1.0 መግቢያ
ኩኩሉ! ኡ ኡ ኡ! ለዓባይ ሸለቆ ሕዝቦች! አዎ! ኩኩሉ! ኡ ኡ ኡ! ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት! አዎ! የዓባይ ሸለቆ ሕዝቦች በታላቅ ዕንቅልፍ ላይ ናቸው! አዎ እነሱንም የአፍሪካ አንድነት ድርጀትንም መቀስቀስ ያስፈልጋል።ዓለም እኮ በግብጽ፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ስለ ሕዳሴው ግድብ ውሃ አሞላል፤ የሚካሄደውን ድርድር በአግራሞት እየተከታተለው ነው።ኢትዮጵያዊው ደግሞ ጠብ ያለሽ ዳቦ እንደሚለው አያጠራጥርም። ጉድ እኮ ነው! የዓባን ውሃ ስዊዝ ካናልን አቋርጦ ጎረፈ እኮ! ‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም›› ይባል የለ ! እንዲያውስ ‹‹ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል ይባል የለም እንዴ!›› የጉድ ጉድ ዕኮ ነው! እኛ በዘር ማንዘር አሳፋሪ ወይም የዝንጀሮ ወሬ ስንደነባበር እራቁታችንን ልንቀር ነው እንዴ! የረኃብ ተምሳሌቷ አገራችን ክብሯ የሚመለሰው መቼ ነው፡፡
ሰው ሰው ነው ብለን ስናምንና፤ ስለ ሰው ልጅ መብት ስናስብና መቆርቆር ስንጀምር ነዋ! ስለዚህ ዝንተ ዓለም መዘባበቻ እንዳንሆንና የዓባይን ልጆች ወሃ ጠማቸው እንዳይባልም የዓባይ ሸለቆ ሕዘቦች በሙሉ በአንድ መንፈስ እየተናበብን መንቀሳቀስ ይኖርብናል።ታዲያ የሰሞኑ በግበጽ፤ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል የሚካሄደው ውይይት ለዚህ ይረዳ ይሆን?
ውይይቱ በስልት የጋራ አጀንዳ ተቀርጾ፤ ከተወያዩበት ጠቃሚ ውጤት ሊገኝበት ይችላል።ነገር ግን፤ አሁን እንደምንሰማው፤ የኅዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል ላይ ብቻ የሚያተኩር ከሆነ፤ አስተዛዛቢ ውይይት ወይም ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ የሚል ዓይነት ፍሬ አልባ ድርድር ይሆናል።ስለዚህ አንድ በአንድ ስብሰባ፤ የውይይቱ ርዕስ በመላው የዓባይ ሸለቆ አገሮች ስምምነት መሠረት መቀረጽ ይኖርበታል።ርእሱ ከተቀረጸ በኋላ በዝርዝር ነጥቦቹ እየተነሱ አስፈላጊው ውይይት ወይም ድርድር በስነ ሥርአት መካሄድ ይኖርበታል።
