እንደመንደርደሪያ፤ የዛሬው የፍረዱኝ ተረኞች በኦሮሚያ ክልል በበረህ ወረዳ የሀብሩ ቀኖ ኩራጊዳ እና አቃቂ ቂሌ ገበሬ ማህበር አባላት ናቸው። ቅሬታ አቅራቢዎቹ በ2003 ዓ.ም አላግባብ ስለተወሰደባቸው የእርሻ መሬት አስመልክተው ለዝግጅት ክፍላችን አቤት ብለዋል። አርሶ አደሮቹ አላግባብ ተወስዶብናል የሚሉት የእርሻ መሬት መጠኑ (ስፋቱ) ከ165 ሄክታር በላይ ነው።
አርሶ አደሮቹ ለእርሻ ሥራ ይጠቀሙበት የነበረው መሬት ለተለያዩ የልማት ሥራዎች እንደሚውል፣ በአካባቢው የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይገለጽላቸው እና በብዙ ማግባባት መሬቱ ይወስድባቸዋል። ቆይቶ ግን ለተባለው እና ለተነገራቸው ዓላማ አልዋለም። ይልቅም ለአዲስ አበባ ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃነት እንዲውል ይደረጋል። በአካባቢው ቆሻሻ መደፋት ሲጀምርም ሕዝቡ ቅሬታ ማንሳት ይጀምራል። በ2010 ዓ.ም የተነሳውን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ተከትሎም ቆሻሻው መደፋቱ እንዲቆም ይደረጋል። አሁን ምን ቀራቸው? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም።
ዝርዝር አቤቱታ
ይህ የእርሻ መሬት ምንም አገልግሎት ሳይሰጥ በሽቦ ታጥሮ ከሰባት ዓመታት በላይ መቆየቱን አርሶ አደሮቹ ያስታውሳሉ። በኋላም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተሰበሰበውን ደረቅ እና ፍሳሽ ቆሻሻ መድፊያ ማድረጉን ይናገራሉ።
ሲደፋ በነበረው ቆሻሻ ብክለት መጎዳታቸውን፣ የቤት እንስሳቶቻቸውም በበሽታ መጠቃታቸውን እና ብዙ ጎረቤቶቻቸው በሞት መለየታቸውን፤ ከብቶቻቸውም ማለቃቸውን እንዲሁም ለድህነት መዳረጋቸውንም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ይናገራሉ።
በእርግጥ ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚያመለክቱት፤ በ2010 ዓ.ም የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ ንቅናቄ ተከትሎ ሲደፋ የነበረው ቆሻሻ እንዲቆም ተደርጓል። ስለተወሰደባቸው የእርሻ መሬት ግን ከመንግሥት ምላሽ እንዳላገኙ እና የእርሻ መሬቱ ሊመለስላቸው እንዳልቻለ ያመለክታሉ። አብዛኛው መሬት ቆሻሻ ተደፍቶበት ለማረስ በማያመች ሁኔታ እንደሚገኝም ይጠቁማሉ።
ቆሻሻው ያልተደፋበት ንጹህ እና ሊታረስ የሚችል መሬት ያለምንም አገልግሎት ለ10 ዓመታት ታጥሮ ተቀምጧል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ መሬቱ ቢታረስ ኖሮ ከውጭ ሀገር መንግሥት በግዢ የሚያስገባውን ስንዴ በጥቂት መጠን እንደሚቀንስና ድህነታቸውንም ለመቅረፍ ድርሻ ይኖረው እንደነበርም ነው የሚገልጹት። የዘንድሮ የእርሻ ወቅት ከማለፉ አስቀድሞም የመፍትሄ እርምጃ ሊሰጣቸው እንደሚገባም ነው የሚጠይቁት። አቤቱታቸውን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ማስገባታቸውንም ነው የሚናገሩት።
