ባለፉት 27 ዓመታት የትግራይን ህዝብ ሲመራ ፣ ቆሜልሃለው ሲል የኖረው ወንጀለኛው የህወሓት ጁንታ አንዴም ለህዝቡ ጥቅም ሳያስብ የራሱን ሥልጣን ሲያራዝምና የደለበ ሀብት ሲሰበስብ ከርሟል ። ‹‹ቡድኑ የቆምኩት ለትግራይ ህዝብ ነው፤ የወጣሁት ከትግራይ ህዝብ ነው›› ቢልም በተግባር ግን የጥቂት ቡድኖች መበልጸጊያና የቤተሰብ ስልጣን መቆናጠጫ ሆኖ ቆይቷል።
በትግራይ ህዝብ ስም ያቋቋማቸው የንግድ ተቋማት ባልተገባ መልኩ የሚያገኘውን ከፍ ያለ ገቢ ሳይቀር የኢኮኖሚ አቅሙን ከማፈርጠም ባለፈ ለህዝቡ ያተረፉለት ነገር የለም ። ይልቁንም ራሱን በማፈርጠም ህገመንግስቱን እስከመናድ የደረሱ ተግባራትን ፈጽሟል። ከህግና ሥርዓት ውጪ በክልሉ ምርጫ በማድረግ ጭምር ክልሉንና ህዝቡን ከኢትዮጵያዊነት የማውጣት ስራን ዓላማው አድርጎ ተንቀሳቅሷል ።
የጁንታው ቡድን ሀገራዊ ሆነ ክልላዊ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በመቆጣጠር በህዝብ ላይ አድሎና መድሎ ሲፈጽም፣ በፖለቲካ አቋማቸው ዜጎችን ሲያሳድድ ፣ ሲያስርና ሲገል ኖሯል ። ይህ እውነታ ደግሞ በትግራይ ህዝብ ላይ የከፋ እንደነበር የአደባባይ ሚስጥር ነው ። የክልሉ ህዝብ ከሁሉም በላይ እኔ አውቅልሃለሁ በሚል ለመተንፈስ በሚከብድ ጫናዎች ውስጥ አልፏል ።
ባለፉት 27 ዓመታት ከችግርና ጉስቁልናው ሳይወጣ በስሙ ሲነገድበት ቆይቷል። ከለውጡ በኋላም የለውጡ ተጠቃሚ እንዳይሆን በሴራ የተሞላውን ፍጥረታዊ ስብእናውን ይዞ መቀሌ በመክተም ሶስተኛውን ትውልድ ለእልቂትና ለጥፋት ሲያነሳሳና ሲመለምል ቆይቷል ። በዚህም ለትግራይ እናቶች ተጨማሪ የሰቆቃ ጊዜ ለመፍጠር ብዙ መንገድ ተጉዟል ።
ከስልጣን ተወግዶ መቀሌ በመሸገባቸው ሁለጥ ዓመታት ውስጥ ሊገመቱ የማይችሉ ሀገርና ህዝብን አንገት ያስደፉ ወንጀሎችን አቅዶ አስፈጽሟል። አንዱን ብሄር በሌላው ብሄር ፤ አንዱን ሃይማኖት በሌላው ላይ በማነሳሳት ጭምር በህዝቦች መካከል አለመተማመን እንዲፈጠር ፤ የሀገር ሰላም እንዲደፈርስ አድርጓል።
መንግስት በብዙ ሆደ ሰፊነት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በንግግር እንዲፈታ ያላሰለሰ ጥረት ቢያደርግም ጁንታው በማን አለብኝነት የእብሪት ተግባሩን ቀጥሎበት ጥቅምት 24 ቀን 2013 በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ክህደት ፈጽሟል። የሀገር ዳር ድንበር ጠባቂ ፤ የህዝብ ጋሻ ጃግሬ በሆነው የሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው ጥቃት ለመቀበሩ ምክንያት ሆኗል። በስሙ ሲነገድበት የኖረው የትግራይ ህዝብም ይሄ አጋጣሚ የነጻነት ጮራ ፈንጥቆለታል።
የትግራይ ህዝብ ከዚህ ወንጀለኛ ጁንታ በስሙ ከመነገድ ባለፈ ያገኘው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ የለም። እንዳውም ቀና ብሎ ጥያቄ እንዳይጠይቅ፣ መብቱን እንዳያስከብር ከሌላው ማህበረሰብ በባሰ መልኩ ሲጨቆንና ሲሰቃይ ቆይቷል። ዛሬ ድረስ በምግብ ዋስትና የረጂዎችን እጅ ለማየት የተገደደ ጭምር ነው። አሁን ግን እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በቀጣዩ ሀገራዊ የፖለቲካ ድባብ በብዙሃነት የደመቀ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ አንድነት የሚያጣጥምበት ወቅት ላይ ደርሷል።
ዛሬ ወንጀለኛው ጁንታ ሲያሴር የኖረው ሴራ ሁሉ ተገልብጦ ራሱን ወግቶታል። ከስልጣን አውርዶታል። በማይታመን ሁኔታ ተሸንፎና ተንኮታኩቶ ወድቋል። በአንጻሩ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ነጻ ወጥቷል። በማይደራደርበት ኢትዮጵያዊነቱ ኮርቷል። ይሄንንም ነጻ ያወጣውን የመከላከያ ሰራዊት እንኳን ደህና መጣችሁ ብሎ ተቀብሎ በማስተናገድ አጋርነቱን አስመስክሯል።
ከጁንታው የጥፋት ፕሮፓጋንዳ ሰምተውና ፈርተው ቀያቸውን ለቀው የተሰደዱት ጭምር ወደ መኖሪያቸው በመመለስ ላይ ናቸው። የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ የነበሩትን ጨምሮ የዞንና የወረዳ አመራሩ፣ የልዩሃይልና የሚሊሺያ አባላቱ ሁሉ እጃቸውን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
የትግራይ ክልል የተለያዩ የልማት፣ የዴሞክራሲና የማንነት ጥያቄዎቻቸውን ለመመለስም አሁን በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሞ ወደ ስራ ተገብቷል። ህብረተሰቡ የተነፈገውን መብቱን የሚያጣጥመው ፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄው የሚመለሰው ከእንግዲህ በኋላ ነው። የትግራይ ህዝብም ከፊት ለፊቱ ለሚታየው ብሩህ ተስፋ አጥፊዎች በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ፣ ለውጡም ወደፊት እንዲራመድ እውነቱንም ንጋቱንም ተገንዝቧል።
ወንጀለኛው ጁንታ አሁን ሙሉ ለሙሉ አስተዳደሩን ለቋል ። በምትኩም ጊዜያዊ አስተዳደር በመቋቋም ላይ ነው። ህዝቡን በማረጋጋት የተፈናቀለውን በማቋቋም እንዲሁም የሰላም አየር እየተነፈሰ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የለውጡ ተቋዳሽ መሆን የሚቻልበት መልካም አጋጣሚ ከፊት ለፊት ቀርቧል ። የትግራይ ህዝብ የፈነጠቀለትን ብሩህ ተስፋ በማስተዋል በአግባቡ ሊጠቀምበት ይገባል!
አዲስ ዘመን ህዳር 26 ቀን 2013 ዓ.ም