ግርማ መንግሥቴ
ኪሳችን እንጂ የሳሳው በሥነ ቃልስ የሚስተካከለን ያለ አይመስልም። በዘርፉ ሥር በሚዘረዘሩት ዘውጎቹ ሁሉ ቱጃሮች ነን። ቃል ግጥሙ፣ ተረትና ምሳሌው፣ ዘይቤው፣ አፈታሪኩ፣ ቅኔው ወዘተ ሁሉ በጃችን ሲሆን፤ የሚገርመው ደግሞ ሁሉም የኢትዮጵያ ፍልስፍና መፀነሻዎች ብቻ ሳይሆኑ ማደጊያ፣ መስፋፊያ፣ መግለጫዎች መሆናቸው ነው።
ይህንን ለማረጋገጥ የሚፈልግ ካለ ስነቃላችንን መሰብሰብና ከዕለት ተዕለት ህይወት ጋር በማስተያየት ማመሳከር ነው። በቃ፣ ያኔ ሁሉም እዚያ ውስጥ ተጠቃሎ ያገኘዋል- ልክ እንደ “አንችም ጨካኝ ነበርሽ . . .” ማለት ነው።
ስነቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ቃላዊ ሀብት (ትውፊት) ነው የሚለው አገላለፅ ሥር የሰደደ ይሁን እንጂ ስነቃል አያት ቅድመ አያቶች ያለ የሌለ እውቀታቸውን አንጠፍጥፈው የፈጠሩትና ለፍሬ ያበቁት መልዕክት ማስተላለፊያ፣ ታሪክ መሰነጃ፣ የፍልስፍናችን ቋት፣ የማንነታችን መገለጫ፤ የአስተሳሰባችን፣ አተያያችን፣ ክዋኔያችን፣ ማህበረ-ባህላዊ ዕሴታችን መንፀባረቂያ ወዘተ ቃል-ጥበብ (Oral Art) ሲሆን፤ ይህንንም በአፍሪካ፣ በተለይም በናይጄሪያውያን (ኦጎኒ ማህበረሰብ ስነቃል (Ogoni Folk Tales)) ላይ ጥልቅ ፍተሻን ያደረጉት የአካባቢው ተወላጅ ኬን ሳሮ-ዊዋ ለፈጣሪዎቹና ለትውልድ አስተላላፊዎቹ ተገቢውን ክብር፣ ዋጋና አድናቆት በሚሰጥ መልኩ የአረጋዊያን ጥበብ “elders’ wisdom” ይሉታል። (ለተገቢው ቃል-ጥበቡ ግንዛቤ “The Singing Anthill: Ogoni Folk Tales” ሥራቸውን ያነቧል።) እኛም ይህንኑ መነሻ በማድረግ “ሰው በላ”ንና “አንችም ጨካኝ ነበርሽ . . .”ን ይዘን ተነሳን።
አንድን ጉዳይ ወይም ሀሳብም ሆነ አስተሳሰብ ለሰሚው፣ ተመካሪው፣ ተቀባዩ፣ ታዳሚው ወዘተ በተመቸ (ሊቀበለው በሚያስችል) መልኩ ማስተላለፍ ከተቻለ ማንም ይህን ማድረግ የሚጠላ የለም። ችግሩ ይህን ለማድረግ እራሱን የቻለ አቅምና እውቀት መጠየቁ ነው። እነዚህ አቅሞች ካሉትና መልዕክቱን በእነዚህ አድምቆ ማስተላለፍ ከቻለ ሀሳቡ ማህበራዊ ፋይዳ ያለው ከመሆኑም በላይ ዘመን ተሻጋሪ ለመሆኑ መጠራጠር አይቻልም።
ለዚህም ነው በንጃሚን ፍራንክሊን ሠራተኛነትን በሚያበረታታና ስንፍናን በሚያዳክም መልዕክቱ “Early to bed, early to rise, makes a man healthy, wealthy and wise” (ቶሎ መተኛት፣ ቶሎ መነሣት፣ ሰውን ጤንኛ፣ ባለፀጋና አዋቂ ያደርገዋል።) የተናገረው ዘመናትን ተሻግሮና እየተሻገረም የሚገኘው። በእኛው ዘንድም ይህን መሰል ስነቃል በብዛት አለና በዘርፉ ሀብታም ስለመሆናችን ሌላው ማረጋገጫ ነው።
“አንችም ጨካኝ ነበርሽ …”ም እንዳዛው። በተለይ ተግባሩ አነጋገሩ ወይም የተገለፀበት ብልሀት ሁለት አካላት (በዳይና ተበዳይ፣ አጥቂና ተጠቂ፣ ገዳይና ሟች …)ን ያካተተ ከመሆኑ አኳያ፤ በተለይም በርእዮተ-አለማዊው ዓለም (ፖለቲካም እንበለው – አንዳንድ ምንም አይነት ርእዮት ሳይኖራቸው ዝም ብለው፤ ልፊያ እየመሰላቸውም ይሁን እንጃ፣ ወደ ትግል የሚገቡ አሉና) ቁልፍ ከሆነው የኃይል ግንኙነት (power relation) አኳያ ትርጓሜውም ሆነ ሚናው ከዚህ መለስ የሚባል አይደለምና እዚህ ልንወያይበት ምክንያት ብናደርገው አይከፋም።
