ከጆብራ አባጎሞል
ሰዎች ለሚናገሩት ነገር አጽንኦት ለመስጠት ሲፈ ልጉ ‹‹ልብ በል›› ይላሉ። አንዳንዴ ደግሞ ምስክር እንድትሆኑላቸው ይፈልጉና ‹‹ልብ አርጉልኝ›› ይላሉ። ልብ ላለው፤ ልብ ማለትም ይሁን ልብ ማድረግ ያላቸው ፋይዳ ቀላል አይደለም። በአሁኑ ወቅት እየፈተነን ያለው የምንሰማውንም ይሁን የምናየውን ነገር ልብ ብለን አለመረዳታችን ነው። ይሄም የሚመነጨው ረጋ ብለን ሰምተንና አይተን በጥልቀት መረዳት ካለመቻላችን ነው።
ይህም በመሆኑ ያገኘነውን መረጃ በአግባቡ ተንትነንና ተረድተን አስፈላጊውን ዝግጅትና ምላሽ እንዳንሰጠውና ከሚያደርስብን አደጋ ለመከላከል እንዳንችል አድርጎን ቆይቷል። የሆነውም እየሆነ ያለውም ያለምክንያት አይደለም ዘመኑ የመረጃ ዘመን በመሆኑ የመረጃ ማዕበል ውስጥ ገብተን የቱ ዐብይ፣ የቱ ንዑስ፤ የቱ ቀላል፣ የቱ ከባድ ብለን በመለየት በሕይወታችን ላይ ጉልህ ተጽእኖ ለሚኖረው ሀሳብ ድጋፍና ተቃውሞ እንዳንሰጥ በመጋረዳችን ነው።
ይሄን ሁሉ ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም። በቅርቡ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሁለቱ የምክር ቤቶች የመክፈቻ ስብሰባ ላይ ካደረጉት ንግግር ውስጥ ‹‹ወይ ሁላችንም በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንሄዳለን፣ ካልሆነም ማናችንም አንሄድም›› ያሉትን በጥሞና ካነበብኩኝ በኋላ ነው።
እርግጥ ነው ጥቅሱ መነሻ አለው። መነሻውም ዴሞክራሲ መብትና ግዴታ ያለው መሆኑን እና በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው የዴሞክራሲ አረዳድ በስህተት የተሞላ መሆኑን እንዲሁም ይሄን አስታከው እየተከሰቱ ያሉት የሕግ ጥሰቶች የዜጎችን ነፍስ እየቀጠፈና ንብረትን እያወደመ ያለውም የዴሞክራሲ ግዴታን በመዘንጋት የሚያጎናጽፈውን መብት በመጠየቅ ላይ በማተኮሩ በቀጣይ ዴሞክራሲ የሚባል ነገር ሊያሳጣን የሚችል አደገኛ ልምምድ መሆኑን በማሳየት ነው።
ልብ በሉ! ይህቺ ጥቅስ ጽንፈኞችና ‹‹ሕገመንግስት አጣቃሽ ሕገወጦች›› መብትና ግዴታችንን በማምታታት በስንት መከራና ጭንቀት እንዲሁም በስንት የህይወት መስዋዕትነትና ያካል ጉዳት ያገኘነውን የዴሞክራሲ ግንባታ ጅምር ለማጨናገፍ ምን ያህል የመንግሥትን ትዕግስት እንደተፈታተኑም ጭምር የምታሳየን ናት።
አይሳካም እንጂ ተሳክቶላቸው ዴሞክራሲውን ቢያጨናግፉብን ይህ አስነዋሪ ተግባራቸው ከኛ አልፎ ቀጣዩን ትውልድ ጭምር በጨለማ ውስጥ እንደሚከት ስንቶቻችን በቅጡ ተረድተነዋል፤ ተረድተንስ እነዚህ እኛ ያልሰጠነው ዴሞክራሲ ገደል ይግባ ብለው እየታገሉ ያሉትን ሕገወጦች ለመታገል ምን ዝግጅት አድርገናል።
እነሱ ትላንት ወንድምና ወንድምን አጋጭተዋል፣ መንጋ አሰማርተው ተጠያቂነት እንዲጠፋ ሰርተዋል፣ ንብረት አውድመዋል፣ ሕይወት ቀጥፈዋል። ዛሬ ደግሞ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በኩል ሽፍታ አሰማርተው ወገን እየፈጁ፣ በመሀል አገር ደግሞ ከመስከረም 25 በኋላ መንግሥት የለም የሚል ጥሩምባ እየነፉ በወሬ አገር እየፈቱና ከውጭ ጠላት ጋር አብረው የአገር ሰላምን እየተፈታተኑት ይገኛሉ። ታድያ ይሄ ሁሉ ሲሆን እኛስ ምን ሰራን።
