
አዲስ አበባ፦ በሀገሪቱ ካሉ 22 ሺህ የጤና ተቋማት 6 ሺ የሚሆኑት ከለውጡ ወዲህ የተገነቡ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 42ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ትናንት ተካሂዷል። በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጤና ተቋማትን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያም፤ በሀገሪቱ ካሉ ከ22 ሺህ ገደማ የጤና ተቋማት መካከልም 6 ሺህ ያህሉ ከለውጡ ወዲህ የተገነቡ ናቸው፤ የግል ዘርፍ የሕክምና ተቋማትም እየተስፋፉ ነው። ሆኖም አሁንም ችግር አለ፣ ከመሠረተ ልማትና ከጤና ባለሙያዎች ጥያቄ አንጻር ምላሽ እየሰጠን መጓዝ ያስፈልጋል ብለዋል።
ማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅንን በማስፋት የጤና ሥርዓቱን ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
በትምህርት ረገድም በዚህ ዓመት 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሕፃናትን በቅድመ መደበኛ ትምህርት ተቀብለናል። 26 ሺህ ደግሞ የልዩ ፍላጎት ሕፃናት ናቸው። በዚህ ልክ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች መገንባትና መምህራንን ማፍራት ላይም ሠርተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር፤ የመምህራን ልማትን በሚመለከት ወደ 68 ሺህ መምህራን ሠልጥነዋል፤ ዘንድሮ 80 ሺህ መምህራን በትምህርትና መማር ማስተማር ይሠለጥናሉ ብለዋል።
30 ገደማ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ መሆኑን ገልጸው፤ ማኅበረሰቡ በትምህርት ለትውልድ ባዋጣው ገንዘብ፤ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመጽሐፍና ትምህርት ጥምርታን ማሟላት ተችሏል። እነዚህን ተግባራት እያጠናከርን ስንሄድ ተጨባጭ ውጤት እንደሚመጣም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው እንደገለጹት፤ የትምህርት ቤት ግንባታ ለትምህርት ሚኒስቴር የተሰጠ ኃላፊነት ባይሆንም የትምህርት ጥራትን ለማምጣት ሲባል ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች ምሳሌ የሚሆን ሞዴል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን እየገነባ ነው። በተለይ ማኅበረሰቡ ትምህርት ለትውልድ በሚል ባዋጣው ገንዘብ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
46 ሚሊዮን መማሪያ መጽሐፎች ታትመው ለሁሉም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለአንድ ተማሪ አንድ መጽሐፍ በሚል መጽሐፍ ተሰጥቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በኩል ያለው የመጽሐፍ ሥርጭት ላይ ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ገለፃ፤ አራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል። 29 ሺህ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተገንብተዋል። ለእነዚህ ትምህርት ቤቶችም መምህራን ተቀጥረዋል። ይህም የሚደረገው ትውልድን ለመቅረጽና ለማሳደግ ነው።
ልጆች 10 ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት የሚያገኙበትን ሥነ ምኅዳር የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ በዚህ እድሜ መሠረት ያለው ሥራ መሥራት ከተቻለው ብቃት ትውልድ መፍጠር ይቻላል። ይህንንም እየሠራንበት ነው ብለዋል።
አጠቃላይ በትምህርት ዘርፉ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ሲጠናከሩ የትምህርት ጥራትን ማሻሻል እንደሚቻል ተናግረው፤ በጦርነት የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን በመጠገን አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 27 ቀን 2017 ዓ.ም