“በእጃችን ያለውን ሁሉ የመጠቀም ጥሪ”
ኮሮና ቫይረስ የሚባል አደገኛ ወረርሽኝ መከሰቱንና የዓለም የጤና ስጋት መሆኑን አስመልክቶ በአገራት አባልነት አማካኝነት የሰው ልጆችን ጤና በበላይነት የመጠበቅ ኃላፊነት የተሰጠው የዓለም የጤና ድርጅት ከዛሬ ስድስት ወራት በፊት ጥር 30 ቀን 2020 አስቸኳይ ጉባኤ በጠራበት ወቅት ዓለም ላይ የነበሩት የታማሚዎች ቁጥር ከመቶ አይበልጥም ነበር። “በበሽታው ከተያዙት ሰዎች ውስጥም አብዛኞቹ ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገኘባት የቻይናዋ የሁዋን ከተማ የነበሩ ሲሆን ከዚያች አገር ውጭ በወረርሽኙ ምክንያት የሞተ ሰውም አልነበረም” ይላል ከትናንት ወዲያ ከወደ ጀኔቫ የተሰማው የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ዘጋቢዋ የሊዛ ሽላይን ዜና። ሆኖም በብዙ መልኩ ዓለምን እንደገና አፍርሶ እየሰራት የሚገኘው “ግዙፉ-ሚጢጢ” ቫይረስ ኮሮና ከአስራ ሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለመያዝ፣ ከ750 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ህይወታቸውን በመንጠቅ ሰው ከማይኖርባቸው ከሁለቱ የአርክቲክና አንታርክቲካ አህጉራት በስተቀር መላውን ዓለም በቁጥጥሩ ሥር ለማዋል የወሰደበት ጊዜ አንድ መቶ ሰማንያ ቀናትን ብቻ ነው።
ወረርሽኙ ከዚህም በላይ እየተባባሰ ሊሄድ እንደሚችል የሚያስከትለው ጉዳትም እጅጉን የከፋ ሊሆን እንደሚችል የህክምና ጠቢባኑ ያስጠነቅቃሉ። አሁን ላይ በየአገሩ በተጨባጭ እየታየ ያለው ሁኔታም የሚያሳው ይህንኑ እውነታ ነው። እናም ጉዳዩ በእጅጉ ያሳሰባቸው እና በዚህ ቀውጢ ሰዓት ደርጅቱን የመምራት ዕድል የገጠማቸው (የተገጣጠመባቸው ቢባል ይቀላል) የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኢትዮጵያዊው ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምም ወረርሽኙ ከተከሰተ ጀምሮ ሰሞኑን ለአራተኛ ጊዜ በጠሩት አስቸኳይ ጉባኤ “ሁኔታው አሁንም ከፊታችን ከባድ ጊዜ እየጠበቀን መሆኑን የሚያመላክት ነው” ብለዋል። በርቀት መሰብሰቢያ ቴክኖሎጅ አማካኝነት በተደረገው አስቸኳይ ጉባኤ ከሰላሳ ስድስት የሚበልጡ ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ የህክምና ጠቢባንና አማካሪዎች ዓለም አቀፉን ወረርሽኝ ለመታገል የሚደረጉ ብሔራዊ፣ ቀጠናዊና ዓለም አቀፍ ጥረቶችን ለመምራት የሚያግዙ ምክረ ሃሳቦችን አቅርበዋል። ከቀረቡት ምክረ ሃሳቦቹ መካከል አንደኛው ለወርርሽኙ አስተማማኝ ክትባትና መድሃኒት ለመፍጠር በየአገራቱ የሚደረጉትን ጥረቶች ማገዝ ነው።