በመግቢያችን ላይ ይህን ያህል ከተንደረደርን ወደ ተነሳንበት እንሂድና ሀሳብ እንለዋወጥ፤ ለዚህም ከቃሉ ከ”ጨካኝ” እና “ጨካኝነት” በመጀመር አሁንም ትንሽዬ ማብራሪያ ብጤ እንስጥ።
ሰው በላነት ከጨካኝነት ስለመነሳቱ እስካሁን ምንም አይነት ሙግት የለም። “ጨካኝ”ም ሆነ “ጨካኝነት” አንድ ቤተሰብ ናቸው፤ ይለያያሉ ከተባለም በሰዋሰው ክፍሎቻቸው ሲሆን እሱም፤ ቀዳሚው ቅፅል ቀጣዩ ስም መሆናቸው ነው።
እንኳን አምሳሉ ለሆነው የሰው ልጅ፤ የሰው ልጅ ለእንስሳት (“non-human animal” መባል ከጀመሩ – ሰውም እንስሳ መሆኑን፤ ልዩነቱ ያ “ማሰብ” የሚባለው ነገር መኖሩን (እንስሳት የማያስቡ ከሆነ) ለማመልከት) እንኳን ፍቅር ካልሰጠ (“animal abuse, animal neglect ወይም animal cruelty” ከፈፀመ)፣ ምግብና መጠለያቸውን ካላሟላ ወዘተ እሱ ጨካኝ፤ ተግባሩም የጭካኔ (act of cruelty)፤ ባህርይ/ ሰብእናውም ጨካይነት የተሞላበት መሆኑ ከተረጋገጠ ሰንብቷል።
(በነገራችን ላይ አንድ አንድን እንስሳ በጭካኔ ከጎዳ ሰው፣ ሌላ ሰውን በተመሳሳይ ጭካኔ ከጎዳ ሰው በአምስት እጥፍ፣ ንብረት ከዘረፈ በአራት እጥፍ፣ በተለያዩ ምክንያቶች አካባቢና ማህበረሰብን ከረበሸ ሰው በሦስት እጥፍ የሚቀጣባቸው አገራት መኖራቸውን እናውቃለን? ለምሳሌ ባሌሩስ። ባሌሩስ እጅግ የከፋ የእንስሳት መብት አያያዝ ያለባትና በ2018 ከዓለም 143ኛ መውጣቷ (አሜሪካ 118ኛ) ይታወቃል።) እንኳን በሰው በእስሳትም ጨካኝነት እዚህ ድረስ ያስጠይቃል እያልን ነው።
“ለመሆኑ የጭካኔና ሰው በላነት መናው ምንድን ነው?” ብለን ከጠየቅን የተለያዩ መልሶችን የምናገኝ ሲሆን እንደ ፈላስፋው ፍሬደሪክ ኒች ከሆነ ሰው በተፈጥሮው ጨካኝ ሲሆን፤ እንደ እንግሊዛዊው ፈላስፋ በርትራን ራስል እምነት ደግሞ የጨካኝነት ምንጩ ልክ ያጣ ፍርሀት ነው። ዶስቶቭስኪ፣ ሼከስፒር እና ሌሎች በርካቶችም ጨካኝነትን በሥራዎቻቸው በሚገባ ያሳዩ ሲሆን በሁሉ በኩል ተግባሩ የተወገዘ እንጂ ተወዳጅ ሆኖ አይታይም።
ከአለማዊው አውድ ወጥተን “ጨካኝ”ንም ሆነ “ጨካኝነት”ን ከመንፈሳዊ አንድምታቸው አኳያ ብንመለከታቸው ከእነሱ ጋር በተያያዘ የተለያዩ መጽሐፍ ቅዳሳዊ ጥቅሶችን የምናገኝ ሲሆን ጥቂቶቹን እንደሚከተለው መጥቀስ ይቻላል። (ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ ጭካኔን፣ ችላ ማለትንና የመሳሰሉትን ለመግለጽ በታሪኩ ውስጥ ሁለት የተራቀቁና የረቀቁ ገጸ-ባህሪያትን መጠቀሙን ማስታወስ ተገቢ ሲሆን፤ አቤል /ቃኤል፣ ብርሀን/ጨለማ፣ ሰላም/ጦርነት፣ ፍቅር/ጥላቻ፣ ቀን/ሌሊት፣ ክፋት/ደግነት፣ ሀብታም/ደሀ ወዘተ መጥቀስ ይቻላል።)