ይቅርና መስራት ድርጊታቸው በራሱ ምን ያህል አገራችንን እንደሚጎዳ፣ ምን ያህል የህዝባችንን የዴ ሞክራሲ ጥማት እንደሚያደርቅና እድገታችንን እንደ ሚያደናቅፍ እንኳ አጀንዳ አድርገን ስንወያይበት አይታይም። መንግሥት በሆደሰፊነት የፖለቲካውን ምህዳር ሲያሰፋ በውስጡ እየሮጡ በማንቦጫረቅ አገሪ ቷን የሽብር ሜዳ ለማድረግ ይጥራሉ። የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና መደማመጥን ለማስፈን ቀንደኞችን ሲቆጣጠር ደግሞ አምባገነንነት ሰፈነ በማለት ሙሾ ያወርዳሉ።
እዚህ ጋ አንድ የኦሮምኛ ተረት ላጫውታችሁ፤ በድሮ ጊዜ ነው አሉ ጌታና አሽከር በነበሩበት ጊዜ፤ ጌታው የቅቤ ቡና አስፈልቶ ለአሽከሩ ‹‹በል እስቲ ቅዳና አጠጣን›› አለው። አሽከሩም እሺ ብሎ ጀበናውን አንስቶ መቅዳት ሲጀምር ጌታው ጀበናውን አታዘቅዝቅ አንተ ይደፈርሳል አለው። አሽከሩም እሺ ብሎ ጀበናውን ቀና አደረገው። ጌታውም መለሰና አታቃናው አንተ ቅቤው አይወርድም አለው። ከዚያም አሽከሩ ጀበናውን በቦታው ላይ አስቀመጠውና እንግዳውስ እጄን አስገብቼ ላውጣው? በማለት ጠየቀ ይባላል።
እስቲ ልብ በሉ አሽከሩ ምን ያህል እንደተቸገረ። እንዴት አድርጎ የቅቤ ቡናውን ከጀበና ያውጣው። ልብ ያለው ልብ ይበል ያልኩትም ለዚህ ነው። የአሽከሩ ችግርና የሀገራችን መንግሥት ችግር ይመሳሰላል። ወዳጆች መንግሥትን ከአሽከር ጋር አዛመድከው ብላችሁ እንደማትቀየሙኝ እርግጠኛ ነኝ። ምክንያቱም መንግሥት በራሱ እኔ አገልጋይ ነኝ፤ የሕዝብ አገልጋይ እያለ እራሱን ሲገልጽ ሰምቻለሁና ነው።
ወደ ቁምነገሩ እንመለስና እነዚህ የለውጥ አደናቃፊዎች የተለያዩ አዋኪ ምክንያቶችን እየደረደሩ መንግሥትና ሕዝብን በማወናበድ የተጀመረው የዴሞክራሲ ግንባታ ጅምር እንዲደናቀፍ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ይሄ እንዲሆን የሚፈልጉትም ዴሞክራሲው ተጨናግፎ መንግሥት በነሱ መንገድ መጓዝ እንዲጀምር በማድረግ ምኑን የተለየ ነገር አመጣ ትላንትም ዴሞክራሲ የለም ዛሬም ያው ነው በማለት ሕዝቡን የለፋበትን ሕይወት የገበረበትን የትግሉን ውጤት አስጥለውት እንደገና ወደትግል ገብቶ ሰላሙን በማጣት በድህነት አዙሪት ውስጥ እንዲኖር ለማድረግ ነው።
ይህ አልበቃ ብሏቸው፣ ከቃላት ማደናገሪያ ትርክታቸው እና ከንጹሃን ዜጎች ጭፍጨፋ ብሎም ማፈናቀል ድርጊታቸው አልፈው አገርን ለአደጋ የሚጋብዝ ተግባራቸውን መፈጸማቸው እውን ሆኗል። እናም የአገር ጋሻና ዋልታ በሆነው መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸም ክህደታቸውን አሳይተዋል።
ከዚህ ሁሉ የሴራ መንገዳቸው በኋላ ይህ አሳፋሪም አሰቃቂም ተግባራቸው ታዲያ እኔ ካልሆንኮ ህዝብም አገርም አይኖሩም የሚል የቀቢጸ ተስፋ ጉዟቸው ፍጻሜ መሆኑ የታወቀ ሆኗል። ስለዚህ ሕዝቡ ይሄን ሸፍጥ ልብ ብሎና ተረድቶ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት እነሱን አደብ በሚያስገዛው ሁሉን አቀፍ እርምጃ ውስጥ የድርሻውን በማበርከት፤ ከመንግሥት ጋር በመሆን የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደቱን መንከባከብ ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን ህዳር 28/2013