ሆኖም የድርጅቱ ዋና ዳሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ለቫይረሱ አስተማማኝ የሆነ ክትባትና መድሃኒት መፍጠር ላይ የተጣለውን ተስፋ በሚገባ የሚረዱት መሆናቸውን አመላክተው፤ ይሁን እንጅ ሰዎች በዚህ ብቻ እንዳይተማመኑ መክረዋል። ቫይረሱ ለዓመታት ሊቆይ የሚችልበት ዕድል መኖሩንም ጠቁመው “ከዚያ ይልቅ በእጃችን ባለው መሣሪያ መታገል ይኖርብናል” በማለት የክትባቱ እና የመድሃኒቱ መገኘት ጉዳይ አስተማማኝ አለመሆኑን በማስታወስ አሁንም የተለመዱትን “እጅ ነክ” የመከላከያ መንገዶች ለወረርሽኙ በዋነኛ መፍትሔነት አቅርበዋል።
በስልጣኔ ላይ ሰልጥኖ የቀጠለው ኮሮና
እርግጥ ነው አሁን የምንገኝበት ዘመን ዓለም በከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ እንደደረሰች የሚታሰብበት፣ የሰው ልጅም እጅግ ከፍተኛ በሆነ በተራቀቀ የስልጣኔ ደረጃ ላይ ደርሷል ተብሎ የሚታመንበት ታላቅ የስልጣኔ ዘመን ነው። ለዚህ ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ መፈጠርና የሰው ልጅም በእንዲህ ዓይነት የስልጣኔ ከፍታ ላይ መድረስ ደግሞ ሳይንስና ቴክኖሎጅ በከፍተኛ ደረጃ በማደጉ ነው። ሆኖም ሳይንሱ በከፍተኛ ደረጃ ባደገበት፤ የዓለም ህዝብና የህክምና ሳይንስ በየሴኮንዱ አዲስ ነገረን በሚያፈልቀው፤ በታላቁ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የዕድገትና የስልጣኔ ዘመን ላይ ሆነንም ሰዎች በወረርሽኝ እያለቁ ይገኛሉ። ያኔ በጥንቱ ዘመንስ በወረርሽኝ ምክንያት ዓለም ብትጨነቅ፣ ሰው በበሽታ ቢያልቅ ሳይንሱ ገና ስላላደገ ነበር፤ ዛሬስ? እናም ኮሮና በስልጡኑ ዘመን ላይ መፍትሔ የሌለው ችግር ሆኖ፤ በስልጣኔ ላይ ሰልጥኖ መኖሩን ቀጥሏል።
የሳይንስና የዘመናዊ ሕክምና ውለታ
እርግጥ ነው ሁሌም በማያቋርጥ የለውጥ ማዕበል ውስጥ ሆኖ በዓይነት፣ በብዛትና በጥራት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣው ሳይንስና ቴክኖሎጅ በተለይም ከሰው ህይወት ጋር ተፈጥሯዊ ቁርኝት ያለው የሥነ ህይወት ጥናትና የህክምና (የመድሃኒት) ሳይንስ የሰው ልጅ አሁን ላይ ለደረሰበት ስልጣኔ የአንበሳውን ድርሻ አበርክቷል።
