እንደ አንድ የልማት ተቋም በአገሪቱ እየተካሄደ ያለውን የልማት እንቅስቃሴ በመደገፍ በኩል የተጣለበት ኃላፊነት ከፍተኛ ነው።ለመኖሪያ፣ ለንግድ፣ ለድርጅቶችና ለሌሎች ግልጋሎቶች የሚውሉ ቤቶችን በማቅረብ የተሰጠውን ኃላፊነት እንዲወጣ የሚቻለውን ሁሉ ጥረት እያደረገ ይገኛል-የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን።
የቀድሞው የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በሚል አዲስ ስያሜ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ በደንብ ቁጥር 398/2009 የተለያዩ አላማዎች ተሰጥተውት የመንግስት የልማት ድርጅት ሆኖ እንደ አዲስ ሲቋቋም በተለይም በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ የሚታየውን ከፍተኛ የቤት አቅርቦት ችግር ለመፍታት የሚያስችለውን አቅም ለመፍጠር በርካታ ኃላፊነቶች ተሰጥተውታል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ክብሮም ገብረ መድህን እንዳሉት፤ ኮርፕሬሽኑ እንደ አንድ የልማት ድርጅት በራሱ ገቢ የሚተዳደር ተደርጎ እንደ አዲስ የተቋቋመው በአዋጅ በ2009 በየካቲት ወር ነው።ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ የገባውም በ2010 ዓ.ም ሲሆን፤ ስትራቴጂ ቀይሶ፣ የቤት ቆጠራ አካሂዶ፣ የኪራይ ተመን ማሻሻያ አድርጎ ለአመታት አቋርጦት ወደነበረው ቤት ግንባታ የተመለሰው ደግሞ ከ2010 ወዲህ ነው።በዚህ ጊዜ ለቤቶች ዋጋ ማውጣትም ጀምሯል፡፡
ተቋሙ እንደ አንድ የልማት ድርጅት ሲቋቋም ያሉትን ቤቶች ዘመኑን በሚመጥን መልኩ እንዲያስተዳድር፣ ሲበላሹ እንዲጠግን፣ ከሚሰበስበው ገቢ በከተማዋ ለንግድና ለመኖሪያ በኪራይ የሚቀርቡ ቤቶችን እየገነባ መንግስት ቤት ለሚያቀርብላቸው ባለስልጣናት፣ ዲፕሎማቶች፣ወዘተ የሚሆኑ ቤቶችን በመገንባትና በማዘጋጀት በኪራይ ለማቅረብ ነው።በቀጣይም አቅሙን እያጎለበተ ለሰራተኞች ጭምር ቤቶችን እየገነባ በኪራይ እንዲያቀርብ በሚል ነው። በሂደት እያደገ ሲሄድ ገቢውን እያሻሻለ ቤቶችን እየገነባ ሲቀጥል ደግሞ በመንግስት የስልጣን ተዋረድ ውስጥ /በፌዴራል ደረጃ/ ላለው ሰራተኛ ሁሉ የሚከራይ ቤት በማቅረብ ከዚያም አልፎ የንግድ ቤቶችን ለንግዱ ማህበረሰብ በኪራይ በማቅረብ የግብይት ስርአቱን መደገፍን ታሳቢ በማድረግ ተቋቁሟል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ 18ሺህ153 ቤቶች እንዳሉት አቶ ክብሮም ጠቅሰው፣ ከእነዚህ መካከል የንግድና የድርጅት ወደ 6ሺህ 500 አካባቢ መሆናቸውን የተቀሩት የመኖሪያ ቤቶች መሆናቸውን ያብራራሉ።ኮርፖሬሽኑ በመልሶ ልማትና መሰረተ ልማት ግንባታ በሚል ከአንድ ሺህ በላይ ቤቶችን ማጣቱንም ዳይሬክተሩ ያመለክታሉ።
ኮርፖሬሽኑ ቤት የሚያከራየው ለፌዴራል መንግስት ኃላፊዎች በመሆኑ አመራር ሲለቅ አመራር ይተካል።በሌላ በኩል የሚለቀቅ ቤት ግን የለም።በጣም ውስን ቤቶች የሚለቀቁበት ሁኔታ ቢኖርም፣ የቤት ጥያቄ በሚሊየን እየተቆጠረ እየተለቀቀ ያለው ቤት መጠን እና አቅርቦት ግን ‹‹አለ የሚያሰኝ አይደለም›› ይላሉ።