ለዚህም (ለምሳሌ ከዘፍጥረት 24:19 በመጥቀስ) ፃድቅን እንደ ደግ፣ ሩህሩህና ቸር፤ ጨካኝን በሰው በላነት የሚጠቅሱ አሉ። ይህን በምሳሌነት የሚጠቅሱ መኖራቸው እንዳለ ሆኖ፤ በዚሁ የፈጣሪ ቃል ውስጥ ያሉት ፍጡራን ተነፃፅረው የሚገኙት በሁለት ተቃራኒ ጎራዎች (አዳምና ሄዋን፤ ቃኤልና አቤል፤ ወዘተ) መሆኑ ለእምነቱ ተከታዮችም ሆነ ለመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪዎች የተሰወረ አይደለም።) በዳይና ጨካኝ በዚህኛው ብቻ ሳይሆን በሌላውም እምነት ተመሳሳይ ስለመሆኑ መጠራጠር አይቻልም።
“ኢየሱስም አባት ሆይ: የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” (ሉቃስ 23:34) የሚለውን እንዳለ ለአንባቢ ትተን በቀጥታ ስለ ጭካኔና ሰው በላነት ተግባር ምን እንደተፈፀመ፡ በማን እንደተፈፀመ፣ ለምን እንደ ተፈፀመ ወዘተ እና በፈጣሪ በኩል ምን ምን እርምጃዎች እንደተወሰዱ እንመለከት። (“እንመልከት” ስንል እንደ አንድ ጸሐፊና አንባቢ እንጂ እንደ ሃይማኖት ሊቅ አለመሆኑን ልብ ይሏል።)
“ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” (ገላትያ 5:14) የሚለው ታላቅ ሕግ እንዳለ ሆኖ (ወይም፣ በሻሪዎች ተሽሮ) “ሰው ማረድ በፈጣሪ ዘንድ ምንድን ያስከትላል?” ብሎ ለሚጠይቅ ማቴዎስ 11:11 ላይ “ጨካኝ የነበረው ንጉሥ ሄሮድስ ሕፃኑን ኢየሱስን ለማጥፋት ባደረገው ሙከራ በቤተልሔምና በአውራጃዋ የሚገኙትን እድሜያቸው ሁለትና ከዚያም በታች የሆናቸውን ወንድ ልጆች ያለ ርኅራኄ እንዲታረዱ አድርጓል።” የሚለውን በማንበብ መረዳት ይችላልና እሱኑ እንጋብዘዋለን።
በምድርም እየሆነ ያለውና እየተሰቃየንም ቢሆን እያየንና እየሰማን ያለነው ይህንኑ አይነት ያለርህራሄ ወንድም ወንድሙን ሲያርድ ነውና ሰው በላነት በገሀድ አለ ማለት ነው። ክፉስ? በምሳሌ 17:11 እንደተገለፀው “ክፉ ሰው አመፅን ብቻ ይፈልጋል፤ በእርሱም ላይ ጨካኝ መልዕክተኛ ይላክበታል።”
ተመሳሳይ ሀሳብ በ”የሐዋሪያ ሥራ 20:26-28”ም ተመልክቶ እናገኛለን። ይህ የሚነግረን ሰው በላነት ዋጋ የሚያስከፍል ሲሆን፤ ከእነ ሂትለር ጀምሮ ስንመለከት የኖርነውም ይህንኑ ነው።
እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት (የማቴዎስ ወንጌል 25:35-40) ሲላቸው ምን ማለት እንደ ሆነ ግልፅ ነው። ግልፅ ነው ስንል የሰው ልጅ ለብጤው ከክፋት ይልቅ ደግነትን፣ ከጭካኔ ይልቅ ርህራሄን ካሳየና ካደረገ እውነትም እሱ የተባረከና በፈጣሪው ዘንድም የተወደደ ነው ማለታችን ነው። ችግሩ “አለ ወይ?” የሚለው ነው። አለ? ካለ ታዲያ ለምን ማይካድራ ላይ አልታየም? (ጥያቄው ይሄ ነው።) ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውሃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም። (የማቴዎስ ወንጌል 10:42) የሚለውንም እንደዚሁ ማሰብና ከጥቅሱም መረዳት ተገቢ ነው እንላለን።
