ከመስኮት ድራማዎች

ዓለምና ሕይወት ሁሌም ቢሆን መስኮቶች ናቸው። ቀረብ ሲሉ ከትንሹ ውስጥ አስግገው የሚመለከቱት አድማስ ከሚመስለው በላይ ነው። ዓለምንም ይሁን ሕይወትን የምንቃኝበት አንደኛው መስኮትም ኪነ ጥበብ ነው። ሁለተኛውም በቴክኖሎጂ የታነጸ መስኮት ከነመዘወሪያ ሪሞቱ ሕዝብ ፊት ገጭ ይላል።

ዓለምንም ጥበብንም ከዚሁ ይኮመኩማል። ታዲያ በዚህ መስኮት ፖለቲካውና ያዩት የሰሙት ሁሉ ድራማ እየሆነ ሲያስቸግረን “ይህስ ድራማ ነው” እንላለን፤ ቅጥፈት የተሞላበት ማስመሰል እንደሆነ ለመናገር። “ድራማ” የሚለውን ትርጓሜ በተቀበልንበት እሳቤ ወስደን ለኪነ ጥበብ እንግጠመው ብንል ግን፣ ምኑም ከምኑ አይዝልን፣ መስኮቱም አይገጥም። ከፊል እውነት ቢኖረውም አባባሉ ሙሉ ለሙሉ የድራማን ባሕሪና ምንነት የሚገልጽ አይደለም።

ምክንያቱም፤ ውሸት የሆነውን ነገር ለመግለጽ በምንጠቀምበት እሳቤ ውስጥ ድራማ ውሸት ብቻ ነው። ነገር ግን፤ ድራማ ውሸት የምንለው ከትወናው ምናልባት ደግሞ ከተዋናኞቹ አንጻር ብቻ ነው። በድራማው ውስጥ የሚናገሩት፣ የሚሆኑትና የመሰሉት ነገር የእነርሱ ማንነትና ታሪክ ባይሆንም፣ በሌላ በኩል ለብዙዎች የራሳቸው እውነተኛ ታሪክና ማንነት ነው። ስለዚህ ድራማን ሙሉ ለሙሉ ውሸት ብቻ አድርገን ልንቆጥረው አንችልም። ከእነዚህም መካከል በእውነተኛ ታሪኮች ላይ ተመስርተው የሚሠሩ ይበልጥ አባባሉን ውድቅ ያደርጉታል።

ወደ መስኮቱ ከማንጋጠጣችን በፊት ግን፣ ድራማ በሦስት ልንከፍለው እንደምንችል እንመልከት። በመጀመሪያው ሲሦ ውስጥ ድራማን መድረክ ላይ እንመለከተዋለን። የመድረክ ድራማ ብለን የምንጠራው ነው። የመድረክ ድራማ ከሦስቱም ቀዳሚ ከመሆኑም፣ ድራማ የመጣበትና የታወቀበትም ጭምር ነው። ልክ እንደ ቲያትር ሁሉ የሚታየው በመድረክ ላይ ነው። አሁን አሁን ይህን ዓይነቱን አቀራረብ የምንለከትባቸው አጋጣሚዎች እጅግ አናሳ ናቸው። ቀደም ባሉት ጊዜያቶች ግን ከየትኛውም በላይ ተመራጭ የነበረበት ብቻ ሳይሆን፣ ብቸኛውም አማራጭ የነበረበት ዘመናቶች አሉ። ይህን ተመራጭነትና ግርማ ሞገስ የተወሰደበትም በቴክኖሎጂዎች ብቅ ማለት ነው። ቀጣዮቹ ሁለት የድራማ ክፋዮችም ወደ ቴክኖሎጂው ይወስዱናል። ዓለማችን አሁን ላይ ከደረሰችበት የቴክኖሎጂ ምጥቀት አንጻር ቀለል ያሉ መስለው ቢታዩንም፤ ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ግን እስካሁንም ያልተሻሩ ቴክኖሎጂዎች ናቸው።

