ጽጌረዳ ጫንያለው
የትምህርት ደረጃቸውም ሆነ የአገልግሎት ሁኔታቸው አንቱ የሚያስብላቸው ቢሆንም እድሜያቸው ግን አንቱታን አያላብሳቸውም ።ስለዚህም ወጣት በመሆናቸው ከአንቱታው ይልቅ አንቺን መርጠናልና በዚህ እንድንቀጥል ይሁንልን ።
እንግዳችን ዶክተር ሀና የሺንጉስ ትባላለች ።ከሰርተፍኬት ተነስታ ሦስተኛ ድግሪን የተቆናጠጠች ወጣት ነች ።በዚያ ላይ በዶክትሬት ድግሪ ቀደም ሲል ያልተለመደውን የክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚነት ሆና ለማሳየትና አገሯን ለማገልገል ገብታበት እየሰራች ትገኛለች ።
ከትምህርቷ ስንወጣ ደግሞ በግማሽ ማራቶን ማለትም በ21 ኪሎ ሜትር ሩጫ ካሸነፉ አትሌቶች መካከልም ትጠቀሳለች ።16 ጊዜም በአለማቀፍ የማራቶን ውድድር ላይ ተሳትፋለች ።በህይወቷ ከባድ የሚባሉ ፈተናዎችን ብታሳልፍም ወድቄያለሁ፤ ከዚህ በኋላ አልጓዝም ብላ የማታውቅም ነች ።ነገ ሌላ ብርሀን እንዳለ አልማ የምትሰራ፤ ከልጅነቷ ጀምራ በእቅድ የምትመራም እንደሆነች ትናገራለች ።በተለይ ልዩ የሚያደርጋት በህይወቷ ውስጥ መወዳደርን አጥብቃ መውደዷና ይህንንም ውድድር ከራሷ ጋር ማድረግ የሚመቻት መሆኗ ነው ።
ሩጫ በራስ ከሆነ ከግብ ላይ ያደርሳል የሚል እምነት ስላላትም ከፍታዋን ሁልጊዜ የምትለካው ከምትሮጠው ሩጫ አንጻር ነው ።ስለዚህም ይህን ልምዷ ብዙዎችን ያስተምራልና ለዛሬ ‹‹ የህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አድርገናታል፤ መልካም ንባብ ።
ራስን መሆን በልጅነት
እናትና አባቷ የመንግስት ሰራተኛ በመሆናቸው በአንድ ቦታ ስለማይቀመጡ እርሷም አብራቸው ትዞራለች። ይህ ደግሞ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ከተሞች እንድታይ ከማድረጉም በላይ በባህልና ወጋቸው እንድታድግ አግዟታል ።እድገቷም በአንድ ከተማ ብቻ የተወሰነ እንዳይሆን ረድቷታል ።በዚህም ባህርዳር፣ ጅማ፣ ሚዛን ቴፒ ፣ ወሊሶ፣ አንቦ፣ አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ መሀልሜዳ፣ ወዘተ እያለችም ነው የልጅነት ጊዜዋን ያሳለፈችው ።
የቤተሰቡ የመጀመሪያና ብቸኛ ሴት ልጅ በመሆኗ ደግሞ ይበልጥ እንክብካቤና ልዩ ትኩረት ይሰጣታል ።በተለይ እናቷ በቀጣይ ለልጆቿ መልካም እናት፣ መልካም ሚስትና መልካም ሰው እንድትሆን በብዙ መልኩ ሰርተዋታል። ሴት ልጅ ትሰራዋለች ተብለው የሚገመቱትን የቤት ውስጥ ሥራም ቢሆን ጠንቅቃ እንድትሰራ ሆና ነው ያደገችው።
ቤተሰብ የተማሩ መሆናቸው አንድ ነገር እንደቀነሰባት የምታነሳው ባለታሪካችን፤ የጨዋታ ጊዜ ያላት ትምህርት ቤት እንጂ በቤት ውስጥ አይደለም ። በዚህም ቤት ውስጥ ስትገባ አንድም ስራ አንድም ጥናት ብቻ ነው ተግባሯ ።በእርግጥ ይህንን ባህሪያቸውን አንዳንድ ጊዜ ብትቃወመውም በእነርሱ በኩል ስትሆን እውነትነት እንዳለውም ታምናለች ።