የውይይቱ ዓላማም ሁሉንም በእኩል ዓይን በወንድማማችነት መንፈስ የሚመለከትና፤ የአፍሪካውያንን ጥቅም አሳልፎ የማይሰጥ መሆን አለበት።በዚህ መሠረትም የዓባይ ውሃ ከአፍሪካ አህጉር ውጪ እንዳይወጣ፤ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ዋና መሠረታዊ መርህ መሆን አለበት።የዚህም ዋናው ምክንያት፤ ወደፊት ሊመጣ ከሚችል የውሃ እጥረት ለመከላከል ነው።ስለዚህ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን በንቃት ድርድሩን እንዲከታተሉ ኩኩሉ ! ኩኩሉ ! እያልን ጩኸታችንን ማሰማት ይኖርብናል።ይህንን ታሳቢ በማድረግ ስለ ዓባይ ውሃ አጠቃቀም የሚከተለው ታሪካዊ ሁኔታን በመጥቀስ መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ ነጥቦች ከዚህ በታች በአጭሩ ቀርበዋል።
ግብጽና ሱዳን በእንግሊዝ አስተዳደር በነበሩበት ወቅት፤ እንግሊዛውያኑ ፍርደ ገምድል እርምጃ በመውሰድ፤ ግብጻውያኑም የያዙትን የተዛባ የብቸኛና ታሪካዊ ባለመብትነት አስተሳሰብን በመደገፍ ፤ ኢትዮጵያን ያገለለ አድሎአዊ የውሃ ክፍፍል ስምምነት ለግብጽና ለሱዳን በማዳላት እንዲፈረም አድርገዋል።ከዚህም የተነሳ ግብጻውያኑ የሚይዙትን የሚጨብጡትን አጥተው፤ መላውን የተንጣለለውን የቶሺካ በረሀ በማልማት ሰበብ፤ ከፍተኛ የጥቁር ዓባይ ውሃ ሱስ ይዟቸዋል።በሌላ በኩል የዓባይን ውሃ በስዊዝ ቦይ ስር አሾልከው በመውሰድ፤ ለአካባቢው አገሮች ለማቅረብ አሳፋሪ የድለላ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛሉ።
ቆፍጣናው የኢትዮጵያ ገበሬ ግን፤ለመስኖ እርሻ የሚውል ውሃ ለዝንተ ዓለም የሚያቀርብለት አስታዋሽ ቢያጣም፤ በየዘመኑ ወራሪ ጦር መጣ ሲባል፤ ሞፈር ቀንበሩን እየሰቀለ በቆራጥ መንፈስ ወደጦር ግንባር በመገስገስ በዓለም ታዋቂነት ማትረፉ አይዘነጋም። ይህ ኩሩ ህዘብ ግን አስታዋሽ አጥቶ ኋላ ቀር በሆነና በዝናብ ላይ ሙጥኝ ያለ የእርሻ ስልት በመከተሉ፤ ከመላው ዓለም የድሆች ድሀ ተብሎ ለመመዝገብ በቅቷል።ይኸውም ለእያንዳንዳችን ቁመን ለምንሄድ ሰው ነን ለምንል ኢትዮጵያውያን፤ የሀፍረት ካባ ለባሽ መሆናችንን አመላካች ነው።ስለዚህም ኩኩሉ! ኡ ኡ ኡ ! ለዓባይ ሸለቆ ሕዝቦች! አዎ ኩኩሉ ! ኡ ኡ ኡ! ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት! በማለት የውሃ ሀብታችን ዘረፋ ለማስቆም ከያዘን አሳፋሪ ዕንቅልፍ እንድንነቃ ፤ በጋራ በማጮህና በማሳሰብ ወደ ታሪካዊው የዓባይ ሸለቆ አጭር ዳሰሳ አመራለሁ፡፡
2.0 የዓባይ ሸለቆ የውሃ ሀብት ሁኔታ አጭር ዳሰሳ