አርሶ አደሮቹ በተወሰደባቸው የእርሻ መሬት ምክንያት በርካታ ጉዳቶች እንደደረሱባቸው ይዘረዝራሉ። ከእርሻ ተግባር ሌላ የተለየ ሙያ የሌላቸው በመሆኑ መሬታቸው ሲወሰድባቸው ለከፍተኛ ድህነት መዳረጋቸውን ያስረዳሉ። ካሳ ክፍያን አስመልክተው ግምቱ ዝቅተኛ በመሆኑ የተከፈላቸው አነስተኛ ገንዘብ መሆኑን ይናገራሉ። ቤተሰብ ማስተዳደር ባለመቻላቸውም ቤተሰቦቻቸው የተበታተኑባቸው እና ትዳራቸው የፈረሰ መኖራቸውንም ነው የሚጠቅሱት። በድህነት ምክንያት ልጆቻቸውን ማስተማር ባለመቻላቸውም ልጆቻቸው መሃይም መሆናቸውን እንዲሁም እንደተሰደዱባቸውም ይገልጻሉ።
ለተወሰደባቸው የእርሻ መሬት ምክንያት የተሰጣቸውን ገንዘብ በአግባቡ ለመጠቀም እንዲችሉ መንግሥት የባለሙያ እገዛ አላደረገላቸውም። ገንዘቡ ወዲያው በማለቁ ሀብታም የነበሩ ገበሬዎች ድሃ መሆናቸውንም ነው የሚናገሩት። መሬታቸውን የተነጠቁት ድንገት ያለማስጠንቀቂያ እንደነበረ ድህነትን ለመቋቋም የጊዜ ዝግጅት እንዳልነበራቸውም ይገልጻሉ። በወቅቱ የነበረው የመንግሥት አስተዳደር መሬት መውሰዱን እንጂ ስለወደፊቱ አወዳደቃቸው ግድ እንዳልነበረው ይጠቁማሉ። ችግር ላይ እንዲወድቁ ምክንያት መሆኑንም ያብራራሉ።
እንደቅሬታ አቅራቢዎቹ አቤቱታ፤ መሬታቸውን በግፍ ተነጥቀዋል። ይህ ሳያንስ በእዚሁ የእርሻ መሬት ላይ የአዲስ አበባን ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ መድፊያ መደረጉ በጤና ላይ የደረሰባቸውን ጉዳት በመጠን መግለጽ ይከብዳል። አስም እና ልዩ ልዩ የቆዳ በሽታ ከደረሱባቸው የጤና ጉዳቶች የሚጠቅሱት ነው።
ከሚደፋው ቆሻሻ በክረምት ጎርፍ እየታጠበ የሚወርደው ፍሳሽ ቆሻሻ ውሃውን በሚጠጡ እና የግጦሽ ሳር በሚመገቡ የቤት እንስሳቶቻቸው ላይ ከፍተኛ እልቂት ደርሷል። ከብቶቻቸው በብክለቱ ተመርዘው እየሞቱባቸው እንደሚገኙም ነው የሚጠቁሙት። ከተወሰደባቸው ጊዜ አንስቶ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ያህል 165 ሄክታር መሬት ምንም አገልግሎት ሳይሰጥ ማሳለፉንም ይናገራሉ። አገልግሎት ሳይሰጥ መቆየቱ የአገሪቱ ጉዳት መሆኑን በይበልጥ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚገነዘቡት መሆኑን እናምናለን ይላሉ። ለአዲስ አበባ ከተማ ቅርብ እንደመሆናቸውም ያመርቱ የነበረውን ስንዴ፣ ጤፍ፣ ምስር ሽንብራ እና የመሳሰሉ ምርቶቻቸው በኮተቤ እና ሾላ ገበያዎች ያቀርቡና ገበያውን ይሸፍኑ እንደነበረ ያስታውሳሉ።
የጨቢሲሬ ጎዩ ልዩ ስሙ አቃቂ ቂሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪው አቶ ለገሰ መገርሳ የእርሻ መሬቱ ለምን ዓላማ እንደሚውል ባግባቡ ሳይነገራቸው እንደተወሰደባቸውና ጥር 2002 ዓ.ም በአካባቢው ተሽከርካሪ እየተመላለሰ ሲቃኝ እንደነበር ይጠቁማሉ። ያኔ እህሉ ተነስቶ ገለባው መሬት ላይ ተከምሮ ነበር፣ በኮትቻው መካከል መኪናው ለምን ይመላለሳል? ብለው መጠየቃቸውን ያስታውሳሉ። አርሶ አደሩ የሚያመርተው አንዴ ብቻ ነው። የከርሰ ምድር ውሃ አውጥተንላችሁ በዓመት ሁለቴ እና ሦስት ጊዜ እንድታመርቱ ለማድረግ ነው የሚል ምላሽ ነበር ያገኘነው ይላሉ። ማዳበሪያ ፋብሪካ ይተከላል ተብለው እንደነበረ፣ መስኖ ለማልማት የተገባው ቃልም እንዳልተፈጸመ ነው የሚገልጹት።