ስራ ወዳድ፤ ቅንና ታዛዥ፤ በትምህርቷም ቢሆን ጠንካራ እንድትሆንላቸው ስለሚፈልጉ እንደሆነ ታስባለች ።በዚህም ሳታሳፍራቸው የሚሏትን ሁሉ ታደርጋለች ። በአንድ ዓመት ሁለት ክፍሎችን በደብል መማር የጀመረችው በዚህ ክትትላቸው የተነሳ እንደሆነ ትናገራለች ።
በራስ የመተማመን ባህልንም ያዳበረችው በዚህ መልኩ ሆና በማደጓ እንደሆነ አትዘነጋም ።ይህ ሁኔታ ከአራተኛ ክፍል ጀምሮ የራሷን ልብስ ራሷ እንድታጥብም እንዳደረጋት አጫውታናለች። የምትፈልገውን ለማግ ኘትም ቢሆን ሳንቲም አንድም ቀን ቤተሰቧን ጠይቃ እንዳታውቅ፤ ከዚያ ይልቅ ጫማቸውን በመጥረግ ውጪ የሚከፍሉትን ለእርሷ እንዲሰጡ ታደርግ እንደነበር ታነሳለች ።
በቤት ውስጥ ቤተሰቦቿ ነጻነት ቢሰጧትም የመጫወት ሁኔታዋ አናሳ ስለሆነ በባህሪዋ ጭምት የምትባል አይነት ልጅ ነበረች። ሆኖም በትምህርት ቤት ግን ተጨዋችና ሩህሩህ ነች። ያላትን በማካፈል የምታምን፤ ሰዎች ሲቸገሩ የሚያማትና ለችግራቸው መፍትሄ ለማግኘት የምትታትር ልጅም ነች ።ሰዎችን መርዳት፣ ጥሩ ተናጋሪ መሆን፣ ስልጠናዎችን መስጠት እና የሦሥተኛ ድግሪ ምሩቅ መሆን የልጅነት ህልሟ ነበር ።በዚህም ገና በልጅነቷ ጀምሮ ራሷን ዶክተር ሀና እያለች ነበር የምትጠራው ።
በእያንዳንዱ ህልሟ ውስጥ እቅድ ግዴታ እንደሆነ አስባ የምትንቀሳቀሰው እንግዳችን፤ የእቅዷን ሁኔታ ራሷ ብቻ ሳትሆን ቤተሰብ ጭምር ያውቀዋልና 12ኛ ክፍል ስትወድቅ እቅዱ ከሸፈ ያላት ወንድሟ እንደነበር አትረሳውም ።ወዲያውም እቅዷን የጻፈችበትን ሶፋ ገልብጣ እንዳስተካከለችው አጫውታናለች ። ዶክተር ሀና እናትና አባት ለልጆች መሰረት የሚሆኑት ትዳር በቤት ውስጥ መኖር እንዳለበት ታምናለች ።ምክንያቱም ልጆች በቤተሰብ ባህሪ ይገራሉና ።ለዚህ ደግሞ የእርሷ ቤተሰቦች ምስክር መሆናቸውን ትናገራለች ።
ቤተሰቦቿ ጸብና ብጥብጥን ሳያውቁ 37 የጋብቻ እድሜያቸውን አሳልፈዋል ።ይህ ደግሞ ጥላቻ የሚለውን ስሜት ሳያውቁት እንዲያድጉ እንዳደረጋቸው፤ ኢትዮጵያዊነት መደጋገፍ ምን ማለት እንደሆነ እንዲረዱ እንዳስቻላቸው ትገልጻለች ።በተለይ ከሁሉም የማይረሳትና ለዛሬ ማንነቷ ያበቃት ደግሞ ሁሌ ጀግና ሆነው ያጀገኗትንና ጀግና እንደሆነች እየነገሩ የኮተኮቷትን ነው ።
ፈተናና ድልን ያነገበው ትምህርት
ዶክተር ሀና እንደ እድገቷ ሁሉ ትምህርቷንም ቤተሰብ በከተመበት ቦታ ላይ ነው ስትከታተል የቆየችው። በዚህም በቤት ውስጥ ከሚደረግላት ልዩ ክትትልና ፊደል ቆጠራ በተጨማሪ ክፍል ውስጥ ገብታ ትምህርትን ‹‹ሀ›› ብላ የጀመረችው ከእናቷ ጋር በመሆን በባህርዳር ካቶሊክ መዋለ ህጻናት ትምህርት ቤት ነበር ።
ከዚያ ወደ አባቷ ጋር ሚዛን ተፈሪ ጋቸብ በሚባል አካባቢ በመሄድ አንደኛ ክፍልን መማር ችላለች ።ዳግም እናቷ ጋር ባህርዳር በመመለስ በአጼ ሰርጸድንግል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብታ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ክፍልን በደብል በአንድ ዓመት እንድትማር ሆናለች ።
