የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመጀመሪያው አዳራሽ በአዲስ አበባው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ግቢ ውስጥ ይገኛል ። ከእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ወደ ታላቁ ቤተመንግስት በሚወስደው መንገድ በስተቀኝ በኩል የሚገኘው ይህ አዳራሽ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እኤአ ግንቦት 25 ቀን 1963 የተመሰረተበትም ነው።
የዚህ ህንጻ አርክቴክቸር በ18 ወራት ውስጥ ተሰርቶ እኤአ መጋቢት 1961 መጠናቀቁን የዊኪፒዲያ መረጃ ያመለክታል። ህንጻው በ75 ሺ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን ፣ለሌሎች አገልግሎቶች የዋለ ሌላ 13 ሺ800 ካሬ ሜትር ቦታም አለው።3ሺ600 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው አዳራሾችም ተካተውበታል።5ሺ500 ካሬ ሜትር ላይ ያረፉ ቢሮዎች አሉት፤ለሌሎች አገልግሎቶች የዋለ 4ሺ700 ካሬ ሜትር ቦታም አለው።
ህንጻው በዋናነት ከሚታወቅባቸው መካከልም ግቢው ለቀቅ ያሉ ውብ ክፍት ቦታዎች ያሉት መሆኑ ላይ ነው።ከአስር አመት በኋላ እኤአ በ1971 ግቢው በተባበሩት መንግስታት ወጪ የማስፋፋት ስራ ተከናውኖለታል።ይህም ግንባታ በአራት አመታት ውስጥ ተከናውኖ እኤአ በ1974 ተጠናቅቋል።በዚህ የማስፋፋት ስራም 800 አዳዲስ ቢሮዎች ተገንብተዋል።ባለ 6 ወለል ለተለያዩ አገልግሎቶችና ለግዙፍ ቤተ መጻህፍትነት የዋለ ህንጻም ተገንብቶለታል።የማስፋፋት ስራው በተጨማሪ 130 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ነው የተካሄደው።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አዳራሽና የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽን የመሳሰሉ ሁለት ግዙፍ ግንባታዎችን በማካሄድ ‹‹ታላላቅ ህንጻዎችን በኢትዮጵያም መገንባት ይቻላል›› በሚለው የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ አቋም መሰረት ግንባታው መካሄዱንም መረጃው ያመለክታል።የግንባታው ፋይዳም የታየው ከህንጻዎቹ ውስብስብነትና መጠን አንጻር ሳይሆን የሐገር ውስጥ ምርቶችን በሚገባ መጠቀም ላይ ነው።ግንባታው ሀብቱን በፍራሹ ስር መደበቅን ስራ ያረገውን መካከለኛ ባለሀብቱን በግንባታው ዘርፍ እንዲሰማራ እንደሚያነቃቃም ታምኖበት ነው የተካሄደው።ይህን በማድረግም ባለሀብቶች ታላቋን አዲስ አበባ ወደ እውነተኛ ከተማ ለመለወጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ርብርብ እንዲያደርጉ ታስቧል።
የአፍሪካ አዳራሽ የአፍሪካ ሀገሮች በሙሉ ከቅኝ ግዛት መላቀቅ አስፈላጊነት የሚያሳየውና 150 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የታዋቂው ኢትዮጵያ ሰዓሊ የአለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ስእልም ይገኝበታል።ስእሉ የአፍሪካ ሀገሮች ከድህነት እና በሽታ ለመላቀቅ የሚያደርጉትን ግብግብ የሚያመለክትም ነው።በአዳራሹ ሌሎች የሰዓሊው ስራዎች አሉበት።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2012
ኃይሉ ሣህለድንግል