በ2003 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ ጤፍ አብቦ ስንዴ ደርሶ በነበረበት ወቅት የወቅቱ የበረህ ወረዳ እና የቀበሌው አስተዳዳሪዎች እንግዶችን ይዘው እንደገና ወደአካባቢያቸው መድረሳቸውንም ያስታውሳሉ። ‹‹በአካባቢው ባለው ትልቅ ዛፍ ስር ሰብስበው አናገሩን። በተለያዩ አቅጣጫዎች ናሙና ተወስዶና ጥናት ተደርጎ የተመረጠው የእኛ ሰፈር መሆኑን አረዱን›› ይላሉ። እንደወረዳው፣ እንደኢትዮጵያና አልፎም እንደአፍሪካ የተለየ የልማት ሥራ ለመስራት እንደተመረጠ እንደገለጹላቸው ነው አቶ ለገሰ የሚናገሩት።
ኅብረተሰብን የሚያሳድግ ልማት እንደሚተገበር በደፈናው ተገለጸልን። ምርቱ እንዴት ይሆናል ብንልም አስቸኳይ ትእዛዝ ነው የሚል ምላሽ ተመለሰልን ሲሉም ይናገራሉ። አንለቅም ብለው አሻፈረኝ ማለታቸውን ያስታውሱና፤ ዳግም ሰብስበው መሬቱን እንድንለቅ ውሳኔ መተላለፉን፣ በቂ ካሳ እንደሚከፈለንም አሳወቁን። ሌሎች አካባቢዎች አነስተኛ ካሳ እየተከፈለ መሆኑን እና ለእነርሱ ግን በቂ ካሳ እንደሚከፈል መነገሩንም ይጠቅሳሉ። ‹‹ትምህርት ቤት እንደሚገነባልን፣ ክሊኒክ በደጃችን እንደሚቋቋምልን፣ የውሃ መሠረተ ልማትና የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደሚገባልን ጭምር ገለጹልን›› ይላሉ አቶ ለገሰ።
እምብዛም ባይጠቅምም የአስር ዓመት የካሳ ክፍያ እንደሚከፍሏቸው እና በሄክታር አንድ ሚሊዮን 80 ሺ ብር ይታሰባል እንደተባሉም ይገልጻሉ። ግን የተባለው እንዳልተፈጸመ ነው የሚጠቅሱት። ኮሚቴ ተዋቅሮ ካሳው እንዲከፈል ተደረገ። ምን ያህል እንደሚያመርቱ ተጠይቀው፤ መሬቱ ለም በመሆኑ ጤፍም ሆነ ስንዴ በሄክታር እስከ 70 እና 80 ኩንታል እንደሚያመርቱ ቢገልጹም ኮሚቴው እንደዚያ አይመረትም እንዳላቸውም ይናገራሉ። 45 ኩንታል ይመረትበታል በሚል ተይዞ ግምቱ እንደተሰላ ይገልጹና፤ የአከፋፈል ሥርዓቱም ግልጽ እንዳልሆነላቸውም ነው የሚያስታውሱት። እርሳቸው አምስት ሄክታር መሬት ተወስዶባቸው የደረሳቸው የካሳ ክፍያ ግን አራት መቶ ሺ ብር ገደማ መሆኑን ነው የነገሩኝ።
ካሳ ክፍያው ትክክል አይደለም ብለው መጠየቃቸውን የሚያስታውሱት አቶ ለገሰ ፤ እንደሚስተካከል ተገልጾ ላቸው ቀጠሮ ተይዞላቸው እንደነበረም ይናገራሉ። በቀጠሯቸው መሠረት ተመላልሰው ቢጠይቁም አጥጋቢ ምላሽ እንዳላገኙም ነው የሚጠቅሱት።
በእዚህ ክርክር ላይ እያሉ ከአርሶ አደሮቹ የተወሰደውን መሬት ዙሪያ ያጥሩና ጥበቃ ያቆማሉ። ቆይቶም ቁፋሮ ይጀመራል። ለምን እንደሚቆፈር ቢጠይቁም ምላሽ እንዳልተሰጣቸውና ካሳ ስለከተከፈላችሁ አያገባችሁም መባላቸውን ነው የሚገልጹት። ሂደቱ የተከናወነው በአብዛኛው በስምምነት ሳይሆን በኃይል ነው የተነጠቅነው ባይ ናቸው። ታጥሮ በተቆፈረው ቦታ ላይ የቆሻሻ መጣያ ስፍራ መደረጉን ነው አቶ ለገሰ የሚገልጹት።
እየቆየ አካባቢው ሽታ ፈጠረ። የዝንብ መናኸሪያ ሆነ። አሞራ ቆሻሻ እያነሳ ደጃችን ላይ ይጥል ነበር። ቀን ቀን ውሾች ሌሊት ደግሞ የጅቦች መሰባሰቢያ ሆነ። ከብቶቻችንም እየገቡ ቆሻሻ እየተመገቡ ተቸገርን። ሽታው ነዋሪውንም መውጫ መግቢያ አሳጣ። ሽታ ስለሚስብ ልብስ ቀዬ ማስጣት አዳጋች ነበር። ጤንነታችንንም አቃወሰን። ድርጊቱም አስከፋንም። ዙሪያውም በሽቦ እንዲታጠር ተደረገ። መሬት ለተወሰደብን 270 አርሶ አደሮችም ካሳው እንዲስተካከል ተወሰነ። ቆሻሻውም እንዳይደፋ ታገደ ሲሉ ይናገራሉ።