ቤተሰብ ወደ ወሊሶ ሲቀየር ደግሞ እነርሱን በመከተል አራተኛ ክፍልን በወሊሶ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንድትከታተል ሆነ ።አሁንም ቤተሰቡ ወደ አንቦ በመቀየሩ የተነሳ አምስተኛና ስድስተኛ ክፍልን የተማረችው በአንቦ ቤተክህነት ትምህርት ቤት ነው ።ቀጥላ አሁንም ቤተሰብ አዲስ አበባ ስለገባ ገርጂ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍልን እንድትማር ሆነች ። ከዘጠነኛ ክፍል እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ ቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብታ ነው የተማረችው ።
በትምህርቷ የደረጃ ተማሪ ብትሆንም 12ኛ ክፍል ግን የማትሪክ ውጤት አልመጣላትም ።ይህም ጊዜ እጅግ በህይወቷ የማትረሳው ሆኖ አልፏል ።እንደውም በተማረ ቤተሰብ ውስጥ ሆኖ መውደቅ እጅግ ከባድና ሁልጊዜ መታመም ነው ትላለች። ቤተሰቧ ብቸኛ ሴት ልጃቸው ስለሆነች ባይናገሯትም ፊታቸውን ስለምታነበው በጣሙን እንደተበሳጩባት ስለምትረዳ ታዝንም እንደነበር ታስታውሳለች። ሆኖም ከማዘን ያለፈ ነገር መስራት እንዳለባት አመነች።
አንድ ነገር መወሰን ግዴታዋ ነው ።አንድም የግል ኮሌጅ ገብቶ መማር፤ አለዚያም ኮተቤ በሚያስገባት ነጥብ ገብታ ትምህርቷን መከታተል ።ስለዚህም ቤተሰብ ላለማስቸገርና ዳግም ላለማስከፋት ስትል እንዲሁም እልኸኛ በመሆኗ ለምን ወደኩ በሚል ቁጭት አባቷን ለምና በሰርተፍኬት ለመማር ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ተመዘገበች፤ አልፋም ትምህርቷን ጀመረች ።
በእርግጥ በወቅቱ ውጤቷ ዲፕሎማ ያስገባት ነበር ።ሆኖም የወደቀችበትን ትምህርት ማለትም ታሪክን ዲ ያመጣችበትን አብይ በማድረግ በመመዝገቧ የምርጫዋ ስህተት ዲፕሎማውን አስትቶ ሰርተፍኬት ውስጥ አስገባት ።በዚህም ገና ስትገባ ስድስት ሰዎችን ያስቀራሉ የሚለውን ሰምታለችና ሰቅሎ መቅረትን እያሰበች ተማረች ።
እቅዷ ሰምሮም ከአራት መቶ ተማሪ ሁለተኛ በመውጣት ኮሌጁ የትምህርት እድል ሰጥቷት ዲፕሎማዋን ወዲያው ለመቀጠል በቃች ።እድሉም ሌላ እድል እንዲያመጣ በማሰብ በሚገባ ተጠቀመችበትና በእንግሊዝኛ ትምህርት መስክ በማዕረግ ተመረቀች።
በተቋሙ ድግሪ ባለመሰጠቱ ምክንያት ለጊዜው በዚያው መቀጠል ባትችልም ሦስተኛ ድግሪ መያዝ ህልሟ ነውና መማሯን አላቆመችም ።ስለዚህም በአባቷ ምክረ ሀሳብ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሜርስ አካውንቲንግ ተመዘገበች ።ሆኖም ፍላጎት አልነበረምና ከዓመት በላይ አልቀጠለችበትም ።
ግን ሳይኮሎጂ መማር ትፈልግ ነበርና በማታ ትምህርት እየሰራች እንግሊዝኛ እና ጎን ለጎን ከሳይኮሎጂ ጋር ግንኙነት ያለውን የልዩ ፍላጎት ትምህርት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መማር ጀመረች። ከዚያ ሁለቱንም በመጀመሪያ ድግሪ ማጠናቀቅ ቻለች። ነገር ግን እዚህ ላይ ትልቅ ትግል አድርጋለች ።
