ሰላማዊት ውቤ
ከተሞች ለኢኮኖሚ፣ ለማህበራዊና ለፖለቲካ እንቅስቃሴ የጎላ ሚና አላቸው ። ከተሞች 22 በመቶ በሕዝብ ብዛት፣ 0 ነጥብ 6 በመቶ የቆዳ ስፋት እና 58 በመቶ ሀገራዊ ምርት ድርሻ አላቸው። የክትመት ዕድገት ምጣኔያቸውም 5 ነጥብ 4 በመቶ ነው። ከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚና ብክለት አመንጪ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን ከዚህ አንፃር ለነዋሪዎቻቸው የችግር ምንጮች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመታል።
ከተሞች በአግባቡ ከተመሩ ግን ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊም ሆነ ሁለንተናዊ ዕድገት፣ ለውጥ፣ ፍጥነት፣ ጥራትና ዘላቂነት ጉልህ ሚና ያላቸው መሆኑ አያጠያይቅም። ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመት ውስጥ ብቻ እንኳን በሀገራችን እየተመዘገበ ያለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለአስተዋጿቸው ማሳያ ነው።
ከተሞች ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸውን ሚና በአግባቡ እንዲወጡ ይጠበቅል። ለዜጎቻቸው ምቹ እንዲሆኑም ይታሰባል። ይሁንና እንደ ሀገር ስንቃኛቸው የጉድለት ደረጃቸው ይለያይ እንጂ የትኞቹም ይሄን ሚዛን የደፉ አይደሉም። ዋናው ምክንያት የሀገራችን ከተሞች ለዘመናት እጅግ ኋላ ቀር የአስተዳደር ሥርዓት ውስጥ የመቆየታቸው መዘዝ ነው። በመሆኑም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቱን ተከትሎ የተከሰተውን የከተሜነት ግስጋሴ መቋቋም እንደተሳናቸው በግልፅ ማስተዋል ይቻላል። ለዚህ ከነዋሪዎቻቸው ጋር እንደ ኮሶ የተጣቡት ተግዳሮቶቻቸው አብነቶች ናቸው።
ከነዚህ ችግሮቻቸው መካከል ሰቅዘው የያዝዋቸው የመልካም አስተዳደር፣ የመሰረተ-ልማት፣ የጽዳትና ውበት፣ የሥራ ዕድል እጦት፣ የፍትሃዊነት መጓደል፣ የአካባቢ ብክለት፣ በፕላን ያለመመራት፣ የመኖሪያ ቤትና የትራንስፖርት እጥረት፣ የማያቋርጥ ከገጠር ወደ ከተማ ፍልሰት ይጠቀሳል ።
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪው አቶ ሰናይ ተስፋ እንዳሉን ከተሞች በተለያየ ደረጃ ለመዘመን በሚያካሂዷቸው ግንባታዎች የተቀናጁ አለመሆናቸውነ ነዋሪዎቻቸውን ምቾት ከመንሳት ባሻገር ውበታቸውን ሲያጠለሹት ይታያል። በተለይ የሀገሪቱና የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ መንገድ፣ ቴሌኮም፣ ውሃና መብራት ኃይል ችግራቸው በመገናኛ ብዙሃን ሳይቀር ተደጋግሞ ቢነገራቸውም አሁንም ድረስ ተቀናጅተው በመሥራት ተደራቢ ችግር ፈጣሪ ከመሆን መውጣት አልቻሉም። በብዙ መዋዕለ ነዋይ ዛሬ የተገነባው አስፋልት ነገ በቴሌ ወይም በውሃ መስመር ቁፋሮ ሲፈርስ ማየቱ አልቀረም። ቁጥሩ ይነስ እንጂ በዚህ ጉድጓድ እና ክፍት በሆኑ ቱቦ ለአካል ጉዳትና ሞት የሚዳረጉ በርካታ ናቸው። በግንባታ ምክንያት የእግር መንገዶች በመዘጋታቸውና በመጣበባቸው ለመኪና አደጋ ያጋለጣሉ። ስካቫተሩ፣ ሲኖ ትራኩ እንዲሁም በየቦታው የተደፋው አሸዋና ጠጠር ያደነቃቅፋል። በየአካባቢው የሚካሄዱ የህንፃ ግንባታዎች ከጥንቃቄ ጉድለት ቀን የአጎራባቾቻውን ነዋሪ ከማማረር አልፈው ሌት እንቅልፍ እስከ መንሳትና ለተጎጂነት እስከማጋለጥ ሲደርሱ ማየት ተለምዷል።
ወይዘሮ ተዋበች እጅጉ የመዲናችን አዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው። እሳቸውም ከላይ የተነሱትን ሀሳቦች ያጠናክራሉ። ወይዘሮዋ በሥራ ምክንያት አብዛኞቹን የኢትዮጵያን ከተሞች የማየት ዕድል ገጥሟቸዋል። አዲስ አበባን ጨምሮ ባህር ዳር፣ ሀዋሳ፣ ጅማና መቐለ ከጎበኟቸው የሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ይጠቀሳሉ። በዚህ አጋጣሚ የታዘቡት ከተሞቹ በተገቢው ፕላን ባለመመራታቸው ዕድገታቸው አልተመጣጠነም። ለከተማው ነዋሪ ተገቢ የሥራ ዕድል፣ መኖሪያና መዝናኛ ስፍራ ማቅረብ አልቻሉም። እርስ በእርስም ሆነ ከአካባቢያቸው አልተሳሰሩም። እንደ ሀብታቸው ሚናቸው ያልተለየ፣ በዘፈቀደ የሚጓዙ ሆነው ነው ያገኝዋቸው። በተለይ በየጊዜው ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ የህዝብ ፍልሰት ለከተሞች ራስ ምታት እንደሆነባቸው መታዘብ መቻላቸውን አውግተውናል።
ወጣት ሄኖክ ባዴቦን ሀዋሳ ከተማ ላይ ነው ያገኘነው። እንደ እሱ ዕምነት አሁን በሀገራችን ከተሞች ላይ ጉልተው የሚስተዋሉት ችግሮች የተፈጠሩት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቱን ተከትሎ የተከሰተውን ፈጣን የከተሜነት ዕድገት በአግባቡ መምራት ባለመቻሉ ነው። በእርግጥ ካለፈው ዘመን ኋላ ቀር የአስተዳደር ስርዓት ጋር ሲነጻፀር አሁን ላይ በጣት ከሚቆጠሩ ዓመታት ወዲህ አመራራቸው የመሻሻልና የመዘመን ተስፋ እያሳየ ነው። ቢሆንም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የከተሞቻችንን ውስብስብ ችግር እንዲህ በቀላሉ በአንድ ጊዜ ይፈታል ማለት ዘበት ነው። በመሆኑም አሁንም ላለንበት ክፍለ ዘመን የሚመጥን ውጤታማ የአስተዳደር ሥርዓትን መፍጠር ግድ ይላል። የአመራር ችሎታ ያላቸውን አመራሮች በቦታቸው ማስቀመጥም ይመከራል።