ምክንያቱም ሰው በህይወት ካልኖረ፣ ጤናማም ካልሆነ ምንም ነገር ሊያደርግ አይችልምና የህክምና ሳይንስ ደግሞ ከፈጣሪ በታች ክቡር የሆነውን የሰው ልጆች ህይወት ከተለያዩ አደጋዎችና በሽታዎች ለመከላከልና በጤንነት ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችል የዕውቀት ዘርፍ በመሆኑ በሌሎች ሳይንሶችና በአጠቃላዩ የሰው ልጆች የዕድገትና የስልጣኔ ጉዞ ውስጥ ማዕከላዊውን ሥፍራ ይዞ ስለሚያገለግል ነው። ስለሆነም የሰው ልጆች በምድር ላይ መኖር ከጀመሩበት አንስቶ በጉዟቸው ሁሉ ራሳቸውን ሊጎዱ ከሚችሉ ከማናቸውም ነገሮች ለመጠበቅና በአደጋ፣ በበሽታና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ህይወታቸውን ያለጊዜው ከመነጠቅ ለመታደግ የዘመናቸው ሁኔታና የዕውቀት ደረጃቸው የፈቀደላቸውን ያህል የህክምና ጥበብና ዕውቀትን ሲጠቀሙ ኖረዋል።
እርግጥ ነው ከፈጣሪ በታች የሰው ልጅ ህይወት ያለው በህክምና ዕውቀት እጅ ላይ ስለመሆኑ አስረጅ ፍለጋ መድከም አያስፈልግም። ህይወት ራሷ ምስክር ናት። በቀደሙት ዘመናት የህክምና ሳይንስ ዕድገት እንደ አሁኑ ባለመሆኑ እንደ ፈንጣጣና ኩፍኝ የመሳሰሉ ዛሬ ላይ ከምድረ ገጽ የጠፉ በሽታዎች ሳይቀር በወረርሽኝ መልክ እየተቀሰቀሱ ህዝብን ይጨርሱ ነበር። ከአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ወዲህ ግን ሳይንስና ቴክኖሎጂ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ የህክምና ሳይንስም ከጊዜ ወደ ጊዜ እተሻሻለና እያደገ በመምጣቱ በርካታ የህይዎት ጥፋቶችን ማስቀረት ተችሏል።
እናም እንዲህ እንዲህ እያለ ህክምና ከሚገጥሙት ፈተናዎች እየተማረ፤ አዳዲስና ምርጥ ተሞክሮዎችን እየቀመረ፣ በየጊዜው ራሱን እያሻሻለ፣ በየዘመኑ አመርቂ ድሎችን እያስመዘገበ፣ በተለይም ባለፉት ሁለት መቶ ዓመታት ከፍተኛ ዕድገት በማሳየት እንደ ኩላሊት ዓይነት እጅግ ጠቃሚና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልጉ ውስጣዊ ብልቶችን ሳይቀር ነቅሎ እስከ መትከል የሚያስችል ውስብስብ የረቀቀ ጥበብ የተሞላበት የዕድገት ደረጃ ላይ ደርሷል።
በአጭሩ በአሁኑ ሰዓት የህክምና ዕውቀት የእመርታ ዘመን ላይ ደርሷል ቢባል ማጋነን አይሆንም። ያም ሆኖ ግን ዛሬም ድረስ ዓለምን በአንድ እግሩ አስቁመው የሚያስጨንቁ መድሃኒት ያልተገኘላቸው እንደ ኮሮና ዓይነት ገዳይ ወረርሽኞች ባልጠፉበት ሁኔታ የሳይንሱ ዕድገት ምልዑ ነው ለማለት ያስቸግራል።
ምክንያቱም የዘመናዊው ህክምና ዕድገት መገለጫ ምልክት ተደርጎ የሚወሰደው ወረርሽኞችንና ተላላፊ በሽታዎችን የመቆጣጠር ሥራ ከምዕተ ዓመት ዕድገት በኋላ ዛሬም በእነዚህ ችግሮች ምክንያት ዓለምን ከጥፋት መታደግ አልቻለምና! እንዴያውም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ከእስካሁኑ ጊዜ ሁሉ በላይ ዛሬ ዓለማችን በከፋ ጭንቀትና በከባድ ፍርሃት ውስጥ ትገኛለችና!
