ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ለህዝብ ይፋ ያደረገውን የሦስት ዓመት ስትራቴጂና የ2012 በጀት ዓመት እቅድ ተግባራዊ በማድረግ ተቋሙን በደንበኞቹና በአጋሮቹ ዘንድ ተመራጭ ለማድረግ ሰፊ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። የኢትዮ ቴሌኮም ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ የ2012 በጀት ዓመትን ስራ አፈፃፀም አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
እንደእርሳቸው ማብራሪያ ከሆነ፤ በበጀት ዓመቱ የተያዙ ስትራቴጂያዊ ግቦችን ለማሳካት መጠነ ሰፊ የለውጥና የማሻሻያ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን፤ በዋናነትም የደንበኞች ተሞክሮን ማሻሻልና እርካታን ማሳደግን ታሳቢ ያደረገ የኦፕሬሽን ልህቀት ለማምጣት ጥረት ተደርጓል።የአገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን የማሳደግ፣ የደንበኞችን አቅም ያገናዘበ የታሪፍ ማሻሻያ የማድረግ፣ የሀብት አጠቃቀም ማሻሻልና የፋይናንስ አቅምን ማጎልበት፣ የገጽታ ግንባታ ሥራዎችን ማከናወን፣ ስትራቴጂን የመንደፍ፣ የማስፈጸምና የመፈጸም እንዲሁም ውሳኔ የመስጠት አቅምን ማጎልበት የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል። የወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩን በአጠቃላይ በስራ አፈፃፀሙ ዙሪያ የሰጡትን ማብራሪያ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ከቴሌኮም መሰረተ ልማት አንፃር
በበጀት ዓመቱ የቴሌኮም አገልግሎት ለማስፋትና የኔት ወርክ ትራፊክ መሸከም የሚችሉ ማስፋፊያ ስራ ተከናውኗል።የኮቪድ ወረርሽኝ በመከሰቱ በሁለተኛው ግማሽ ዓመት እንደተፈለገው ስራዎች መከናወን አልቻሉም ነበር።በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት የተሰሩ ማስፋፊያዎች ውጤታማ ስለነበሩ በሁለተኛው ግማሽ ዓመት የተፈጠሩትን ጫናዎች መቋቋም አስችሏል።
በአዲስ አበባ የ4ጂ ማስፋፊና አድቫንስድ 4ጂ ማስፋፊያ ተሰርቶ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።በዚህም የኮቪድ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ የተፈጠረውን የትራፊክ መጨናነቅ ማቃለል አስችሏል።የ4ጂ አገልግሎት ቀደም ብሎ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ የነበረ ቢሆንም በሁሉም ቦታ ተደራሽ ስላልነበረ የማስተካከል ስራ ተከናውኗል።
በአዲስ አበባ የሚገኙ ደንበኞችን የዳታና የኢንተርኔት ፍላጎት ሲሟላ የነበረው በ3ጂ ኔት ወርክ ነበር።በአሁን ወቅት ግን በአዲስ አበባ የዳታና የኢንተርኔት ፍላጎት በ4ጂ ቴክኖሎጂ እየተሟላ ይገኛል።በዚህም የ4ጂ ኔትወርክ በእጥፍ ማለትም በ200 በመቶ እንዲያድግ ተደርጓል።የ4ጂ ኔት ወርክ ተጠቃሚ በመብዛቱ የ3ጂ ኔት ወርክ የሚጠቀሙ ሰዎችን የኔት ወርክ መጨናነቅ አስቀርቶላቸዋል።በቀጣይ የ4ጂ አድቫንስ ኔት ወርክ በአዲስ አበባ አጠቃላይ አካባቢ ለማዳረስ እቅድ ተይዟል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለመስራት እቅድ ተይዞ የነበረው በክልል ከተሞች የ4ጂ ኔት ወርክ ማስፋፊያ ስራ ነበር።ነገር ግን በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በግብይት ሰንሰለቱ ላይ በተፈጠረ ችግር በተፈለገው ደረጃ መስራት አልተቻለም።በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተሰሩት ማስፋፊዎች አጠቃላይ በውስጥ አቅም የተከናወኑ ናቸው።ካሉት 58 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዲቫይሶች ውስጥ 32 ነጥብ 6 ሚሊዮን ስማርት ስልክ ናቸው።የስማርት ስልክ ማደግ ደንበኞች ኢንተርኔት እንዲጠቀሙ እገዛ ያደርጋል።
የቴሌኮም ቅድመ ክፍያ አሰራርን ወደ ኤሌክትሮኒክ ለማሳደግ ስራ ተጀምሯል።የኤሌክትሮኒክ አሰራሩ ያስፈለገው የካርድ አገልግሎት ለማከናወን የሚረዳው ካርድ ተሰርቶ የሚመጣው ከውጭ ነው።ሌላው ደግሞ የካርድ አገልግሎት ከአየር ንብረት ጋር ተስማሚ ባለመሆኑ ነው።ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ የካርድ አገልግሎት ሳይቆም የኤሌክትሮኒክ አገልግሎት እንዲጀመር ተደርጓል።በዚህም የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል።