በእነዚህ ሁለት ቴክኖሎጂዎች ውስጥም ድራማ ሁለት ዓይነት ሆኖ እናገኘዋለን። ሬዲዮ በዓለማችንም ሆነ በሀገራችን ከቴሌቪዥን ቀድሞ የመጣ ነው። የመድረክ ብቻ የነበረው ድራማም ሁለተኛውን መልኩን በሬዲዮ ገልጧል። ለውጡ ሁለተኛው የድራማ ዓይነት መጨመሩ ብቻ ሳይሆን፤ የድራማ ጥበብ ከፍ ብሎ የታየበት፣ ዕድገታዊ ሽግግር የታየበት ነው። ቀደም ሲል አንድ ድራማ ከአንድ አዳራሽ የሰፋ አድማስ አልነበረውም። በተለያዩ መድረኮች ላይ ሊታይ የሚችል ቢሆንም፤ ምንም ያህል ምርጥና ተወዳጅ ቢሆንም፣ እይታው አዳራሹ ሊያስተናግደው በሚችለው የታዳሚ መጠን የተገደበ ነው። የሬዲዮ ድራማ የሰበረው አጥር አንድም ይህንን ገደብ ነው።

ጥሪ ሳይደርሰው፣ ትኬት ሳይቆርጥ፣ ጊዜና ቦታን ለማመቻቸት ሳይቸገር ድራማ ከቤቱ ድረስ ይመጣል። ድራማው ተከታታይም ቢሆን የአንድ ጊዜ፤ ከሌሎቹ አንጻር ለባለሙያውም ሆነ ለአቀራረብ ምቹና ቀለል ያለ ነው። የትወናውን ድባብ ወይም ሙድ ለማምጣት ካልሆነ በስተቀር የቁሳቁስ ግብአትን አይጠይቅም። ተዋናዩ በሱፍ ዘንጦ፣ የባለቁምጣውን ባላገር ገጸ ባህሪ ሊጫወተው ይችላል። ከፊቱ ባስቀመጣት የሃይላንድ ውሃ ጥንብዝ ብሎ መስከር መብቱ ነው፤ ውሃውንም ሳይጠጣና ቆሞ ሳይንገዳገድ ቢሠራው የሚያስነቅፈው ሙያዊ ጉድለት ሊሆን አይችልም። በአንዲት ጠባብ ስቱዲዮ ውስጥ ቁጭ ብሎ ዓባይ በረሀ ላይ ነኝ ቢል መሆንና ማስመሰል እስከቻለ ድረስ መብቱ ነው።

ሦስተኛውና በቴክኖሎጂ ውስጥ ለየት ብሎ የመጣው የቴሌቪዥን ድራማ ነው። ምስል፣ ድምጽ ብቻም አይበቁትም። ቁሳቁስን ይሻል። መቼቱ የእውነትም በጊዜና ቦታ መስሎ መታየት ይኖርበታል። ሁሉም የቴሌቪዥን ድራማዎች ትውን ጥበባት ቢሆኑም፣ እኚህንም በዋናነት በሁለት ልንከፍላቸው እንችላለን። የመጀመሪያውና ቀደም ሲል በስፋት የሚታወቀው የአጭር ጊዜ ቆይታ ያለውና በአንድ ጊዜ እይታ የሚጠናቀቅ ነው። አለፍ ካለም ከሁለትና ከሦስት ክፍሎች የዘለለ ላይሆን ይችላል። የሚያተኩረው በአንድ በተወሰነ ነገር ላይ ይሆናል። ጭብጦቹ ውስብስብነት የማይታይበትና ግልጽ በሆኑ ሀሳቦች ይጓዛል። አዝናኝ ወይም መልዕክት አዘል ማስተማሪያ ነው። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያሉ ድራማዎች ለአንድ ዓላማ ታስበው የሚሠሩም ናቸው።

ሁለተኛው የቴሌቪዥን ድራማ ዓይነት፣ አሁን ባለንበት ጊዜ በስፋት የምንመለከተው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ነው። ቃሉ እንደሚገልጸው ድራማዎቹ ተከታታይ ናቸው። ነገር ግን ተከታታይነታቸው ከምን አንጻር ነው…ተከታታይ ሲባል በጥቅሉ እንጂ እያንዳንዱ ነገር ላይከታተል ይችላል።