ከድንጋይ ዳቦ ዘመን አንስቶ የረዥሙ የዓባይ ወንዝ አስደናቂ የሱዳንና የምደረ ግብጽን ምድር አቋረጦ፤ ሜዲትራንያን ባሕር መደባለቁ የታወቀ ተደናቂ ጉዞ ነው፡፡ይኸውም ግብጽ የዓባይ ስጦታ ናት የሚለውን ታሪካዊ አባባል አስከትሏል።ከዚህም ተከትሎ የዓባይን ወንዝ ፍሰት የሚቆጣጠሩ ግብጻውያኑ የሚያመልኳቸው አማልክት እንዳሉም ይነገር ነበር ። አማልክቶችን የማምለኩ ግለትም እንደ ፍሳሹ መጠን የመቀነስና የመጨመር ሁኔታ ከፍና ዝቅ ይል እንደነበር ተዘግቧል።ወንዙ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቶ ዳርቻዎቹን ጥሶ በሚነጉድበት ወቅት ግብጻውያኑንና አካባቢውን ጠራርጎ ታላቅ እልቂት ስለሚያስከትል የከፍተኛ ሰቆቃና የዋይታ ወቅት ይሆን እንደነበር ተዘግቧል።
በሌላ ዓመት ደግሞ ወንዙ ደርቆ ወይም ጭል ጭል እያለ ሲንቀራፈፍ የእርሻ መሬትን ማጥለቅለቁ ስለሚቀር ፤ የድርቅና የችግር ወቅትን ስለሚያመለክት ረሀብ አይቀሬ ሆኖ ችጋር ይከተላል።በዚህም ምክንያት የግብጻውያኑ ኑሮ ከፍሰቱ ጋር በመቆራኘቱ የአማልክቱ ቁጣ ያስከተለው እንደሆነ ተደርጎ ስለሚቆጠር፤ አማልክቱን የመማጸኑ ሁኔታ ይጠናከር ነበር ።እንግዲህ እነዚህ የተፈጥሮ ሁኔታዎች ናቸው ምንም ዓይነት ዝናብ ጠብ በማይልባት ግብጽ ከዓባይ ጋር ያለውን ጠንካራ ቁርኝት የፈጠሩት።ከዚህም በተረፈ ታላቋ ብሪታንያ ግብጽንና ሱዳንን በምታስተዳድርበት ወቅት ግብጽ የዓባይ ወንዝ ብቸኛ ባለመብት ተጠቀሚ ናት የሚል አስተሳሰብ እንዲሰርጽ አድርገዋል።ይኸውም ግብጻውያኑ ከመጠን በለይ የልብ ልብ እንዲሰማቸው አስተዋጽኦ አድርጓል።እንግሊዛውያኑ በዚህ በወገንተኛነት አቋማቸውም አድሎአዊ የውሃ ክፍፍል በማድረግ፤ ኢትዮጵያንና ሌሎቹን የዓባይ ተፋሰስ አገሮችን በማግለል፤ ለግብጽና ለሱዳን ብቻ የተዘጋጀ የውሃ ክፍፍል ስምምነት አዘጋጀተው አፈራርመዋል።እንግዲህ በእነዚህ ፍርደ ገምድል ስምምነቶች በመንተራስ ግብጻውያኑ ከነሱ ውጪ በዓባይ ላይ በሚደረግ ማናቸውም የልማት እንቅስቃሴ፤ የተቆጣጣሪነት አባዜ ምርኮኛ በመሆን፤ በመባዘን የአገሮችን ጤነኛ ግንኙነትን ጥርጣሬ ውስጥ በመክተት ላይ ይገኛሉ።ከዚህም የተነሳ በኅዳሴው ግድብ የውሃ አሞላል ዕቅድ ላይ ጣልቃ በመግባት ተጽእኖ ለማድረግ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እየታዘብን ነው።በጣም የሚገርመውና የሚያሳዝነውም፤ ውይይቱ የሚካሄደው በሦስት አገሮች ብቻ መሆኑና የውይይቱም ርዕስ በግብጻውያኑ ፍላጎት ተወስኖ፤ በኅዳሴው ግድብ ውሃ አሞላል ብቻ ላይ መሆኑ ነው።ግብጻውያኑ ከዓባይ በተጨማሪ አማራጭ የውሃ መገኛ ካላዘጋጁ ለአፍሪካ በሙሉ የሰላም ጠንቅ ስለሚሆኑ መላው የተፋሰሱ አገሮች ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ሰፋ ያለ የውይይት ርእስ አዘጋጅቶ በመወያየትና በመደራደር አጠቃላይ ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል። ከዚህ እሳቤ በመነሳት ብዙ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችና ግብጻውያኑም በስፋት የሚያውቋቸው ትኩረት ሊሰጥዋቸው የሚገቡ አማራጭ የውሃ መገኛዎች ከዚህ በታች ቀርበዋል።እነዚህ የውሃ ምንጭ አማራጮች ግብጽንና ሱዳንን ሙሉ ለሙሉ ጥቁር ዓባይ ላይ እንዳይንተራሱ ስለሚረዱ፤ ከዚህ በታች በዝርዝር ቀርበዋል።