ከገቢ አንፃር
በበጀት ዓመቱ ኩባንያው 47 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ በማግኘት የእቅዱን 105 ነጥብ አንድ በመቶ በማሳካት የላቀ አፈጻጸም አስመዝግቧል።ይህ ውጤት ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ31 ነጥብ አራት በመቶ አድጓል።ይህን ከፍተኛ እና ከእቅድ በላይ የሆነ ገቢ ማግኘት የተቻለው የደንበኞች የቴሌኮም አጠቃቀምን ለማሳደግና ተሞክሯቸውን ለማሻሻል የሚያስችሉ የኔትወርክ ማስፋፊያና የአገልግሎት ጥራትን ለመጨመር የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን በመተግበር፤ የ4ጂ አገልግሎትን በመላው አዲስ አበባ እና ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የ4ጂ አድቫንስድን በተወሰኑ አካባቢዎች በመዘርጋት፤ የባለገመድ ብሮድባንድ አገልግሎት ላይ ሰፊ ማሻሻያዎችና እጅግ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ እንዲሁም ከመደበኛ የቴሌኮም አገልግሎቶች በተጨማሪ ሌሎች እሴት የሚጨምሩ 16 አዳዲስ እና 25 ነባር የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ምርትና አገልግሎቶችን በማሻሻል ለደንበኞች በማቅረብ ነው፡፡
የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች 147 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተገኘ ሲሆን፤ ይህም የእቅዱን 107 በመቶ እንዲሳካ ማድረግ አስችሏል።ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ50 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።በውጭ ምንዛሪ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የቴሌኮም ማጭበርበርን በተለያዩ ስልቶች በመከላከል እና የተቋም ደህንነትን ከማረጋገጥ አኳያ ልዩ ትኩረት ማድረግ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ቢዝነስ አጋሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻሻልና ለማጠናከር ሰፊ ሥራዎች ተከናውነዋል።
ገበያው በሚጠይቀው መሠረት አዳዲስ አሰራሮችን በመከተል የተገኘው ገቢ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የሞባይል ድምጽ ገቢ ድርሻ 49 በመቶ፣ የዳታና ኢንተርኔት ገቢ ድርሻ 29 በመቶ፣ የዓለም አቀፍ ንግድ ገቢ ድርሻ ዘጠኝ በመቶ፣ እሴት ከሚጨምሩ አገልግሎቶች ዘጠኝ ነጥብ አራት በመቶ እንዲሁም ከሌሎች አገልግሎቶች የተገኘው ገቢ ድርሻ ሶስት ነጥብ ስድስት በመቶ ይይዛል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑ ዋና ዋና ክፍያዎች መካከል 11 ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር ታክስ እና አራት ቢሊዮን ብር ዲቪደንድ ለመንግስት የተከፈለ ሲሆን፤ በቬንደር ፋይናንሲንግ ሞዳሊቲ ለተከናወኑ ፕሮጀክቶች ብድር 10 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ወይም 318 ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ተፈፅሟል።እነዚህንና ሌሎች ክፍያዎችን ፈጽሞ ወደ ቀጣዩ በጀት ዓመት በጥሩ የጥሬ ገንዘብ መጠን ተሸጋግሯል፡፡
በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ የደንበኞች ብዛት 46 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ካለፈው በጀት ዓመት ማጠናቀቂያ ሲነጻጸር የአምስት ነጥብ ስምንት በመቶ እድገት አሳይቷል።በአገልግሎት አይነት ሲታይ የሞባይል ድምፅ ደንበኞች 44 ነጥብ አምስት ሚሊዮን፣ የዳታ እና የኢንተርኔት ተጠቃሚ 23 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን፣ የመደበኛ ብሮድባንድ ደንበኛ 212 ነጥብ ሁለት ሺህ እንዲሁም መደበኛ ስልክ 980 ሺህ ደንበኞች ናቸው።በበጀት ዓመቱ በባለገመድ ብሮድባንድ አገልግሎት ላይ በተደረጉ የአገልግሎት ማሻሻያዎችና ከፍተኛ የታሪፍ ቅናሽ ምክንያት የብሮድባንድ ደንበኞች ቁጥር በ135 በመቶ ማሳደግ ተችሏል።በዚህም አጠቃላይ የቴሌኮም ስርጸት 46 ነጥብ አንድ በመቶ ደርሷል፡፡