ለምሳሌ በድራማ ውስጥ የሚነሱ ታሪክና መቼቶች በአራትና በአምስት ክፍሎች አንዳንዴም በአንድ ክፍል ተቋጭቶ ድራማው ግን ይቀጥላል። መቼት በመቼት፣ ታሪክ በታሪክ ሊፈራረቅበት ይችላል። ከዋና ገጸ ባህሪያት ውጪ ያሉ ሌሎች ገጸ ባህሪያቶች፣ በክፍሎች ወይም ምዕራፍ ጠብቀው የሚጠፉና እስከወዲያኛው የማይታዩ ብዙ ይኖራሉ። እስከየት ድረስ መዝለቅ እንዳለባቸው የሚወስነው ደራሲው ነው። እንደ አንድ አጋጣሚ ብቅ አድርጎ በሴኮንዶች ቆይታ ብቻ የሚሰውራቸውም ይኖሩበታል። ብዙ ነገሮች ቀጣይነት የሌላቸውና እየተቋጩ የሚሄዱበት ነው።

በተከታታይ ድራማ ውስጥ ደራሲዎቹ ሦስትና ከዚያ በላይ ሊሆኑም ይችላሉ። የረዥም ጊዜ ቆይታ ያለው በመሆኑ አንዱን ገጸ ባህሪ ሁለት አሊያም ከዚያም በላይ ተዋንያን እየተተካኩ የሚጫወቱበት አጋጣሚም ይኖራል። ልዩነቶች የበዙበት፣ ውስብስብና የተንቦረቀቀ እንደመሆኑ ባለሙያዎች የሚጠበቡበት ብቻ ሳይሆን እጅግ የሚፈተኑበትም ነው። ብዙ የተበታተኑ ነገሮች ባሉበት በዚህ ዓይነት ድራማ ውስጥ ሁሉንም ልጦች ወደ አንድ የሚያመጡ መሠረታዊ ማሠሪያዎች አሉት።

ከጅምር እስከፍጻሜው ድረስ በደራሲና ዳይሬክተሩ እርምጃዎች ውስጥ ሊዘነጓቸው የማይገቡ እኚህ መሠረታዊ ነገሮችም፤ ታሪክና የታሪክ ፍሰት እንዲሁም ጭብጦች ናቸው። ተከታታይ ድራማዎች በአካሄዳቸው የመለጠጥ ባህሪ አላቸው። ለሦስት ምዕራፎች የታሰበው፣ አራትና አምስት ምዕራፎች ላይ ሊደርስ የሚችልበት አጋጣሚ አለ። አብዛኛውን ጊዜ ለእይታ ከመቅረቡ በፊት ሊጠናቀቅ የሚችለው የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው። ምክንያቱም የድራማው ባለቤቶች ለማሳያነትም ጭምር የሚያቀርቡት ከመሆኑም፤ ለሥራውም አስቀድሞ በቂ ጊዜ ሊኖራቸው ስለሚችል ነው።

ነገር ግን፤ አንድን ተከታታይ ድራማ እንደ ፊልም ሙሉ ለሙሉ ሥራውን አጠናቆ ለእይታ የሚቀርብበት ዕድል ከመቶ አንድ ፐርሰንት እንኳን አይሆንም። በተለይ እንደኛ ሀገር ደግሞ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው። ለዚህ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፤ የሚጠይቀው የገንዘብ አቅም ብቻውን ምክንያት ለመሆን ይችላል። እንደ ፊልም በአንድ ጀንበር የማይጠናቀቅ መሆኑ ትልቅ ጥቅምም አለው። ድራማው ዓመታትን የሚጓዝ እንደመሆኑ አሁናዊ ሁኔታና ክስተቶችን እያካተቱ ለመሥራት ያስችላሉ።

