በአራት ኪሎ አካባቢ በጫማ ጠረጋ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ኃይሉ ዘበርጋ በደርግ ዘመን ከገጠር ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን ይናገራሉ።ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት እና የአምስት የልጅ ልጆች አያት የሆኑት አቶ ኃይሉ ዘበርጋ የ65 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ናቸው።ወደ አዲስ አበባ እንደመጡ ከአጎታቸው ጋር በጫማ ጠረጋ እየሠሩ በደባል ይኖሩ ነበር።አጎታቸው ቤት ሠርተው ወደ ጀሞ አካባቢ ሲሄዱ እሳቸው መኖሪያ ቤቱን ለቀው በግለሰብ ቤት ተከራይተው ኖረዋል፡፡
በግለሰብ ቤት ተከራይቶ መኖር በሸገር ችግር ነው የሚሉት አቶ ኃይሉ የቀበሌ ቤት ጭምር ሸንሽነው የሚያከራዩ ሰዎች የመጀመሪያ ጥያቄያቸው “ላጤ ነህ ወይ? “ የሚል ነው ይላሉ፤ ባለትዳር ከሆንክ ልጆች ካሉህ ሊያከራዩህ አያስቡም ።ባለትዳር ከሆኑ ውሃና ኤሌክትሪክ በብዛት ይጠቀምብናል ብለው ያስባሉ።ይሄ ደግሞ የስነምግባር እና ሰብአዊነት ችግር ነው፡፡
ባለትዳር ስለሆኑ በእንግልትና በመንከራተት የግለሰብ ቤት ኪራይ አልጋ አንድ ወንበር እና ምድጃ የምታስቀምጥ ቤት ከስድስት ዓመት በፊት መከራየታቸውን ይናገራሉ።በሰበብ አስባቡ የኪራይ ዋጋ ሲጨምርም ሌላ ቤት ፍለጋ ደክመዋል።ብዙ ዓመት ተከራይቼ ኖሬያለሁ ይላሉ፤ በ400 ብር የገባሁበት ቤት ኪራይ በየሦስት ወሩ አከራዬ ዋጋ ትጨምርብኝ ነበር የሚሉት አቶ ሀይሉ፣ በወቅቱ የቤት ቁሳቁስ መግዛት ቀርቶ ያለኝንም በርካሽ ዋጋ እሸጥ ነበር ሲሉ ያስታውሳሉ፡፡
ሆኖም የተከራዩት ቤት ከትንሽ ጊዜ በኋላ የኪራይ ዋጋ ተመልሶ እየጨመረ መቸገራቸውን ይናገራሉ።በአምስት መቶ ብር መከራየት የጀመሩት ቤት ቀስ በቀስ እየጨመረ ከአንድ ሺህ ብር በላይ እስኪሆን ድረስ በአራት ኪሎ አካባቢ የተለያዩ ቤቶችን ተከራይተው ኑሮዋቸውን ለመግፋት ሞክረዋል፡፡
“ቤት አከራዬ ኪራይ እየጨመረች ከአንድ ሺ ብር በላይ ሆነብኝ፤ አልቻልኩም ቀንሺልኝ አልኳት፤ ‘ትወጣታለህ ‘ አለችኝ ።ተስፋ ቆረጥኩ መውጣትማ እወጣለሁ አባቴና እናቴ የሠሩት ቤት አይደለም አልኳት።ወሬ አልፈልግም ነቅለህ ውጣ አለችኝ፤ እስከ ሦስት ወር ድረስ ቤት እስካገኝ የመንግሥት መብት አለኝ አልኳት።ሌሊቱን ተክዤ መተኛት አልቻልኩም ጧት ምንም አማራጭ ስላልነበረኝ አስፋልት ዳር ሸራ ወጥሬ ለመኖር ተገደድኩ።
በአዲስ አበባ ከተማ ዳር የሚገኙ ቤቶች ኪራይ ርካሽ ቢሆንም የትራንስፖርት አቅርቦቱ እና መጉላላቱ አሳሰባቸው፤ ከአራት ኪሎ ሠርቼ ሠርክ ከከተማዋ ዳር ባሉ አካባቢዎች ቤት ተከራይቼ መመላለስ ስለሰጋሁ አልሞከርኩትም ይላሉ፡፡
በሚኖርበት በአራት ኪሎ አካባቢ አንድ አልጋ የምታስቀምጥ ጠባብ ቤት ጫማ ጠርጌ ከአንድ ሺህ ብር በላይ መክፈል አልቻልኩም “ ቸገረኝ ከፋኝ አማራጭ ሳጣ አስፋልት መንገድ ዳር ሸራ ወጥሬ ኖሬያለሁ።“ ሲሉ ይገልጻሉ።መንገድ ዳር ሸራ ወጥረው ለአራት ዓመታት መኖራቸውን የሚገልጹት አቶ ሀይሉ፣ በዚህ መሃል በቀበሌ ቤት ፍለጋ ያለመሰልቸት በተደጋጋሚ ሲመላለሱ እንደነበር ይናገራሉ።አዛውንቱ አመራሮቹ በየጊዜው ይቀያየሩ ስለነበር ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ችግሬን እንደ አዲስ አስረዳ ነበር ይላሉ፡፡
ከለውጡ ወዲህ እኔም ከነቤተሰቦቼ ከጎዳና ተዳዳሪነት ወጥቼ የቀበሌ መኖሪያ ቤት ማግኘት ችያለሁ የሚሉት አቶ ሀይሉ፣በቀበሌ ተደጋጋሚ የሚያደርጉት ምልልስና የሚያስገቡት ማመልከቻ የምስራች ይዞላቸው ይመጣል።በኮንዶሚኒየም ዕጣ ከደረሳቸው መሀል አንዱ ቤቱን አስረክቦ በመሄዱ እሳቸው ዕድሜያቸው፣ ጎዳና ተዳዳሪና ለፍቶ አዳሪ መሆናቸው በቀበሌ ተደጋጋሚ ጊዜ መመላለሳቸው ከግምት ገብቶ የቀበሌ ቤት ተሰጣቸው።
