መላኩ ኤሮሴ
የአራራት ሆቴል- ኮተቤ – ካራ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት በ2009 ዓ.ም ሥራው ሲጀመር በሁለት ዓመት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል በሚል ነው ወደ ሥራ የተገባው ።ስድስት ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍነው ይህ ፕሮጀክት 534 ሚሊዮን ብር በጀት ነው የተመደበለት። በ2011ዓ.ም ይመረቃል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት መንገድ ግን ዛሬ ድረስ የውሃ ሽታ ሆኗል።
ፕሮጀክቱ ከሶስት ዓመት በፊት ድሪባ ደበርሳ እና ተክለብርሃን አምባዬ ለተሰኙ ሁለት ተቋራጮች ተከፍሎ የተሰጠ ሲሆን፤ ከአራራት ሆቴል እስከ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ያለውን ሶስት ኪሎ ሜትር በድሪባ ደበርሳ ሥራ ተቋራጭ ድርጅት ግንባታው እየተከናወነ ይገኛል ።
ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ እስከ ካራ ድረስ ያለው ሶስት ኪሎ ሜትር መንገድ ደግሞ ተክለ ብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ግንባታውን ይዞ ነበር ። የመንገዱን ግንባታ በሁለት ዓመት ለማጠናቀቅ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም እስካሁንም ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ አልተጠናቀቀም ።በተለይም በተክለ ብርሃን አምባዬ ተይዞ የነበረው የፕሮጀክቱ ክፍል ከፍተኛ መጓተት ታይቶበታል ።
የፕሮጀክቱ በጊዜ አለመጠናቀቅ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታ ፈጥሮ ቆይቷል ።በተለይም መንገዱ ተቆፋፍሮ ለረጅም ጊዜ በመቆየቱ ለተለያዩ ችግሮች መዳረጋቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ያነሳሉ። በአካባቢው የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ እና በመንገዱ የሚተላለፉ አሽከርካሪዎችም ለግንባታ ተብሎ የተቆፋፈረው የመንገዱ ወጣ ገባነት በተሽከርካሪ እቃዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ እና ለአላስፈላጊ ወጪ እየዳረጋቸው መሆኑን ያነሳሉ፡፡
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢያሱ ሰለሞን እንደሚሉት፤ መንገዱ ቀደም ሲልም የጥበት ችግር የነበረበት በመሆኑና ማስፋት በማስፈለጉ የግንባታ ሥራው ተጀምሯል ። ሰባት ሜትር የጎን ስፋት የነበረውን መንገድ ወደ 30 ሜትር በማስፋት ግንባታው እየተከናወነ ይገኛል፡፡
ከመንገድ ግንባታው በተጨማሪ፤ ፈጣን የአው ቶብስ መስመር በጋራ የሚገነባለት መንገድ መሆኑን ያነሱት አቶ ኢያሱ በዚህም ምክንያት በርካታ ነዋሪዎችን የማንሳት ሥራ ይጠይቅ ነበር ።በመሆኑም የወሰን ማስከበር ሥራው እጅግ ከባድ ነበር ።በተለይም ለተነሺዎች ቅያሪ ቦታ የማዘጋጀት ሥራ የወሰን ማስከበር ሥራውን አዳጋች አድርጎት ቆይቷል።
መንገዱ በፊት ከነበረው አንጻር እንዲሰፋ በመደ ረጉ ሰፊ የወሰን ማስከበር ሥራ መጠየቁን ይገልጻሉ። ሰፊ የወሰን ማስከበር ሥራ የሚጠይቅ ፕሮጀክት መሆኑ አፈጻጸም ላይ የራሱን አሉታዊ ጫና አሳድሯል ያሉት አቶ ኢያሱ፣ በወሰን ማስከበር እና በተደጋጋሚ የዲዛይን ክለሳ ምክንያት መንገዱ መዘግየቱን ያብራራሉ። ሆኖም የከተማ አስተዳደሩ የመንገዶች ባለስልጣን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት በአሁኑ ወቅት ችግሩን መቅረፍ መቻሉን አብራርተዋል። የተቋራጮች የአቅም ውስንነት ፕሮጀክቱ እንዲጓተት ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ነው።
በድሪባ ደበርሳ የሚከናወነው ከአራራት እስከ ኮተቤ የሚገኘው የፕሮጀክቱ ክፍል ግንባታው በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ሲሆን ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ወደ ካራ የሚወስደው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ላይ የፍጥነት ችግር መታየቱን ያብራራሉ፡፡
ከኮተቤ እስከ ካራ ያለውን የፕሮጀክት ክፍል የያዘው ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን የግል ድርጅት በሚፈለገው ፍጥነት ግንባታውን እያከናወነ ባለመሆኑና ማስተካከያዎችን እንዲያደርግ ማስጠንቀቂያ በተደጋጋሚ የተሰጠው ቢሆንም ተጨባጭ ለውጥ ባለማምጣቱ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ሁኔታውን ተመልክቶ ውሳኔ እንዳሳለፈበት አብራርተዋል፡፡
በዚሁ መሰረት በተክለ ብርሃን አምባዬ ተይዞ የነበረው ከኮቶቤ ሜትሮፖሊታን እስከ ካራ ያለው የመንገድ ፕሮጀክት ውሉ እንዲቋረጥ ተደርጎ በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በራሱ ኃይል ግንባታውን እያከናወነው መሆኑን ይናገራሉ ።
እንደ አቶ ኢያሱ ማብራሪያ፤ የከተማው መንገዶች ባለስልጣን ግንባታውን ከተረከበው ወዲህ ፕሮጀክቱ እየተፋጠነ ነው ።አጠቃላይ ፕሮጀክቱን በተያዘው በጀት ዓመት ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እና ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል፡፡
መንገዱ ሲጠናቀቅ የትራፊክ ፍሰቱን እንደ ሚያስተካክል፣ የህዝቡ የረጅም ጊዜ ቅሬታ እንዲፈታ፣ የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ የላቀ ሚና እንደሚጫወት አቶ ኢያሱ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ነባር ከሚባሉ መንገዶች አንዱ የሆነው የኮተቤ መንገድ አዲስ አበባን ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍሎች ጋር ከሚያገናኙ መንገዶች አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡
ከፍተኛ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች በሚበዛባቸው እንደ ኮተቤ አካባቢ ባሉ ቦታዎች ላይ የሚካሄዱ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተጠናና አዋጭ በሆነ ዲዛይን ቢጀመር የጊዜና የሀብት ብክነት መቀነስ ስለሚቻል ከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሊያደርግባቸው ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 26 ቀን 2013 ዓ.ም