3.ለግብጽና ለሱዳን አማራጭ የውሃ
መገኛዎች
ከዚህ በታች የተዘረዘሩት አማራጮች ትኩረት ተሰጥቶአቸው በጥናት ላይ በመመርኮዝ ሊተገበሩ ይችላሉ፡፡
ሀ) በጠጣሩ የኑብያ አሻዋማ ከርሰ ምድር የተከማቸው ውሃ
ለ) የቀይ ባሕርንና የሜዲትራንያንን ባሕር ከጨው የማላቀቅ አማራጭ
ሐ)ከላይኛው የዓባይ ተፋሰስ በጆግላይ ቦይ አማካይነት ሊመጣ የሚችለው ውሃ
መ) ከታላቁ ኮንጎ ወንዝ ሊጨለፍ የሚችለው ውሃ
ሠ) ከቤት፣ ከኢንዱሰትሪ እና ከመስኖ ፍሳሽ እንደገና ተጣርቶ ለጥቅም ሊውል የሚችል ውሃ
i. የኑብያ ጠጣር አሻዋማ ስነምድር ውስጥ የሚገኝ የከርሰ ምድር ውሃ
ይህ የከርሰ ምደር ውሃ መላዋ ግብጽን፣ ምስራቃዊ ሊቢያን ፣ሰሜን ቻድንና ሰሜን ሱዳን ውስጥ ተከማችቶ
ይገኛል። በቅርቡ በተደረገ ግምትም ወደ 450,000 (አራት መቶ ሀምሳ ሺ) ኪውቢክ ሜትር እንደሚጠጋ ታውቋል።ውድ የሀገሬ ዜጎች! በጣም ብዙ ክምችት ነው።ይኸውም ለታላቁ ለሀገራችን ሕዝብ አስደሳች ዜና ነው።ምክንያቱም በጥቁር ዓባይ ተቀናቃኝ ሲቀርልን ዓባይን ወደ አዋሽ በመጥለፍ እንደፈለግን እስከ አፋር ደረስ እንዝናናበታለን እንቦራጨቅበታለን።ብሩህ ተስፋ ለታታሪው ለአፋር ሕዝብም ይሆናል።ከአገራቸው ከዓባይ ውሃ ተጠቃሚ ይሆናሉ።በከፊል የዓባይን ውሃ ወደ አፋር ለመጥለፍ የሚያስችሉ ቦታዎች እንዳሉ የታወቀ ነው።ስለዚህ የኅዳሴው ግድብ የመወያያ ርእስ ተስተካክሎ የኢትዮጵያን ህዝብ የመታደግ ዓላማ መያዝ አለበት፡፡
ወደ ኑብያ የከርሰ ምድር ውሃ ክምችት ርእስ ስንመለስ ስለ አጠቃቀሙ ፣ ሊቢያ የተባለችውን አገር በምሳሌነት ልንጠቀስ እንችላለን።ያቺ አገር የከርሰ ምደሩን ውሃ አውጥታ ሰው ሠራሽ የተባለውን ወንዝ ፈጥራ ጥቅም ላይ በማዋል የአረቡን ዓለም በእርሻ ምርት በሥጋና በፍራፍሬ በማጥለቅለቋ፤ ሊቢያውያን ከፍተኛ የኑሮ እርከን ላይ መድረሳቸው የታወቀ ነበር።ስለዚህ ግብጻውያን ወንድሞቻችንም ይህንን ፈር በመከተል ሙሉ ለሙሉ በጥቁር ዓባይ ላይ መመርኮዝ ማቆም ይኖርባቸዋል።ከሰው ልጅ ቁጥጥር ውጪ የሆነ አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥም ግን ሁሉም የሸለቆው አገሮች በጋራ የመቆማቸው ግዳጅ ከጥርጣሬ መግባት የለበትም።ለዚሁ የሚጠቅም መርህ በቅድሚያ ማዘጋጀት ግን የሚጠበቅ ነው፡፡
