መስከረም 27 ቀን 1965 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥብቅና ለቆሙለት ደንበኛቸው በሚከራከሩበት ወቅት ዘለፋና የፌዝ ንግግር ወጥቷቸዋል የተባሉ ጠበቃ ላይ ፍርድ ቤት ቅጣት ማስተላለፉን የሚገልጽ ዘገባ አስነብቦ ነበር፡፡
ጠበቃው በዘለፋ 500 ብር ተቀጡ
ግራዝማች ደገፉ ባልቻ የተባሉ የሕግ ጠበቃ በተከሰሱበት የዘለፋና የፍርድ ቤት ሥራ በማሰናከል ወንጀል አድራጎታቸው በማስረጃ ስለተረጋገጠባቸው 500 ብር መቀጫ ከፍለው በሦስት ወር እስራት እንዲቀጡ የጭላሎ አውራጃ ፍርድ ቤት ባለፈው ሐሙስ ፈረደ፡፡
የሕግ ጠበቃው የገንዘብና የእስራት ቅጣት የተወሰነባቸው ለባለጉዳዮች በጥብቅና በሚነጋገሩበት ወቅት የዘለፋና የማፌዝ ንግግርን በማሰማት የፍርድ ቤትን ሥራ ለማሰናከል መሞከራቸው ስለተረጋገጠባቸው ነው፡፡
በዚህም አፈጻጸማቸው ወዲያውኑ በዓቃቤ ሕግ በኩል ተከሰው በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 443 መሠረት 500 ብር መቀጫ ከፍለው በሦስት ወር እስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው መሆኑን የጭላሉ አውራጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ግራዝማች ሻረው ደባልቅ ገልጸዋል፡፡
************************
ጥቅምት ሁለት ቀን 1965 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ አንድ ትምህርት ቤት ጸጉራቸውን የሚያሳድጉ እና አጭር ቀሚስ የሚለብሱ ተማሪዎችን አስጠንቅቋል ሲል ተከታዩን ዘገባ አስነብቦ ነበር፡፡
የነቀምቴ ትምህርት ቤት ጸጉር ለሚያጎፍሩ ማስገንዘቢያ ሰጠ
ነቀምቴ ከተማ በሚገኘው አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጸጉራቸውን የሚያሳድጉ ወንዶችና አጭር ቀሚስ የሚለብሱ ልጃገረዶች ተማሪዎች በትምህርት ቤቱ ውስጥ ገብተው እንዲማሩ የማይፈቀድላቸው መሆኑ ትናንት ተገለጸ፡፡
የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ይስሐቅ አንጎሳ በሰጡት ማስገንዘቢያ የወንዶች ተማሪዎች ጠጉር ማሳደግ አቧራ እያጠራቀመ ቆሽሾ ለዓይን ከማስቀየም በስተቀር ምንም ጥቅም የሌለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ልጃገረዶችም ቢሆኑ አጭር ቀሚስ እየለበሱ ለባህል መናጋት ምክንያት ከሚሆኑ ረዘም ያለ ቀሚስ ቢለብሱ የተሻለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ትምህርት ቤቱ ሰሞኑን ያወጣውንም መመሪያ በመከተል ስምንት ጠጉራቸውን አሳድገው የነበሩ ወንዶች ተማሪዎች በአጭር የተስተካከሉ ሲሆን፤ 30 ልጃገረዶችም ለብሰውት የነበረውን አጭር ቀሚስ በመለወጥ ረዘም ያለ ቀሚስ መልበሳቸው ተረጋግጧል፡፡
************************
መጋቢት ስምንት ቀን 1957 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሁለት ጓደኛሞች ከግብዣ በኋላ ሒሳቡን ሁለቱም መክፈል በመፈለጋቸው ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት ተጣልተው አንደኛው ሌላኛውን ተኩሶ መግደሉን የሚገልጽ ተዘገባ አስነብቦ ነበር፡፡
በመገባበዝ ተጣልተው ተጋደሉ
ሰውዬው ጓደኛውን ጋብዞት ሁለቱም ቁርሳቸውን ከበሉ በኋላ «እኔ እከፍላለሁ» አይ «እኔ እከፍላለሁ» በመባባል ተጣልተው ተጋባዡ ጋባዡን በጥይት የገደለው መሆኑን ከቤሩት የተላለፈልን ዜና አመልክቷል፡፡
ጠቡ የተነሳበትን ምክንያት ፖሊስ ሲገልጽ ጓደኛሞቹ አንደኛው ጋባዥ ሆኖ ወደ ሆቴል ቤት ገቡ፡፡ ከተመገቡ በኋላም ተጋባዡ እኔ እከፍላለሁ በማለት ስለተግደረደረ ጋባዡ ሰደበው፡፡ ወዲያውም በጥፊ መታው፡፡ ተመቺው ተጋባዥ ከሆቴል ቤት ሲሮጥ ወጥቶ ሽጉጥ ይዞ መጣ፡፡ ወዲያውም ጓደኛውን ገደለው ብሏል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2012
የትናየት ፈሩ