ራስወርቅ ሙሉጌታ
የግለሰቦች ውድቀት ድምር በሀገር እድገት ላይ የሚያመጣው የራሱ ተጽእኖ አለው። በአንጻሩ እያንዳንዱ ግለሰብ የተቃና ሕይወት የሚኖር ከሆነ በግለሰቦች ድምር ውጤት ሀገርም የበለጸገች ትሆናለች። ሞኝ ከራሱ ብልህ ከሰው ስህተት ይማራል ይባላል፤ ለመሆኑ ለመማር የግድ መሳሳት አለብን ይሆን? ለመነሳትስ የግድ መውደቅ ይጠበቅብናል? ስንል የማህበራዊ ልማትና አመራር ባለሙያ ከሆኑትና በቲቪ ዘጠኝ የክሊፍ ሞቲቬሽን ወይም አፋፍ ለመድረስ ዝግጅት አዘጋጅና አቅራቢ አቶ ዘላለም ይትባረክ የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው አዘጋጅተናል።
ውድቀት በእጃችን ያለ የምንፈራውና የምናፍርበት ብሎም ያልተጠቀምንበት ነገር ግን ትልቅ አቅምና የስኬት ብቸኛው መሰላል ነው። የውድቀት አቻ ትርጉም ካለመሆን፣ ካለመሳካት፣ ከመሸወድ፣ ከማጣት፣ ከመሳሳት፣ ከመክሰር፣ ከመጎዳት፣ ካለመነሳት ጋር ይዛመዳል። ውድቀትን ከስኬት፤ ስኬትንም ከውድቀት ነጥለን ልንተረጉመው ወይም ልንረዳው አንችልም። የውድቀት መለኪያው ስኬት ሲሆን የስኬት መለኪያውም ውድቀት ነው።
የሰው ልጅ ከሁለት ነገር የተሰራ በሚመስል መልኩ ከስኬት እና ከውድቀት፣ ከመቻል እና ካለመቻል፣ ከማሸነፍ እና ከመሸነፍ፣ ከመሳሳት እና ትክክል ከመሆን ወዘተ በሁለትዮሽ የሚገለጽ ሕይወትና ማንነትን የተጎናጸፈ ነው። ውድቀት ማለት የሙከራ አንደኛው ውጤት ሲሆን አንድን ነገር ለማድረግ ስንጀምር የይሳካል ግምት እንደሚኖር ሁሉ በአንጻሩ መሳሳት ወይም ውድቀት ሌላኛው ተጠባቂ ውጤት ነው።
ይህም ሆኖ ከውድቀት ቀጥሎ ስንጀምር የምንጀምረው ከመጀመሪያው ሳይሆን ከተገኘው ልምድ ሲሆን ካልወደቅን ግን ስላልሞከረን የምንጀምረው ከምንም ይሆናል። በዚህም ውድቀት ተሞክሮ ወይም ልምድን ስላነገበ ወደ ስኬት ለሚደረግ ጉዞ መስፈንጠሪያ በመሆን ያገለግላል።
በተራ ሰዎች እና በስኬታማ ሰዎች መካከል ያለው መሠረታዊ ልዩነት ውድቀትን የሚያዩበት አቅጣጫ እና ለውድቀታቸው ከሚመልሱት ተግባር ይመነጫል። ለምሳሌ ስኬታማ ሰዎች ውድቀትን ካለመፍራታቸው በተጨማሪ ለውድቀት የሚዘጋጁ ሲሆን ለውድቀት ያላቸው ትርጉምም ያልተዛባ ነው። ስለዚህ የሰውን ስኬት ከሚወስኑ አራት ነገራቶች ማለትም ከሰዎች ጋር የሚኖረን ግንኙንት፣ የቡድን ሥራ፣ አመለካከትና የአመራር ብቃት በተጨማሪ ውድቀትን ለስኬት መጠቀም መቻል አንዱ ነው።
ውድቀትን ለስኬታችን ላለመጠቀም ዋናው ምክንያት ስለውድቀት ያለን የተዛባ አመለካከት ሲሆን ከእነዚህም መካከል ከታች የተዘረዘሩት ጥቂቶቹ ናቸው።
ውድቀትን ፈጽሞ የሚወገድ አድርጎ ማሰብ፡-
ሰው ሆኖ ከመሳሳት ሊድን የሚችል የለም። ማንም ሰው ከውድቀት ውጪ የሆነ ሕይወት ፈጽሞ ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ ስኬትን ወይም ድልን ካሰብን የምንሰራው እየወደቅን መሆኑን መዘንጋት የለበትም። ይልቁንም መታሰብ ያለበት ስህተትን ላለመድገም፣ ለመቀነስና ከስህተት ለመማር ብሎም ወድቆ ላለመቅረት ብቻ መሆን አለበት።
