አፍሪካ ድንቅ እንስሳት፣ ሥነ ምህዳር፣ አየር ንብረት፣ የሚያምሩ ደኖች፣ ልዩ ልዩ ባህሎች፣ወዘተ ይገኙበታል። በተጨማሪም ለኑሮ ምቹና ለዓይን ማራኪ ከተሞችም ከትመውባታል። ከተሞቹ የራሳቸው ባህልና ታሪክ አላቸው። ለዛሬ ከአህጉሪቱ ውብና ማራኪ ከተሞች ዘጠኙን እንመልከት።
ኬፕ ታውን- ደቡብ አፍሪካ
ኬፕታውን አስደናቂ የባህር ዳርቻዎች፣ ውብ ተራሮች እና በአፍሪካ ውስጥ ካሉ ምርጥ የወይን እርሻዎች የተወሰኑትን የያዘች ውብ እና ማራኪ ከተማ ናት። እነዚህን ውብ መስህቦች ለመመልከት በኬብል መኪና መጓዝ፣ በተራራ አናት ላይ በምትወጣው ፀሐይ መውጫ ወይም መግቢያ ላይ መገኘት የግድ ያስፈልጋል። ከከተማዋ መዝናኛ ስፍራዎች በባሕሩ ዳርቻ የሚገኘው የመጫወቻ ሜዳ ሁሉንም ሰው በአንድ ላይ የመያዝ አቅም አለው።
ኢሶሪያ – ሞሮኮ
በ 18 ኛው ክፍለ ዘመን በባህር ዳርቻ ከተመሰረቱ ከተማዎች ኢሶሪያ አንዷ ናት። ከተማዋ ማራኪ የባህር ወደብ እና የዓሣ ገበያ ከሚዘወተሩባቸው መዲናዎች መካከል ትጠቀሳለች። በአህጉሪቱም ከሚጎበኙ በጣም ውብ ከተሞች ውስጥ አንዷ ነች። ከሀገሪቱ ታላላቅ ከተሞች ርቀው ከሚገኙት እና ሞቃታማ ከሆኑት የሞሮኮ ከተሞች ሁሉ ኢሶሪያ በኑሮ የተረጋጋች ትባላለች። በከተዋ ከፍተኛ ንፋስ የሚንፍስባት ስትሆን፣ በባህር ላይ ለሚደረጉ የመንሸራተት መዝናኛዎች ምቹ ነው። ለውሃ ላይ ስፖርት አድናቂዎች መናኸርያም ነች።
ሉክሶር – ግብጽ
አንዷ የጥንቷ የግብጽ ዋና ከተማ ቴብስ ሉክሶር ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በርካታ ግብጻውያንን ጭምሮ ተጓዦችን በመሳብ ትታወቃለች። ጎብኚዎች አሁንም የከተማዋን መልክዓ ምድር በመዘዋወር የጥንት አስደናቂ ነገሮችን እየቃኙ ይገኛሉ። ሉክሶር የሚለው ስያሜ ግብጽ ውስጠግ ከነበረ ፓላስስ ቋንቋ የመጣ ነው። ከተማዋ አስደናቂ የናይል አካባቢ እና በረሃማ ስፍራዎች ያሉባት ውብ ከተማ ናት። የፈርዖን መቃብር፣ ውቡ የካርናክ መቅደስ፣ የሀታስፖት ቤተመቅደስ እና ሌሎች አስደናቂ ሸለቆዎችንም ይዛለች።
ጀንኔ – ማሊ
የጀንኔ ከተማ ከማሊ ቀደምት ከተሞች አንዷ ናት። ከተማዋ የተመሰረተችው ከክርቶስ ልደት በፊት 250 ላይ ነው። በጭቃ ጡብ የተሠሩ ቤቶች እና መስጊዶች በስፋት የሚገኙባት ስትሆን፣ ይህም አስደናቂ እና ውብ ገጽታ እንድትላበስ አርጓታል። በዓለም ትላልቆቹ እና በጭቃ የተሠሩ የአስደናቂ ህንፃዎችና ታላቁ መስጊድ መገኛም ናት። ሙስሊሙ ማህበረሰብ በበዓላት ወቅትም በእነዚህ በጭቃ የተሠሩ ህንፃዎች በከተሙባት ከተማ በብዛት ይታያል።
ስቶን ታውን – ታንዛንያ
በሕንድ ውቅያኖስ አካባቢ ከታንዛኒያ የባህር ዳርቻ በስተቀኝ የዛንዚባር ደሴት ይገኛል፤ የስቶን ታውን ከተማ። ከተማዋ አስደሳች እና የበለፀገ ታሪክ ባለቤት ናት። የሚያምሩ ነጫጭ አሸዋማ የባህር ዳርቻዎች እና የክሪስታል ንፁህ ውሃ መገኛም ናት። ካለፉት 200 ዓመታት ወዲህ በዚህች አሮጌ ከተማ ውስጥ ብዙም ለውጥ አልተደረገም። በእንጨት በተሠሩ በሮች፣ የሱልጣኖች አብያተ መንግሥት፣ ጠመዝማዛ መከለያዎች፣ ጠባብ መንገዶች እና አዝናኝ የገበያ አዳራሾች ስቶን ታውንን አስደናቂ ከተማ አድርገዋታል። ይህ የስዋሂሊ የባሕር ዳርቻ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይንስ፣ ትምህርትና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ተመዝግቦ ይገኛል።