ii. የቀይ ባሕር እና የሜዲትራንያንን ውሃ ከጨው የማላቀቅ አማራጭ
አሁን ባለንበት ክፍለ ዘመን የባሕርን ውሃ ከጨው የማላቀቁ ሂደት በጣም እየቀለለና በዋጋም እየረከሰ መምጣቱ የታወቀ ነው። ወደፊትም ይበልጥ ዋጋው እየቀነሰ እንደሚሄድ ይገመታል።ግብጻውያን ወንድሞቻችንም ጨዋማን ውሃ የማጣራት በቂ ልምድ ስላላቸው ምንም የሚቸግራቸው ነገር እንደሌለ ስለሚገመት በውቅያኖስ ውሃ በማጣራት ሊምበሸበሹ እንደሚችሉ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው።
iii.በላይኛው ዓባይ ላይ ውሃ አጠቃቀም የዓባይን ፍሰት ማጎልበት
ይኸ አማራጭ ቀደም ብሎ ግብጽና ሱዳን በታላቋ ብሪታንያ አስተዳደር በነበሩበት ወቅት ተጀምሮ፤ ደቡብ ሱዳን ውስጥ ተነስቶ በነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት የተቋረጠ ነው።መሠረተ ሃሳቡም ቪክቶሪያ ሀይቅ ላይ ግድብ ሠርቶ ውሃ በማጠራቀም፤ ውሃው ወደ ነጭ ዓባይ እንዲፈስ በማድረግ ሱድ የተባለውን 8000 (ስምንት ሺ) ኪሎ ሜትር ካሬ የሚሸፍነውን ረግረጋማ መሬት በካናል በማሳለፍ፤ እንደገና ነጭ ዓባይ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ወደ ሱዳንና ወደ ግብጽ የጎለበተ ውሃ እንዲወርድ የታቀደ ነበር።ዕቅዱ መታረም ያለባቸው ሁለት መሠረታዊ ችግሮች ነበሩበት።የመጀመሪያው ችግር የመጥለፊያው ቦይ ግዙፍ እንደመሆኑ በአካባቢው ለሚኖሩት ህዝቦችና እንስሳት የመሸጋገሪያ ድልድይ ታሳቢ አድርጎ ይሁን አይሁን የታወቀ ነገር የለም።ባለበት ሁኔታ ግን ቦዩ ግዙፍ ከመሆኑ አንጻር ሰውም እንስሳቱና የዱር አውሬዎቹ መተላለፊያ በማጣታቸው ከባድ ችግር ውስጥ መግባታቸው ይታወቃል፡።በተለይም የዱር እንስሳቱ በአመት ውስጥ ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ የመጓዝ የተፈጥሮ ልማድ ስላላቸው፤ የቦዩ ግንባታ ከሁለት መቶ ኪሎ ሜትር በላይ ተቆፍሮ በእርስ በርሱ ብጥብጥ ምክንያት በመቋረጡ ችግሩ ጎልቶ ወጥቷል።የመሸጋገሪያ ድልድይ አስፈላጊነቱ በዕቀዱ ውስጥ ይረሳ አይረሳ የሚታወቅ ነገር የለም።ሆኖም እንዳስፈላጊነቱ ሦስትም ሆነ አራት ድልድይ እንዲሠራ ማቀዱ አያስቸግርም፡፡
በተጨማሪም የእንግሊዞቹ ጥናት በሱድ አካባቢ በከብት እርባታ ኑሮአቸውን መሠረት ላደረጉት የኒሎቲክ ህዝቦችን ተጠቃሚ አላደረገም።ዋና ትኩረታቸው ግብጽን በውሃ አቅርቦት ሰበብ ጥገኛ እንዲሆኑላቸውና በስዊዝ ቦይ ተጠቃሚነታቸውን ለማጠናከር ታሳቢ ያደረገ እንደነበር ይታወቃል።እርግጥ አሁን ሁኔታዎች ተቀያይረው፤ በቪክቶርያ ኃይቅ አካባቢም የነዋሪዎች ቁጥር በጣም አሻቅቧል።ዕቅዱ በአሁኑ ወቅት ካስፈለገም ክለሳ ያስፈልገዋል ።
