የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አሁንም ዓለምን በማስጨነቅ ላይ ነው። የህክምና ጠበብቶችን፣ ተመራማሪና ሳይንቲስቶችን ማነጋገሩን ቀጥሏል። አዳዲስ በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እያሻቀበ ይገኛል። የቫይረሱን ስርጭት መቆጣጠራቸውንና የሟቾችም ሆነ የህሙማን ቁጥር እየቀነሰ መሆኑን ሲገልጹ የነበሩ አንዳንድ የዓለም ሀገራት ጭምር በአሁኑ ወቅት የቫይረሱን ማገርሸት እያስታወቁና የከፈቷቸውንም ማህበራዊ አገልግሎቶች እየዘጉ ይገኛሉ።
በዓለም ላይ በኮሮና የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከ17 ሚሊዮን 265 ሺ 800 በላይ ሆኗል። ለህልፈት የተዳረጉት ደግሞ ከ673 ሺ 200 በላይ ደርሷል። በዚህ ሰዓት የወረርሽኙ ስርጭት እየተስፋፋ ያለው በአፍሪካ ውስጥ መሆኑ ደግሞ ስርጭቱን አሳሳቢ፣ ጉዳቱንም የከፋ ያደርገዋል የሚል ስጋት ፈጥሯል። የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ መሆን፣ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት እና የህክምና አገልግሎቱ አቅምና ብቃት ከህዝብ ቁጥር ብዛት ጋር ተዳምሮ ለአፍሪካውያን አሁንም ትልቅ ስጋት ሆኗል።
በኢትዮጵያም ያለው እውነታ ከዚህ የተለየ አይደለም። በአሁኑ ወቅት ቫይረሱ እጅግ ፈጣን በሆነ መልኩ እየተሰራጨ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር በየዕለቱ የሚያወጣው ሪፖርት ያመለክታል። ቀደም ባሉት በሁለት እና ሦስት ወራት ያልተመዘገቡ በቫረሱ የተያዙ አዳዲስ ሰዎችና ሟቾችን ቁጥሮች አሁን በየቀኑ ማደመጥ ጀመሯል። ይሄ የቁጥር ጨዋታ አይደለም። የሰው ህይወት ነው። ከትናንት በስቲያ ብቻ በአንድ ቀን 915 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተገልጿል። እስከአሁን የጤና ሚኒስቴር ባስታወቀው መሰረት 17 ሺ 530 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፤ የ274 ሰዎች ህይወት አልፏል። ከእዚህ ውስጥ ያገገሙት 6 ሺ 950 ናቸው። ይሄ የሚያሳየው አሁንም መዘናጋቱን ወደጎን በማድረግ በመከላከሉ ሥራ ላይ ማተኮር ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም ላይ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ አስቀድሞ የጥንቃቄ ዝግጅቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። ህዝቡም በቂ ግንዛቤ እንዲኖረውና ጥንቃቄም እንዲያደርግ አስፈላጊው የግንዛቤ ማሳደጊያ ትምህርትና ቅስቀሳም ሲሰጥ ከርሟል። ቫይረሱ ወደ ሀገር ቤት መግባቱን ተከትሎ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ወሳኝ ናቸው የተባሉ ዕርምጃዎችም ተወስዷል። ይሄ ሁሉ ሂደት የቫይረሱ ስርጭት ከሚጠበቀው በላይ እንዳይሆንና ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጣ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ሆኖም ግን አሁን እየታየ ባለው ሁኔታ አብዛኛው ሰው ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር እና ማስጠንቀቂያ እየተገበረ አይደለም። አሁንም መዘነጋቱ በስፋት አለ።
በእምነት ተቋማት፣ በገበያ ስፍራዎች፣ በትራንስፖርት መጠበቂያ፣ በጤና ተቋማት ግቢ እንዲሁም ሌሎች የማህበራዊ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቦታዎች ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው። የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በተገቢ ሁኔታ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ጥቂት ሰው ነው። ማህበራዊ ፈቀቅታ ደግሞ ጭራሽ የለም ማለት ይቻላል። እንዲሁም በየክልል ከተሞች ያለው አጠቃላይ ወረርሽኑን የመከላከል እንቅስቃሴ ደካማ ነው። በህብረተሰቡ ውስጥ ያለው የተሳሳተ አመለካከት አሁንም አልተቀረፈም። በኮቪድ 19 የወገኖቻችንን ህይወት ከአጠገባችን እያጣን፣ በየቀኑ በርካታ ቁጥር ያለው የቫይረሱ ተጠቂ መሆኑ እየተሰማም መዘናጋቱ አሁንም ተባብሶል።
አሁን የኮሮና መስፋፋት ለሀገራችን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ትልቅ ስጋት ሆኗል። ይህንን ስጋት ማቆም የሚቻለውም ከመንግሥት እና ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ ትዕዛዛትን በትክክል መተግበር ሲቻል ብቻ ነው። ይሄ ካልሆነ ግን ሀገርና ህዝብን የሚያስከፍለው ዋጋ የከፋ ይሆናል።
ሀገሪቱ ባላት የጤና ተቋማት እና ባላት አቅም መሰረት እስከአሁን ህሙማን አስፈላጊውን ህክምናና ድጋፍ እያገኙ ነው። አብዛኛዎቹ ለዚሁ ህክምና ተብለው የተዘጋጁ የጤና ተቋማት በመሙላት ላይ ናቸው። በቫይረሱ የሚያዘው ሰው ቁጥር አሁን በሚታያው ሁኔታ እየጨመረ የሚሄድ ከሆነ ከሀገሪቱ አቅም በላይ ሊሆን እንደሚችል መገመት የሚከብድ አይደለም።
ታሞ ታክሞ መዳን እንዳለ ሁሉ ህክምና አጥቶ ተሰቃይቶ መሞት ሊያጋጥም እንደሚችል ማሰብ ይገባል። መዘናጋቱ አሁንም የበለጠ ዋጋ እንዳያስከፍለን የመከላከያ መንገዶችን በተገቢው መንገድ መጠቀም ያስፈልጋል። ‹‹ኮሮና የለም፣ ሀበሻን አይዝም፣ ታሞ መዳን ይቻላል›› ከሚሉ ማዘናጊያ ወሬዎች ወጥተን እያንዳንዳችን ራሳችንን ልንጠብቅ ይገባል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2012