ከአሥር ቀናት በፊት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ በተካሄደ የጥበብ ባለሙያዎች ምክክር መድረክ ላይ አንጋፋና ወጣት ሰዓሊያን፣ ጸሐፊ ተውኔት፣ ተዋኒያን፣ የስነ ፅሁፍና ኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ስሜት ቆንጣጭና ቁጭት ቀስቃሽ ሃሳቦችን መለዋወጣቸውንና የድርሻቸውን ጠጠር ለመጣል ቃልኪዳን መግባታቸውን የዝግጅት ክፍላችን በዚሁ የዘመን ጥበብ አምድ ላይ መዘገቡ የሚታወስ ነው።
ከዚህ የምክክር መድረክ ላይ ደግሞ የብዙሃንን ቀልብ በሳበ መንገድ ሃሳባቸውን አንስተው የነበሩትና ጠቃሚ ምክረ ሃሳብ የሰጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር፣ ገጣሚ፣ ተርጓሚና ጸሐፊ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ነበሩ። ታዲያ እኛም በመድረኩ ካነሱት ሃሳብ በተጨማሪ ዘርዘር ያሉ ጭውውቶችን ለማድረግ የዘመን ጥበብ አምድ እንግዳችን አድርገናቸዋል። መልካም ቆይታ!
አዲስ ዘመን፦ በመጀመሪያ ለቃለ መጠይቁ ፍቃደኛ ሆነው ጊዜዎትን ስለሰጡን በዝግጅት ክፍላችን ስም እናመሰግናለን።
ጸሐፊ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ፦ እኔም እንግዳችሁ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን፦ ጋሽ አያልነህ ከስነ ፅሁፍ ጋር አብረው አደጉ እንጂ ስነ ፅሁፍን ዘግይተው አልተቀላቀሉም ይባላል። እስቲ ስለዚህ ጉዳይ በትውስታ መለስ ብለው ያጫውቱን?
ጸሐፊ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ፦ መልካም። የተወለድኩትም ያደኩትም በገጠሪቷ የኢትዮጵያ ክፍል ነው። ቤተሰቦቼ ገበሬዎች የነበሩ ቢሆኑም በጣሊያን ጦርነት ወቅት ዘምተው በሰሩት ጀብድ ‹‹የፊት አውራሪ›› ማእረግ ያገኙ ነበሩ። በዚህ ምክንያት የአንድ አካባቢ ገዥ መሆን ቻሉ።በዚህ ምክንያት እኔም ፊደል በመቁጠሬ የገበሬውን አቤቱታና እሮሮ በማመልከቻ መልክ እፅፍ ነበር። እንዲህ እንዲህ እያልኩ ከስነ ፅሁፍ ጋር ተገናኝቻለሁ። በዚህ ምክንያት የትምህርት ደረጃዬም እየተሻሻለ ከፍተኛ ትምህርት ላይ እስክደርስ ድረስ የስነ ፅሁፍ ስሜት እያደረብኝና አብሮ እያደገ ሊመጣ ችሏል። በአጠቃላይ ለአባቴ በየጊዜው መጽሐፍት ማንበቤ ወደ እዚህ የጥበብ ዘርፍ እንደመራኝም አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፦ ተማሪ በነበሩበት ወቅት ስነ ፅሁፍን በተመለከተ ምን ያስታውሳሉ?
ጸሐፊ ተውኔት አያልነህ፦ የገበሬውን አቤቱታና እሮሮ እየሰማሁ ማደጌ ለዚያ ቆሜ እንድታገል ስሜቴን አነሳስቶታል። በዚህ ምክንያት ይህን የሚገልፁ ግጥሞች የተቃውሞ መልክቶችን እፅፍ ነበር። ሆኖም ግን ጭፍን እይታና ተቃውሞ የነበረባቸው ናቸው። በጊዜው በጣም ልጅ ነበርኩ። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ስቀጥልም ሆነ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስገባ ስነ ፅሁፍን በመጠቀም የተማሪዎች እንቅስቃሴን በማቀጣጠል ላይ እሳተፍ ነበር። ይሄን ሁሉ የኔ የህይወቴ አካል ነው። በግጥም ውድድር ላይ አሸናፊ ሆኜ ዋንጫ ተሸልሜ አውቃለሁ።
አዲስ ዘመን፦ ስነ ፅሁፍን ለማጥናት ከፍተኛ የትምህርት እድል አግኝተው ወደ ውጭ አገር ሄደው ነበር። ይሄን እድል እንዴት ነበር ያገኙት?
ጸሐፊ ተውኔት አያልነህ፦ ነጻ የትምህርት ዕድል ደረሶኝ ወደ አሜሪካን አገር ለመሄድ እየተዘጋጀሁ ነበር። በዚያን ወቅት የደራሲያን ማህበር ዋና ጸሐፊ የነበሩት ታላቁ ባልቅኔ መንግስቱ ለማ ግን ውሳኔዬን ተቃወሙት። ስነ ፅሁፍ ለመማር ራሺያ መሄድ ተመራጭ መሆኑን ነግረውኝ ሃሳቤን አስቀይረው ወደዚያው ላኩኝ። የድራማ ስነ ፅሁፍ ልማር ብሄድም እሱ ቀርቶ ስነ ፅሁፍና ጋዜጠኝነት ተማርኩ። በዚያ ብዙ በመቆየቴም የራዲዮ ጣቢያ ተሰጥቶኝ የደራሲው ደብተር የሚል ዝግጅት ቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ማሰራጨት ጀመርኩ። በዝግጅቱ ፀረ ፊውዳል ጉዳዮች ይስተናገዱ ስለነበረም በንጉሳዊው ሥርዓት ተወዳጅ አልነበረም። ጊዜው ከ1963 እስከ 1967 ዓ.ም ነበር። የውጭ አገር የትምህርት ቆይታዬ ይህን ይመስላል።
አዲስ ዘመን፦ በርካታ የስነ ፅሁፍና የኪነ ጥበብ ሥራዎች ላይ አሻራ እንዳሳረፉ ይታወቃል። በዚህ አርበ ጠባብ ጋዜጣ ሁሉንም ሥራዎች መጥቀስ ባንችልም ዘመን ተሻጋሪው ‹‹የህዝብ ለህዝብ›› ዋና አስተባባሪና የሃሳቡ አፍላቂ ከመሆኖት አንፃር እስቲ ስለርሱ ትንሽ ያንሱልን?
ጸሐፊ ተውኔት አያልነህ፦ በኢሰፓ ውስጥ የባህል ሚኒስትር የበላይ ሆኜ እመራ ነበር። የህዝብ ለህዝብን ሃሳብ ያቀረብኩትም ኮሚቴ ያቋቋምኩት እኔ ነበርኩ። ጓድ መንግስቱ ኃይለማርያም ድረስ የሚታወቅና ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ነበር። ህዝብ ለህዝብ እንዲዘጋጅ ሃሳብ ሳቀርብ ዋና አላማዬ የኢትዮጵያን ገፅታ መቀየር ስላለበትና ኪነ ጥበብ ደግሞ ያን የማድረግ ኃይል ስላለው ነው። ይህን እንዲመጥን ተወዛዋዡም፣ ሙዚቀኛውም ሆነ ሁሉም የዝግጅቱ አካል በጥንቃቄና በውድድር ተመርጦ ነበር።
አንጋፋው ሰዓሊ ታደሰ መስፍን የባህል አልባሳትን ሲያዘጋጅ፤ ጋሽ ሙላቱ አስታጥቄና ሌሎች ኪሮግራፈሮችም ቀድሞ የነበሩ ሙዚቃዎችን በድጋሚ ለዝግጅቱ እንዲሆን በድጋሚ የማዘጋጀት ሥራው ላይ ተሳትፈዋል። በዚህ አግባብ ስኬታማ ሥራ ተሰራ። የተለያየ አገር ላይ በአጋጣሚ የተቀረፀው ምስል ተቀናብሮ ለታሪክ በቃ።
ሆኖም ሁለም ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም። ሥራው ተጠናቆ ወደ አገር ስገባ ደርግ በኤርትራ ውስጥ የሚያደርገውን ጦርነት ይቃወማል። ኤርትራም እንድትገነጠል የተቀረፀው የሙዚቃዊ ድራማ ቲያትር ይደግፋል በሚል ለእስር ተዳርጌ ነበር። ይህም ቢሆን ግን ስኬታማና ለታሪክ የሚበቃ ሥራ በቡድኑ መስራት ተችሏል።
አዲስ ዘመን፦ ከላይ ያነሳናቸውን ታላላቅ አበርክቶዎች ቢኖሮትም አሁንም ድረስ ከጥበቡ ዓለም የመራቅ ፍላጎት አይታይም። ከመምህርነት ባሻገር በህዳሴው ግድብ ዙሪያና ህዝብ ለህዝብን የሚስተካከል ፕሮጀክት ለሚመለከተው አካል አስገብተው ምላሽ ማጣቶትን በአንድ የውይይት ወቅት አንስተው ነበር። እስቲ ስለዚህ ጉዳይ ይንገሩን?
