አዲስ ዘመን ጋዜጣ በተለያዩ ዘመናት የሀገር ውስጥ የውጭ ዜናዎችን ሲዘግብ ቆይቷል፡፡ ከዜናዎቹ መካከልም አስደናቂ እና ወጣ ያሉ ዜናዎች ይገኙባቸዋል፡፡ ለአብነትም በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ ከቀረቡት ዜናዎች መካከል ጥቂቶቹን ይዘን ቀርበናል፡፡
ሃያ ሁለት ዓመት የደነቆረችው በማንጠስ ዳነች
የዕቁብ ገንዘብ አጭበረበረች የተባለችው ፍርድ ቤት ቀረበች
ጂን ሐይምስ የተባለች የሃያ ሁለት ዓመት ቆንጆ በኃይል በማንጠሷ የተነሳ የወደፊት ኑሮዋ ከፍተኛ ለውጥ ሊያገኝ መቻሉን ሮይተር ኰቤንተሪ ከተባለችው የኢንግላንድ ከተማ ገለጸ።
የፋብሪካ ሠራተኛ የነበረችው ጂን ማስነጠሱ ሲተዋት በደንብ ለመስማት ችላለች። ከተወለደች ጀምሮ እስከ አስነጠሳት ቀን ድረስ ደንቆሮ ነበረች።
እሁድ ዕለት የመረመሯት ሀኪሞች በኃይል በማንጠሷ የተነሳ ተዘግቶ የነበረው የጆሮዋ የውስጥ አካል ቧንቧ ሊከፈት ችሏል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም ጂን ስትተኛ ጆሮዋን በጥጥ መጠቅጠቅ ግድ ሆኖባታል። ይኸውም በምትተኛበት ወቅት ሰምታው የማታውቀው የማንኰራፋት ድምፅ ከእንቅልፏ ስለሚነቀንቃት ነው። ግን አትማረርም።
በጥር 2 ቀን 1965 የወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ደግሞ በኢትዮጵያ ደቡብ ምዕራብ ግዛቶች በሚገኙ አንዳንድ ከተሞች የደረሰውን የመሬት መንቀጥቀጥ ዘግቦ ነበር። እንደሚከተለው ይነበባል።
ጥር 1 ቀን 1965 ዓ.ም የወጣ አዲስ ዘመን
የዕቁብ ዳኛና ገንዘብ ሰብሳቢ ለመሆን ተመርጣ የዕቁብ ገንዘብ አጭበርብራ አዋለች በመባል የተከሰሰችው ብርቱካን ኃይለማርያም አዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀረበች። አዲስ አበባ ገዳም ሠፈር ኗሪ የሆነችው ብርቱካን ኃይለማርያም የተከሰሰችው ወይዘሮ ዘነበች ወልደ ጻዲቅ የተባሉት ዕቁብተኛ በህዝብ ፊት የደረሳቸውን 600 ብር ዕቁብ በቀጥታ ለባለገንዘቧ በመስጠት ፋንታ በዘወርዋራ መንገድ ለግል ጥቅሟ በማዋሏ መሆኑን የቀረበባት የዐቃቤ ሕግ ክስ ይገልጻል።
ተከሳሿ በመጀመሪያ አዲስ አበባ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ ቀርባ ቃሏን ስትሰጥ ሚያዝያ 27 ቀን 1964 ዓ.ም ከዕቁብተኞች የሰበሰበችው 200 ብር ብቻ እንደነበረ ተናግራ ፤ቀሪውን 400 ብር ሌሎች ዕቁብተኞች አሟልተው ያልሰጧት መሆኑን ገልጻ ነበር። ለዚህ አባባሏ በቂ ማስረጃ ባለማግኘቷ ተከሳለች።
የፖሊሱ ጣቢያው የምርመራ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተከሳሿ በዕቁብ ዳኝነት ገንዘብ የምትቀበልበት መዝገብ በላፒስ የተፋቀና ስርዝ ድልዝ የበዛበት መሆኑን ይጠቅሳል።
የገዳም ሠፈሯ ሴት ፈጽማለች በመባል የተከሰሰችበት የማጭበርበር ወንጀል አዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት ቀርባ ጥፋተኛ አይደለሁም በማለት ቃሏን ሰጥታለች ፤ የችሎቱ ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ አቀራረብ የሚያስረዱ ምስክሮችና የጽሑፍ ማስረጃ አለኝ ስላሉ ተከሳሿ በዋስ ቆይታ ክርክሩ ቀጥሏል።
ዐቃቤ ሕጉ በአቀረቡት የጥፋተኛነት ክስ መሠረት ጉዳይ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረበችው የሴት ዕቁብ ዳኛ ጉዳይ ምስክር መሰማቱ ቀጥሏል። ተከሳሿ ዳኛ የነበረችው በገዳም ሠፈር 62 ሰዎች ሆነው አቋቁመው በየሳምንቱ ሐሙስ እያንዳንዱ ሰው 10 ብር በሚከፍልበት ዕቁብ መሆኑን ከፍርድ ቤት የተከፈተው የዓቃቤ ሕግ ክስ ይዘረዝራል።
ጥር 2 ቀን 1965 ዓ.ም የወጣ አዲስ ዘመን
የጦጣ ኩላሊት ከዝንጀሮ ተሻለ
ከኒው ኦርሊያንስ፡- የ44 ዓመት ዕድሜ ያለው አንድ የወደብ ሠራተኛ በሕመም ምክንያት በታወኩት ኩላሊቶቹ ምትክ የጦጣ ኩላሊቶች ከተተኩለት በኋላ የበፊት ጤናው ተመልሶለት ከታከመበት ሆስፒታል ሊወጣ እየተዘጋጀ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
የኩላሊት ህክምና የተደረገለት ይህ ጄፈርሰን ዴቪስ የተባለው ሰው የጦጣ ኩላሊት ተተክቶለት ሙሉ ጤንነቱን ካገኘ በኋላ ከሆስፒታል ለመውጣት የመጀመሪያ ሰው መሆኑ ነው፡፡ 39 ደቂቃዎች በመፍጀት ለሚስተር ዴቪስ የተፈፀመው ይህ የኩላሊት ኦፕራሲዮን የተከናወነው ከስድስት ወር በፊት ሲሆን ኦፕራሲዮኑም የተከናወነው በአስራ ሁለት ሐኪሞች መተባበር ነው፡፡
በሕመም የታወኩት የሚስተር ዴቪስ ኩላሊቶች ወጥተው የጦጣው ኩላሊቶች ወዲያውኑ እንደተተኩ ተግባራቸውን ማከናወን የጀመሩ መሆናቸውን ዶክተሮቹ አረጋግጠዋል፡፡
ባለፈው ጥቅምት ወር እነዚሁ ሐኪሞች 32 ዓመት ለሆናት ላንዲት ሴትዮ በታመሙት ኩላሊቶቿ ፋንታ የዝንጀሮ ኩላሊቶች ተክተውላት ነበር፡፡ ነገር ግን የዝንጀሮው ኩላሊቶች ከአንድ ሳምንት በኋላ ሥራቸውን ስላቋረጡ ሴትዮዋ ሞታለች፡፡
( ሮይተርስ ) ታኅሣሥ 9 ቀን 1956 ዓ.ም የወጣ አዲስ ዘመን
አዲስ ዘመን ህዳር 28/2013