አሁንም በሰላማዊ መንገድ ጥያቄ እያቀረብን እንገኛለን። ካሳ የተከፈለን አነስተኛ በመሆኑ ሊስተካከልልን ይገባል ይላሉ። የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢነጂነር) አካባቢውን እንደጎበኙት ያስታውሳሉ። የተከመረው ቆሻሻ መፍትሄ እንደሚሰጠው ቃል መግባታቸውን፤ በገቡት ቃል መሠረት ቆሻሻው መፍትሄ እንዲሰጠው ለኦሮሚያ ልዩ ዞን አቤቱታቸውን ማስገባታቸውንም ነው አቶ ለገሰ የሚናገሩት። ወረዳ አስተዳደሩን በማነጋገር መሬቱን ሁለቱ ማህበራት ኩራጊዳ እና አቃቂ ቂሌ ገበሬ ማህበራት በስምምነት በህብረት እንዲያርሱት ምላሽ እንደተሰጣቸውም ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ ሁለቱ ማህበራት እርስ በእርስ መግባባት እንዳልቻሉ ይናገራሉ። ብዙ መሬት ያልተነካባቸው በመኖራቸው በግል እናርሳለን የሚል እና በጋራ ማረስ አለብን የሚል ሃሳብ አላግባባንም ሲሉም ይገልጻሉ። በህብረት ለማረስ የተፈቀደው መተግበሩ አግባብ መሆኑን እና በጋራ አልምተው በጋራ መጠቀም እንደሚገባ ነው አቶ ለገሰ የሚናገሩት።
የ79 ዓመቱ አቶ ለታ ፈይሳ በሀብሮ ቀኑ ኩራጊዳ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። በእዚህ አካባቢ ተወልደው አድገውበታል። መሬቱንም ከጥንት ጀምሮ ከአባታቸው ጋር በጭሰኛነት በማገልገል እንዳገኙት ይጠቁማሉ። አባታቸው ለባለ መሬት ተገዢ በመሆን፣ ለፍተው ጥረው ግረው በኃይለሥላሴ ዘመን ወደአባታቸው እንደተላለፈላቸው ነው የሚጠቅሱት።
‹‹የእኛ ሆኖ ሳለ ግልጽ ባልሆነ መንገድ መሬታችን ተወሰደብን። በወቅቱ ከፍተኛ ቅሬታ አሳድሮብናል፤ የ10 ዓመታት ካሳ ይከፈላችኋል እስከልጅ ልጆቻችሁ ይበቃል በማለት መሬቱን እንድንለቅ አስገደዱን። እኔ ለምሳሌ 12 ልጆች አሉኝ። እነዚህን ልጆች ምን እናደርጋቸዋለን? ብለን ብንጠይቅም ቢፈልጉ ጫካ እየመረጡ ማረስ ይችላሉ፤ የሚል ምላሽ ሰጡን። አሁን እኛ አርጅተናል የምናደርግላቸው ነገር የለም ብዬ ተስፋ ቆረጥኩ። በእግዚአብሔር ላይም አለቀስኩ›› ይላሉ። መሬታቸውን በግፍ እና አግባብ ባልሆነ መንገድ ተወስዶ እየተንገላቱ መሆኑን በመጥቀስ።
መንግሥት አያታልልም ካታለለ ደግሞ ምንም ማድረግ አይቻልም፤ በውድ ባይሆንም በግድ እንደሚወስዱት እና ባይስማሙ እስር እንደሚጠብቃቸው እንደተነገራቸው ነው የሚጠቅሱት። ሥራ ሲጀመር ከጥበቃ አንስቶ ቅድሚያ ሥራ ዕድል የሚፈጠረው ለእኛ ልጆች መሆኑን ነገሩን ሲሉ ያመለክታሉ። የካሳ ክፍያው በካሬ ሜትር 18 ብር ከ40 ሳንቲም መሆኑን ፤ በዚህም አነስተኛ ገንዘብ መውሰዳቸውን ይጠቁማሉ። የደረሳቸው ገንዘብ 200 ሺህ ብር እንደሆነና ይህችኑ ገንዘብ ለልጆቻቸው ማከፋፈላቸውን ነው አቶ ለታ የሚናገሩት። አሁን የተረፋቸውን አነስተኛ መሬት እያረሱ እንደሚገኙና ልጆቻቸውን በተለያዩ አካባቢዎች ሥራ እንዲቀጥሩ መሞከራቸውን ነው የሚናገሩት።