ጸሐፊ ተውኔት አያልነህ፦ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ እና የደረሰበትን ምእራፍ በማስመልከት ከአስር ቀናት በፊት መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር። በዚህ ላይ የተሰማኝን ሃሳብ ሰንዝሬያለሁ። ከሁለት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበርን በመወከል በግብፅ አገር ቆይታ አድርጌ ነበር። በጊዜው ከግብፅ ደራሲያን ማህበር ጋር ተገናኝቼ በተወሰኑ ነጥቦች ላይ ውይይት አድርገን ነበር።
በቆይታዬ የግብፅ ቤተ መፅሐፍትን የመጎብኘት እድል አጋጥሞኛል። በወቅቱ የቤተ መጽሐፍቱ አስጎብኚ ‹‹መጥፎ አጋጣሚ ሆኖ የግብፅ የመጀመሪያዎቹ ቀኝ ገዥዎች ኢትዮጵያውያን ነበሩ›› በሚል የተናገረችው ንግግር መቼም አረሳውም። ግብፃዊያን በተንኮል ድርጊት የተካኑ መሆናቸውን ለመገንዘብም በአገራቸው የአስዋንን ግድብ የገነቡት በቀድሞው የሜሮይ ስልጣኔ በነበረበት ስፍራ መሆኑን ማንሳት በቂ ነው። በጊዜው የኢትዮጵያውያን ስልጣኔ ማሳያ የነበረውን ይህን ስፍራ በማጥፋት ውሃ ሞልተውበታል። አሁንም ድረስ በውሃው ውስጥ ትልቅ ኢትዮጵያዊ ቅርፅ መኖሩን ከታሪክ ድርሳናት መረዳት ይቻላል። የፈርኦን መልክም የኢትዮጵያውያን እንጂ ከሌላ ስፍራ ፈልሰው የመጡ የአረቦች አለመሆኑን ታሪክም መዝግቦታል። አይደለም የአባይ ወንዝ ግብፅም የኢትዮጵያውያን የስልጣኔ ማሳያ ስፍራ ነች። ይሄን የተዛባ ታሪክ በታላላቅ የኪነ ጥበብና ስነ ፅሁፍ ሥራዎች ማጋለጥና ማስተዋወቅ አለመቻላችን ይቆጨኛል።
በሁለተኛ ደረጃ በቁጭት የማነሳው የሁለት መቶ ዓመታት ታሪክ የተሰራበት ሚሊኒየም ክብረ በዓልን አንድም የረባ የኪነ ጥበብ ሥራ ሳይሰራ ማለፉ፤ ንጉሰ ነገስቱ ትልቅ አሻራ ያሳረፉበት የአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት ክብረ በዓልም እንዲሁ የኢትዮጵያውያን የኪነ ጥበበብ አሻራ ሳይነካው ማለፉን የሚያንገበግብ ነው።
ግብፆች የአስዋን ግድብን ሲገነቡ ‹‹አይዳ›› የሚል ኦፔራ ለዓለም ህዝብ አስተዋውቀዋል። ይህ የጥበብ ሥራ ዓለምን ያንቀጠቀጠና እስካሁንም ድረስ በቢሊዮን የሚቆጠር ገቢ የሚገኝበት ነው። ይህች የኢትዮጵያውያን ንግስት እንደግብፃዊ ተቆጥራ ግድባቸውን ሲገነቡ የጥበብ ማነቃቂያ አድርገው ኦፔራ ከሰሩ እኛ ኢትዮጵያውያን ምንድን ይጠበቅብናል?
ይህን ጥያቄ ለመመለስ ከባልደረቦቼ ጋር ጥረት አድርጌ ነበር። ከሙላቱ አስታጥቄ ጋር በጋራ ሆነን የህዝብ ለህዝብን መሰል ሥራ ለመስራት ከአራት ዓመት በፊት ለመንግሥት ጥያቄ አስገብተን ነበር። እስካሁን መልስ አላገኘንም። በኪነ ጥበብ መስክ እስካሁን የአይዳን ኦፔራ በሚመስል ግዝፈት ምንም አለመሰራቱ ያሳስበኛል። ይህን መሰል ሥራ ደግሞ የመንግሥት ድጋፍንና ቁርጠኝነትን ይፈልጋል። ህዝብ ለህዝብ ስሰራ ያን ግዜ እኔ ኃላፊነት ነበረኝ። ውሳኔ የማስወሰን ስልጣንም እንዲሁ። በዚያ ምክንያት ሥራው ስኬታማ ልሆን ችሏል። ይሄን መሰል ቁርጠኝነት በኪነ ጥበብ ባለሙያውም ሆነ በመንግሥት በኩል መኖር አለበት። በቀጣይ ሁሉም የጥበብ ባለሙያ በየዘርፉ ነቅቶ ታላቅ ሥራ ማበርከት አለበት። በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከዚህ ቀደም ባልተሞከረ መልኩ ኪነጥበቡን ሊወክል የሚችል ግዙፍ ሥራ መስራት ይገባል።
አዲስ ዘመን፦ ለየትኛው አካል ነበር ፕሮጀክቱን ነድፋችሁ ያስገባችሁት? ውሳኔ ተሰጥቶበት ወደ ትግበራ ያልተገባበትን ምክንያት ለማወቅ ጥረት አድርጋችሁ ያገኛችሁት ምላሽ ነበር?