ከእጃችን በተጨማሪ እጃችን ላይ የሚገኙ የመዳኛ መንገዶች
የህክምና ዕውቀት እጅግ ጥንታዊ መሆኑን የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። የባህል ህክምና ከጥንት ጀምሮ አሁንም ድረስ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ከሰው ልጆች እኩል ዕድሜ ያለው ታላቅ ዘመን አይሽሬ ጥበብ ነው። ዘመናዊው የህክምና ሳይንስ ተወልዶ ያደገውም ከባህላዊው የህክምና ዕውቀት ለመሆኑ ሁሉም የዘርፉ ምሁራን ይስማሙበታል።
ዘመናዊው የህክምና ሳይንስ ሊሻገራቸው ያልቻላቸው ችግሮች አብዛኞቹ በባህላዊው የህክምና ጥበብ መፍትሔ ያላቸው መሆናቸውን በጉዳዩ ላይ የተጻፉ ጥንታዊ መዛግብትና ዘርፉን በጥልቀት የመረመሩ የባህል ህክምና ጠበብቶች ይናገራሉ። በተለይም ኢትዮጵያውያን አበው አባቶችና ጥንታዊ ጥበቦችን የመረመሩ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የእስልምና ጠበብቶች ዘመናዊ ህክምና ያልተሳካለትን እንደ ኤች.አይ.ቪ፣ ጉበትና ካንሰር ለመሳሰሉ መድሃኒት የለሽ ገዳይ በሽታዎች ማዳን የሚችል መድሃኒት እንዳላቸው በመገናኛ ብዙሃንና በተለያዩ የህትመት ዘዴዎች ሳይቀር ሲያስተዋውቁ ማየትና መስማት የተለመደ ሆኗል። በዚህ ረገድ ዓለምን እያስጨነቀ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ በተመለከተም በሳይንሳዊ ምርምር በተደገፈ መንገድ የሀገር በቀል እውቀት ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር በማቀናጀት ቫይረሱን ለማከም የሚያስችል መድሃኒት በዝግጅት ሂደት ላይ መሆኑን ኦፊሻላዊ መግለጫ መሰጠቱ ይታወሳል። በዚህ መንገድ እየተጋጁ የሚገኙት ሃገር በቀል መድሃኒቶችም መሰረታዊ የምርምር ሂደት በማለፍ ተደጋጋሚ የቤተ ሙከራ ሞዴሊንግ ሂደቶችን በስኬት ማለፋቸው መገለተጹም አይዘነጋም።
ምርምሩ የኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ መከሰቱ ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ ከተለያዩ በሃገር ውስጥና ከአገር ውጭ ከሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ሲካሄድ የቆየ ሲሆን ተደጋጋሚ የምርመር ሂደት አልፎ ወደ ምርት እና ቀጣይ የእንስሳት ፍተሻ እና ክሊኒካል ፍተሻ ሥራዎች እንዲሸጋገር መደረጉንም ሰምተን ነበር። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያዊያን የባህል ሐኪሞች ጋር እና የህክምና ተመራማሪዎች ጋር በመሆን የሀገር በቀል እውቀቶችን በሳይንሳዊ ሂደቶች በማሳለፍ ለዘመን አመጣሹ ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ -19) ወረርሽኝ ህክምና የተዘጋጀውን መድሃኒት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችላቸውን ሥራ በመሥራት ላይ መሆናቸውን አስታውቀው ነበር። መድሃኒቱ የመከላከል አቅም የሚጨምር፣ መርዛማነት የሌለው እና አዋጭነቱ የተረጋገጠ ነው መሆኑንም የጤና ባለሙያዎቹ አረጋግጠዋል። የምርምር ሂደቱ ተጠናቅቆ ወደ ምርት ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም በጉዳዩ ላይ ተሰጥቶ የነበረው መግለጫ ያመላክታል።