ቆሻሻው በጤናቸውና በእንስሳቶቻቸው ደህንነት እንዲሁም በእህል ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳስከተለባቸውም ነው የሚናገሩት። ‹‹ፀሐይ ሁለቴ አይወጣም ግን ለውጡ ሲመጣ ሁለቴ ፀሐይ ወጥቶልናል ብለን አዲሱን መንግሥት በደስታ ተቀብለናል›› ሲሉ ያስታውሳሉ። አሁን ቆሻሻው መደፋት ማቆሙን በበጎነት ያነሳሉ፣ ድምጻቸው ተሰምቶ ቀሪው ጥያቄያቸውም ተገቢ ምላሽ እንዲሰጣቸውም ያመለክታሉ።
አርሶ አደሮቹ የሚጠይቁት ፍርድ፤
መሬቱ ከተወሰደበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ከእርሻ መሬታቸው ያጡት ጥቅም በባለሙያ ተሰልቶ በቂ ግምት እንዲሰጣቸው፣ የእርሻ መሬቱ ለኢንቨስተር የሚተላለፍ ቢሆን በአሁን የገበያ ዋጋ ተሰልቶ ግምቱ በአፋጣኝ ተሰጥቷቸው ከችግራቸው እንዲላቀቁ ይጠይቃሉ። እንዲሁም ከሁለት ዓመታት በላይ ሲደፋ ቆይቶ በታመቀ ፍሳሽ ቆሻሻ ሽታና ኬሚካል ብክለት ምክንያት በአካባቢው በሚኖሩ አርሶ አደሮች የጤና የማህበራዊ እና የሥነ ልቦና ጫና እያደረሰባቸው እንደሚገኝ በመግለጽ መንግሥት አካባቢውን በማጽዳት ለመፍትሄው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ አፋጣኝ መልስ እንዲሰጣቸው አቤቱታ አቅራቢዎቹ ይጠይቃሉ።
በአካባቢያቸው የፍሳሽ እና ደረቅ ቆሻሻ ብክለት ምክንያት በቤት እንስሶቻቸው ላይ የደረሰው እልቂት ጥናት ተደርጎ በቂ ካሳ እንዲከፈላቸው የሚያመለክቱት አቤቱታ አቅራቢዎች፤ በሚኖሩበት አካባቢ ዙሪያ በሽቦ አጥር ተከርችሞ ቅርብ የነበረው የመግቢያ እና መውጫ መንገድ እንደራቀባቸው ነው የሚጠቅሱት። በመሆኑም እንደ ቀድሞው በሩ ተከፍቶላቸው ወደ አዲስ አበባ እና ሌሎች አካባቢዎች በአጭር መንገድ ለመንቀሳቀስ እንዲችሉም ይጠይቃሉ።
በ2003 ዓ.ም ቆሻሻ የተደፋበት ከ165 ሄክታር (አንድ መቶ ስልሳ አምስት ሄክታር) በላይ መሬት የአብዛኞቹ ይዞታ ይለካ የነበረው በይዞታቸው ላይ ሳይገኙ እንደነበረ ይጠቅሳሉ። ልኬቱን እና ግምቱን በጣም አሳንሰውባቸው ስለነበር በአዲስ መልክ ይዞታቸው ተለክቶ ግምቱ እንዲስተካከልላቸውም ያመለክታሉ።
መንግሥት እንደ እነርሱ በአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ ከእርሻ መሬታቸው ለተፈናቀሉ አርሶ አደሮች በቂ ካሳ እና መቋቋሚያ እየሰጠ መሆኑን የሚያመሰግኑት አርሶ አደሮቹ፤ እነርሱም በእነርሱ አይን እንዲታዩ ይጠይቃሉ።
የበረህ ወረዳ አስተዳዳሪ ምላሽ
በኦሮሚያ ልዩ ዞን የበረህ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ሰኚ፤ ቀደም ሲል ቦታው ከአርሶ አደሮች ካሳ ተከፍሎ ሲወሰድ በቂ ካሳ እንዳልተከፈለ ይገልጻሉ። ስፍራው ለታሰበለት ዓላማ ስላልዋለ ቅሬታ እንደነበራቸው ይናገራሉ። መሬቱ ሲወሰድ ለማዳበሪያ እና ለተለያዩ ፋብሪካዎች ይውላል ተብሎ መወሰዱን ነው የሚያስታውሱት።፡ ሆኖም ወደ ተግባር ሲገባ ቦታው ለአዲስ አበባ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ እንዲውል መደረጉን ነው የሚያነሱት።