ጸሐፊ ተውኔት አያልነህ፦ ታላቅ የኪነ ጥበብ አሻራ ለማሳረፍ ፕሮጀክቱን ያስገባነው የህዳሴው ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ነበር። ደብዳቤ ፅፈን ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አስገብተን ምላሽ ብንጠብቅም ምላሽ ሳናገኝ ቀረን። የህዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ብሄራዊ ቲያትር ፕሮጀክቱን በየደረጃው እንዲያስፈፅሙ ጥረት ቢደረግም ያልረባ ምክንያት እየሰጡ ጉዳዩን እንደ ተራ ነገር አይተውት ነው ያስቀሩት። እኛ የህዝብ ለህዝብን ሥራ ስንሰራ የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ ከሰባት ጊዜ በላይ እየመጡ ትኩረት ሰጥተው በማየት አስተያየት ይሰጡበት ነበር።
አሁን አሁን ለኪነ ጥበባዊና ባህላዊ ጉዳዮች ትኩረት የሚሰጥ እየጠፋ ነው። ከጥበባዊ ሥራዎች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ሃይ የሚልና የሚያርቅ እየጠፋ ነው። አሁን አሁን የሚሰሩ የገፅታ ግንባታና የግንዛቤ ማስጨበጫ የኪነ ጥበብ ሥራዎች አሰልቺና ቀጥተኛ መልእክት ያላቸው ናቸው። ጥረቱ የሚመሰገን ቢሆንም የፈጠራ ንጥፈትና የጥራት ችግር ይታይባቸዋል። እኛ ቀርፀን ያስገባነው ፕሮጀክትንም በዚህ መልኩ አይተውት ትኩረት የነፈጉት ይመስለኛ። እውነታው ግን ይሄ አልነበረም።
አዲስ ዘመን፦ በመጨረሻም አሁን ያነሷቸው ህፀፆች እንዲሻሻሉም ሆነ ከዚህ ቀደም እንደነበረውና ከዚያም በተሻለ መንገድ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ የኪነ ጥበብ አሻራዎችን ለመስራት ምን መደረግ ይኖርበታል ብለው ያስባሉ?
ጸሐፊ ተውኔት አያልነህ፦ መንግስት በኪነ ጥበብ ማመን መቻል አለበት። አገርን የሚመራው ፖለቲካ አይደለም። አገርን የሚመራው ኢኮኖሚ ብቻ አይደለም። አገርን የሚመራው ባህል ነው። ባህሉ ያልዳበረ አገር በምንም ታእምር መሪ መፍጠር አይችልም። አገር የሚመራ ትውልድ አያፈልቅም። የኛ ባህል በነጭ ስለተወረረና ስርዓተ ትምህርታችን መሰረቱን ያጣ በመሆኑ ችግር ውስጥ ወድቀናል። በብሄር ብሄረሰቦች ቱባ ባህልና በአገር በቀል ሥርዓት ባልተገነባ ትምህርት ስርዓት ትውልዱን እየቀረፅነው ስለሆነ እየፈረስን ነው። ኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ፣ ስነ ፅሁፍ፣ አብሮ የመኖር፣ የእርቀ ሰላም፣ የኪነ ህንፃ እንዲሁም የበርካታ ባህል ባለቤቶች ነች። ይሄን ትተን ኢኮኖሚና ፖለቲካ ነው የሚመራን ስንል እዚህ አዘቅት ውስጥ ወድቀናል። ስለዚህ ባህል በተለይ ደግሞ ኪነ ጥበብ አገር እንደሚመራ ሊታወቅና በዚህ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል። ኪነጥበብ የማይመራው ኢኮኖሚም ሆነ ፖለቲካ ደረቅ ነው። እጥፍ እያለ የሚሰበር እንጨት ዓይነት ነው። ለዚህ ነው እየተሰበሩ ለትውልድ ቅርስ ሳይተው የሚሄዱት።
በአዲስ አበባ የቆሙ ህንፃዎች ውስጥ እኛነታችንን፤ የኪነ ህንፃም ሆነ ጥበባዊ አሻራችንን አናይም። የአክሱም፣ የላሊበላም ሆነ የሌሎች የስነ ህንፃ አሻራዎችን ማግኘት አይቻልም። ይሄ የሆነውአንድ ቦታ ጥለነው የሌሎችን አሻራ ለመከተል ስለሞከርን ነው። በኪነ ጥበቡም ይህ እየሆነ ነው። ስለዚህ መንግሥት መሰረታዊ ወደሆነው የኢትዮጵያ አገር በቀል እውቀት ትኩረት ሊያደርግ ይገባል እላለሁ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2012
ዳግም ከበደ