የጨካኝ ተምሳሌት ሆኖ በሃይማኖት በኩል የሚታወቀው ወንድሙን የገደለው ቃል ሲሆን፤ እሱም በሁሉም ዘንድ ከመጠላቱም ባለፈ የእሱ ባህርይ ሁሉ ተምሳሌት እንደሆነ አለ። ለዚህ ደግሞ ተገቢ ማሳያው የሰው ልጅ ለልጁም ሆነ ለወዳጁ ስም ሲያወጣ “አቤል” እንጂ በገዳዩ “ቃኤል” ስያሜ ሲሰይም እስከ ዛሬ በታሪክ አላጋጠመምና ጨካኝነት ይህን ያህል የተጠላና የተወገዘ ነው ማለት ነው። (ሰይጣንም የሰው ልጅ ስም ሆኖ እንደማያውቀው ሁሉ ማለት ነው።)
አማኝ ከዓለም ይልቅ እግዚአብሔርን ይወዳል (1 ዮሐ. 2፡15) የሚለውም ሆነ “ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል።” (ዮሐ 15 18-19) የሚለው ከክፋት፣ ምቀኝነት፣ ተንኮል፣ ጨካኝነት ወዘተ በተቃራኒ የቆሙ አንቀጾች ናቸው። መልዕክታቸውም የሰው ልጅ ከአለማዊነት ማለትም ለገንዘብ፣ ለዝና፣ ለስልጣን … ሲል ሃጢያትን መውደድና መሥራት እንደ ሌለበት ሲሆን፤ ከዚህ ውጭ የሆኑት ግን እንደ ሠሩት መከራና የጭካኔ ተግባር ሁሉ የሚጠብቃቸውም ያውና የባሰ መሆኑ ነው።
(ከበደ ሚካኤል በሥራዎቻቸው ያስተላለፉት መልዕክትም ከዚህ ጋር አብሮ የሚሄድና የሰው ልጅ ከክፋትና ጭካኔ ተግባሩ መለስና ሰከን እንዲል የሚያሳስብ ሲሆን እሱም “ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም / ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም” የሚለውና ከተጠቃሽ የሥነ ግጥም ሥራዎቻቸው ውስጥ አንዱ ነው።)
ካለንበት የከፋ ወቅት አንፃር ለጉዳዩ አፅንኦት ለመስጠት ሲባል ወደ ሃይማኖቱ ባደላ መልኩ ገፋ አድርገን መሄዳችን ግልፅ ነው። ምንም እንኳን ከፀሐፊው ቅርበት አንፃር በአንዱ ላይ እናተኩርና ከእሱም እንጥቀስ እንጂ በየትኛውም ሃይማኖት ጨካኝ እና ጨካኝነትም ሆነ ሰው በላነት የሚደገፍ አይደለም፤ ይልቁንም የሚያስቆጣና የሚያስፀይፍ፤ ከዚያም አልፎ ሃጢያት የሆነ ተግባር እንጂ።
በተለይም “ደመሰስኩት” ያለውን ሥርዓት “ሰው በላው ሥርዓት” ሲል የነበረ አካል ተመልሶ፣ በከፋ ሁኔታ እራሱ ሰው በላ ሆኖ ሲገኝ ከማየት በላይ አሳፋሪና በታሪክም አስጠያቂ ነገር ያለ አይመስልምና ከላይ በታላቁ መጽሐፍ አማካኝነት እንደተመለከትነው የእጁን ያገኛል።
ምንም ጥያቄ የለም፤ አለማችን በርካታ ችግሮችንና የከፉ የጭካኔ ተግባራትን አስተናግዳለች። እነ ኢዲ አሚን ጋጋ፣ ኤመርሰን ምናንጋግዋ አይነት ሰው በላ መሪዎችን ሁሉ አስተናግዳለች። ጦርነቶችንም እንደዛው። ከጦርነቶቹም የከፉት ጦርነቶች አንድ ሁለት ተብለው የሚቆጠሩ ሲሆኑ እነሱም በ1910ዎቹ የተከሰተውና የሰውን ልጅ ያለ ሀጢያቱ ቅርጥፍ አድርጎ የበላው ጦርነት ነው።
