ከቃሊቲ አደባባይ ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ፕሮጀክት ጋር ይገናኛል። የከተማዋን የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ እንደሚያሳልጥ ይጠበቃል። የከተማዋን የመንገድ መረብ በማሳደግ ረገድም ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተገምቷል- የቃሊቲ ቀለበት መንገድ አደባባይ- ቂሊንጦ-ቡልቡላ መንገድ ፕሮጀክት።
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እያሱ ሰለሞን እንደሚገልፁት ከቃሊቲ ቀለበት መንገድ አደባባይ ተነስቶ በቂሊንጦ አደባባይ አርጎ ቦሌ ቡልቡላን አካቶ የውጪ ቀለበት መንገድ ላይ የሚደርሰው የመንገድ ግንባታ ክፍል በአጠቃላይ 10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፣ ከ40 እስከ 50 ሜትር የጎን ስፋት አለው።
የመንገድ ፕሮጀክቱ የቃሊቲ ማሰልጠኛ አደባባይ ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ፕሮጀክትን በሚገነባው በቻይናው ኮሚዩኒኬሽን ኮንስትራክሽ ኩባንያ /cccc/ የግንባታ ስራው እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን፣ የክትልልና ቁጥጥር ስራው ደግሞ በሃይዌ ኢንጂነርስና ኮንሰልታንሲስ እየተሰራ ይገኛል።
የከተማዋን የመንገድ መረብ ለማስፋት እየተሰራ ያለው የቃሊቲ ቀለበት መንገድ አደባባይ- ቂሊንጦ- ቡልቡላ መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ በመጋቢት ወር 2009 ዓ.ም ነው ግንባታው የተጀመረው፤ለግንባታውም 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት ተመድቦለታል።
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት በተለይ ቡልቡላ አካባቢ ትልቅ የመሸጋገሪያ ድልድይና ሌሎች ተያያዥ የመንገድ ግንባታዎችም እየተከናወኑ ይገኛሉ። እስከ ሰኔ ወር 2012 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ባለው አፈጻጸም 66 ከመቶ ደርሷል።
የመንገድ ግንባታው እየተፋጠነ ሲሆን፣ እስካሁን ባለው ሂደት የቤዝ ኮርስ፣ሰብ ቤዝና ከቂሊንጦ አደባባይ እስከ ቡልቡላ ድልድይ ድረስ ያለው አስፓልት ማንጠፍ ስራዎችና የድልድይ ግንባታዎች ተከናውነዋል። ትልቁ ስራ የሚሆነውና የፕሮጀክቱን አብዛኛውን ስራ የያዘው ቡልቡላ አካባቢ እየተገነባ ያለው ትልቅ የመሸጋገሪያ ድልድይ ሲሆን፣ ይህም ግንባታ እየተነከናወነ ይገኛል። ሌሎች በመንገድ መጋጠሚያ አካባቢዎች ላይ የሚቀሩ ስራዎችም እየተካሄዱ ይገኛሉ።
የዚህ መንገድ ፕሮጀክት ዋነኛ ተግዳሮት የወሰን ማስከበር ስራ ነበር፤ መንገዱ በእምነት ተቋማት አካባቢዎች የሚያልፍ በመሆኑና ሌሎች መኖሪያ ቤቶችም የሚነሱባቸው ሁኔታዎችም ስለነበሩ በፕሮጀክቱ ላይ መዘግየቶች ተፈጥረዋል። እነዚህን የወሰን ማስከበር ስራዎች በመፍታት ረገድ የከተማ አስተዳደሩ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት መሰረት ምክትል ከንቲባውን ጨምሮ የሚመለከታቸው የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በየጊዜው ክትትል በማድረግ ችግሮቹ እንዲፈቱ ተደርገዋል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚገልፁት፤የመንገድ ፕሮጀክቱ ከፍተኛ ወጪ እየተደረገበት ይገኛል። በአጠቃላይ ለከተማዋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል። ለተሽከርካሪዎችም የትራፊክ መጨናነቅ ሳይፈጠር አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል። የሃገሪቱ ወጪና ገቢ ንግድ የሚከናወንበት ዋነኛ ኮሪደር በመሆኑም ይህን በማሳለጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ከከተማዋ ወደ ምስራቅና ደቡብ አቅጣጫ ለሚደረጉ ጉዞዎችም እንደ ዋና መውጫ በር ሆኖ ያገለግላል።
