ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ላይ የመጣ ጠላትን ሲመክት ለኖረው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፋቸውን ያላረጋገጡበት ወቅት የለም። መከላከያ የራሱ በጀት አለው ብለው ቆመው ተመልክተው አያውቁም። ድጋፋቸውን ሞራል፣ ገንዘብ፣የአይነትና የመሳሰሉትን ድጋፍ በማቅረብ ሲያረጋግጡ ኖረዋል።
ኢትዮጵያ በ1960ዎቹ መጨረሻ የሶማሊያው የዚያድ ባሬ መንግሥት በእብሪት ተነሳስቶ ታላቋ ሶማሊያን እፈጥራለሁ በሚል በጣም ሰፊ የኢትዮጵያን አካባቢ በወረረበት ወቅት ገንዘባቸውን ብቻ አልነበረም የለገሱት ።በወቅቱ ያንን ጠላት ለመደምሰስ በታጠቅ ጦር ሰፍር ለሚሰለጥነው ከ300 ሺ በላይ ሚሊሺያ መጠለያ እንዲሆን እድሮች ድንኳናቸውን ሰጥተዋል፤ሴቶች በሶ እያዘጋጁ ልከዋል፤እናቶች ከአዲስ አበባ በጭነት መኪና ጭምር እየተመላለሱ እንጀራ እየጋገሩ ሰራዊቱን መግበዋል።
በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅትም ቢሆን የእናት ሀገር ጥሪ በሚል ሠራተኛው የወር ደመወዙን ፣የተቀረው የህብረተሰብ ክፍልም በሚችለው መንገድ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ለመከላከያ ሰራዊቱ አጋርነቱን አረጋግጧል።ድጋፋቸውን ግንባር ድረስ በመሄድ አረጋግጠዋል።ድሉንም አብረው አጣጥመዋል።
በቅርቡም ወንጀለኛው የትህነግ ጁንታ ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው ጥቃት እሱንም በእጅጉ አሞታል።ሰራዊቱ የሀገሩን ዳር ድንበር ብሎ በበረሃ ሲቃጠል በኖረ የከሀዲውን ኃይል የስልጣን ጥማት ለማርካት በተገዙ የገዛ ባልደረቦቹ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሏል።እነዚህ ጨካኞች ይህን የሀገር ባለውለታ ገድለው ብቻ አላቆሙም፤በአስከሬኑ ተዘባብተዋል።የማረኳቸውን የምርኮ ወግ ነስተዋቸው ልብሳቸውን ገፈው ራቁታቸውን ለቀዋቸዋል።በእዚህ ድርጊት መላ ኢትዮጵያውያን በእጅጉ አዝነዋል።
ጥቃቱን ተከትሎ መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት ድርጊቱን አውግዟል፤አጋርነቱን በጥልቅ ስሜት ውስጥ ሆኖ ገልጧል።ከሰላማዊ ሰልፍ ባሻገር ድጋፉን ባለው አቅም አረጋግጧል፤እያረጋገጠም ነው።በግልም በተቋምም እየሆነ የማንንም አነሳሽነት ሳይጠብቅ ለመከላከያ ሰራዊቱ ያለውን አጋርነት በሚገባ አረጋግጧል። ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ህዝቡ በጎች ፍየሎችና ከብቶችን ሰጥቷል፤ይህንንም ግንባር ድረስ ወስዶ ያስረከበበት ወቅት አለ።ገንዘቡን በጥሬ ገንዘብም በተከፈተው የመዋጮ ማሰባሰቢያ ኤስኤም ኤስ በኩል ሰጥቷል።
ሰራዊቱም ለድጋፉ ምስጋና እያቀረበ የህግ የበላይነትን የማረጋገጡን ሥራ በተሳካ ሁኔታ አጠናቋል።ከዚህ በኋላ የህግ የበላይነትን የማስከበሩ ሥራ በዋናነት በፖሊስ ኃይል የሚሰራ ይሆናል።እንዲያም ሆኖ አንዳንድ ተቆርጠው የቀሩ የከሀዲው ቡድን አባላት ሊኖሩ ይችላሉ፤ተስፋ ያልቆረጡ የቡድኑ አባላት የአልሞት ባይ ተጋዳይነት እርምጃ ሊወስዱ የሚችሉበት ሁኔታ ሊኖርም ይችላል።ይህን አስቀድሞ ማክሸፍም ሆነ መመከት የሠራዊቱ ቀጣይ ሥራ ይሆናል።
አሁን በሙሉ ቁመና ላይ እንደመሆኑ እነዚህ ስጋቶች ለሰራዊቱ ብዙም ችግር ባይሆኑም ጉዳዩን ግን በንቃት የሚከላከለውና የህዝብ ድጋፍን የሚጠይቅም ነው።ህዝቡ ለሰራዊቱ ድጋፍ በማድረግ የእስከ አሁን ስኬት ዘላቂ ማድረግ ይገባዋል።
ምንም እንኳ ጦርነቱ ያበቃ ቢሆንም ለመከላከያ ሰራዊቱ እስከ አሁን ሲደረግ የቆየው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። እንደሚታወቀው ሰራዊቱ በወንጀለኛው ከሀዲ ቡድን በብዙ መልኩ ጉዳት ደርሶበታል።ጓዶቹን ወንድም እህቶቹን በከሀዲው ቡድን አጥቷል፤በዚህ ቡድን በመከዳቱም ማመን የሚቸግረው ሁኔታ ውስጥ የገባ ነው።ቤተሰቦቹ የተለያየ ጉዳት ሰለባ ሆነዋል።ነገሮችን ወደቀድሞ ሁኔታቸው ለመመለስ አሁንም የኢትዮጵያውያን ድጋፍ ይጠይቃል። ይህን ባለውለታ በቀጣይም በመደገፍ ከደረሰበት ጉዳት እንዲያገግም ማድረግ ያስፈልጋል።
የመከላከያ ሰራዊቱ ላጎናጸፈን ታላቅ ድል ምስጋና ሊቸረውም ይገባል።ምስጋናው ደግሞ አንድም እየተከናወነ ያለውን የድጋፍ ሥራ በማጠናከር ሊሆን ይገባል።ኢትዮጵያውያን በጦርነቱ ከጎኑ መቆማቸው በሰላማዊ ሰልፍ፣ በፋይናንስ፣ በተለያዩ መንገዶች እንዳረጋገጡ ሁሉ ምስጋናቸውንም በተለያየ መልኩ በሚገባ ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ያሉ ዜጎች ፣ተቋማት ፣ክልሎች.ወዘተ ለእዚህ ታላቅ ተግባር ራሳቸውን ማዘጋጀትና ድጋፋቸውን ማረጋገጣቸውን ማጠናከር ይኖርባቸዋል።አንዳንድ ባለሀብቶች ለመከላከያ ሰራዊት እና ለቤተሰቦቻቸው የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግ ቃል እየገቡ ይገኛሉ።ይህ አርአያነት ያለው ድጋፍ በሁሉም ባለሀብቶች፣ዜጎች፣ተቋማት ፣ወዘተ፣ዘንድ መዝለቅ ይኖርበታል።
ይህን ከባድ የሕግ የበላይነት የማስከበር ዘመቻ በአጭር ጊዜና በንጹሃን ላይ ጉዳት ባላስከተለ መልኩ ላጠናቀቀው የመከላከያ ሰራዊት በእርግጥም ታላቅ ክብር ልንሰጠው ይገባል።ይህን ደግሞ ድጋፋችንን ከእስከ አሁኑም በላይ በማረጋገጥ ሊሆን ይገባል።
አዲስ ዘመን ህዳር 28/2013