አቶ ክብሮም ኮርፖሬሽኑ አሁን ከሁለት አስርት አመታት በፊት ያደርግ ወደነበረው የቤት ልማት መመለሱን ጠቅሰው፤ በአዲስ አበባ ከተማ አምስት ሳይቶችም ግንባታዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ያመለክታሉ።ግንባታዎቹም በአቧሬ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ አካባቢ፣ በመካኒሳ፣ ብሪቲሽ ካውንስልና ቦሌ ላይ እየተካሄዱ ሲሆን፣ ህንጻዎቹ እስከ 10 ፎቅ የሚደርሱና ለቅይጥ አገልግሎት (ለንግድ እና ለመኖሪያ) በሚል እየተገነቡ መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡
እንደ አቶ ክብሮም ገለጻ፤ ቤቶቹ ግንባታቸው ሲጠናቀቅ ዘመናዊ በሆነ የቤት አስተዳደር ስርዓት እንዲተዳደሩ ይደረጋል።ዘመናዊ የአኗኗር ስልትን የሚፈልጉ ተደርገው እየተገነቡ ይገኛሉ።‹‹ለከተማዋም ጥሩ ገጽታ ይሆናሉ›› ተብለው የታሰበባቸው ሲሆን፤ ጥሩ የግብይት ስርዓት በመፍጠር የአካባቢውን ኢኮኖሚ የሚያነቃቁ እንዲሆኑ ታስቧል።
እንደየቦታው ስፋት መንታ /ትዊን/ ተደርገው የተገነቡም አሉ። የመካኒሳው ፕሮጀክት ሁለት መንታ ግዙፍ ህንጻዎች ያሉት ሲሆን፤ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ያለውም እንዲሁ ባለሁለት ግዙፍ ህንጻዎች ነው።የብሪቲሽ ካውንስል አካባቢውም ባለሁለት ህንጻ ነው።የቦሌው አንድ ግዙፍ ህንጻ ነው፡፡
አንዳንዶቹ ህንጻዎች ባለሰባት፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ባለ 10 ወለሎች ሲሆን፤ እየተገነቡ ያሉት በከተማ አስተዳደሩ የየአካባቢው ፕላን መሰረት ነው።በአጠቃላይ ግን የንግድ ተቋማቱ ብዛት በካሬ ሆኖ ወደፊት የሚለይ ሲሆን፤ የተቀሩት ግን ለቀቅ ባለ /ሌግዠርየስ/ በሆነ መልኩ ወደ አንድ ሺ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ቤቶች እየተገነቡ ነው።
‹‹በቀጣይ ደግሞ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች እንደሚኖሩ ይጠበቃል›› ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የአሁኖቹ ፕሮጀክቶች ልምድ የሚቀሰምባቸው፣ አቅም እና ካፒታል የሚሰባስብባቸው መሆናቸውን ይናገራሉ።
‹‹አሁን እየሰራን ያለው በውስጥ አቅም ነው።በቀጣይ ግን በተለያዩ መንገዶች እንመጣበታለን፡፡›› ያሉት አቶ ክብሮም፤ ለምሳሌ በመንግስትና በግል አጋርነት፣ ከባንክ ብድር በመውሰድ የሚሰራበት ሁኔታ ይኖራል።የፌዴራል መንግስት እንዲሰራለት የሚፈልጋቸው ቤቶችም በኮርፖሬቱ የሚሰራበት ሁኔታ ይኖራል ይላሉ፡፡
በእዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስትራክቸር አደራጅቶ፣ የሰው ሀይል አዘጋጅቶ፣ ሀብቱን ለይቶ፣ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ወደ ግንባታ መግባት ትልቅ ስኬት መሆኑን የገለጹት አቶ ክብሮም፤ ሌሊት እና ቀን በመስራት በተቋሙ ላይ ለውጥ ለማምጣት ጥረት መደረጉን ይጠቅሳሉ።በተለይ ግንባታ ላይ ያለውን እንቅስቃሴ የፓርላማ አባላት እንደጎበኙትና ለስራውም አድናቆቱ እንዳላቸው መግለጻቸውንም ነው ያብራሩት፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ የተጠቀሱት ግንባታቸው እየተካሄደ የሚገኝ ቤቶች ትንሽ ቁጥር አይደለም፤ ዘመናዊ የንግድና የመኖሪያ አካባቢን ከመፍጠር አኳያ ታስቦበት የሚሰሩ በመሆናቸው ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።መሀል ከተማ ላይ ቦታ ተፈልጎም የተገነቡ ናቸው።ለቅይጥ አገልግሎት ማለትም ለመኖሪያ፣ ለንግድ እና ለድርጅት አገልግሎት እንዲሰጡ ታስቦ እየተገነቡ ይገኛሉ ፡፡
