እየሩስ አበራ
ኢትዮጵያውያን የተዋበ ባህል ተላብሰው በአብሮነት እሴት ተጋምደው ዛሬ ላይ ደርሰዋል ። የእርስ በርስ ትብብርና ህብረታቸው ደግሞ ልዩ መለያቸው ነው ።ትናንት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የታየው ያልተለመደው ተግባር ግን ተለየ ። በኢትዮጵያ ምድር ይሆናል ብሎ ለማሰብ ቀርቶ ለመገመት የሚያዳግት ከህሊና በላይ የሆነ ልብ ሰባሪና አሳፋሪ ድርጊት ተፈፀመ። በህገ ወጡ ጁንታ ህግን የሻረ በዚህ ምድር ተሞክሮ የማያውቅ የጭካኔ ድርጊት ተተገበረ ፡፡
ይህ ህገ ወጥ ቡድን በወገኖቻችን ላይ የፈጸመው ግፍና የጣለው ጠባሳ ታሪክ መቼም አይረሳውም ። ይህ አስነዋሪ ድርጊት ለመግለጽ ቃላት በላይ ነውና ብዙ ቢባልለትም አይገለጽም ። ድርጊቱ እንዲህ ሆኗል ተብሎ ከተነገረለት በላይ ፤ እኛ እሩቅ ሆነን ከሰማነው የላቀ ፤ በቃላት ለመግለጽ የሚከብድ እኩይ ድርጊት መሆኑ ተረጋግጧል ።ህገወጡ ቡድንም የዚህ ተግባር ባለቤት መሆኑን በተግባር ያረጋገጠበት ወቅት ላይ የደረስን ይመስለኛል ።
ዘረኝነት፣ የስልጣን ልክፍት፣ እብደት፣ ጎጠኝነት፣ ዘራፊነት፣ ነፍሰ ገዳይነት፣ ጨካኝነት፣ አሸባሪነት፣ ከፋፋይነት፣ ምቀኝነት፣ ታሪክና አገር ከሀዲነት ዋነኛ መግለጫዎቹ የሆነው ጁንታ፣ እድሜ ልኩን በውሸት ፕሮፖጋንዳ መሠረቱን ያነጸ እስከዕለተ ፍጻሜው የውሽት ፕሮፖጋንዳ እየደሰኮረ አልሞት ባይ ተጋዳይነቱን ቀጥሎ እድሜውን ለአንዲት ሌሊት እንኳን ለማስረዘም ያልማል ።
ባረጀና ባፈጀ ዘመኑን በማይመጥን አስተሳሰብ የሚያራምደው የሽማግሌዎቹ ቡድን እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቅል በሚል ራስ ወዳድነት ስሜት ተለክፎ ፤ እኔ ከሌለሁ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች በሚል ፈሊጥ ራሱን የኢትዮጵያ ፈጣሪ በማስመሰል ፈላጭ ቆራጭ እና አድራጊ ፈጣሪ ሆኖ ቆይቷል ። በስልጣን የኖረበት ዘመን አልበቃ ብሎ የስልጣን ጥሙን ሊወጣ የሚችልበትን እሳቤ እያሰበ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ሲያናፍስ እና ሀገሪቷን በሁከት ሲንጥ ህይወቱን ፈጅቷል፡፡
ሀገር የመምራት እድሉን አግኝቶ በስልጣን በነበረባቸው ዓመታት ያሻውን ሲፈጸም ሀገር ሲዘርፍና ሲበድል ቆይቶ ከስልጣን ከለቀቀለ በኋላም ለውጡን ባለመቀበል መቀሌ ተደብቆ የተለያዩ ሴራዎች ሲጎነጉንና የፈጠራና የሀሰት ድርሰት ሲደርስ ቆይቷል ።የኢትዮጵያን ህዝብ በፈጠራ ወሬ እያሸበረ፤ አብሮ የኖረን ህዝብ የተለያዩ ተቀጽላ ስሞችን በመስጠት ህዝብን ከህዝብ ፤ ብሔርን ከብሔር ፤ ጎሳን ከጎሳ ፤ እርስ በርሱ እያጋጨ በጥላቻ እንዲተያይና እንዲጠራጠር ሲያደርግ ፤ የኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የራሱን እኩይ ተግባር እያራመደ ሊሰሙት የሚቀፍ በደል ፈጽሟል፡፡
ይህም አልበቃ ብሎት የትግራይ ህዝብን ከጎኑ ለማሰለፍ «ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሃል፡፡ »እንዲሉ ጁንታው እራሱ በድሎ ነገር ግን እራሱን የተበደለ በማስመሰል የአዞ እንባ እያነባ የሀሰት ፕሮፖጋንዳውን በማሰራጨት በሀገር ውስጥ ሆነ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ለመሳብ ሲሞክር እንደነበር ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡
“እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል” እንደሚሉት አበው የተሰወረ የመሰለው ተግባሩ በአደባባይ አፍጥጦና አግጥጦ ብቅ ብሎ ሊሰወር፤ ሊደበቅ የማይችል የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ ድፍን ኢትዮጵያውያን አስደመመ፤ ድብቁ ሴራው ይፋ ወጥቶ ለዓለምም ትንግርት ሆነ ።