የወጣትነት ጊዚያቸውን በመምህርነት ሙያ በማገልገል አውለው አሁን ላይ ወደ ጎልማሳነት ዕድሜ ለመሸጋገር እየተንደረደሩ ያሉት ደራሲ አሸናፊ መለሰ እንዳጫወቱን በተለይ ህዳር 14 ቀን 1879 ዓ.ም በዳግማዊ አፄ ምኒልክና ባለቤታቸው በእቴጌ ጣይቱ ብጡል የተቆረቆረችው የሀገራችን ዋና መዲና አዲስ አበባ ከሦስት ዓመት ወዲህ መሪዎች ያገኘች ይመስላቸዋል። እስከ 1882 ከመሯት ወልደ ፃዲቅ ጎሹ ጀምሮ ህሩይ ወልደ ስላሴ ከ1910 እስከ 1914 ዓ.ም፣ መኮንን እንዳልካቸው ከ1924 እስከ 1926፤ ራስ መስፍን ስለሺ ከ1934 እስከ 1938 አዲስ አበባን የመሯት እንደነበርም ያስታውሳሉ። ሆኖም ግን የዕድገት ደረጃዋ በፕላን የተመራና ለኑሮ ምቹ ነበር ለማለት ይከብዳል።
በያዝነው ህዳር ወር 134 ኛዋን ዓመት የያዘችውን የሀገራችን ኢትዮጵያና አፍሪካ ዋና መዲና የመምራት ዕድል ያገኙትና ለክፍለ ዘመኑ የምትመጥንና ከዓለም ታላላቅ ከተሞች የምትፎካከር ለማድረግ ደፋ ቀና እያሉ ያሉት 32ኛዋ የመጀመሪያ ሴት ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ የሚል እምነት አላቸው።
ይሄ ማለት ግን ከ2010 በፊት የነበሩት 30 አመራሮች ለከተማዋ ሁለንተናዊ ዕድገት የየራሳቸውን አሻራ አላሳረፉም ህፀጾቿን ለመንቀስ አልሰሩም ማለት አይደለም። በተለይም ቀደምቶቹ ከንቲባዎቿ የመጀመሪያውን አስፋልት መንገድ ከመገንባት ጀምሮ ለመጠጥ ውሃ ጉድጓድ እስከ ማውጣት በመድረስ ለደረጃዋ የምትመጥን እንድትሆን በእውቀታቸው ልክ ለፍተዋል። ያኔ የነበረው የንጉሳዊው ስርዓት አሁን ላለውም የመንግስት አስተዳደር ጭምር የምጣኔ ሀብት እምብርት ሊያደርጋት የሚችል አሻራ አሳርፈዋል።
ሆኖም ግን የሀገራችን ከተሞች በደረስንበት የቴክኖሎጂ ዘመን አንፃር ሲቃኙ ብዙ የሚቀራቸው ናቸው። ክፍተታቸውን መሙላት የሚቻለው ደግሞ የከተሞቹ አመራሮች እርስ በእርሳቸው ተገናኝተው አስፈላጊውን ልምድና መረጃ ለመለዋወጥ፣ ለመደጋገፍ፣ የጋራ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ሲችሉ እንደሆነ በመጠቆም ደራሲው አሸናፊ አስተያየታቸውን ያሳርጋሉ።
በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ላቀው አበጀ በሀገራችን ደረጃ ከንቲባዎች በቋሚነት ተገናኝተው ስለከተሞች ጉዳይ የሚመካከሩበት፣ የእርስ በእርስ ትስስር የሚፈጥሩበትና በችግሮች ዙሪያ በጋራ መፍትሄ የሚፈልጉበት መድረክ እስከ ቅርብ ጊዜ አንዳልነበረ ይናገራሉ። ሆኖም በዓለም አቀፍ፣ በአህጉር አቀፍና በቀጣናዎች ደረጃ የተፈጠሩ የተለያዩ የትስስርና የቅንጅት አውዶች አሉ። በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ የከተማ አመራሮችና የሚመለከታቸው አካላት መድረክ ዓለም አቀፍ ዕይታና ግንዛቤ ይዞ የከተሞችን ልማት ለማፋጠን ይረዳሉ። ቢሆንም ሀገሮች የየራሳቸውን ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት አድርገው በጋራ ጉዳዮቻቸው ዙሪያ የሚመክሩበትና መፍትሄዎችን በጋራ የሚያፈላልጉበት መድረክ ቢፈጥሩ በጣም ጠቃሚ እና አስፈላጊም ነው። ምክንያቱም በአገራችን በከተሞች የሚስተዋሉ ችግሮችን በጋራ ለመፍታትና ሁሉን አቀፍ ልማት በከተሞች ለማስመዝገበ እንዲቻል ይረዳል። ከተሞችን የሚመሩ አመራሮች በግል ብቃት ከሚኖራቸው አቅም ባልተናነሰ አንዱ ከአንዱ ልምድ መቅሰምና መደጋገፍ ይገባቸዋል። ይሄን ማድረግ ከተሞችን ውጤታማና ተወዳዳሪ ያደርጋል። ከዚህ አኳያ የእስከ አሁኑ ሂደት ሲታይ ውስንነት እንደነበረው ይጠቅሳሉ።
በኢትዮጵያ ከተሞች ያሉ ከንቲባዎች ተገናኝተው በጋራ የሚመክሩበት፣ ትስስር የሚፈጥሩበት፣ የተሻለ ሥራ የሰሩ ከተሞች ተሞክሯቸውን የሚያካፍሉበት መድረክ መኖር አለበት። ይሄን ዕውን ለማድረግ የሚደጋገፉበትና አዳዲስ ሀሳቦችን በማፍለቅ በከተሞች ለመተግበር ተነሳሽነት የሚወስዱበት የኢትዮጵያ ከንቲባዎች ፎረም ተመስርቷል። ፎረሙ ለከተሞች ሁለንተናዊ ዕድገትና ችግሮቻቸውን በአጭሩ ለመፍታት ጠቀሜታው የጎላ ነው። የፎረሙ አባል ከተሞች የህዝብ ብዛታቸው ከ20 ሺህ በላይ መሆኑም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹልን። በምክር ቤት የተዋቀሩና በከንቲባ የሚተዳደሩ ሁሉም ከተሞች በአደረጃጀት መሰረታቸው አባል የሚሆኑበት ሁኔታ አለ።
እንደ አቶ ላቀው ማብራሪያ እስከ አሁን ከተሞች ለመምራት የተሞከረው በተናጠል ከተማን ብቻ ማዕከል ባደረገ ፕላን ነበር። እሱም ከ74 በመቶ በላይ የተተገበረ አይደለም። እናም ይህን ክፍተት ለመሙላት በህግና ስትራቴጂ ማዕቀፍ ደረጃ ሀገራዊና ክልላዊ ፕላን እንዲኖር ተደንግጓል። በዚህ መሰረትም በ2008 ዓ.ም ሀገራዊ ፕላን ተዘጋጅቶ እንደነበርም ይጠቅሳሉ። ፕላኑ የክልሎችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና አካባቢያዊ ሁኔታን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ ነው።
ፕላኑ ከተሞችን እንደ ሀብታቸው ይለያል። እንተደጋጋፊነትና ትስስር አስፈላጊነታቸውም ያስተሳስርና ተጠቃሚነታቸውን ያሰፋል። የቱ ከተማ ከየትኛው ከተማ ተጣምረው ቢሄዱ የተሻለ እንደሚሆንና ተጠቃሚነታቸውንም እንደሚያሰፋ ያመላክታል። ይህ ፕላን በተወሰነ ደረጃ የኢንዱስትሪ ፓርክ ስራዎችን ለመምራት ማገዙን አቶ ላቀው ያስረዳሉ።
ነገር ግን በተሟላ ደረጃ ልማቱን እንዲመራና ሃሳቡን ወደመሬት ለማውረድ፣ ህጋዊ ድጋፍ ለመስጠት ክልላዊ ስፓሻል ፕላን መዘጋጀት ይኖርበታል የሚል እምነት አላቸው። ይሄም ከተሞች እንደ ልማት ማዕከል የሚኖራቸውን ሚና በመለየትና በማሳደግ ሰፊ ገበያ በመፍጠር የገጠርና ከተማ ትስስር ማጠናከር የሚቻልበትን ዕድል መፍጠር ያስችላል። በትስስር ከባቢ ደረጃ የሚከሰት አላስፈላጊ ፍትጊያና ተቃርኖ ለመቀነስና ከተጻራሪነት ይልቅ ተደጋጋፊነትን ለማጎልበት ይረዳቸዋል።