በዕቅዱ መሰረት እንደሚያልቁ ይጠበቃል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በግንባታው ላይ በጣም ክትትል እንደሚደረግ እና ምንም እንኳ ባለፈው አመት መጋቢት እና ሚያዚያ ላይ ቢጀመሩም አንዳንዶቹ አምስተኛ ፎቅ ላይ መድረሳቸውን ይገልፃሉ፡፡ሚያዚያ እና ግንቦት ላይ ከፍተኛ ዝናብ እየጠላም ግንባታው እየተካሄደ ነበር።የመጀመሪያ ግንባታ በመሆኑ እና ህዝባዊ አመኔታን ለመፍጠር እንዲሁም የተቋሙን ገጽታ መሻሻሉን ለማሳወቅ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሁሉ ግንባታ ሲካሄድ እንደነበርም ነው የገለፁት፡፡
በእዚህ አመት በአንድ በኩል ኮሮና በሌላ በኩል የፀጥታ ችግሮች እያጋጠመ ቢሆንም፤ ህንጻዎች እስከ አምስተኛ ወለል የደረሱበት ሁኔታ መኖሩን እና የፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ ያብራራሉ፡፡ ፕሮጀክቶቹ በአጭር ጊዜ መጨረስ እንደሚቻል በማሳየት በኩል ሚና እንደሚኖራቸውም ይገልፃሉ፡፡
እንደአቶ ክብሮም ገለጻ፤ ግንባታዎቹ የሚካሄዱት በኢትዮጵያውያን ነው።ያጋጠሙ ፈተናዎችን በመፍታት በተያዘው ጊዜ ለመጨረስ እየተሰራ ነው።የግብዓት ችግርም ሆነ ሌሎች ችግሮች ቢያጋጥሙ እንዴት በተያዘው ጊዜ ማጠናቀቅ ይቻላል የሚለው ታስቦበታል።ግንባታው በጥሩ ደረጃ ላይ ሊሆን የቻለው ለእዚህም ነው ።
‹‹እያሸነፍን ያለፍናቸው ብዙ ፈተናዎች ነበሩ፡፡›› ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በዚህ እርምጃ መሰረት በድል መወጣት እንደሚቻል እና የፕሮጀክት ስኬት ዋናው ሚስጢር የክትትል ስርአቱ መሆኑንም ያመለክታሉ፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በስነ ስርዓት በተደጋጋሚ ጉብኝት ይደረጋል።ጉብኝቱን ከሚያደርጉት መካከል አንዱ የተቋሙ ማኔጅመንት ካውንስል /የስራ አመራር ኮሚቴው/ ተጠቃሹ ነው።የተቋሙ ቦርድም ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል።የፓርላማው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ቋሚ ኮሚቴም ክትትል ያደርጋል።እነዚህ ሁሉ ተባብረው ይሰራሉ።ሰራተኛውም፣ ተቋራጮቹም፣ መሐንዲሶቹም እንዲሁ ሁሉም በጋራ ይሰራሉ።በመረዳዳት መንፈስ ስለተሰራ ስኬታማ መሆን ተችሏል፡፡
በግንባታ ላይ የሚገኙትን የመኖሪያ ቤቶች ለተከራይ የምታስተላልፉበት መንገድ እንዴት ሊሆን ይችላል በሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ዳይሬክተሩ ፣ ኮርፖሬሽኑ የተቋቋምንበት አላማ እንዳለ እና የመንግሥት ውሳኔም እንደሚያስፈልገው ይናገራሉ።በቅድሚያ የቤቶቹ ግንባታ ካለቀ፤ ከዚያም ኮርፖሬቱ እስከ አሁን ያካበታቸውን ልምዶች በመቀመር እንዲሁም የቤት አስተዳደር መመሪያውን በመጠቀም የሚፈጸም መሆኑን ገልጸዋል።
በቅድሚያ የሚነሱትን ጥያቄዎች በመመለስ በሂደት ወደ መንግስት ሰራተኛው ወደ ታች እንደሚወርድ ተናግረው፤ ጉዳዩ የገበያ ጉዳይ እየሆነ ሲመጣ ወደ አጠቃላይ ህዝቡ ይገባል ይላሉ።‹‹ይህን ጥያቄ የምንመልሰው አሁን በምንሰራቸው ህንጻዎች አይደለም፤ ሰፊ ግንባታ ውስጥ በመግባት ይሆናል።ይሄ እንደ መነሻ ይወሰዳል።ልምድ የምናካብትበት ነው፡፡ቀጥሎ ያለው ትልቅ ስራ ይሆናል›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ኮርፖሬሽኑ በቀጣይም ግንባታዎችን እንደሚያካሂድ ይጠበቃል።ግንባታውን አሁን በራሱ ይዞታዎች ላይ እያካሄደ ሲሆን፤ በቀጣይ ግን ሁለት አይነት ስልቶችን እንደሚጠቀም ነው ዳይሬክተሩ ያመለከቱት።