ለምሳሌ በበዓላት ወቅት በዓሉን የመሰሉ ክፍሎችን ለማከል ያስችላል። ከአሁናዊ እኛነታችን ጋር መሳ ለመሳ እየሄደ የማሕበረሰቡን ፍላጎትና ስሜት እያጠና ይበልጥ ሳቢና የቅርብ እንዲሆን ያግዘዋል። ለአንድ ተከታታይ ድራማ የመለጠጥ ምክንያት ከሚሆኑ ነገሮች መካከልም ይህን መሰሉ አንደኛው ነው። ለሌላው ደግሞ በደራሲው ምናብ የሚመላለሱ አዳዲስ ሀሳቦችና ፈጠራዎች ብዕሩን እንዲያረዝም ያደርገዋል። እንዲህ ዓይነቶቹ ነገሮች ብልሃትና ጥንቃቄ ይሻሉ። ምክንያቱም ከተነሱበት ታሪክና ጭብጥ ጋር በመሃል ተጠፋፍተው መመለሻና መቋጫው ሲጠፋም ተመለክተናል። ቅልብጭ ብሎ ባማረ መልኩ ለመጠናቀቅ የሚችለውን ተወዳጁን ድራማ ቋቅ እስኪል አሰልቺ የሆኑ ጥቂቶች አሉ።

ነገር ግን… “ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነ…” የሚያስብል ነገር ደግሞ አለበት። ረዝሞና ተንዛዝቶ መሄዱንም አጥተን እምጥ ይግቡ ስምጥ ሳናውቅ፣ ልባችንን እንዳንጠለጠለ የቀሩ፣ ሳንወድ የረሳናቸው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎችን ቤቱ ይቁጠረው። “ክፍል አንድ” ብለው በጀመሩት ተከታታይ ድራማ ውስጥ “ምዕራፍ 1 ተጠናቀቀ” ብሎ በቴሌቪዥን መስኮቱ ብቅ ማድረግ፣ ተመልካቹን ቢያበሽቅም ለባለሙያው ግን ትልቅ እርካታ ነው። ምክንያቱም ያን ለማየት ዕለት ዕለት የሚያልፉበት መንገድ ድራማውን እንደመመልከት አይደለም። ከዚህ የባሰው መብሸቅና እርካታ ያለው ግን ከዚህ በኋላ ነው።

“ምዕራፍ 2 ክፍል 1” ብሎ መጀመርን አብዛኛዎቹ የታደሉት አይመስልምና ከሄዱበት የምዕራፍ ዕረፍት መመለሱ አንድ ነገር ነው። የሚጀምሩትን እንጂ የሚቀጥሉትን መመልከት የተናፈቁባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም። ልብ አንጠልጥለው ልብ ሰቅለው፣ ማወረዱን በመዘንጋት በዚያው እንደሚጠፉት መሆንም አለ። ለዚህ ዋነኛው መንስኤም በባለሙያውና በቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ መካከል ሲሆን እንመለከታለን። በሁለቱ መካከል የሚደረጉ የውል ስምምነቶች እየፈረሱ፣ ተመልካችም ጥበብም መና ሲቀሩ መመልከት በተለይ እንደ እኛ ሀገር እንደ ፋሽንም የሚታይ ነው የሚመስለው። ጉዳዩ ቀላል የሚመስል ግን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የከፋ ነው። አሁን አሁን የተሻለ ቢሆንም፤ እንደ ሀገር በኪነ ጥበብ ኢንዱስትሪው ውስጥ አንድ የራሱ የሆነ የሚመራበት ሕገ ደንብ የሚያስፈልገው ነው።

የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መበርከት ድራማ ከትልቅ ፈተና ጋር እንዲላተም አድርጎታል…የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የድራማን ጥበባዊ ጉልበት በመጠቀም ጣቢያቸውን አሸናፊ ማድረግ የሚችሉበት ነው። ተመልካች ሁሌም “ጣቢያው ምን አለው?” ይላል። እንደ ድሮ የተሰጠውን ብቻ የሚመለከትበት ጊዜ አይደለም። መቆጣጠሪያ ሪሞቱ በእጁ ነው፤ ደስ ካላሰኘነው ወደ ሚፈልገው ለመሄድ ብዙ ምርጫዎች አሉት። እንደ ድሮ “አንድ ለእናቱ” በሆነው መስኮት ሊያንጋጥጥ አይችልም። አሁን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የፈሉበት ጊዜ እንደመሆኑ ውድድሮቹም የሚካሄድበት ነው። አንድን የቴሌቪዥን ጣቢያ አሸናፊ ሊያደርጉት ከሚችሉ ነገሮች መካከል የቴሌቪዥን ድራማዎች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። አሁን ላይ የበዙት መስኮቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ እኚህ ድራማዎችም ጭምር ናቸው። ነገር ግን፤ በዚህ ውስጥ ማሕበረሰቡን ለመያዝ የቀረብነው በምንና እንዴት ነው?

ድራማና ማሕበረሰብ…በሁለቱ መካከል ያለው ቅርበት የወዳጅነት ያህል ነው። በትውን ጥበባት ውስጥ እንደ የቴሌቪዥን ድራማን ያህል ለማሕበረሰብ ምቹ ሆኖ የሚታይ ሌላ ያለ አይመስልም። ለአብነት ፊልምን ብንወስድ በዕድሜ ክልል፣ በጊዜና ቦታ እንዲሁም በተደራሽነቱ የተገደበ ነው። ጭብጥና ይዘቱ ለሁሉም ምቹ ቢሆን እንኳን የሚመለከተው ሰው ምርጫና ፍላጎት ይወስነዋል። ቲያትርንም ሆነ የመድረክ ድራማ ለመመልከት ጊዜና ቦታ ወሳኝ ነገሮች ናቸው። የአንድ ጊዜ እንደመሆናቸው አማራጮች የሏቸውም። ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማን ለማሕበረሰቡ የቅርብ ያደረገው ዋነኛው ነገር፤ የሚሠራበት መንገድ ግዙፉን ማሕበረሰብ ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ነው። ድራማው ለእይታ የሚቀርበው በአንድ ትልቅ የቴሌቪዥን መስኮት ነው። ቴሌቪዥን ደግሞ ሕጻን አዋቂ፣ ምሁር መሃይም፣ ከተሜ ባላገር…ሳይል በሁሉም ቦታና ማንነት፣ እንዲሁም ሃይማኖት ውስጥ እኩል የሚገኝ እንደመሆኑ እልፍ ጥንቃቄዎች ይደረጉበታል። ሁሉንም ሊያማክል የሚችልበት መንገድ በጥልቅ ይጤንበታል።

አብዛኛውን ጊዜ ርዕሰ ጉዳዮች ቤተሰባዊ፣ ማሕበረሰባዊ እና ሀገራዊ ናቸው። በአንድ ቤተሰብ ውስጥ በእያንዳንዱ የዕድሜ ክልሎች ውስጥ የተወከሉ ገጸ ባህሪያትና ጭብጦች አይጠፉበትም። ከምንም በላይ ቤተሰባዊነትን የሚያንጸባርቁ በመሆናቸው፣ ያለምንም ክልከላ በአንድ ላይ እንዲመለከቱት ይጋብዛቸዋል። በሳምንት አንድ ጊዜ የሚቀርቡና ልብ አንጠልጥለው የሚሰነብቱ መሆናቸው እንዳይረሱና በጉጉት እንዲጠብቁ ያደርጋቸዋል። ከክፍል ክፍል ከምዕራፍ ምዕራፍ በዘለቀ ቁጥር የቤተሰቡንም አንድነት እያጠናከረ ይሄዳል።

በሀገራችን የተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ታሪክ ውስጥ ስማቸውን ግንባር ላይ ለማስፈር ከቻሉት ጥቂቱን ለማሳያ እንመልከታቸው። ከእነዚህም አብዛኛዎቹ ወደ ቀድሞውና ብቸኛው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚወስዱን ናቸው።

