
አዲስ አበባ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበለትን የ2018 በጀት ዓመት የፌደራል መንግሥት በጀት አፅድቋል።
ምክር ቤቱ 42ኛ መደበኛ ስብሰባው የምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ የ2018 ዓ.ም የፌደራል መንግሥት ረቂቅ በጀት የውሳኔ ሀሳብ እና ሪፖርት አቅርበዋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳቡን በመመርመር የ2018 የፌደራል መንግሥት ረቂቅ በጀትን አፅድቋል። በሪፖርቱ ላይ የቀጣይ በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት በጀት 1 ነጥብ 93 ትሪሊዮን ብር መሆኑ ተመላክቷል።
ከ2018 ረቂቅ በጀት 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር ለመደበኛ ወጪ፣ 415 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ወጪ፣ 315 ቢሊዮን ብር ለክልል መንግሥታት ድጋፍ እንዲሁም 14 ቢሊዮን ብር ለክልሎች የዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈፀሚያ ድጋፍ የሚውል እንደሆነ ተገልጿል።
በበጀቱ 1 ትሪሊዮን ብር ወይም 73 በመቶውን ከታክስ ገቢ 236 ቢሊዮን ብር ከልማት አጋሮች ቀሪውን ደግሞ ከፕሮጀክቶች ድጋፍና ልዩ ልዩ ገቢዎች ለማግኘት ታቅዷል።
በጀቱ ከጥቅል ሀገራዊ ምርት አንፃር ያልተጣራ የበጀት ጉድለት 2 ነጥብ 2 በመቶ እንዲሁም የተጣራ የበጀት ጉድለት 1 በመቶ መሆኑ በሪፖርቱ ላይ ተገልጿል።
መንግሥት የበጀት ጉድለቱን በቀጥታ ከብሔራዊ ባንክ ብድር በመውሰድ ሳይሆን በግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ እንደሚሸፍንም ተጠቁሟል።
የ2018 በጀት የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን እና የ10 ዓመቱን መሪ የልማት እቅድ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተዘጋጀ እንደሆነም በሪፖርቱ ላይ ቀርቧል።
በሳሙኤል ወንደወሰን
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 27 ቀን 2017 ዓ.ም