
አዲስ አበባ፡– ከነዳጅ ኩባንያዎች ለመዲናዋ የሚቀ ርበው የነዳጅ ኮታ ፍትሐዊነት የጎደለው መሆኑንና ከተማዋ በሚያስፈልጋት ልክ አለመሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ገለፀ፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከነዳጅ ማደያዎች እና ከነዳጅ ኩባንያዎች ጋር ትናንትና ውይይት ባደረገበት ወቅት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ የነዳጅ ዲጂታል ሽያጫ ቁጥጥር የተጠናከረ በመሆኑ ምክንያት ኩባንያዎች ነዳጅ በስፋት ቁጥጥር ወደ ሌለባቸው አካባቢዎች እየላኩ ነው።
አዲስ አበባ በርካታ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያለባት ከተማ ከመሆኗም በተጨማሪ፤ በሀገሪቱ ካሉ አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን መኪኖች 750 ሺህ የሚሆኑት አዲስ አበባ የሚገኙ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በየቀኑ በርካታ መኪናዎች እቃ ለመጫን ከሌሎች አካባቢዎች ወደ መዲናዋ የሚገቡ መሆኑን ተከትሎ፤ ከሌሎች ክልሎች የበለጠ የነዳጅ ፍላጎት እንዳለ፤ ነገር ግን በሀገር ደረጃ ከሚቀርበው ነዳጅ ኩባንያዎች ለመዲናዋ የሚያቀርቡት ፍትሐዊ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
ወይዘሮ ሀቢባ እንደተናገሩት፤ በታኅሣሥ ወር የነዳጅ እጥረት ሲፈጠር ቶታል እንደ ሀገር ከሚሰጠው ለአዲስ አበባ ሲያቀርብ የነበረው 29 በመቶ ነበር፤ ነገር ግን አሁን ላይ 18 በመቶ ነው፡፡ የተባበሩት ከ16 በመቶ ወደ ሁለት ነጥብ ስድስት ዝቅ አድርጓል፡፡ በተመሳሳይ ሌሎችም ከዚህ ቀደም እያስገቡት ካለው መጠን ቀንሰዋል፡፡ ኖክ ከ23 ወደ 30 ያሳደገበት ሁኔታ ቢኖርም፤ አሁንም ትንሽ ካስገቡት ውስጥ ነው፡፡
እንደ አዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ጥፋት ያጠፉ ነዳጅ ማደያዎችን እንዲሁም ከእነሱ ጋር የተባበሩ ሠራተኞች ከዚህ በፊት ተቀጥተዋል፡፡ ኩባንያዎች ላይ ሪፖርት ቀርቦ የነበረ ቢሆንም፤ የሚተዳደሩት በሀገር ደረጃ በሚመራ አካል እንደመሆኑ፤ ቢሮው የመቅጣት ኃላፊነት ስለሌለው አልተቻለም ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ነዳጅ በተገቢው ልክ ሳይገባ ነዳጅ ማደያዎቹ ላይ በቀን ሁለቴ ቁጥጥር ቢደረግ ለውጥ የለውም ያሉት ኃላፊዋ፤ በቀን እንደሀገር ከሚቀርበው ነዳጅ አንድ ሦስተኛው ለአዲስ አበባ እንዲቀርብ ጠይቀዋል፡፡
በታኅሣሥ ወር ላይ የነዳጅ እጥረት በተፈጠረበት ወቅት የቴሌብር የነዳጅ ግብይት የሚያሳየው 96 ነጥብ 4 በመቶ ነበር፤ አሁን ላይ 54 በመቶ አካባቢ ነው፡፡ ይህም ከዲጂታል ሲስተም ውጭ ነዳጅ እየተሸጠ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህንን በቀጣይ ከቴሌ ብር ጋር በመሆን ነዳጅ ማደያዎቹን የመለየት ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱል ሐኪም ሙሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መንግሥት በ11 ወራት 195 ሚሊዮን ብር የነዳጅ ድጎማ አድርጓል፤ ከመደጎምም በተጨማሪ 526 ሕገወጥ ሥራ ሲሠሩ የተገኙ ነዳጅ ማደያዎች ተቀጥተዋል ብለዋል፡፡
በዘንድሮ ዓመት በ11 ወራት የገባው ነዳጅ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 10 በመቶ ከፍ ያለ መሆኑን በመግለጽ፤ የኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እድገት ስምንት በመቶ እንደሆነና የነዳጅ አቅርቦቱም 10 በመቶ ያደገበት ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰው፤ ይህም እንደ አጠቃላይ ሲታይ አቅርቦቱ ጤናማ መሆኑን ያሳያል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ነገር ግን በሚዲያዎች በተወሩ ወሬዎች አማካኝነት ነዳጅ ይጨምራል በሚል የመደበቅ ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰዋል፡፡
አብዱል (ዶ/ር) በቀጣይ ማደያዎችን ብቻ ሳይሆን፤ እንደ ሀገር ያሉት ነዳጅ አቅራቢ 60 ኩባንያዎች ላይ ክትትል በማድረግ፤ ውል እስከ ማቋረጥ የሚደርስ ቅጣት የሚጣል መሆኑን አፅንዖኖት ሰጥተዋል፡፡
በነዳጅ ማጓጓዝ ሂደት የመሠረተ ልማት ችግር እንዳለ ያመኑት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህን ችግር ለመፍታት በባቡር ትራንስፖርት ነዳጅ ለማጓጓዝ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
እንደሀገር እየቀረበ ያለው የነዳጅ መጠን ከፍላጎት ጋር የተመጣጠነ አለመሆን እና የመሠረተ ልማት ችግር መኖር ከተለያዩ የነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች ተነስቷል፡፡
በተጨማሪም በየጊዜው የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ የካፒታል እጥረት እያጋጠመ እንዳለ፤ የሚተመነው ዋጋ አሮጌ ማሽኖችን ታሳቢ ያደረገ አለመሆኑ፤ መዘግየት እንዲሁም፤ የሚመጣው ነዳጅ አንዳንዴ ከ300 እስከ 800 ሊትር ጉድለት የሚሳይ መሆኑ ከነዳጅ ማደያዎች ከተነሱ አስተያየቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 27 ቀን 2017 ዓ.ም