ከወራት በኋላ ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም ደግሞ “በኮሮና ቫይረስና በሌሎች ወረርሽኞች ዙሪያ አገር በቀል የባህል መድሃኒቶች ህክምና ዕውቀቶች ሊያመጡ የሚችሏቸው መፍትሔዎች” በሚል ርዕስ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴር፣ ሚኒስትሮችና የዘርፉ ምሁራን ውይይት አካሂደው ነበር። በዚህም ሃምሳ ስምንት የሚሆኑ የባህል መድሃኒት ህክምና ናሙናዎች ተለይተው በቅደም ተከተል እየተሰራባቸው መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከነገረን ቆየን። በውይይቱ ወቅት የባህልና ቱሪዝም ሚንስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው እንደገለጹት ከዚህ ቀደም ወደ ምርምር ሂደት እንደገቡ የተገለጹት ሃምሳ ስምንት የባህል ህክምና ናሙናወች በቅደም ተከተል ወደ ተግባር እንዲገቡ ሥራ እየተሰራባቸው ቆይቷል። የባህል መድሃኒት ናሙናዎቹ የኮሮና ቫይረስን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ እና ሰዎች በበሽታው ከተያዙ በኋላ ለማከም የሚያስችሉ ተብለው በባለሙያወች እስከመለየት ደረጃ መድረሳቸውንም ሰምተን ነበር።
በዚህም ኮቪድ 19ኝን ለማከም የሚያገለግሉት የባህል መድሃኒቶቹ በማጨስ፣ በማጠን፣ በመቀባትና በመዋጥ የሚወሰዱ ተብለው እንደ ተከፈሉም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተናግረዋል። የበሽታውን ስርጭት ለመግታትና የሚያደርሰውንም ጉዳት ለመቀነስ የአገር በቀል ዕውቀትን መጠቀም ግዴታ መሆኑንም ከተወያዮቹ መካከል አንዷ የሆኑት ዶክተር ሂሩት ካሳው አስታውቀው ነበር። የራሷን አገር በቀል ዕውቀቶች በመጠቀም አሳሳቢውን የኮሮና ወረርሽኝ ከማከም በተጨማሪም አገሪቱ በቀጣይ በባህል መድሃኒት ህክምናዎቿ በዓለም ዙሪያ ለመታወቅ የሚያስችል ይህንንም ማድረግ እንደሚገባ ሚንስትሯ አመላክተው ነበር። በሳይንስ የተደገፈው ዘመናዊ ህክምና የጠቆሙት ሚንስትሯ አገር በቀል የባህል መድሃኒት ዕውቀቶች መሰረት መሆናቸውንም አስረድተዋል። ይህንንም በዘርፉ የተሰማሩ የህክምና ባለሙያወች በትኩረትና በጥልቀት መመርመርና ማጥናት እንደሚገባቸው ተገልጾ ነበር። ማንኛውንም ባህላዊ መድሃኒት ወደ ዘመናዊ መድሃኒት የመቀየር አቅም እንዳለም ከሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር፣ የጤና ሚንስቴርና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተወያዮች አመላክተው ነበር። የባህልና ቱሪዝም ሚንስትሯ ዶክተር ሂሩት፤ “በዘርፉ በቂ ዕውቀትና ሃብት እያለን አዕምሯችን በምዕራባዊ ዕውቀት ጥገኛ ማድረግ የለብንም” የሚል ጠቃሚ መልዕክት አስተላልፈው ነበር።
ለዚህ ጊዜ ያልሆነ መድሃኒት….
