ላለፉት አምስት አስርት ዓመታት በትግራይ ህዝብ ላይ እንደመዥገር የተጣበቀው የህወሓት ጁንታ ከውልደቱ ጀምሮ በአንድ በኩል በአደባባይ ስለ ነፃነት፣ ፍትህና ዴሞክራሲ እየጮኸ በሌላ በኩል ስለ ነፃነት፣ ፍትህና ዴሞክራሲ የሚናገሩ አንደበቶችን በብርቱ መዳፉ እያፈነ ከውልደቱ እስከ ውድቀቱ ድረስ ረጅም መንገድ ተጉዟል። በዚህም የትግራይ ህዝብ የከፋ የሚባል ዋጋ ከፍሏል።
የትግራይ እናቶች ልጆቻቸውን ስለከንቱ የነፃነት፣ የፍትህና የዴሞክራሲ ስብከቶች እንዲገብሩ አድርጓል። በተለይ ከደርግ ጋር በነበሩ የ17 ዓመታት የትግል ዘመን ከ60 ሺ በላይ ደሃ የትግራይ ወጣቶች ለነፃነትና ለፍትህ ህይወታቸውን ገብረዋል፡፡ ከዚያ የማይተናነሱ ሌሎች ወጣቶች ደግሞ ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ እንደወጡ የውሃ ሽታ ሆነው የቀሩና ለቤተሰባቸው ጸጸት የሆኑ ወጣችንም ቤት ይቁጠራቸው፡፡
በእነዚህ የትግል ዓመታት ታዲያ ከጀርባ በመሆን ወጣቱን ሲማግዱ የነበሩት አብዛኞቹ የትግሉ መሪዎች ዛሬም በህይወት አሉ፡፡ የእነዚህ ኃይሎች ዋነኛ ሥራ ራሳቸውን ከእነዚህ ንጹሐን የትግራይ ዜጎች ጀርባ በመሆን ወጣቱን ለጦርነት የሚማግዱበትን መንገድ መፈለግ ነው፡፡ በዚህም በተለይ ህዝቡ ከሌላው ወንድምና እህቶቹ ጋር በሰላም እንዳይኖር በተለያዩ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎች በማወናበድ ዋስትና እንዳይሰማው በማድረግ እና እነሱ ባዘጋጁት የጦርነት መንገድ ውስጥ በማስገባት ለእሳት ሲማግዱት ኖረዋል፡፡ ከዚህ አልፎ አንዳንድ ጊዜ ራሳቸው በሚያዘጋጁት ወጥመድ ህብረተበሱ በደርግ ኃይሎች እንዲመታ በማድረግ ህብረተሰቡን ሰላም እንዳይሰማው ለማድረግ የሄዱበት መንገድም ሴረኝነታቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ ለዚህም የሃውዜን ጭፍጨፋ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
በዚህ ዓይነት ሁኔታ ለዓመታት ህይወቱንና አካሉን ከሌሎች ወንድም እና እህት የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ገብሮ ነፃነቱን የተቀዳጀው የትግራይ ህዝብ ግን በድሉ ማግስት የጠበቀውን ልማትና እድገት ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ይባስ ብሎ ለአፈናና ለከፋ ድህነትና ልመና ተዳርጎ ቆይቷል፡፡
በትግሉ ወቅት ለድሉ መገኘት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አርሶአደሮች፣ ለትግሉ ሲሉ ትምህርት ያላገኙ ዜጎችና አካል ጉዳተኞችም ገና በማለዳው በትግሉ ማግስት የተከዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ የማፍያው ቡድን በስሙ የመሰረተውና ለህዝቡ አንዳችም ፋይዳ ሳይሰጥ የጁንታው ብቸኛ ሀብት ሆኖ የቆየው ኤፈርት ተጠቃሽ ነው፡፡
ይህ ግዙፍ ድርጅት በህዝብ ስም ከውጭ በተገኘና ከራሱ በተዘረፈ ሀብት ሲመሰረት በጦርቱ ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖችና በጦርነቱ ጧሪና ቀባሪ ላጡ አረጋውያን እና ወላጆቻቸውን ላጡ ሕፃናት መርጃ በሚል ነበር። በሂደት ግን መስመሩን ስቶ የጥቂት የጁንታው አባላት መንደላቀቂያ፤ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለሽብር ተግባር እንዲውል ተደረገ፡፡ ከሁሉ በላይ አሳዛኙ ደግሞ እነዚህ አካላት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የዘረፉትን ሀብት ይዘው አርፈው እንዲቀመጡ ዕድል ቢሰጣቸውም፤ አሻፈረኝ በማለት ዳግም ህዝቡን ለሌላ ጦርነት ሲያዘጋጁ ቆይተው ሀገር ሉአላዊነት መገለጫ በሆነው የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በመሰንዘር ክልሉን የቶርነት አውድማ ለማድረግ አቅደው ሠርተዋል፡፡ እንደለመዱት ልጆቻቸውን ከባህር ማዶ አሻግረው እነሱ ከኋላ ሆነው የደሃውን ልጅ ለሌላ ጦርነት አሰልፈዋል፡፡
“አበው ስትሄድ የመታህ ድንጋይ ስትመለስ ከመታህ ድንጋዩ አንተ ነህ” እንደሚሉት እነዚህ ስግብግብ ጁንታዎች ታዲያ እንደለመዱት ቀደም ሲል ያታለሉት ህዝብ ዳግም የሚያታልሉትና ከጎኑ የሚያሰልፉት መስሏቸው ወደማይወጡት ትንኮሳ በመግባት ሞታቸውን አፋጥነዋል፡፡ ህዝቡ እውነተኛ ማንነታቸውን በመረዳቱ እና በናንተ የጥፋት ድግስ አይመለከተኝም በማለቱ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተንኮታኩተው ላይነሱ ወድቀዋል፡፡ እነሆ በአሁኑ ወቅትም ጁንታውን የማደንና ክልሉን መልሶ የማልማት ሥራ ተጀምሯል፡፡ በአንዳንድ ከተሞችም ጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮችን እየሾመ ህዝቡ ፊቱን ወደልማት እንዲመልስ እያደረገ ይገኛል፡፡
የትግራይ ህዝብ ልክ እንደሌሎች ክልሎች በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ያሉበት ነው፡፡ እዚህን ችግሮች ለመፍታት ደግሞ ዜጎች ከመንግሥት ጎን በመሆን ክልሉን ለማልማት ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዓመታት አፍኖ ያኖረው ጨቋኝ ስርዓት እንዳይመለስም አካባቢውን በንቃት በመጠበቅና ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በማድረግ መሥራት ላይ ሊረባረብ ይገባል፡፡
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎችም በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ህብረተሰቡን ለሰላም እና ለልማት በማንቀሳቀስ የትግራይ ህዝብ ከችግሮቹ ተላቆ ወደብልጽግና እንዲጓዝ የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል፡፡ አሁን ሰንኮፉ ጁንታ በመነቀሉ ዋነኛው ጠላት ድህነት ብቻ ሆኗል፤ ድህነትን መዋጋት ደግሞ ቀጣዩ የትግራይ ህዝብ ዋነኛ የቤት ሥራ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 27/2013 ዓ. ም