ከተሞች እንደ ልማት ማዕከል የሚኖራቸውን ሚና በመለየትና በማሳደግ ሰፊ ገበያ በመፍጠር የገጠርና ከተማ ትስስር ማጠናከር የሚቻልበት ዕድልም ይፈጥራል። ከተሞቹ እንዳላቸው ፀጋ በማሳደግ ያለንን ሰብዓዊ ሀብት ወደ ምርት ሃይል ቀይሮ መምራትም ያስችላል። ልማትን አቀናጅቶ በማቀድና በመተግበር ሀብትን በቁጠባ ለመጠቀምና በፍጥነት ለማደግ የሚያስችል ነው። የከተሞችን ሚና፣ የእርስ በርስ እና የከተማ ገጠር ትስስር ለማጠናከር የሚረዳ የልማት ማዕቀፍም ነው።
ለዝግጅቱና ትግበራ የፌደራል ሚናን አስመልክተው እንደተናገሩት ሀገራዊ ፕላን ወደ መሬት ለማውረድ የሚረዱ ተዋረዳዊ ፕላኖች እንዲዘጋጁ ማስተዋወቅና መደገፍ፤ ከክልሎች ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ማከናወን ዋናው ነው።
ክልሎች በሰጡት ይሁንታ መሰረት ለክልሎች የፋይናንስና ቴክኒካል ድጋፍ ማድረግ፤ በዚህ መሰረትም ስራውን በፋይናንስ ለመደገፍ አጋር አካላት ማፈላለግ፣ (ለመነሻ ዓለም ባንክና ሲዳ) ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል። ለፕላን ዝግጅቱ የስራ ቢጋር ማዘጋጀት የተጠናቀቀው በፌዴራል ነው። ሀገራዊ ፕላኑን ወደ መሬት ለማውረድ የሚረዱ ተዋረዳዊ ፕላኖች እንዲዘጋጁ ማስተዋወቅና መደገፍ፤ ከክልሎች ጋር የግንዛቤ ማሰጨበጫ ውይይት ማከናወን እንዲሁ።
የክልልና ከተማ አስተዳደሮች ሚናን አስመልከተው እንዳብራሩት የክልላዊ ፕላን ዝግጅቱን በሙሉ ባለቤትነት መምራት፣ ለልማቱ ፍጥነት ውጤታማነትና ተደጋጋፊነት አስፈላጊ በሆነ ቦታና ሁኔታ በፕላን ዝግጅቱም ሆነ ትግበራ ከሌሎች ክልሎች ጋር መቀናጀት፣ ለስራው በክልል ደረጃ መሪ አቅጣጫ የሚሰጥ፣ ስራውን በበላይነት የሚመራና የሚቆጣጠር ከባለድርሻዎች የተውጣጣ አብይ ኮሚቴ ማቋቋም፣ የክልላዊ ፕላኑ ከሀገራዊ ፕላንና ከነባራዊው የከተሞችና የሴክተር ፕላኖች ያለውን መናበብና መቀናጀት ለማስጠበቅ እንዲሁም የስራውን ጥራት ለመደገፍና ለማገረጋገጥ በክልል ደረጃ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤትና የቴክኒክ ኮሚቴ ማቋቋምና መምራት ነው።
ከተሞች እርስ በርሳቸውና ከአካባቢያቸው ጋር በሚናበብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ከባቢያዊ መሰረተ ልማት ተሳስረውና ተደጋግፈው እንዲያድጉ ማድረግ የሚችለው የተዋረድ ስፓሻል ፕላን ሲኖራቸው በመሆኑ ለዚህ እውን መሆን መትጋት ይገባል።
አዲስ ዘመን ህዳር 26 ቀን 2013 ዓ.ም