እንግሊዝኛው አራት ዓመት የሚወስድ ሲሆን ልዩ ፍላጎቱ አምስት ዓመታትን ይፈጃል ።ስለሆነም አንድ ዓመቱን በምንም ላለማሳለፍ ስትል በእንግሊዝኛ ትምህርቱ ተወዳድራ ሁለተኛ ድግሪዋን በልዩ ፍላጎት መማር ጀምራለች ።ይህ ደግሞ አንዱ አመት በልዩ ፍላጎት ማስተርም ድግሪም የምትማርበት እንስት አድርጓት ቆይቷል። እንደውም ይህንን ስታጠናቅቅ አራት ነጥብ አምጥታ እንደነበርም ትናገራለች ።
የዶክትሬት ድግሪዋንም ቢሆን ብዙ ጊዜ ሳትወስድ ነበር የጀመረችው። የትምህርት እድል በማግኘቷ ወደ ቻይና ሁዋን ከተማ በመሄድም ነው በአፕላይድ ሳይኮሎጂ ትምህርት መመረቅ የቻለችው። ከዚያ ውጪ የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስዳለች። አሁንም መማር የምትፈልጋቸው ትምህርቶች እንዳሉ አጫውታናለች ።
ሥራን በራስ
ቤተሰቧ ጥሩ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ቢሆኑም አንድም ቀን እንዲያግዟት ጠይቃ አታውቅም። በራሷ ለፍታ፣ ጥራና ግራ ገንዘብ ማግኘትንና ራሷን መርዳት ምርጨዋ ነው። በዚህም ኮተቤ ስትማርም ሆነ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ቻይና ቤተሰብ አስቦ ካላደረገላት በስተቀር የምጠይቀው ነገር እንዳልነበር ታወሳለች። ይህ ደግሞ ሥራ ወዳድና ስራ ፈጣሪ አድርጓታል። ለአብነት
ኮተቤ ላይ እያለች ልጆችን በትርፍ ጊዜ በማስጠናት ራሷን ታግዛለች። ከተመረቀች በኋላ ደግሞ በመምህር ደሞዝ ብዙ ነገር ማድረግ ያስቸግራታልና መጀመሪያ አሰራሩን ለማየት ጁስ ቤት ተቀጥራ ሰርታለች ።ከዚያ የራሷን ጁስ ቤት ከፍታ ሥራውን አጧጡፋለች ።
ሥራ መስራት የምትወደው ከእውቀት ጋር ሲሆን ብቻ መሆኑን የምታነሳው ባለታሪካችን፤ ብዙዎች ኩባንያ ከፍተው ስለሚሰሩት ሥራ አለማወቃቸው ማንም እንዲበዘብዛቸውና ትርፋማ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል፤ እኔ ደግሞ የእዚህ ችግር ሰለባ መሆን አልፈልግምና ተቀጥሬ የሰራሁት በዚህ ምክንያት ነው ትላለች ።ከዚያ አለፍ ብላም ሥራዋ የተሳካ እንዲሆንላት አትክልት ተራ ሄዳ ከሚጭኑትና ከሚያወርዱት እንዲሁም ከሚያከፋፍሉት ጋር ለመግባባት ስትል በህብረት ትበላለች፣ ትጠጣለች ትጫወታለችም ።ይህ ደግሞ ቦታው ላይ ባትኖርም በስልክ ጭምር የፈለገችውን አምነው እንዲልኩላት እድል እንደሰጣትም አጫውታናለች ።
ዶክተር ሀና ተስፋ እንዳልቆርጥ ያደረገኝ በህይወቴ እየተደራረበብኝ የመጣው ፈተናና እርሱን ለማሸነፍ የማደርገው የራስ ትንቅንቅ ነው›› ትላለች ።ህይወት መቼም ቢሆን አልጋ በአልጋ አይሆንም ።በዚህም ይህንን አውቆ የሚያጋጥሙ ችግሮችን እንደ ጥሩ እድል መቁጠር ይገባል ።በተለያየ ፈተና ውስጥ ብንገኝም የምንወድቅበት የመጨረሻ ጥግ አድርገን ልንወስደውም አይገባም። ይልቁንም ያለምነውን ለማግኘት መትጋት ይኖርብናል።
በማንኛውም ጊዜ ፈተና ውስጥ ስሆን ብዙ ጫናዎችና ጭንቀቶች ይኖራሉ። ማልቀስና ችግሩን እንዴት ማለፍም እንደሚቻል ግራ መጋባቶች ግድ ናቸው ።እንደውም ከጭንቀቱ የተነሳ ከመጠን በላይ ክብደት ታይቶብኝ እንደነበር አስታውሳለሁ። ግን ለችግሮች ሁሉ መፍትሄዎች አሉና በትዕግስትና በሥራ አልፌዋለሁ ትላለች ።
ማንም ሰው በችግር ውስጥ ሲሆን እነዚህን ጥያቄዎች መጠየቅ ቢችልና ምላሻቸውን ቢያገኝ ስኬታማ ይሆናል የምትለው ባለታሪካችን፤ ለእኔ አሁን ያለሁበት ህይወት ይገባኛል ወይ? ፣ የአቀድኩት ላይ ያደርሰኛል ወይ ? ምን ምቹ ሁኔታ አለኝ? ፣ ምንስ ይጎለኛል ? የሚሉትን ለራስ መጠየቅና ለመፍትሄው መዘጋጀት ያስፈልጋል ባይ ነች።
አንድ ሰው ጠንካራ የሚሆነው ብቻውን ስለለፋ ሳይሆን ከጎኑ ብዙ ደጋፊዎች ስላሉት መሆኑንም ማመን ይጠበቃል ።ከዚያ ወደ ሥራ መግባት ውጤቱን ያሳያል ።ግን የደጋፊን ውለታ መዘንጋት አይገባም ።ሌሎችን በመደገፍ መመለስ ያስፈልጋል እምነቷ ነው ።
እንግዳችን በተቋም ደረጃ የቀድሞ አስፋወሰን የአሁኑ ምስራቅ ጎህ፤ ገርጂ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ አንድነት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት በእንግሊዝኛ መምህርነት አገልግላለች። ቃሊቲ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እና አሜሪካን ስኩል ደግሞ በልዩ ፍላጎት ትምህርት ኤክስፐርትነት ለሦስት ዓመት ያህል ሰርታለች።
በአጠቃላይ መምህር ሆና 12 ዓመታትን አሳልፋለች ። የዶክትሬት ድግሪ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ደግሞ ወደ አገሯ ሳትመለስ በዚያው በቻይና ጀንጆ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሳይኮሌጂው የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ስትሰራ አራት ዓመታትን ቆይታለች፡፡
ቀጣዩ የሥራ ቦታዋ አገር ውስጥ በሚገኘው አይ ካፒታል አፍሪካ ኢኒስቲትዩት ሲሆን፤ የፕሮጀክት ዳይሬክተር በመሆን ሰርታለች ።ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንን ጨምሮም ሌሎች ድርጅቶችን በማማከር አገልግላለች ። ከዚያ የመጨረሻ ስራዋ አሁን ያለችበት ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነች ።ከዚህ ሥራዋ ጋር ብዙ ሀሳቦችን ያነሳችልን ሲሆን፤ አንዱ ከመማሯ ጋር የተያያዘ ነው ።