አቶ ወርቁ የሚወጣው ፍሳሽ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱ ኅብረተሰቡ ቅሬታ ማቅረቡን ያስታውሳሉ። ጉዳዩን የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውይይት አድርገው ቆሻሻው በአካባቢው መደፋቱ እንዲቆም መደረጉንም ያክላሉ። ቦታው ሳይለማ እንዲሁም ለምንም አገልግሎት ሳይውል ከአስር ዓመታት በላይ አሳልፏል። አርሶ አደሩም የእርሻ መሬቱን ማልማት አለብን አልያም ለተወሰደው ዓላማ ሊውል ይገባል የሚል ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቷል። ተጠቃሚ ሊያደርገን ወደሚችል ኢንዱስትሪና አካባቢው ላይ ችግር ለማያደርስ ልማት መዋል አለበት የሚል ቅሬታ በተደጋጋሚ ሲያቀርቡ ነበር ሲሉም አቶ ወርቁ ያስታውሳሉ።
እስካሁንም መሬቱ ሳይለማ ቆይቷል። አሁን ግን መንግሥትም ባወጣው ስትራቴጂ መሠረት አንድም መሬት ካለልማት መክረም የለበትም። በመሆኑም አርሶ አደሮቹ ተደራጅተው እንዲያርሱ ነው የተፈቀደላቸው። ይህ ሲደረግ ግን መሬቱ ለአርሶ አደሩ ሙሉ ለሙሉ እንዲመለስ ሳይሆን እንዲለማ የመንግሥትን እቅድ ለማሳካት ሲባል ነው። በቦታው አንድ ፋብሪካ አልያም የተለያዩ ሥራዎች እስኪሰራ ድረስ መሬቱ ያለልማት መዋል የለበትም። አርሶ አደሮቹ ተደራጅተው እንዲያርሱ ተወስኗል ይላሉ።
እንደ በረህ ወረዳ አስተዳዳሪ ማብራሪያ፤ መሬቱ የተወሰደባቸው የኩራጊዳ እና ስሬ ጎዮ ቀበሌ አርሶ አደሮች ሲሆኑ፤ ቤተሰቦቻቸው እና ባለንብረቶች የነበሩት ተደራጅተው በማረስ ኑሮን እንዲያሻሽሉ በመንግሥት ስትራቴጂ ላይም ተሳትፎ እንዲያደርጉ በማሰብ ነው መሬቱ እንዲመለስላቸው የተደረገው።
ያኔ ካሳ ቢከፈልም ከእዚያን ጊዜ ጋር ሲነጻጸር የአሁን ገበያ እና የኢኮኖሚ ደረጃ አንድ አይደለም። በቂ ካሳ አልተከፈለንም የሚሉ አርሶ አደሮች ድምጽ ይደመጣል። አካባቢው መልማት ስላለበት መሬቱን የወሰደው አካል አልምቶ የሥራ ዕድል መፍጠር አለበት። ኢንዱስትሪ ተቋቁሞ የአካባቢው ኅብረተሰብ መጠቀም አለበት።
የማያለሙ ከሆነ ማልማት ለሚችል ባለሀብት ማስተላለፍ አለባቸው። የተወሰነ ታግሰን የማያለሙ ከሆነ በደብዳቤ አሳውቀን ወደመንግሥት ካዝና ገቢ እንዲሆን በማድረግ ለልማት እንዲውል ይደረጋል። በኋላም የሚያለማ ባለሀብት ሲመጣ ተጠቃሚ እንዲሆን እናደርጋለን በማለት አቶ ወርቁ ምላሽ ሰጥተዋል።
ይህ መሬት የመንግሥት ነው። ሁለቱ ማህበራት ኩራጊዳ እና ስሬ ጎዮ ቀበሌዎች በጋራ ለማልማት እና አንድ ላይ ለማረስ ስምምነት አድርገው ወደ ልማቱ ገብተዋል ሲሉም አቶ ወርቁ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በመካከላቸው አንዳንድ እርስ በእርስ ስምምነት እንዳይኖር ኅብረተሰብና መንግሥት እንዳይስማሙ የሚያደርጉ ሥራ አጦች አልታጡም። ቦታው ይሄ ይበልጣል በማለት ግጭት እንዲቀሰቀስ ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። ይህንን በአገር ሽማግሌዎች አማካኝነትና እኛም እንደ አስተዳደር ጣልቃ ገብተን ማስተካከል የምንችለው ነው። ሰዎቹ እንዲስማሙ እና በአደረጃጀቱ መሠረት ወደ እርሻ ሥራቸው እንዲሰማሩም እናደርጋለን ይላሉ።