iv. ከኮንጎ ወንዝ ውሃ በመጭለፍ የነጭ ዓባይን ፍሰት ማጎልበት
የታላቁ የኮንጎ ወንዝ በሰከንድ 40,000 ( አርባ ሺ) ኪዩቢክ ሜትር ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ ያፈሳል።ዓባይ በ 6750 ኪሎ ሜትር ርዝመቱ ቢኩራራም ኮንጎ በፍሰት መጠን አባይን 7 ጊዜ በመብለጥ ብድሩን መልሷል።ይሁን ሁለቱም የአፍሪካ አኩሪ ሀብቶች ናቸው። ስለዚህ ኮንጎ በቸርነትም ሆነ ጉራ ለመንፋት ለዓባይ ውሃ ቢሰጥ በፍጹም ቅር አይለውም ።በተለይም ውሃው ከመስኖ እርሻ በተጨማሪ በዓባይ ላይ ለጀልባና ለመርከብ መጓጓዣ ምቹ ለማድረግ ፍሰቱን በመጨመር ቢተባበር ለአፍሪካውያን ጥቅም እስከሆነ ድረስ ቅር አይለውም።ነገር ግን የዓባይ ሸለቆ ህዝቦችን ይሁንታ ሳይገኝ በክህደት ከአፍሪካ አህጉር ውጪ ሲወሰልት ቢገኝ ክህደቱ በአደባባይ ተነግሮ ውርደቱን እንዲከናነብ ይደረጋል።ስለዚህ እንዲህ ያለ ክህደት እንዳይከሰት ከወዲሁ የዓባይ ሸለቆ ሕዝቦች መርህ ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል።አለበለዚያማ እነሱም በክህደትና በንዝህላልነት ሊጠየቁ እና ሊወቀሱ ይችላሉ።
እነዚህ ሁለቱ ከላይ የተጠቀሱት ከአንድ ወንዝ ወደ ተጓዳኝ ወንዝ ውሃ የማስተላለፉ ሁኔታ፤ ጠለቅ ያለ ዘርፈ ብዙ ጥናት እንደሚያስፈልገው መዘንጋት የለበትም፡፡
v.ከቤት፣ ከኢንዱስትሪና ከመስኖ እርሻ የሚወጡ ፍሳሾችን አጣርቶ መጠቀም
ይኸ እየተለመደ የመጣ አሠራር ስለሆነ ዝርዝር ገለጻ አያስፈልገውም።ነገር ግን ኮንጎ ወንዝ በመጠንም ታላቅ ወንዝ መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል።አሁን ተሠርተው ኃይል በማመንጨት ላይ ካሉት ጣቢያዎች በተጨማሪ 44000 (አርባ አራት ሺ) ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል አመቺ ቦታ ኮንጎ ውስጥ ይገኛል።ይህም ኃይል ከአፍሪካ ተትረፍርፎ ለአውሮፓም ተደራሽ እንደሚሆን ከታወቀ ቆየት ብሏል።ስለዚህ ለግለሰቦች ባዶ ዝና ተብሎ በመደናበር በተናጠል ከመፍጨርጨርና ከመዳከር አስተሳሰብን በማስፋት አህጉራዊ ራዕይ በማዳበር፤ እንደዚህ ያሉ ዕቅዶች ላይ ትኩረት መስጠት የብስለትና የአርቆ አስተዋይነት ሚዛን መሆኑን ከግንዛቤ ማስገባት ያስፈልጋል።አለበለዚያ እንደኢትዮጵያ የተደናበረው የብሔር ተኮር ፖለቲካ በዓለም መሳቂያ ሆኖ ሲደነባበሩና ሲተረማመሱ መኖር ነው።
vi.መደምደሚያ