ይህ በእጅጉ ሕዝብን የሚጠቅምና አገርንም ከችግር የሚታደግ ታላቅና መልካም ጅምር ነበር። ከተባለ በመቆየቱ “ነበር” ሆነ እንጅ። ሆኖም በፍጹም በነበር ሊቀር አይገባውም። ምክንያቱም ወረርሽኙ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተ በኋላ ሁለት ወራትን ዘግይቶ መጋቢት 10 ቀን 2012 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የአገሪቱን አቅም ባገናዘበ መልኩ ቀስ በቀስ በሃዘኔታ እያጠቃ የቆየ ቢሆንም አሁን ላይ ግን በአደገኛ ሁኔታ ወደፊት እየገሰገሰ ይገኛል። በመሆኑም በአጭር ጊዜ ውስጥ የስርጭት አድማሱን በማስፋፋት ይህ ጽሁፍ እስከተጠናቀቀበት እስከ ትናንትና ወዲያ ምሽት ድረስ ከ19 ሺህ 280 ሰዎችን ይዟል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በቀን ይይዝ የነበረው የሰው ብዛት ከመቶ በታች የነበረው የአገራችን ኮሮና ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ ግን በአንድ ቀን ብቻ 915 ሰወችን በመያዝ ከባዱን ዱላውን እያሳን ይገኛል። እስካሁን ድረስ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ የነበረ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ 336 ደርሷል። በአንድ ቀን የሞቱ ሰወች ቁጥርም ከአንድ ወደ ሃያ ስድስት ከፍ ብሏል።
በሚያስፈራ ሁኔታ ከአሁኑ የሆስፒታሎች አልጋ እየሞላ መሆኑም ተሰምቷል። የችግሩን አስፈሪነት በሚሊኒየም የኮቪድ-19 የህክምና ማዕከል ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ሸምሰዲን ሰኢድ “እስካሁን ድረስ ብዙም ፍርሃት አይሰማኝም ነበር። አሁን ግን አስፈሪው ጊዜ እየመጣ መስላል፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ፈራሁ፤ ምክንያቱም በህክምና ማዕከላችን ውስጥ ያሉት አልጋዎች በታካሚወች ሞልተውብናል፤ ተጨማሪ ህሙማን ለመቀበል ተቸግረናል፣ አንዳንድ ህሙማኖቻችንም ከዚህ ቀደም አይተነው በማናውቀው መልኩ በፍጥነት እየሞቱብን ነው” በማለት ገልፀውታል።
ታዲያ እስከ መቸ ነው በእጃችን ላይ ያሉትን አገር በቀል መድሃኒቶቻችን ለመጠቀም የምንጠብቀው? ወይንስ ማንን ነው የምንጠብቀው? የማንንስ ይሁንታ ነው የምንፈልገው? የመከላከል አቅም የሚጨምሩ፣ መርዛማነት የሌላቸው እና አዋጭነታቸው በባለሙያ የተረጋገጡት እንኳንስ የእኛዎቹ ተፈጥሯዊ መድሃኒቶች በራሳቸው የምግብና የመድሃኒት ቁጥጥር ጉዳት እንዳለው የተገለፀው መርዛማው የወባ መድሃኒት ክሎሮክዊን ጥቅም ላይ ሲያውሉ እነ አሜሪካና ጣሊያን የማንን ይሁንታ ጠየቁ? የሕዝብን ህይወት ለመታደግ ፈቃዱ ራስ ነውና! ነው ወይስ በእጃችን ላይ የራሳችን መዳኛ መንገድ እያለ በፈረንጅ ሳይንስ የተቀመመ መድሃኒት እየጠበቅን እንለቅ? ሳይንስ መድሃኒቱን ባያገኘውስ? ደግሞም እኮ “መድሃኒቱ ላይሳካ ይችላል በእጃችሁ ላይ ያለውን ተጠቀሙ” እየተባልን ነው። በእጃችን ላይ ያለው አማራጭ ደግሞ እነርሱ እንደሚሉን “እጅን መታጠብ” ብቻ አይደለም፤ አባቶቻችን ያወረሱን ከሳይንስ ያልሆነ ነገር ግን ከሳይንስም በላይ የሚበጅ፣ ከጥበብ የሆነ መድሃኒትም በእጃችን ላይ አለና እንጠቀምበት። መድሃኒቶቹ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ወይም የዓለም የጤና ድርጅት ሳይሆን የራሳችን መንግሥት ፈቃድ ይስጥ፤ ልክ እንደ ዓባይ ውሃ በራስ ሀብት ለመጠቀም የማንንም ፈቃድ መጠየቅ አያስፈልግምና! ማንንም ሳትጠይቅ በሀብቷ እና በጥበቧ እንድትጠቀም እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፣ ኮሮናን እና ክፋትን ሁሉ ከዓለም ያርቅ!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2012
ይበል ካሳ