አዳዲስ መሬቶችን ከከተማ አስተዳደሩ በጋራ እየተነጋገረ የሚገነባቸው ቤቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ወደ ግንባታው በስፋት የሚገባ ከሆነ፣ የታሰቡት ስራዎች ስኬቶችን ካስገኙ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት፣ ከባንክ ብድር በመውሰድ፣ የመንግሥትን የግንባታ ፍላጎት በማካተት የሚሰራ ከሆነ መሬት ከከተማ አስተዳደሩና ከፌዴራል መንግስት ማግኘት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡
‹‹ሌላኛው መንገድ የራሳችን ይዞታ ነው፡፡በዚህ መሬት ውድ ሀብት በሆነበት ዘመን መሬትን በአግባቡ መጠቀም ይገባል።በሰፊ መሬት ላይ ባለ ትንሽ ቤት አንድ ሰው የሚኖርበት ሁኔታ አለ።ለእዚህ ለነዋሪ ምትክ ቤት በማቅረብ በዚያ ቦታ ላይ አዲስ ግንባታ ማካሄድ ውስጥ መግባትም ይኖራል።እዚህም እዚያም ያለውን የተበጣጠሰ የኮርፖሬቱን መሬት ህጋዊ ማእቀፎችን በመፈጸም ለከተማ አስተዳደሩ አስረክበን በምትኩ ሰፊ እና በቂ መሬት እንዲሰጡን ለማድረግም እንሰራለን፡፡››ሲሉም ያመለክታሉ፡፡
በአገሪቱ ከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ የመኖሪያ ቤት ጉዳይ ወሳኝ አጀንዳ መሆኑ ይታወቃል።መንግስት ከ1997 ዓ.ም አንስቶ የከተማዋን ቤት ፈላጊዎች ጥያቄ ለመመለስ በኮንደሚኒየም ቤቶች ግንባታ ላይ የተጠመደ ቢሆንም፤ እስከ አሁንም ጥያቄውን መመለስ አልቻለም።እርግጥ ነው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን ገንብቶ ለተጠቃሚዎች በእጣ አስተላልፏል።ይሁንና ፍላጎቱ እና አቅርቦቱ ሊጣጣም ባለመቻሉ የዛሬ አስር አመት ቤት ለማግኘት ከተመዘገቡት መካከል ዛሬም ቤት ያላገኙ በርካታ ናቸው።በዚህ ላይ በቅርቡ ቤት ለማግኘት የተመዘገቡት እስከ አሁንም ጥያቄያቸው ምላሽ አላገኘም፡፡
መንግስት የቤት ጉዳይን አሁንም ዋና አጀንዳው ካደረጋቸው ተግባሮች መካከል ይገኝበታል።የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በሚቀጥሉት አስር አመታት 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ቤቶችን ለመገንባት ማቀዱም ይህንኑ ያመለክታል።ቤቶቹን ለመገንባት ደግሞ መንግስት 20 በመቶውን ድርሻ የሚይዝ ሲሆን፣ የተቀረውን ደግሞ የግሉ ዘርፍ ፣ነዋሪዎች፣ሪል ስቴት አልሚዎች፣በመንግስትና በግሉ አጋርነት ለመገንባት አቅዷል።
በዚህ የቤት ልማት ለኪራይ አገልግሎት የሚውሉ ቤቶች እንደሚገነቡም ይጠበቃል።በደርግ ዘመን በአዋጅ የተወረሱ ቤቶችን ሲያስተዳደር የቆየውና ከሃያ አመት በፊት ራሱም ቤቶችን እየገነባ የሚያከራየው ቀድሞ በተለያዩ ስያሜዎች የሚታወቀው የዛሬው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እንደ አንድ የመንግስት የልማት ድርጅት ቤቶችን እየገነባ ለማከራየት እየሰራ ይገኛል።ይህ የኮርፖሬሽኑ ተግባር በቀጣይ የመንግስትን አንድ ሸክም የሚያቃልል ይሆናል ተብሎ ይወሰዳል፡፡መንግሥት የቤቶች አቅርቦትን የኪራይ ቤቶችን በመገንባት ጭምር ለማሳካት አቅዶ እየሰራ ባለበት በዚህ ወቅት ኮርፖሬሽኑ የሚከራዩ ቤቶችን ወደ መገንባት በመመለስ እያሳየ ያለው የቤቶች ልማት አፈጻጸም ወቅታዊና አስፈላጊ ተብሎ ሊወሰድ ይገባዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2012
ኃይሉ ሣህለድንግል