አርሶ አደሮቹ በአዲስ መልክ ይዞታቸው እንዲለካ መጠየቁን አስመልክተው አቶ ወርቁ ሲመልሱ፤ ካሳው የተከፈለው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አማካኝነት መሆኑን ያነሳሉ። ምን ያህል ሄክታር እንደተወሰደባቸው፣ ምን ያህል እንደቀረ፣ የወሰደውና ያልወሰደው እና ክፍተት የተፈጠረው የት ቦታ ላይ እንደሆነ መረጃውን በወረዳው ማግኘት እንዳልተቻለ ነው የሚገልጹት።
አሁን ግን መሬቱ ጾሙን ማደር የለበትም የሚለውን አቅጣጫ ተግባራዊ ማድረግ ይሆናል። ቦታውን የወሰደው ድርጅትም ሆነ የአካባቢው አርሶ አደሮች መሬቱ መልማት አለበት። የአካባቢው አርሶ አደሮች በሁለት ነገር መጎዳት የለባቸውም። በቂ ካሳ አልተከፈለንም የሚል ቅሬታ በሚያነሱበት፣ የመሬት ልኬቱም ትክክል እንዳልሆነ የሚጠቁሙበት ሁኔታ ስላለ እነርሱን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል የልማት ተግባር መከናወን ይኖርበታል ብለን እናምናለን ብለዋል አቶ ወርቁ።
የኦሮሚያ ልዩ ዞን ምላሽ
የኦሮሚያ ልዩ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ፍቃዱ ቱሉ፤ ኅብረተሰቡ ያነሳቸው ቅሬታዎች በመንግሥት የሚታወቅ መሆኑን ያመለክታሉ። በማህበረሰቡ ጤና ላይ፣ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግርች ማስከተሉንም ይጠቅሳሉ። የተባለውን ዓላማም አለማሳካቱንም ነው የሚናገሩት። በአካባቢው ኅብረተሰቡ ብዙ የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር፣ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ወደ አካባቢው እንደሚገቡ፣ ግብርናን በተመለከተም በመስኖ እንደሚያለሙ ልዩ ቃል ቢገባላቸውም ሳይተገበር መቅረቱን ያመለክታሉ። ሕዝቡም ቅሬታውን ማሰማቱን እና ለአመጽ ምክንያት ሆኖ እንደነበረም ያክላሉ።
ቀደም ሲል አርሶ አደሮቹ ለእርሻ ሥራ ይጠቀሙበት የነበረውን መሬት አዲስ አበባ ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ተብሎ ተወስዶባቸው እንደነበረ ያስታውሳሉ። ቆሻሻ በአካባቢው ይጣል ስለነበረ ሕዝቡ ባነሳው ቅሬታ እና ኅብረተሰቡ ከማህበረሰቡ ጋር በተደጋጋሚ ጊዜ ውይይት ማድረጉን ያነሳሉ።
ጥያቄው ትክክል መሆኑ ታውቆ እና ታምኖበታል፤ መንግሥት የኅብረተሰቡ ጥያቄ ምላሽ ማግኘት አለበት በሚል እምነትም ለጊዜው ቆሻሻ መደፋቱ እንዲያቆም መደረጉንም አቶ ፍቃዱ ያክላሉ። ከአንድ ዓመት በፊት የአዲስ አበባ ከንቲባ እና የኦሮሚያ ክልል አመራሮች በተገኙበት ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይት ተደርጎ እንደነበር እና የቆሻሻው መደፋት በመቆሙ ለሕዝቡ በተወሰነ ደረጃ ጥያቄው መመለሱንም ነው የሚጠቁሙት።
አርሶ አደሮቹ እንዴት እንደሚቋቋሙ እና ወደኑሯቸው ሊመለሱ የሚችሉበትን አቅጣጫ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር መነጋገራቸውን አቶ ፍቃዱ ጠቅሰው፤ አርሶ አደሩን በሚጠቅም መንገድ መሬቱ የሚለማበትን፣ የሥራ ዕድል በሚፈጥርላቸው መንገድ እና ተጠቃሚ በሚሆኑበት ሁኔታ ላይ ተቀርጾ ተግባራዊ እንደሚደረግ ነበር ምላሽ ያገኘነው። ይህንን እየጠበቅን እንገኛለን ነው ያሉት አቶ ፍቃዱ። እስካሁን ተጠቃሚ አልሆኑም፣ የሥራ ዕድልም አልተፈጠረላቸውም። ይህንን የሚያስተገብር ሌላ ፕሮጀክት አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመነጋገር የሚጠቅማቸው ፕሮጀክት እንዲቀረጽ ነው ተግባቦቱ ይላሉ።