የስኬት ዋስትናችን ኪሳችን ውስጥ ያለ ገንዘብ ሳይሆን የሥራ ትጋታችን ነው የሚል እምነት ያላት ባለታሪካችን፤ ወገንን ለማገልገል የትምህርት ደረጃም ሆነ ልዩ ሁኔታ መስፈርት ሊሆን አይገባውም ትላለች ።ዶክትሬቷን ይዛ የተለየ የሥራ አማራጭ ቢኖራትም የክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆና ለማገልገል የወሰነችውም ማህበረሰቧን በቅንነት ለማገልገል እንደሆነ ታነሳለች ።በተጨማሪ መማር ብቻውን የምንፈልግበትን ቦታ አይሰጠንም። ለአገር ማበርከትና የመስራት ፍላጎት ሲኖረን ነው የአቀድነው ቦታ ላይ የምንደርሰው፤ የሚል እምነት አላትና በዚህ ምክንያት ክፍለከተማውን መቀላቀል እንደቻለች ትናገራለች ።
በሌላ በኩል ወደዚህ ቦታ የመጣችበትን ምክንያት ስታነሳ ብዙ ጊዜ የምንሰራው ለኪሳችን ነው። መንግስት ይህንን አላደረገልንም፣ ይህንን ቢያደርገው ወዘተ ይባላል። ሆኖም የለውጡ አካል ሆኖ መስራት ያማል። ልክ መንግስተሰማያት መግባት እንፈልጋለን መሞት አንፈልግም አይነት። ስለዚህም ያንን ላለመሆንና ራስን ከወቃሽነት ለመታደግ እንዲሁም የማህበረሰቡ ችግር ለመፍታት ስትል ቦታውን መርጣ እንደገባችበትም አጫውታናለች ።
ሰዎች ጥሩ አነቃቂ ተናጋሪ ለመሆን የተለያዩ የአገራት ተሞክሮን ይወስዳሉ። እኔ ግን ማድረግ የምፈልገው የኖርኩትን ህይወት ማጋራት ነው ብላ የምታምነው እንግዳችን፤ በጥሩ ቦታና በጥሩ ወንበር ላይ መቀመጥ ብቻ ለውጥን አያመጣም ።አብሮ ተቀራርቦ መስራትን ይጠይቃል። በመሆኑም በአገር ደረጃ ዋነኛ ችግር እየሆነ ያለው መማር የአስተሳሰብ ችግርን ይለውጣል ብሎ አለማመን ነውና ይህንንም መፍታት ስለምፈልግ አድርጌዋለሁ ትላለች ።ተማርን የምንል ሰዎች ማህበረሰቡ ለተማረ ሀይል የሚሰጠው ክብር ትልቅ በመሆኑ በሚሰጠው ክብር ልክ በአስተሳሰብ፣ በአነጋገርና በኑሮ መልካም አርአያ ሆኖ መገኘትም እንዳለበት ታሳስባለች ።
ብዙ ተከታይ እንዳለን መረዳት፣ በምናደርገው ድርጊት ትውልድ መግደልና ማዳን እንዳለ ማወቅ ይጠበቅብናል። መማር ማለት ያልተማረ ወገናችንን እኛ የደረስንበት የብቃት ደረጃ ላይ ማድረስ እንደሆነም መገንዘብ ይገባል። ቀድሞ የመሄዱም ጉዳይ የተቸገርነውን ሌሎች እንዳይቸገሩበት ለማሳየትና መንገድ ለመጥረግ ነውና አይመለከተኝምን ትተን ወደፊት ማሻገር ላይ ማተኮር የሁልጊዜ ሥራችን መሆን አለበትም ባይ ናት ።
አትሌቷ ዶክተር
ለዚህ ምክንያት የሆናት ክብደቷ ከመጠን ያለፈ መሆኑ ነው። በዚህም አባቷ ጠዋት እየቀሰቀሱ የማትወደውን ስፖርት ያሰሯት ጀመር። መጀመሪያ በእርምጃ ቀጥላ ደግሞ በዱብዱብ ከዚያ በጣም ስትበረታ በሩጫ እያለችም ነበር ከሩጫው ጋር የተወዳጀችው ።አብረዋት የሚሮጡትን አባቷን በርትታ አልፋቸው ብትሄድም እርሳቸው በተለያዩ ቃላት ያበረቷት ነበር ።
በተደጋጋሚ ይህ ሲሆን ስታይ ግን አንድ ነገር ተረዳች ።ሰው ከራሱ ጋር እንጂ ከሰዎች ጋር አይወዳደርም፤ በራሱ ልክ መፍጠንና መሮጥ አለበት። የሰው ልጅ የራሱን ሩጫ ትቶ የሌላ ሰውን የሚሮጥ ከሆነ ይጎዳል፤ መወዳደርም ያለበት ከራሱ ግብና ራዕይ ጋር እንጂ ከሰዎች ጋር መሆን የለበትም ።ያ ከሆነ መቼም መለወጥ አይችልም የሚል ፍልስፍና እንዲኖራትም የሆነችው ከዚህ አንጻር ነው ።
ዛሬ ከትናንት የተሻልኩ ነኝ ብለን ራሳችንን መመርመርና ስህተቶቻችንን ማረም ስንችል ነገን የተሻለ አድርገን መኖር እንጀምራለን ።ለዚህ ደግሞ በምክንያት የተጀመረው ሩጫዬ 16 አለማቀፍ ግማሽ ማራቶን ላይ እንድሳተፍ ከማድረጉም በላይ ብዙዎቹን ሩጫዎች የማሸነፍ ሀይልን አቀዳጅቶኛል ትላለች ።
አሜሪካን ስኩል በምታስተምርበት ጊዜም የሩጫ አሰልጣኝ የመሆን እድልም አግኝታ ስለነበረ ይህም ከሩጫው ጋር እንድትቀራረብ እንዳደረጋት ትናገራለች። ከዚያ ቻይና ከተማ ላይ በምትማርበት ወቅት ታላቁ ሩጫ ነበርና እዚያ ላይ ተሳተፈች ።በወቅቱ ቻይንኛ ቋንቋ አትችልም ነበርና ችግር እንዳይገጥማት በመስጋት ኢትዮጵያዊያን እንዲያግዟት ከእነርሱ ጋር ነበር የሮጠችው።
ሆኖም እንዳይጠፉባት ስትከተላቸው የቆየችው ዶክተር ሀና እነርሱን ትታ ነጎደች ።ሩጫውንም አሸነፈች። ሆኖም በጊዜው ይህ መሆኑን አልተረዳችም ነበር። አንድ ቻይናዊ እጇን ሲይዛትና ከብዙ አለመግባባት በኋላ በእጇ ላይ በፓርከር ‹‹ዊን›› ብለው ሲጽፉላትም ነበር የተረዳችው። ከዚያ በኋላ በሩጫው ማን ይቻለኝ በማለት በርከት ያሉ ማራቶኖች ላይ ተሳተፈች ።ድሏንም ማጣጣም ጀመረች ።
ቀጣይ እቅድ
‹‹አንቺ አንድ ዘር ነሽ፤ ቢተውሽ አንድ ዘር ሆነሽ ትቀሪያለሽ፤ ቢተክሉሽ ግን ጫካ ትሆኛለሽ›› የሚለው የአባቷ ንግግር ለዛሬ ማንነቷ እንዳበቃት የምትናገረው እንግዳችን ፤ መልካም ተክል መትከልን የዘወትር ስራዋ አድርጋ መጓዝ ይመቻታል ።በዚህም በተሰማራችበት የሙያ መስክ ሁሉ ይህንን ለማድረግ ትታትራለች ።አሁን ባለችበት ቦታ ላይም የመጀመሪያ እቅዷ የመልካም አስተዳደር ችግርን መፍታትና ማህበረሰቡ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኝ ማገዝ እንደሆነም አጫውታናለች።
ያላትን ልምድ ማካፈል፣ ልምዱን ተጠቅሞ የመፍትሄ አካል መሆን፤ ከሌሎች መማርና የእነርሱን ሀሳብም መፍትሄ ማድረግ ሌላው እቅዷ ነው ።በተለይ የተለወጠ ወጣት በአራዳ ክፍለከተማ መፍጠር ዋነኛ አላማ እንደሆነ ለዚህም ‹‹ቅንነት ለአራዳነት›› የሚል ለስድስት ወር የሚቆይ ፕሮጀክት እንደጀመረች አጫውታናለች ።
ፕሮጀክቱ በብዙ ገንዘብ የሚሰጥ ስልጠና ቢሆንም ‹‹ቅን›› የተባሉ የቀድሞ ባልደረቦቿ ቡድኖች በነጻ ለመስጠት ተስማምተውላታል ።በዚህም በማህበረሰቡ ዘንድ አራዳነት ማለት መደባደብ፣ መስረቅና ሌላ ያልተገባ ባህሪ ማሳየት የሚለውን አስተሳሰብ ቅን፣ የገባው፣ የተለወጠና ሥራ የሚፈጥር በሚል ለመተካት እየጣረች ትገኛለች ።
ወቅታዊ ሁኔታው ላይም እንዲሁ እቅድ አላት ። በተለይ በጸጥታ ዙሪያ አራዳን የሰላም ተምሳሌት ለማድረግ ከብሎክ ጀምረው ካሉ የህዝብ አደረጃጀቶች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ተግታ እንደምትሰራ ገልጻልናለች። ከዚህ ባሻገር የምትመራው ክፍለ ከተማ ውስጥ ህዝቡ የሚያነሳቸው የተከማመሩ የመጥፎ አሰተዳደር መንስኤ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ቆርጣ መነሳቷንም አጫውታናለች ።የመንግስት ህግ የማስከበርና ህልውናን የማስጠበቅ እርምጃ አላማ ላይ ከመላው ነዋሪ ጋር በዝርዝር በመወያየት መግባባትን ለመፍጠር አበክራ እንደምትሰራም ነግራናለች ።