ውድቀትን የአንድ ጊዜ ክስተት ማድረግ፡- ውድቀት ልክ እንደስኬት በተለያየ አጋጣሚ በሕይወት ጉዞአችን ላይ የምናስተናግደው ነገር ወይም ሂደት መሆኑን መገንዘብ። የሰው ልጅ ወደ ምድር ከመጣበት ጊዜ አንስቶ እስኪሞት ድረስ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ምክንያቶች እየወደቀ እየተነሳ ማወቅና ከውድቀት በመነሳት ስኬትን ማጣጣም እንደሚቻል ማሰብ።
ውድቀትን እንደጠላት መመልከት፡- የሃይማኖት ተቋማትን መፈጠር ብንመለከት ዋናው ምክንያት የሰው ልጅ በሀጢያት መውደቅ ነው። ስለዚህ የሚረዳን የሚደግፍና መንገድን የሚያሳየን ያገኝንበት ምክንያት የሰው መውደቅ ስለነበረና ስለሚኖርም ነው። ውድቀት የስኬታማ ሰው ወዳጅ እንዲሁም ስለስኬት የሚማርበት መጠቀሚያ ትምህርት ቤቱና እቅዱ ነው። ቶማስ ኤድሰንን አምፖልን ለመፍጠር ከአንድ ሺህ ጊዜ በላይ ሞክሮ አልተሳካለተም። የሚገርመው ግን ለምን ሲባል ‹‹999 ጊዜ እንዴት አምፖል እንደማይሰራ ተምሬበታለሁ›› ሲል መናገሩ ይህንን ሀሳብ ያጠናክርልናል።
ውድቀትን የማይቀለበስ የመጨረሻ ውጤት እንደሆነ አድርጎ መመልከት፡-
ከእያንዳንዱ ሽንፈት ወይንም ስህተት ሊወሰዱ የሚገባቸው ትምህርቶች እንዳሉ መገንዘብና እነሱን ለመለየት ብሎም ለማረም መጣር ይጠበቃል።
የስኬታማ ሰዎች የጋራ መገለጫ
ወደ ፊት መውደቀት
- ኃላፊነት መውሰድ
- ከእያንዳንዱ ስህተት መማር
- ውድቀት ከመሻሻል አንዱ ክፍል መሆኑን ማወቅ
- ቀና አመለካከትን ጠብቆ ማቆየት
- ያለፈባቸው አመለካከቶችን ያለመቀበል እራስን መካድ
- አዲስ አደጋዎችን መጋፈጥ
- አንድ የሞከሩት ነገር እንዳልሰራ ማመን
- ጥረትን መቀጠል
የተራ ሰዎች የጋራ መገለጫ
ወደ ኋላ መውደቅ
- ሌሎችን ተጠያቂ ማድረግ (መውቀስ) ሰበብ መፈለግ
- አንድ ዓይነት ስህተትን መደጋገም አለመማር
- እንደገና አለመወደቅን በፍጹም አለመጠበቅ ፉከራ ከዚህ በኋላ አይደርስ መስሎን
- ውድቀት ሲደርስ ተከታይ ውድቀትን መጠበቅ ተስፋ መቁረጥ፣ በቃ እኔ እኮ ዓይነት ነገር
- ልምዶችን በጭፍን መቀበል
- ባለፉት ስህተቶች ብቻ ተወስኖ መቅረት አለመሞከር
- ውድቀት ውስጥ ያለሁ ሰው ነኝ ብሎ ማሰብ ስለራስ ያለ የተሳሳተ መረዳት
- ጥረትን ማቋረጥ
ስለዚህ ውድቀትን ለስኬት ለመጠቀም በሰዎች የሚሰጡትን አትችልም፣ አይሆንልህም፣ አትረባም፣ ኢ-ተቀባይነት፣ መገለል ወይም መናቅን ችላ ማለት ያስፈልጋል። በተጨማሪም ውድቀትን በጊዜያዊነት መመልከት እና ጥንካሬ ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል። ወደ ውጤት የሚያቀርብን መንገድ ወይም ብልሃት እየቀያየሩ መሞከር። ትናንት ታሪክ ሲሆን ነገ ደግሞ የለም ስለዚህ ዛሬን ስኬታማ ለመሆን ውድቀትን በመቀበልና በመውደድ ከትናንትና ወይም ከቅድም ጋር መታረቅ።
ምንአልባት ውድቀታችን ከራሳችን አልፎ ሌሎችን ሊጎዳ የሚችልበት ከሆነ በመጀመሪያ ለራሳችን ይቅርታ በማድረግ ከመጸጸት መውጣት፤ ቀጥሎ ሌሎችን ይቅርታ በመጠየቅ ስህተትን አለመድገም ብሎም በመካስ አብሮነታችን ማስጠበቅ። ብሎም ዓይናችንን በመክፈት በዙሪያችን ያሉትን ወደ ስኬት የሚያደርሱ ብዙ የውድቀት ሀብቶችን መፈተሽ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ህዳር 29/2012