‹‹የትኛውም መሬት ሳይታረስ መክረም የለበትም›› የሚል መንግሥት ያስቀመጠው አቅጣጫ መኖሩን የሚያመለክቱት አቶ ፍቃዱ፤ በዚህ መነሻነት አርሶ አደሮቹ መሬቱን እንዲያርሱ እንደተፈቀደላቸው ይናገራሉ። ወረዳው አርሶ አደሮቹን በማህበር አደራጅቶ አርሰው እንዲጠቀሙበት መደረጉን ያነሳሉ።
ልኬቱ ተስተካክሎ እንዲለካ የሚለው ከአርሶ አደሮቹ የተነሳው ጥያቄ ለልዩ ዞኑ እስካሁን እንዳልቀረበ አቶ ፍቃዱ ይጠቅሳሉ። ከእዚህ ይልቅ በጥቅሉ የካሳ ክፍያው አነስተኛ ነው የሚል ቅሬታ መነሳቱን ነው የሚገልጹት። ያልተለካ መሬት አለ ወይ በሚለው ጉዳይ ላይ እምብዛም እንዳልተኬደበት ነው የጠቀሱት። በወቅቱ ካሳውን የተመኑት ሰዎች ባገኙት መረጃ መሠረት በወቅቱ መንግሥት ባስቀመጠው የካሳ ክፍያ ዋጋ እንደተከፈለ ነው የሚናገሩት።
ቆሻሻው እንደገና ጥቅም ላይ ይውላል፣ የማዳበሪያ ፋብሪካም ሊገነባ ይችላል የሚልና ሌሎችም አቅጣጫዎች ተቀምጠው እንደነበረ አቶ ፍቃዱ ያስታውሳሉ። የመሬቱ ዕጣ ፈንታን አስመልክተውም የኦሮሚያ ክልል እና የአዲስ አበባ ከተማ የጀመሯቸው ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ይደረጋሉ፣ አርሶ አደሮችን የሚጠቅም ልማትም ይተገበራል ይላሉ።
የተደረገ ስምምነት
ሰኔ 21 ቀን 2012 ዓ.ም የሀርቡ ቀቤ ኩራ ጊዳ እርሻ እና አቃቂ ቂሌ ቀበሌ መካከል የተደረገውን እርቅ በሚመለከት ውይይት አድርገዋል። ነዋሪዎቹ መሬታቸውን በኢንቨስትመንት ስም ከ2002 እስከ 2012 ዓ.ም በሕገ ወጥ መንገድ ተይዞ እንደነበር ያመለክታሉ።
ከሁለቱም ገበሬ ቀበሌዎች ተወካዮች በተገኙበት በተደረገው ስምምነት ድርሻቸው ተከፍሎ ከገበሬ ህብረት ሥራ ማህበሩ ጋር ስምምነት ተደርጓል። በስምምነቱም የሀገር ሽማግሌዎች፣ የገዳ አባቶች የቀበሌ ምክትል ሊቀመንበር፣ የአቃቂ ቂሊ ቀበሌ ጸጥታ ኃላፊ ተገኝተዋል።
ከላይ የተብራራው ጉዳይ በኮሮና ቫይረስ መከሰት ምክንያት መሬቱን ተካፍለን ማልማታችን ከግምት እንዲገባልን በአክብሮት እንጠይቃለን። ይህም በፍትሐ ብሔር ሥነሥርዓት ቁጥር 1989 እና 1990 ይፈጸማል። ይህን ስምምነት ያፈረሰ በሕግ ይጠየቃል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 7ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን ባካሄደበትና የ2012 በጀት አፈፃፀም ሪፖርት በተደመጠበት ከትናንት በስቲያ በነበረው መርሀ ግብር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት በርካታ ዓመታት በከተማው አስተዳደር ትኩረት ሳይሰጣቸው የቆዩ አርሶ አደሮችን በተለያዩ ዘርፎች የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሚገኝ መግለጻቸው ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2012
ዘላለም ግዛው