ትናንት የራሱን የጊዜ ስልት አልፎ ለዛሬ ጥላ የሆነበትን እውነታ ለማረም!

ልዩነቶች፤ በልዩነቶች ውስጥ ራስን አግዝፎ ማየት፤ ለራስ ሃሳብ የገዘፈ ቦታ ሰጥቶ መንቀሳቀስ፤ የራስን ሃሳብ አልፋ እና ኦሜጋ አድርጎ መውሰድ ወዘተ በሰው ልጆች የዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴ ተገማች ሰብዓዊ እውነታ ነው። በዚህ መልኩ የሚፈጠሩ ልዩነቶችን ኃይልን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች በሌላኛው ላይ ለመጫን የሚደረጉ ጥረቶችም ከሰው ልጆች ጋር ዘመናትን የተሻገሩ ናቸው።

በቀደሙት ዘመናት ተፈጥሯዊ የሆኑ ልዩነቶችን፤ አቻችሎ እና እንደ መልካም ተፈጥሯዊ ስጦታ አድርጎ መውሰድ የሚያስችል የአስተሳሰብ ልዕልና መፍጠር ባለመቻሉ የሰው ልጅ ለብዙ ጥፋቶች እና ውድመቶች ተዳርጓል። ከግለሰባዊ አለመግባባት ጀምሮ በቡድናዊ እና ማኅበረሰባዊ አለመግባባቶች የብዙ አንገት አስደፊ ታሪኮች ባለቤት ሆኗል።

ይህም ሆኖ የሰው ልጅ ትናንቶችን ቆም ብሎ የሚያስብበት እና የሚመዝንበት ፍጥረታዊ ማንነት ባለቤት በመሆኑ፤ ከእያንዳንዷ ጥፋት እየተማረ እና ራሱን በአዎንታዊ ዕይታዎች እየገራ ከብዙ ውድቀቶች እና ውድመቶች ወጥቶ አሁን ላይ ደርሷል። አሁናዊ ማንነቱን ከብዙ የትናንት ጥፋቶቹ የተገራ እና የታረመ ነው።

መገራት እና መታረሙም ዕለት ተዕለት በሚመራባቸው የሕይወት መርሆዎቹ እና እነሱ ባጎናጸፉት የአስተሳሰብ ልዕልና የሚመዘን ነው። አሁናዊ የዓለም ሥልጣኔ እና ሥልጣኔው በአዎንታዊ መንገድ ለሰው ልጆች ያበረከተው አስተዋፅዖም የዚህ ተጨባጭ እውነታ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

በየዘመኑ የሰው ልጆች በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች ከገቡባቸው አስከፊ መከራ እና ስቃይ፤ ጥፋት እና ውድመት ወጥተው ዛሬ ላይ የተሻለች የምትባል ዓለም መፍጠር የቻሉት፤ ትናንትን በአግባቡ መጠየቅ እና ላገኙት ትክክለኛ ምላሽ ተገዥ ስለሆኑ፤ ይህንንም የሕይወት መርሕ አድርገው ማስቀጠል ስለቻሉ ነው።

በተለይም አሁን ላይ የበለፀጉ፣ ያደጉ፣ የተሻሉ …ወዘተ የሚባሉ ሀገራት እና ሕዝቦች በዚህ ሂደት ውስጥ ያለፉ ናቸው። በአንድም ይሁን በሌላ ብዙ አስጨናቂ ትናንቶችን በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች ለማለፍ የተገደዱ፤ ብዙ አንገት የሚያስደፉ፣ የሚያስቆጩ፣ ባልተፈጠሩ የሚሏቸውን ትናንቶች ያሳለፉ ናቸው።

እርስ በርሳቸው ጦር ሰብቀው ወንድም ወንድሙን እየገደለ የፎከረባቸውን፤ በተዛቡ አስተሳሰቦች እና ጽንፈኛ አመለካከቶች ከራሳቸው፣ ከቀጣናቸው አልፈው ለዓለም ስጋት የሆኑ ታሪካዊ አጋጣሚዎችን ያስተናገዱ፤ በዚህም የተሻሉ የሚባሉትንና አንገታቸውን ቀና አድርገው የሚያስኬዱ ትናንቶቻቸውን ጭምር ያጡ ናቸው።

ከነዚህ ታሪካዊ አጋጣሚዎች ወጥተው ዛሬን ማሸነፍ የቻሉት ትናንቶቻቸውን እና የትናንት የአስተሳሰብ መዛነፎቻቸውን ማረም የሚያስችል ማኅበረሰባዊ መነቃቃት መፍጠር በመቻላቸው ነው። ትናንትን እስከ ተዛነፈው አስተሳሰቡ ተቀብለው በዚህ የጠለሸን ነገ መፍጠር አንችልም በማለታቸው ነው።

ትናንት የራሱን የጊዜ ስልት አልፎ ለዛሬ ጥላ እንዳይሆን የሚያስችል መነቃቃት፤ ለዚህ የሚሆን ማኅበረሰባዊ መነሳሳት መፍጠር በመቻላቸው ነው። ትናንትን አርሞ ዛሬን ተንከባክቦ፤ ነገን የተሻለ ማድረግ የሚያስችል የታረመ እና የተገራ አስተሳሰብ መፍጠር ስለቻሉም ነው። ይህንንም የማንነት ግንባታ መሠረት አድርገው ስለሠሩ ነው።

ዛሬን ከትናንት ተሻጋሪ በሽታ ማከም፤ ዛሬን በራሱ ማንነት ተቀብለው፤ ነገን ዛሬ ላይ መሥራት የሚያስችል የትውልዶች መነቃቃት መፍጠር እና በትውልዶች መካከል ማስቀጠል በመቻላቸው ነው። ዛሬን በትናንት ከማስታመም ወጥተው ዛሬን ከትናንት በሽታ መታደግ ላይ በመረባረባቸው እና በዚህም ስኬታማ በመሆናቸው ነው።

ይህንን ዓለም አቀፍ ተጨባጭ እውነታ ዓይናችንን ከፍተን ለማየት የምንገደድበት አሁናዊ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ነን። የጀመርነውን ድህነትን ታሪክ የማድረግ አዲስ የታሪክ ጉዞ በስኬት ለመወጣትም ሆነ በትውልድ መካከል በብዙ መሻት የሚጠበቀውን ሀገራዊ የመነሳት ዘመን ለማቅረብ እና ከወደቅንበት ቆመን ለመሄድ ለዚህ እውነት ዓይናችንንና ልቦናችንን ልንከፍት፤ ያየነውም አምነን ተቀብለን ለመለወጥ መትጋት ይኖርብናል።

ትናንት የራሱን የጊዜ ስልት አልፎ ለዛሬ ጥላ የሆነበትን እውነታ ማረም፤ ዛሬን ከትናንት ተሻጋሪ በሽታ ማከም፤ ዛሬን በራሱ ማንነት ተቀብለን፤ ነገን ዛሬ ላይ መሥራት የሚያስችል የትውልድ መነቃቃት መፍጠር እና ማስቀጠል መቻል አለብን። ዛሬን በትናንት ከማስታመም ወጥተን ዛሬን ከትናንት በሽታ መታደግ ላይ በመረባረብ፤ በዚህም ስኬታማ መሆን ይጠበቅብናል!

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You