አስናቀ ፀጋዬ
ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምእራብ የኢትዮጵያ ምድር በርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሀብቶችን አቅፏል። ማእድኑ፣ ደኑ፣ የዱር አራዊቱ፣ ወንዙ፣ ተራራው፣ ሸለቆው፣ ሸንተረሩ፣ ሃይቁ ሁሉ የኢትዮጵያን ገጸ ምድር በረከት ነው። በቀደመው ታሪክ የተገነቡ አብያተ ክርስቲያናትና መስጂዶች፤ በተለያዩ ጊዜ በነበሩ ነገስታት የተሰሩ ቤተመንግስቶችና ሌሎችም ኪነ ህንፃዎችም የኢትዮጵያ ምድር ሀብቶች ናቸው።
ኢትዮጵያ የልዩ ልዩ ማእድናትና የከበሩ ድንጋዮች መገኛ መሆኗም የሚነገርላት ሲሆን ከዚህ የማእድን ሀብት የምታገኘው ገቢ ግን እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት የተሰሩ ጥናቶች ያሳያሉ። የማእድን ዘርፉ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ ዝቅተኛ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ።
ኢትዮጵያ ካሏት የማዕድን ሀብቶች ውስጥ ታዲያ ወርቅ በዋናት የሚጠቀስ ቢሆንም ከዚሁ የማእድን ሀብት የሚገኘው ገቢ በቂ ነው ተብሎ አይታሰብም። ሙስናና ኋላቀር የወርቅ አወጣጥ ዘዴን መከተልና መሰል ችግሮች ደግሞ የማዕድን ሀብቱን በሚገባ ለመጠቀም በዋናነት የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው።
የወርቅ ማእድን ሀብት በኦሮሚያ፣ ትግራይና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በስፋት እንደሚገኝ የሚነገር ሲሆን በጋምቤላ ክልልም በሁለት ዞኖች ላይ ሀብቱ እንደሚገኝ ከክልሉ የማዕድን ሀብት ልማት ኤጀንሲ የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።
የጋምቤላ ክልል የማእድን ሀብት ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አኳዋታ ቻም እንደሚገልጹት ክልሉ በወርቅ ማእድን ሀብት ይበልጥ የሚታወቅ ቢሆንም በሌሎች የድንጋይና የአሸዋ ሀብቶች ይታወቃል። የወርቅ ሀብቱም በዋናነት በክልሉ ባሉ ሁለት ዞኖች ላይ ይገኛል። አንደኛው በአኝዋ ብሄረሰብ ዞን በሚገኙ ሶስት ወረዳዎች ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በመዠንግ ብሄረሰብ ዞን ካሉት ወረዳዎች በአንዱ ውስጥ ይገኛል።
በአኝዋ ብሄረሰብ ዞን ውስጥ የሚገኘው የወርቅ ሀብት በዲማ፣ አቦቦና በጋምቤላ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በመዠንግ ብሄረሰብ ዞን ውስጥ ያለው ደግሞ መንገሺ በሚባል ወረዳ ውስጥ ነው። በነዚህ ሁለት ዞኖች ላይ የሚገኘው የወርቅ ሀብት ምን ያህል እንደሆነ በሚገባ ጥናት ተደርጎ ያልተረጋገጠ ቢሆንም ብዛት ባለው የወርቅ ሀብት እንዳለ ይገመታል።
ይሁን እንጂ በአካባቢው የወርቅ አወጣጥና አመራረት ሂደት ህገወጥ ስርአትን የተከተለ መሆኑ ሃብቱን በትክክል ለመጠቀም ዋነኛ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል። ይህም ክልሉም ሆነ ሀገሪቷ ከሃብቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አላስቻለም።
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ በአሁኑ ወቅት በክልሉ የሚገኘው የወርቅ ሀብት በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ በተደራጁ ማህበራት አማካኝነት እየተመረተ ወደ ብሄራዊ ባንክ እንዲገባ እየተደረገ ይገኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲሱ የቀመር አከፋፈል መሰረት የተወሰነ ድርሻ ክልሉ ተጠቃሚ መሆን እንዳለበት አዲስ መመሪያ ወጥቷል። ከዚህ በኋላ ባለው ሂደትም በመመሪያው መሰረት ክልሉና የፌዴራል መንግስት ከሀብቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከክልሉ የወርቅ ሀብት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ አሁንም ከሚታዩ ችግሮች ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው የኮንትሮባንድ ንግድ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ወርቅ ተመርቶ ሙሉ በሙሉ ወደ ብሄራዊ ባንክ የማይገባበት አጋጣሚዎችም አሉ። ገንዘብን በጥሬ ከማዘዋወር ይልቅ ወደ ወርቅ የመቀየር ሁኔታዎችም ይታያሉ። በወርቅ ማእድን ቦታዎች ያሉ ቆፋሪዎች ወርቅን በባህላዊ መንገድ የሚያወጡ መሆናቸውም ሌላኛው ተጠቃሽ ችግር ነው።
በመሆኑም የወርቅ ሀብት የሚፈለገውን ያህል ጥቅም እንዲሰጥና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚም የራሱን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ዘመናዊ የወርቅ አመራረት ቴክኖሎጂ እንዲኖር በክልሉ የማዕድን ሀብት ልማት ኤጀንሲ በኩል የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት እቅድ ተይዟል። ከህገ ወጥ ነጋዴዎች ወደ ወርቅ ንግዱ ውስጥ እንዳይገቡ ጠንካራ የቁጥጥር ስራም እየተሰራ ይገኛል። እነዚህን ስራዎች አጠናክሮ መስራት የሚቻል ከሆነም በክልሉ የሚገኘውን የወርቅ ሀብት በሚገባ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል።
በጋምቤላ ክልል ከወርቅ ማዕድን ሀብት በተጨማሪ ልዩ ልዩ የድንጋይና አሸዋ ሀብቶች እንዳሉ የሚገመት ሲሆን ገና በጥናት ያልተረጋገጡ ሌሎች ማዕድናትም ሊኖሩ እንደሚችሉና በቀጣይ እነዚህ የማዕድን ሀብት በጥናት ተፈልገው ከተገኙ ሀገሪቱም ሆነ ክልሉ የሀብቱ ተቋዳሽ ሊሆኑ እንደሚችሉ ከክልሉ የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።
አዲስ ዘመን ህዳር 28/2013