸፈን በኩል በቂ ባለመሆናቸው ተጨማሪ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲገቡ ማድረግ ያስፈልጋል።
እነዚህንና መሰል በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እና የአገር ውስጥ አቅምን ለማሳደግ መንግሥት አልሞ እየሠራ መሆኑን በቅርቡ የዘርፉ የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ ላይ በተደረገው ውይይት ላይ የኮንስትራክሽን ሚንስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ገልፀዋል። በዘርፉ በዕቅድ ከተያዙት ተግባራት መካከል በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት 80 በመቶ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ግብዓቶች መተካት አንዱ ነው።
የዘርፉ አንገብጋቢ ችግር የሆነውን የግብዓት አቅርቦት እጥረት ችግርን ለመቅረፍ በዕቅድ መያዙ የሚበረታታ ነው የሚሉት የዘርፉ ባለሙያዎች ዕቅድ ብቻውን ችግሩን ሊቀርፍ አይችልም ብለዋል። በመሆኑም ዕቅዱን መሬት ላይ ለማውረድ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። በየዓመቱ እና በየሩብ ዓመቱ በዚህ ረገድ የተሠሩ ሥራዎች እየተገመገሙ ክፍተቶችን እያሟሉ እና ጥንካሬዎችን እያስቀጠሉ መሄድ ከተቻለ ችግሩን መቅረፍ እንደሚቻል አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 29/2012