አሁን የደስታ ህይወት ይኖራሉ የቀበሌ ቤት ባለቤት ናቸው፤ ለመሥራት ያለኝ ዐቅሜ በዕድሜዬ ጫማ ጠረጋ ነው ሌላም ሙያ የለኝም ጤነኛ ነኝ ሥራዬን እሠራለሁ ይመስገነው ለፈጣሪ ይላሉ፡፡
መንግሥት አባት ማለት ነው፤ ለዜጎቹ መኖሪያ ለመሥራት ሊተጋ ይገባል፡፡አሁን እኮ ያሉት ቤቶች በንጉሡ ዘመን የነበሩ ናቸው።ወጣቶችም ከአልባሌ ነገር ተጠብቀው በዐቅማቸው በሙያቸው እየሠሩ ገንዘባቸውን ቆጥበው መኖሪያ ቤት የሚገኙበትን መንገድ ማመቻቸት አለባቸው፡፡ሲሉ ምክራቸውን ይለግሳሉ፡፡
አዛውንቱ እድሜያቸውን ሙሉ መጠለያ ሲፈልጉ ኖረው ተሳክቶላቸዋል፤ባገኙት የቀበሌ ቤት ተመስጌን ብለው መኖር ጀምረዋል፡፡በሚሊዮኖች የሚቀጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ግን የቤት ያለህ ማለታቸውን ቀጥለዋል፡፡
አዎን የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የአለም አቀፍ እና እህጉር አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ በመኖሪያ ቤት/መጠለያ/በኩል ጥሩ ስም የላትም፤ አብዛኞቹ ነዋሪዎቿ ቤት አልባዎች ናቸው፤የግለሰብ ቤት ተከራይተው ፣ወይ ከዘመድ ተጠግተው የሚኖሩ ናቸው፡ ፡በቤት እጦት ሳቢያ ከቤተሰብ ጋር የሚሩት በርካቶች ናቸው፤በተወልድክበት አልጋ ላይ እስከ መቼ እየተባሉ መኖራቸውን ቀጥለዋል፡፡
ጎዳና ላይ እየሠሩ ጎዳና ላይ የሚያድሩ ደግሞ ወደ 50 ሺህ የሚደርሱ ጎዳና ተዳዳሪዎች እንዳሉባት አንዳንድ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ይህም የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ሸገር በየጊዜው የሚመጡት ኮረዶችና ጎረምሶች ቢካተትበት ቁጥሩ ሊንር እንደሚችል ጥርጥር የለውም።
የመዲናዋ ዋነኛ ችግርዋ የመኖሪያ ቤት እጥረት መሆኑን መናገር ጥናትና ምርምር የማያስፈልገው የአደባባይ ሚስጢር ነው፡፡የጋራ መኖሪያ ቤቶች ህንፃ መገንባት ከተጀመረ ወዲህ ወደ 200 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን የቤት ባለቤት ቢያደርግም የመኖሪያ ቤት ፍላጎቱ ዝቅ ማለት ቀርቶ ፈቅ ማለት እንኳን አልቻለም።
የቀድሞው ኪቤአድ የአሁኑ የፌዴራል ቤቶች ኮርፓሬሽን በቅርቡ ወደ ቤቶች ልማት ተመልሷል፤ በከተማዋ አስተዳደርም እየተገነቡ ያሉ የጋራ መኖሪያ ቤት ህንፃዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው።ከግንባታዎቹ ጎን ለጎን ግን ፖለቲካዊ ትኩረት ቢሰጣቸው ቤቶቹን በፍጥነት ለማደረስ ሚና ይኖራቸዋል።ሰሞኑንም ለዳኞች በመንግሥት በኩል መኖሪያ ህንፃዎች ተገንብተው ተሰጥተዋል።ጅምሩን ስናደንቅ የግል መኖሪያ ቤትም ሆነ የቀበሌም ሆነ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ተከራይ አለመሆናቸው ሊጣራ የሚችልበት መንገድ ማመቻቸት መልካም ነው፡፡
መንግሥት ህዳሴ ግድብን ዘንድሮ የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት ያሳካውና ዜጋውን ሁሉ ያረካው ፖለቲካዊ ትኩረት ስለተሰጠው ነው።ለአዲስ አበባ መኖሪያ ቤቶችም ተመሳሳይ ትኩረት ተሰጥቶ በሚፈለገው ፍጥነት ማድረስ የሚቻልበት መንገድ ማመቻቸት ይገባል፤ ጠቀሜታውም ሁለንተናዊ ነው።ሥራ አጡ በመኖሪያ ቤቶቹ ግንባታ ጊዚያዊ ሥራውን እየሠራ ከአልባሌ ነገር ሲርቅ ቤት አልባውም ቤቱን አግኝቶ በመንግሥት ረክቶ ፈጣሪን አመስግኖ ይኖራል ።ከተማዋም የበለጠ ዘመናዊ እየሆነች ትሄዳለች፤ በሸገር ነዋሪዎች ዘንድ ቅቡልነት ያላቸው ምክትል ከንቲባ ታከለ የበለጠ ስማቸውን ተክለው የመኖሪያ ቤቶችን ችግርን ነቅለው ማሳየት አለባቸው። ቸር ይግጠመን!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