በዚያን ሰሞን በዚያን ጊዜ ተከታታይ ድራማ ማለት የእርሱ ስም እስኪመስል ድረስ የብዙዎችን ልብ ያነሆለለው “ገመና ድራማ” ነው። በሀገራችን ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ታሪክ የመጀመሪያው ነው። በመላው የሀገሪቱ ክፍል ከደቡብ እስከ ሰሜን፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ያልደረሰበት ማሕበረሰብ የለም። ከባሕር ማዶም በአውሮፓና አሜሪካ እንዲሁም በአረብ ሀገራት በሚገኙ ሓበሾች ዘንድ ሁሉ ዝነኛ ድራማ ነበር። ከታሪክና ጭብጦቹ አንስቶ በቤተሰባዊና ማሕበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ በመሆኑ፣ ተመልካቾቹም በቤተሰብ ደረጃ ነበር። ፍቃዱ ተክለማሪያም፣ ሜሮን ጌትነት፣ ጫንያለው ወ/ጊዮርጊስ፣ ዳንኤል ተገኝ፣ መሐመድ ሚፍታ

በእግር ኳስ ጨዋታ በስሜት እንደጋለ ሰው ብዙሃኑን ቁጭ ብድግ ሲያስደርግ የነበረው “ሰው ለሰው” ድራማ ነው። መጋቢት 2002 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መታየት የጀመረበት ነበር። በዚህ ድራማ ድርሰት ላይ መስፍን ጌታቸው፣ ታምሩ ብርሃኑ እና ነብዩ ተካልኝ ተጠበውበታል። ብስራት ገመቹ፣ መስፍን ጌታቸው፣ ዳንኤል ኃይሌ እና ሰለሞን ዓለሙ ደግሞ፤ በአዘጋጅነት የተጣመሩበት ነበር። አበበ ባልቻ፣ ሙሉዓለም ታደሰ፣ ሰለሞን ቦጋለ፣ ማሕደር አሰፋ፣ መስፍን ጌታቸው፣ ዝናሕብዙ ፀጋዬ፣ ሀና ዮሐንስ…እና ሌሎችም ድንቅ ተዋንያን በእጅ ብቻ ሳይሆን በልብም ጭምር ተጨብጭቦላቸዋል። ቤተሰባዊ ፍቅርና ሚስጥር፣ ወዳጅነትና ባላጣነት፣ ደመኝነትና ይቅር ባይነት፣ በወንጀልና የተንኮል ሴራዎች እየተከበቡ ልብ እንደሰቀሉ ከሳምንት ሳምንት ተጉዟል። ከሁሉም ከማንም “አስናቀ” የተሰኘውን ገጸ ባህሪ ማንም ሊረሳው የሚችለው አይደለም።

በግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ውስጥ ወደ ሕዝብ ከቀረቡ የምንጊዜም አይረሴ ድራማዎች “ሞጋቾች” ፈርቀዳጅ ነው። በኢቢኤስ ቴሌቪዥን የሚቀርብበትን ቀንና ሰዓት ያስናፈቀ ነበር። የጣቢያውን ተወዳጅነትም በአንድ ከፍ ያደረገ ነው። ሳይሰለች እንደ ተወደደና ልብ እንዳንጠለጠለ ለተከታታይ 5 ዓመታት ያህል ዘልቋል። እዚሁ ደግሞ “ሰንሰለት” የተሰኘው ድራማ፣ የብዙዎች ትዝታ ያለበት ሌላኛው ነው። እንደ “ዘመን ድራማ” ብዙዎችን ሰፍ አድርገው እንዳንሳፈፉ በመሃል የተቋረጡም እልፍ ናቸው።

እኚህን መጥቀስ ለቅምሻ ብቻ ሳይሆን፣ በብዙ ነገር ፈርቀዳጅ ስለሆኑም ነው። ዛሬ ላይ የቱ ተጠቅሶ፣ የቱ ይተዋል የሚባሉ ዓይነት ድራማዎች የበዙበት ነው። ልጅነታቸውን በቀደመው ጊዜ ያሳለፉ አንድ የጋራ ብሂል አላቸው “እኛ እኮ እንትን ድራማን እያየን ያደግን ነን” የሚል። የአሁኖቹስ ማንን ይጠሩ ይሆን…

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You