ፕሮጀክቱ በከተማው አስተዳደር የበላይ አመራሮች ከፍተኛ ክትትል የሚደረግበት በመሆኑ፣ በየጊዜው አጠቃላይ ስራዎቹ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በመሆን ይገመገማሉ። የቴክኒክ ባለሞያዎችም የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እያደረጉበት የሚገኙ በመሆኑ አጠቃላይ አፈፃፀሙ በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ የመንገድ ፕሮጀክቱ ወደ ጎሮ አደባባይ ሄዶ ከውጪኛው ቀለበት መንገድ ላይ ከወጣ በኋላ ከቃሊቲ አደባባይ ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ክፍል ጋር በመተሳሰር ከአዲስ አዳማ የክፍያ መንገድ ያደርሳል።
በአሁኑ ወቅት የክረምቱ ወቅት ጫን እያለ በመምጣቱ በስራዎች ላይ ጫና ፈጥሯል የሚሉት ምክትል ዋና ስራ አስኪያጁ፣በአሁኑ ወቅት ትልቅ ርብርብ እየተደረገበት ያለው ትልቁን ድልድይ በማጠናቀቅ ስራ ላይ መሆኑን ይገልጻሉ። ከድልድዩ ቀጥሎ ያሉትና ወደ ቡሉቡላ አደባባይ የሚመጣውን ማገጣጠሚያ መስመርንና ወደዚሁ የሚመጡ መስመሮች ቀሪ ስራዎች መሆናቸውን ያብራራሉ።
የመንገድ ፕሮጀክቱ አፈፃፀም አሁን በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አመልክተው፣ቀሪ ስራዎቹ በሚቀጥለው አመት መጨረሻ ላይ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለትራፊክ ክፍት ይሆናል ይላሉ።
አብዛኛዎቹ የከተማዋ መንገድ ፕሮጀክቶች ውል የሁለትና የሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ነው። የዚህ መንገድ ግንባታም በዚህ አመት መጨረሻ መጠናቀቅ ነበረበት። ሆኖም ግን ከዚሁ የወሰን ማስከበር ስራ ጋር በተያያዘ ለጥቂት ወራቶች ዘግይቷል። ይሁንና አሁንም የፕሮጀክቱ አፈፃፀም ጥሩ በመሆኑ በቀጣዩ አመት መጨረሻ ላይ የመጠናቀቅ እድሉ የሰፋ ነው።
ሌሎች መንገዶች ለአብነትም ቡልቡላ አካባቢ ወደሚካኤል የሚወስደው መንገድ ግማሽ ያህሉ ተሰርቷል። ወደ ሳሪስ አቦ አቅጣጫም የሚወጣው መንገድም ተሰርቷል። እነዚህ መንገዶች ተመጋግበውና ተሳስረው እንዲወጡ ስለሚፈለግና የመንገድ ፕሮጀክቱም የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት በማቃለል ረገድ ካለው ፋይዳ አንፃር በቶሎ መጠናቀቅ ይኖርበታል።
የቃሊቲ ቀለበት መንገድ አደባባይ- ቂሊንጦ-ቡልቡላ መንገድ ፕሮጀክት ከቦሌ ሚካኤል ተነስቶ በቡልቡላ በኩል አድርጎ በቀጥታ ከቡልቡላ ቂሊንጦ መንገድ ጋር በቀጥታ የሚያገናኝ ሲሆን፣መንገዱ ወደ ቃሊቲ አደባባይ ለመውጣትም ያስችላል። በዛውም ወደ ምስራቅና ደቡብ የኢትዮጵያ አቅጣጫ የሚወስድ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳው የጎላ እንደሚሆን ይጠበቃል፤ የከተማዋንም የመንገድ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግር ይታመናል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2012
አስናቀ ፀጋዬ