ከአፍሪካ ሳይቀር ናይጄሪያ፣ ጋምቤሪያ፣ ሮድዥያ /ዚምባብዌ፣ ሴራሊዮን፣ ኡጋንዳ፣ ኒያስላንድ/ ማላዊ፣ ኬንያ፣ ጎልድ ኮስት እና የመሳሰሉትን አገራት ሳይቀር ያለ ስራቸው ስቦ ያስገባ፤ በድምሩም 55,000 ዜጎቻቸውን ያሳተፉበትና የ10,000 ንፁሃንን ህይወት በመንጠቅ ዋጋ ያስከፈለው አንደኛው የዓለም ጦርነት (ጁላይ 28, 1914 – ኖቬምበር 11, 1918) ፈረንሳይን 5,651,000 ጦሯን አሳትፋ ከ1 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿን፤ ሩሲያ 12,000,000 አሰልፋ 6,650,000 (ከሁሉም አገራት ትልቁ ቁጥር)፤ በጥቅሉ አለማችን ከ15 ሚሊዮን በላይ የሞቱበት እና ከ20 ሚሊዮን በላይ የተጎዱበት ጦርነት ሲሆን፤ ከዚህ ጦርነት ማንም ምንም ሳይማር በመቅረቱ፤ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት (1932 ዓ.ም. እስከ 1937 ዓ.ም) ተከተለና እሱም በተራው በጠቅላላው የ70 ሚልዮን ሕዝብ ህይወትን ቅርጥፍ አድርጎ ተሰናበተ።
ሦስተኛው የዓለም ጦርነት አይቀሬ ነው የሚሉም የበዙ ሲሆን (እውነት ከሆነና ከተከሰተ) እሱ ደግሞ ምን ሰርቶና ምን አድርጎ እንደሚሄድ አናውቅም። (በሄሮሺማና ናጋሳኪ ላይ (1945) የተጣለውን የአሜሪካ B-29 ቦምብና ከ129,000 እስከ 226,000 ህዝብን መጨረሱን፤ የቅርቡን የሩዋንዳን የእርስ በእርስ እልቂት ስንጨምርበት ጭካኔ የወለደውን ሰው በላነት ጥጉ የት ድረስ እንደሆነ ማየት ይቻላል።)
የቀድሞዋ ጠቅላይ ዐቃቤ ያሁኗ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ “ሰውን እንደ እቃ መነገድና በሕገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ሲበዛ ጨካኝ፣ አሳፋሪ እና ኢሰበአዊ ወንጀል ነው።” ማለታቸው በመገናኛ ብዙሃን ሰፊ የአየር ሰዓትን፣ የገጾች ሽፋንን አግኝቶላቸው እንደ ነበር እናስታውሳለን። ይህ በተባለበት አገር ግን ችግሩ በዚህ አላበቃም። የማይካድራውንና መሰል ስፍራዎች የተከሰተውን እጅግ አሰቃቂና ዘግናኝ ድርጊትን አስተናገደ እንጂ። ለዛውም የማይነካውን በመንካትና መከላከያ ሠራዊቱን በገዛ ወንድሙ በማስጠቃት።
ከዚህ የምንረዳው ነገር ቢኖር የሰው ልጅ ከሰራው ጭካኔ አለመማሩ ብቻ ሳይሆን በሰራው ጭካኔ አለመፀፀቱ እንዲሁም ጭራሹንም ለሌላ ዙር ጭካኔ ሲዘጋጅ የመኖሩና የንፁሃንን ህይወት ለቅጥፈት ሲዳርግ መኖሩ ነው። ለዚህ ደግሞ እኛ እራሳችን ጥሩ ምሳሌ ነን፤ ትላንት “ሀውዜን …” ሲል የነበረ አካል፣ ዛሬ “ማይካድራ …” ላይ ታሪክን ይደግማል ብሎ ማን ያሰበ አለ? “ትናንት የነበው ሥርዓት (ደርግ) ሰው በላ ሥርዓት ነው” በማለት “ታግዬ ደመሰስኩት” ሲል የነበረ አካል፤ እንደዚህ አይነት እጅግ አረመኔያዊና ሰቅጣጭ ተግባር ይፈፅማል ተብሎ እንዴትስ ሊታሰብ ይችላል? ግን ደግሞ ሆነ።
ታሪክ ነውና ወደ ፊት በታሪክ ሲነሳና ሲጣል ስለመኖሩ የማይካድ ነውና ለሱ ትተን እንለፈው። ለታሪክ የመተው ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ግን ይህ ጨካኝና ሰው በላ ቡድን በሕግ የመጠየቁ ጉዳይ በአስቸኳይ መሆን ያለበት ነውና የሕግ የበላይነት ይከበር ዘንድ የሁሉም ፍላጎት ነው።
አዲስ ዘመን ህዳር 29/2012