ዊንድሆክ – ናምቢያ
የናሚቢያ ትልቋ ከተማ ናት። መዲናዋ ዊንድሆክ ንፁህ እና ዘመናዊ ከተማ ስትሆን፣ በፓስቴል ቀለም የተዋቡ ሕንፃዎች እና ባህላዊ የጀርመን ቤቶች ይገኙባታል። በዊንድሆክ ከተማ መሃል መንሸራሸር የከተማዋን ውብ ገጽታ በሚገባ ለማየት እንደሚያስችል ይገለፃል። በመጠን አነስተኛ እና ለእግረኛ ተስማሚ ከተማ እንድትሆን ተደርጋ በመገንባቷ በእግር የሚጓዙ ሰዎች ይበዙባታል። ዘመናዊ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች፣ ኒኦ-ባሮክ ካቴድራሎች እና የጀርመን ቤተ መቅደሶች ለከተማዋ ውበት አጎናጽፈዋታል።
ላሙ – ኬንያ
ላሙ የኬንያ ጥናታዊ የባህር ዳርቻ ከተማ ናት። ለመዝናናት በጣም ትመቻለች። ከተማዋ በጥንታዊነቷ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይንስ፣ የትምህርትና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ተመዝግባ በአግባቡ ጥበቃ ይደረግላታል። ጎብኚዎቿ በጥንታዊቷ ከተማ ውስጥ በሚገኙ ውብ ተራሮች ዙሪያ እየተዘዋወሩ ሰዓቶችን ሊያሳልፉ ይችላሉ። በአቅራቢያዋ በሚገኘው ሌላ የባህር ዳርቻም መዝናናት ይችላሉ። ላሙ በባህር ዳርቻዋ ላይ ያለውን አኗኗር ለመለማመድ በጣም ጥሩ ከሆኑት ስፍራዎች አንዷ ነች።
ስቶን ታውን – ሞዛንቢክ
ይህች የደሴት ከተማ ከሞዛንቢክ እጅግ አስደናቂ ስፍራዎች አንዷ ናት። የስቶን ታውን ከተማ ሦስት ኪሎ ሜትር ርዝመት ባለው የሞዛምቢክ ደሴት ሰሜናዊ መጨረሻ ላይ ትገኛለች። ከተማዋ በአንድ ወቅት የፖርቹጋል የንግድ መናኸርያ ነበረች። በእ.ኤ.አ 1507 ውስጥ የፖርቹጋሎች ምስራቅ አፍሪካ ዋና ከተማ ተብላ ተሰይማም ነበር፤ ነገር ግን እ.ኤ.አ. በ1898 ማፑቶ የሚል መጠሪያ ተሰጣት። ይህች የሞዛምቢክ ደሴት ከተማ በአጠቃላይ እ.ኤ.አ በ1991 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይንስ፣ የትምህርትና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ተመዝግባለች።
በከተማው ያለው ሥነ-ሕንፃ ያለፉትን ዘመናት የባሕል ሁኔታዎች ያንፀባርቃል። የፖርቹጋል፣ የዓረብ እና የህንድ ተጽዕኖዎች የየአገሮቹ ባህሎች በከተማዋ እንዲንፀባረቅ አርገዋል።
ባህር ዳር – ኢትዮጵያ
ባህር ዳር ከተማ በዘንባባዎች፣ በአስገራሚ የሐይቅ ዳርቻ እይታዎችና ሰፋፊ መንገዶች የተዋበች ከተማ ናት። የአማራ ክልል ውብ ዋና ከተማ ባህር ዳር በጣና ሐይቅ ዳርቻ ላይ የተቆረቆረች ስትሆን፣ የዓለም ጥንታዊ ገዳማትና አብያተ-ክርስቲያናት መገኛም ናት። እነሱን መጎብኘት የብዙዎች ምርጫም ነው ። ለጎብኚዎች የሚሆኑ ብዙ የጀልባ ትራንስፖርቶች የሚገኙ ሲሆን፣ በአቅራቢዋ የሚገኘው የዓባይ ፏፏቴም እንዲሁ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ እጅግ አስደናቂ መስህቦች አንዱ ነው። ምንጭ የተለያዩ ዌብ ሳይቶች።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2012
መርድ ክፍሉ