በኅዳሴው ግድብ ውሃ አሞላል ላይ በግብጽ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ተደርጎ የነበረው ውይይት በጣም አስገራሚ ቀልድ ነው።በመጀመሪያ ደረጃ ለአንድ ጉዳይ ውይይት ወይም ድርድር በሚደረግበት ወቅት የውይይቱ ነጥቦች መዘጋጀት ያለባቸው በተሳታፊዎቹ በሙሉ ስምምነት ነው።በተጨማሪም ጉዳዩ መላውን የዓባይ ሸለቆ አገሮችን የሚመለከት ስለሆነ ፤ በሦስት አገሮች መካከል ብቻ መደረጉም ትክክል አልነበረም ።ማናቸውም የዓባይ ወንዝ ጉዳይ የመላው የተፋሰሱ አገሮች ጉዳይ ሆኖ መቅረብ ይኖርበታል።በተጨማሪም አንድ እቅድ ወደ መጠናቀቅ ደረጃ ደርሶ ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ባለበት ወቅት፤ ሦስተኛ ወገን መጥቶ ልፈትፍት ማለቱ አግባብ አይደለም።የማናቸውም ዕቅድ የመተግበሪያ የጊዜ ሰሌዳ የሚወሰነው ከመዋእለ ንዋይ አዋጭነቱ ጋር በተያያዘ በጥናት መርህ መሠረት ነው።ይኸውም ማለት ዕቀዱ ሥራ የሚጀምርበት ወቅት ለዕቅዱ የወጣውን ወጪ የሚመልስበት የጊዜ ሰሌዳ ተዘጋጅቶ በመተግበር ነው። የጊዜ ሰሌዳው እንዳሻን የምንቀያይረው ከሆነ የዕቅዱ አትራፊነት ይከስማል።ስለዚህ የኅዳሴውን ግድብ የውሃ ሙሌት ግብጽ ገብታ ለመንቦራጨቅ ከፈለገች የሚደርሰውን ኪሣራ ሁሉ መሸፈን ይኖርባታል።ከዚህም በላይ የተሞላው ውሃ በየዓመቱ ኤሌክትሪክ በማመንጨት ስለሚጎል እንደገና የጎደለውን ውሃ መሙላት ያስፈልጋል።ታዲያ በየዓመቱ ከግብጻውያኑ ጋር ስንነታረክ ልንኖር ነው እንዴ !
እንደእውነቱ ከሆነ የኅዳሴው ግድብ ከተጀመረ ስምንት ዓመት ሊያልፈው እኮ ነው።ታዲያ ግብጻውያኑ ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት ውስጥ አንድ እንኳን ለመጠባበቂያ ሳይሠሩ ቀሩ ማለት ነው።ስለዚህ ከነዚህ እውነታዎች ስንነሳ፤ በሦስቱ አገሮች የተደረገው የውይይት ወይም የመደራደሪያ ርዕስ ስለ ግብጽ አማራጭ የማግኛ ዘዴ መሆን ነበረበት።ወደፊትም ቢሆን ዋና የድርድሩ ርዕስ ስለ አማራጭ የውሃ ግኝት መሆን አለበት።አማራጮቹም ከዚህ በላይ በግልጽ የተዘረዘሩ ስለሆኑ በአንክሮ ማሳሰብ ያስፈልጋል።ስለዚህ ኩኩሉ ! አሁንም በድጋሚ ኩኩሉ! ግብጻውያኑን ከዕንቅልፍ ለመቀስቀስ እና ለአማራጮቻቸው ትኩረት እንዲሰጡ ለማነቃቃት ሁላችንም ኩኩሉ ! ኩኩሉ ! በማለት እንቀስቅሳቸው፡፡
በመጨረሻም ዶ/ር አብይንና የሥራ ባልደረቦቻቸውን ‹‹ የአካባቢ ጥበቃ አምባሳደር›› ብለን በመሰየም፤ በአፍሪካ የውሃ ማማዎች በተባሉት ቦታዎች ሁሉ የዛፍ ተከላ ዘመቻ ለማድረግ መላ አፍሪካውያንን በማዝመት ታላቅ አህጉራዊ ሥራ እንዲሠሩ እናበረታታቸው !
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2012
ዶክተር ኢንጂነር ጸጋ ጥበቡ