አራዳ ክፍለ ከተማን ትክክለኛነት የአራዳ መገለጫዎችን የተላበሰች ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆነች ኢትዮጲያዊነት በተግባር የሚገለጽባት ለማድረግም ሌት ተቀን እንደምትታትርና ለትልሟ ስኬት መላው የክፍለ ከተማው ነዋሪ ከጎኗ እንዲቆም በዚህ አጋጣሚ ጥሪ አስተላልፋለችም ።
ዘወትር የነገ የተሻለች ሀናን ለመፍጠር ህልሟ በመሆኑ የደረሰችበት ከፍታ መጨረሻዋ ሳታደርግ ወደፊት በመቀጠል ታምናለች ።ምክንያቱም ከፍታዋ ነገ ላይ ያለው እንደሆነ ተማምናለችና ። ለማህበረሰቡ የምታገለግልና የሚተርፍ ህይወትን ሰርቶ የሚያልፍ ሰውን መሆን እንደምትሻም አጫውታናለች ።
መልዕክት
በአለም ላይ የተለያየ ብሄርና ማንነት ባላቸው አገራት፤ በአንድ ብሔር ብቻ የተገነባ አገር የለም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ ደግሞ ብዙ ነገራቸው ይለያል። ምክንያቱም ብቻ የሚለውን ነገር አያውቁትም። መብላታችን፣ መጠጣታችን፣ ማህበራዊ ጉዳዮቻችን በጋራ እንጂ ለብቻ የሚከወኑ አይደሉም ።ዛሬ የመጣው አስተሳሰብ የእኛ ያልሆነና የተገዛ ነው። የአገር ጉዳይ ሲሆን ሁሉ ጭንቀት የሆነ ነገር የሚረሳው ልዩነታችን ውበታችን በመሆኑ ነው። ስለዚህም ይህንን አስተሳሰባችንን ማጎልበት የመጀመሪያ ስራችን መሆን አለበት ።
በመጸሐፍ ቅዱስ ‹‹ ወንድሙን የሚጠላ ነብሰ ገዳይ ነው›› ተብሎ ተቀምጧል ።የሚገድል ደግሞ ምን እንደሆነ መገመት አያዳግትም ።ስለሆነም የሀይማኖት አባቶች፣ የትምህርት ተቋማት ከሽምደዳ ያለፈ እና በተግባር የተደገፈ ትምህርት መስጠት ይኖርባቸዋል ።በህይወት እየኖሩበት መሆኑንም ማረጋገጥ ግዴታቸው እንደሆነ ማሰብ መጀመር አለባቸው። በተለይ በማህበረሰቡ ላይ የመጡ ለውጦችን፣ በአገር ላይ እየተገነባ ያለውን ትውልድ የማየት ሁኔታ በእነርሱ እጅ ላይ ነውና ራሳቸው ሆነው ማሳየት ይኖርባቸዋል፡፡
ወጣቱ በተለይም ሴቶች የተሻለ ቀን እንዳለ ማመንና ዛሬ ያሉበትን የከፍተኛ ጣሪያ አድርገው ሳያስቡ ወደ ፊት መራመድ አለባቸው ። ዛሬ ያለንበት ጨለማ በእርግጠኝነት ስናልፈው ብርሀን አለውና ያንን ብርሀን እያሰቡ መስራትም ይኖርባቸዋል። የተዘጋ በር እያዩ ከመቆዘም የተከፈቱ በሮችን ለማየት መሞከር መጀመርም ለድላቸው መሰረት ይሆንላቸዋልና ቢጠቀሙበት መልካም ነው። “ዛሬ እጄ ላይ ምን አለኝ ብሎ ከመቁጠር ባለፈ ምን የቀረኝ አለ፣ እንዴት ላጎልብተው” ብሎ መትጋትም ሌላው አማራጭ የድል መንገድ ነው ።ብዙ ጉድጓድ ያላት አይጥ አትሞትም እንደሚባለው ሁሉ የተሻሉ አማራጮችን በሙሉ መሞከር ይገባል፤ የእንግዳችን መልዕክት ነው።
አዲስ ዘመን ህዳር 27/2013