ማህበረሰብ አገልግሎትና የገጠሙ ተግዳሮቶች
ኩባንያው ለደንበኞቹ ከሚሰጠው የቴሌኮም አገልግሎት በተጨማሪ ለማህበረሰብ ፋይዳ ባላቸው ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በተቀናጀ መልኩ በሚገባ እየተወጣ ይገኛል።በበጀት ዓመቱ በአይነት፣ በአገልግሎትና በገንዘብ በድምሩ አንድ ነጥብ 15 ቢሊዮን ብር በላይ አስተዋጽዖ አድርጓል።በመላው ሃገሪቱ በትምህርት፣ በጤና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ አረንጓዴ ልማትና ማስዋብ ላይ ተሳትፏል።
ኩባንያው ከሚያደርገው እገዛ በተጨማሪ ሠራተኞችን በበጎ ፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አስተዋፅኦ በማድረግ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ከሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር የገንዘብ እና የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም ደም በመለገስና የመልካም ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት እጅግ የሚበረታታና አርአያነት ያለው ተግባር አከናውኗል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰው ልጆችንና ተቋማትን እየተፈታተነ ያለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም የተለያዩ እርምጃዎች የወሰደ ሲሆን፤ የቴሌኮም አገልግሎት ለድርጅቶች፣ ለመንግስትና ለማህበረሰቡ እንደዋነኛ የመገናኛና የሥራ ማስኬጃ አማራጭ በመሆኑ አብዛኛው ማህበረሰብ በቴሌኮም አገልግሎት ላይ በመመርኮዝ ከቤቱ ሆኖ ሥራውን ማከናወን፣ ማህበረሰቡን ማህበራዊ ርቀትን ጠብቆ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን ማከናወን እንዲችል ለማገዝ ከፍተኛ ቅናሽ ያለው ፓኬጅ ለተጠቃሚዎች አቅርቧል፡፡
በተጨማሪም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ከፍተኛ ሀብት በመመደብና ትኩረት በመስጠት የጎላ ሚና የተጫወተ ሲሆን የአንድ መቶ ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ፤ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የስልክ ጥሪን የኮቪድ-19 መከላከል መልዕክቶች ለማስተላለፍ መጠቀም፤ ማህበረሰቡ ኮቪድን ለመከላከልና መረጃና አስፈላጊ እርዳታ ለማግኘት የሚችልባቸው አጫጭር ቁጥሮች ለፌዴራልና ለክልል መንግስታት በነጻ የማቅረብ፣ የጤና ሚኒስቴርና የማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ወረርሽኙን አስመልክቶ በድረ ገጻቸው የሚስተላልፉትን መረጃ በነጻ ማድረስ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በኮቪድ ምክንያት እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው አካላት የሚሆን የገንዘብ ማሰባሰቢያ አማራጮችን የማቅረብ፣ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አማካይነት በኮቪድ – 19 ላይ ለሚደረግ ምርምር የገንዘብ አስተዋጽኦ የማድረግ እንዲሁም ከወረርሽኙ ጋር በተገናኘ ትምህርት በመስተጓጎሉ ተማሪዎች የትምህርት መረጃዎችን በነጻ የሚያገኙበት ሁኔታ የማመቻቸትና የመሳሰሉ ተግባራት አከናውኗል፡፡
በበጀት ዓመቱ ኢትዮ ቴሌኮም ከገጠሙት ተጋዳሮቶች መካከል፤ የኮቪድ- 19 በዓለም አቀፍና በሀገሪቱ መከሰት ኩባንያው አገልግሎቱን ለማሻሻል በሚያደርጋቸው የማስፋፊያ ሥራዎችና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እንዲሁም አዳዲስ ደንበኞችን ለማፍራት እንቅስቃሴን ገድቧል።
በሌላ በኩል የፋይበርና ኮፐር መስመሮች ስርቆትና መቆረጥ፣ የሃይል አቅርቦት መቆራረጥ፣ የቴሌኮም ማጭበርበር፣ የጸጥታ ችግሮችና የቴሌኮም ጣቢያዎች መትከያ ቦታ አቅርቦት መዘግየት በዋናነት የሚጠቀሱ ተግዳሮቶች ናቸው።በአጠቃላይ ኢትዮ ቴሌኮም የበጀት ዓመቱ አፈጻጸም እጅግ የላቀና ለበለጠ ስኬት የሚያነሳሳ ሲሆን፤ በተለይም በአሁኑ ወቅት በዓለምና በኢትዮጵያ ከገጠመው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አንጻር የቴሌኮም አገልግሎትን ለመስጠትና ለማስፋፋት ካለው ፈታኝ ሁኔታ አንጻር አፈጻጸሙን እጅግ አመርቂ ያደርገዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2012
መርድ ክፍሉ