እነዚህ ከሰው አምሳል ተፈጥረው የሰው መልክ ያላቸው ነገር ግን ህሊና ያልተበጃላቸው የጁንታው ቡድን አባላት በሰው ሊፈጸም የማይችል ከሰይጣን ተግባር በላይ የገዘፈ ድርጊት በሰሜን እዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ከፈፀሙ በኋላ የሰውን ደም መጠጣት ሱስ ሆኖባቸው በማይካድራው የሚኖሩ ንጹሃን ዜጎችን በመጨፍጨፍ አውሬነታቸውን በድጋሜ አስመሰከሩ ። በዚህም ኢትዮጵያ ዳግም ቀና እንዳትል ለማድረግ ሞክረዋል ።የፈጸሙት ዘግናኝ ተግባራቸው ሳያሳፍራቸው እንደ ወንፊት በሚያሽከረክሯቸው በሚዲያዎቻቸው የውንብድና ተግባራቸውን በጀግንነት ሲደሰኩሩ መስማት የቅርብ ቀናት ትውስታችን ነው ።
መንግሥት ሲወስድ የቆየውን ህግ የማስከበር እርምጃ ዘር የማጥፋት ዘመቻ ነው እያሉ ፕሮፖጋንዳ በማስራጨት እስከ እንጥፍጣፊ ህይወታቸው ድረስ ህዝቡን ውሸት ለመጋት ሲሞክሩ አይተናል ። መከላከያ ሠራዊት የትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች ከጁንታው ነጻ አወጣሁ ባለበት ወቅት እነሱ በሚዲያዎቻቸውና በውጭ ጋሻ ጃግሬዎቻቸው አማካኝነት የሀሰት ፕሮፖጋንዳ እየነዙ የእነሱን ማሸነፉና የበላይነት ሲደሰኩሩ ታይተዋል ።በዚህም ጁንታው ጠባይ የኢትዮጵያ ህዝብ ‹‹ሞኝ ባያፍር የሞኝ ዘመድ ያፍር›› ማለቱ አልቀረም ።
ጁንታው ምንም እንኳን ግብዓተ መሬቱ ባይፈጸምም የሽንፈት ጽዋውን ተጎንጭቶ ከመቀሌ እግሬ አውጪኝ ሽሽት ላይ ሆኖ እንኳን ሲፈጠር ጀምሮ የተዋረሰውን የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በማናፈስ የሀገሪቱን የለውጥ ጉዞ ለማስተጓጎል ያለ የሌለ ሃይሉን እየተጠቀመ ይገኛል ።
የዚህ ጁንታ ዘግናኝ ድርጊት ተነግሮ አያልቅምና ትናንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ ልዩ ስብሰባ ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ እስከዛሬ ስላለው የፅንፈኛው ቡድን አስመልክቶ የሰጡት ማብራሪያ ‹‹የባሰ አለና ሀገርህን አትልቀቅ›› የሚለውን የሀገሬ ሰው አባባል አስታወሰኝ ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ጁንታ ቡድን ከተናገሩት አፍ አስከፍቶ ከሚያስቀር ንግግር ውስጥ ለጆሮ ሰቅጣጭ የሆኑት የጁንታው ተግባራት በርካታ ናቸው። ከእነዚህም ቡድኑ ለሁለት ዓመት ተኩል በሀገሪቱ የሚከሰቱ ዋና ዋና ግጭቶችን በመቀስቀስ ሕይወት እንዲቀጠፍ፣ ንብረት እንዲወድም ማድረጉን የሚያወሳ ነው። በዚህም ከለውጡ በኋላ በኢትዮጵያ ቢያንስ 113 ግጭቶች ተከስተዋል ። በኦሮሚያ 37፣ በአማራ 23፣ በቤኒሻንጉል 15፣ በአዲስ አበባ 15፣ በጋምቤላ ሰባት ግጭቶች መከሰታቸውንና ከግጭቶቹ ጀርባም የቡድኑ እጅ እንደነበረበት ብዙ ማሳያዎች አሉ።
ጁንታው እዚህም እዛም በሚፈጥራቸው ማተራመሶች መንግሥት ጊዜውን በማልቀስና መቅበር እንዲያሳልፍ ና ወደ ልማት ፊቱን እንዳይመልስ ከፍተኛ ሴራ ሲሸርብ መቆየቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። በፋይናንስ፣ ሚዲያና ኔትወርክ በመጠቀም የብሄርና የሃይማኖት ግጭት እንዲፈጠር፣ የተጋመደ ሕዝብ እርስ በእርስ እንዲጠራጠርና አብሮ እንዳይኖር መደረጉንም ገልጸው፤ በሁሉም ክልሎች ግጭቶች ቢኖሩም በትግራይ ብቻ ግጭት እንዳልነበረ፤ በተመሳሳይ ክልል ከክልል ጋር ግጭቶች የነበሩ ሲሆን ትግራይ ግን ከማንም ክልል ጋር አለመጋጨቱን የጠቀሱበት ነበር። የዚሁ ሁሉ ድርጊት ፈጸሚና አስፈጻሚው ጁንታ እጁን ለመንግስት ሲሰጥ ገና ያልተሰሙ በርካታ ታሪኮች እንደምንሰማ የሚያጠራጥር አይደለም ።
በመጨረሻም በመንግስት በኩል እየተወሰደው ያለው ትግራይን መልሶ የማቋቋም ስራ ጎን ለጎን ጁንታው እኩይ ዓለማውን ከግብ ለማድረስ ያመቸው ዘንድ በርካታ ርዝራዞች አስቀምጧል ።በመሆኑም የድል አድራጊው የጀግኖቻችን ትኩስ ደም ሳይበርድ የጁንታውን ሰንኮፍ መንቀል እድልና ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ። የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት በዚህ ታላቅ ድል ምክንያት እንዲህ እንደተቀጣጠለ እግር በእግር የሚተካኩ ፈጣን ለውጦች ማሳየት አለበት ባይ ነኝ፤ አበቃሁ፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም